“ጌታ እግዚአብሔር ተገለጠልን” (መዝ. ፻፲፯፥፳፮)

በመ/ር ብዙወርቅ አበበ (ከአምቦ ማእከል)

አስተርእዮ ማለት መገለጥ ፣ መታየት ማለት ነው፡፡ አስተርእዮ የሚለው ቃል በጽርዕ (ግሪክ) ቋንቋ “ኤጲፋኒ” ይባላል፤ ይህም ከላይ መታየት፣ መገለጥ የሚለውን ለየት አድርጎ ያስረዳል፡፡

በክርስትና ሃማኖት ደግሞ አስተርእዮ ወይም ኤጲፋንያ የአምላክን መገለጥ፣ መታየት የሚያመለክት ነው፡፡ ከልደተ ክርስቶስ ዋዜማ ጀምሮ እስከ ዐቢይ ጾም ድረስ ባሉት ሳምንታትና ቀናት “ተወልደ (ተወለደ)፣ አንሶሰወ (ተመላለሰ)፣ አስተርአየ (ታየ)፥ ተጠመቀ፣ …” የሚሉት ቃላት በብዛት ይነገራሉ፡፡

ቤተ ክርስቲያንም እነዚህን ቀናት ዘመነ ጥምቀት ወአስተርእዮ ብላ ታከብራለች፤ በእነዚህ ዕለታትና ሳምንታት በቤተ ክርስቲያን የሚዘመረው መዝሙርም ሆነ የሚነበበው ንባብ ይህንኑ የጌታን መገለጥ የሚናገር፤ ስለ አምላክ ሰው መሆን፤ ስለ ሰማያዊ ሙሽራ መምጣት፣ መታየትና መገለጥ፣ በዚህ ምድር ተመላልሶ ማስተማር የሚያወሳ ነው፡፡

የረቂቅ አምላክን በሥጋ መገለጥ በዓይነ ትንቢት የተመለከተ ነቢየ እግዚአብሔር ዳዊት “እግዚአብሔር እግዚእ አስርአየ ለነ፤ ጌታ እግዚአብሔር ተገለጠልን” ሲል ተናግሯል፡፡
በዚህ ገጸ ንባብ ውስጥ የምንመለከተው እግዚአብሔር በየጊዜው በሕልም፣ በራእይ ወይም በልዩ ልዩ ተምሳሌት የሚደረገውን መገለጥ ሳይሆን ዓመተ ኩነኔን ለማሳለፍ ዓመት ምሕረትን ለማወጅ  በአጭር ቁመት በጠባብ ደረት ተወስኖ ከመካከላችን የተገኘውን የመድኃኔዓለም መገለጥ  ነው፡፡

በብሉይ ኪዳን እግዚአብሔርን በምሳሌ እንጂ ፊቱን ያየው አልነበረም፤ ሙሴ ከባለሟልነቱ የተነሣ “በባሕርይ ሆነህ ልይህ” ቢለው “ፊቴን አይቶ ለአንዲት ደቂቃ እንኳን በሕይወት ለመቆየት የሚችል የለም” ብሎታል፡፡ (ዘፀ. 3፴፭፥፲፯‐፳፭) ኋላም ወንጌላዊው ዮሐንስ “እግዚአብሔርን በባሕርይው ያየው የለም” ብሏል፡፡ (ዮሐ. ፩፥፲፰)

አዳምና ሔዋን የእግዚአብሔርን ትእዛዝ በማፍረሳቸው በመከራ አዘቅት ውስጥ ወድቀው ሲሠቃዩ ወደዚህ ዓለም መጥቶ ሰው ሆኖ ከድንግል ማርያም ተወልዶ፣ ተጠምቆ፣ እየተመላለሰ አስተምሮ፣ ተሰቅሎ፣ ሞቶ፣ ተነሥቶ፣ ሥጋውን ቆርሶ ደሙን አፍሶ እንደሚያድናቸው ተስፋ ሰጣቸው፡፡ የሰጣቸው ተስፋ ዕለቱን አልተፈጸመም፤ በትንቢት እየተነገረ፣ በሱባኤ እየተቆጠረ፣ በምሳሌም እየተመሰለ ብዙ ዘመን ኑሯል፡፡

ስለ ክርስቶስ በሥጋ መገለጥ ነቢያት ብዙ ትንቢት ተንብየዋል፤ ሱባኤም ቆጥረዋል፤ ምሳሌም እየመሰሉ ተናግረዋል፤ የተነገረው ትንቢት ሲፈጸም ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም ተወልዶ በአጭር ቁመት፤ በጠባብ ደረት ተገለጠ፤ ከተወለደም በኋላ አምላክ ነኝ ብሎ ዕለቱን አላደገም፤ እንደ ሕፃናት ቀስ በቀስ አደገ እንጂ፡፡

የዕብራውያንንም ሕግና ሥርዓት አላፋለሰም፤ በተወለደ በስምንተኛው ቀን ወደ ቤተ ግዝረት ገብቶ የግዝረት ሥርዓት ተፈጽሞለታል፤ ስሙም ኢየሱስ ተብሎ ተሰይሟል፡፡ በዐርባኛው ቀን ደግሞ እናቱ ቅድስት ድንግል ማርያምና ቅዱስ ዮሴፍ ዕጕለ ርግብ ዘውገማ ማዕነቅ ይዘው ወደ ቤተ እግዚአብሔር ወስደውታል፤ በዓመትም ሦስት ጊዜያት ወደ ቤተ መቅደስ ይወስዱት ነበር፡፡

ይህ አስተርእዮ በዘመነ ብሉይ ከነበረው መገለጥ በመልክም በጠባይም ይለያል፤ ያኛው በሕልም፣ በራእይ፣ በምሳሌ ነበር፤ አሁን ግን ራሱ የሰው ልጅ ለማዳን ተገለጠ፥ የፊተኛው ለተወሰኑ ሰዎች ነበር፤ አሁን ግን ለመላው ዓለም ሆነ፤ የፊተኛው በሩቅ ነበር፤ አሁን ግን በቅርብ የእኛን ሥጋና ነፍስ ተዋሕዶ ታየ፡፡ በዚህ አስተርእዮ በሰማይ ያለው የእግዚአብሔር መቅደስ ተከፈተ የእግዚአብሔር ድንኳን በሰዎች መካከል ተተከለ፤ ማለትም በሰዎች መካከል ተገኘ፤ ሰዎች የእግዚአብሔር ባለሟሎች ሆኑ፤ በእጃቸው ዳሰሱት፤ በዓይናቸውም አዩት፤ ሲያስተምር ሰሙት፤ አብረውት ተመገቡ፡፡  

ሰው የእግዚአብሔርን ክብር አየ፤ በዚህ አስተርእዮ በምሥጢረ ሥጋዌ ምሥጢረ ሥላሴንም ተማርን፤ አየን፤ በዮርዳኖስና በደብረ ታቦር አብ ስለ ልጁ የተናገረውን የምስክርነት ቃል ሰማን፤ መንፈስ ቅዱስ በርግብ አምሳል መጥቶ በራሱ ላይ ሲቀመጥ ተመለከትን፤ በዚህም የአካል፣ የስም፣ የግብር ሦስትነታቸውን የፈቃድ፣ የሕልውና አንድነታቸውን ተረዳን፡፡

በመንፈስም በገንዘብም ድሆች ተብለው ተንቀው ለነበሩት እግዚአብሔር በመካከላቸው ተገኘ፤ በዓለማዊ ሥልጣናቸው የሚመኩ ትዕቢተኞች ተዋረዱ፤ ትሑታን ከፍ ከፍ አሉ፤ የፍትሕ ሚዛን የሌላቸው ነገሥታት ተንኮታኩተው ወደቁ፤ የተራቡ በአስተርእዮ በረከት ጠገቡ፤ የተጠሙት ረኩ፤ በኃላፊ ሀብታቸው በመመካት እግዚአብሔርን ንቀው የነበሩ ሀብታሞች ባዶ እጃቸውን ቀሩ፡፡

በዚህ በዘመነ አስተርእዮ ወቅት የሚከበሩ በዓላት ከዋሉበት የአስተርእዮ ዘመን የተነሣ የአስተርእዮ በዓላት ይባላሉ፡፡ የሚነገርባቸውም ቃለ እግዚአብሔር ስለ ጌታ መወለድ፣ በግልጥ መመላለስ፣ መጠመቅ፣ አምላክ ሰው ስለመሆኑ ምሥጢረ ሥላሴ ስለመገለጡ ነው። በተለይም ጥር ፳፩ የእመቤታችን የዕረፍት በዓል አስተርእዮ ማርያም ይባላል። በተለየ አስተርእዮ ማርያም መባሏ ለቃል ርደት፣ ለሥጋ ዕርገት ምክንያት ናትና ነው፡፡ እንዲሁም ምሥጢረ ሥላሴ በምልዓት የተገለጠው አምላክ ከእሷ ሰው ከሆነ በኋላ ስለሆነ በዓሉ አስተርእዮ ማርያም ይባላል።

አስተርእዮ ማርያም ብለን የምናከብረው በዓል የእመቤታችንን የዕረፍት በዓል ነው። ቅዱስ ዳዊት “ነኪር ነገሩ በእንቲአኪ ሀገረ እግዚአብሔር፤ እግዚአብሔር ማኅፀንሽን ከተማ አድርጎ ዘጠኝ ወር ከአምስት ቀን የኖረብሽ ሆይ ስለ አንቺ የተነገረው የተደረገው ነገር ዕፁብ ድንቅ ነው” (መዝ. ፹፮፥፫) እንዳለ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም የአምላክ እናት ሆና ማረፏ ይደንቃል። ታላቁ የቤተ ክርስቲያናችን አባት ቅዱስ ያሬድ ሞቷ የሚያስደንቅ መሆኑን “ሞትሰ ለመዋቲ ይደሉ ሞታ ለማርያም የዐጽብ ለኲሉ፤ ሞት ለማናቸውም ሰው ሁሉ የተገባ ነው የማርያም ሞት ግን ሁሉን ያስደንቃል” በማለት ገልጾታል።

ሞት በጥር ነሐሴ መቃብር

የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምን ሞትና ትንሣኤ በነገረ ማርያም አበው እንደሚያስረዱት ዕረፍቷ በጥር ፳፩ እሑድ ነው ። አባቶቻችን በጾመ ፍልሰታ ውዳሴ ማርያም፣ ቅዳሴ ማርያም ሲተረጉሙ የዕረፍቷን ነገር እንዲህ ብለው ይተርካሉ።

የዕረፍቷስ ነገር እንደምን ነው ቢሉ ስድሳ አራት ዓመት በዚህ ዓለም ኖራ ጥር ፳፩ በእሑድ ቀን ጌታ እልፍ አዕላፋት መላእክቱን አስከትሎ መጥቶ “እናቴ ሆይ! ከዚህ ዓለም ድካም ላሳርፍሽ መጣሁ” አላት። “ልጄ ሆይ! ሰማይና ምድር የማይወስኑህ ዘጠኝ ወር ከአምስት ቀን በማኅፀኔ ተሸክሜ በድንግልና ወልጄህ እሞታለሁን?” አለችው። በሲኦል የሚሠቃዩ ነፍሳትን አሳይቶ “እናቴ ሆይ! ሞትሽ ለእነዚህ ቤዛ (የመዳን ምክንት) ይሆንላቸዋል” አላት። እሊህን ከማርክልኝስ ይሁን አለችው። ቅድስት ሥጋዋን ከቅድስት ነፍሷ ለይቶ በቃለ አቅርንት፣ በዝማሬ መላእክት አሳረጋት። ደቀ መዛሙርቱንም ከያሉበት በደመና ጠቅሶ ካለችበት አድርሶ እመቤታችሁን ሥጋዋን በክብር አሳርፉ አላቸው። ሐዋርያት በአጎበር አድርገው ወደ ጌቴ ሴማኒ ይዘው ሲሄዱ አይሁድ “ቀድሞ ልጇን ተነሣ፤ ዐረገ እያሉ ሲያውኩን ይኖራሉ፤ አሁን ደግሞ እሷን ተነሣች፤ ዐረገች እያሉ ሊያውኩን አይደለምን በእሳት እናቃጥላታለን” ብለው ተነሡ። ታውፋንያ የሚባል አይሁዳዊ ተራምዶ አጎበሩን ጨበጠው። መልአክ መጥቶ በሰይፍ ሁለት እጁን ቀጣው፤ ከአጎበሩ ተንጠልጥሎ ቀረ። “በድያለሁ ማሪኝ” ብሎ ቢማጸናት እጁ ተመልሶለታል። ከዚህ በኋላ ጌታችን ከዮሐንስ ጋር በደመና ነጥቆ ከገነት አግብቶ ከዕፀ ሕይወት ሥር አኖራት።

ቅዱስ ዮሐንስን “እንደምን ሆነች?” አሉት ከገነት “ከዕፀ ሕይወት ሥር አለች” አላቸው፡፡ እነርሱም ቅዱስ ዮሐንስ አይቶ እኛ ሳናይ ብለው በነሐሴ መባቻ ጾም ጀመሩ፤ ሁለት ሱባዔ ሲፈጸምም እሑድ አምጥቶ ሰጥቷቸው ቀብረዋታል፤ በሦስተኛው ቀን ማክሰኞ ከመ ትንሣኤ ወልዳ፤ እንደ ልጇ ተነሥታለች።

በቦታው ቅዱስ ቶማስ አልነበረም ደመና ጠቅሶ ከሀገረ ስብከቱ ሲመጣ ስታርግ አገኛት፤ “ቀድሞ የልጅሽን ትንሣኤ ሳላይ ቀረሁ፤ ዛሬም ደግሞ ያንቺን ትንሣኤ ሳላይ ቀረሁን” ብሎ ወፈቀደ ይደቅ እምደመናሁ፤ ከሐዘኑ የተነሣ ሊወድቅ ወደደ፡፡ እመቤታችንም “አይዞህ አትዘን! እሊያ ትንሣኤዬን፣ ዕርገቴን አላዩም፤ አንተ አይተሃል፤ ተነሣች ዐረገች” ብለህ ንገራቸው ብላ የያዘችውን ሰበን ሰጥታ ሰደደችው።

ከዚህ በኋላ ቅዱስ ቶማስ ወደ ሐዋርያቱ ሄዶ “የእመቤታችን ነገር እንደምን ሆነ?” አላቸው “አግኝተን ቀበርናት” አሉት፡፡ “ሞት በጥር በነሐሴ መቃብር ተዉ ይህ ነገር አይመስለኝም” አላቸው። ቅዱስ ጴጥሮስ “አንተ ልማድህ ነው አንተ ብቻ ተጠራጥረህ አትቀርም ሰውን ሁሉ ስታጠራጥር ትኖራለህ” ብሎ ተቆጥቶ ወደ መቃብሩ ሂዶ ቢከፍተው አጣት፤ ደንግጦ ቆመ፡፡ ሐዋርያው ቶማስም አታምኑኝም ብዬ እንጂ እመቤታችንስ ተነሣች፤ ዐረገች አላቸው፤ የያዘውንም ሰበን ሰጣቸው፤ ለበረከትም ተካፍለውታል።

በዓመቱ ሐዋርያት ቅዱስ ቶማስ “ትንሣኤሽን ዕርገትሽን አይቶ እኛ ሳናይ” ብለው ጾም ጀመሩ፡፡ በ፲፮ኛው ቀን እመቤታችንን መንበር አድርጎ ቅዱስ ጴጥሮስን ካህን ዘይትራድኦ ቅዱስ እስጢፋኖስን ሠራዒ ዲያቆን አድርጎ በዚያው ላይ ቀድሶ አቁርቧቸዋል።

ቤተ ክርስቲያንም ይህንን መሠረት አድርጋ የጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከእመቤታችን ከሥጋዋ ሥጋ፣ ከነፍሷ ነፍስን ነሥቶ መወለዱን (መገለጡን) እንዲሁም የእመቤታችንን ዕረፍት ምክንያት በማድረግ መታሰቢያ በዓሉን ጥር ፳፩ ቀን በየዓመቱ ታከብረዋለች።

0 replies

Leave a Reply

Want to join the discussion?
Feel free to contribute!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *