መንፈሳዊ ብስለት
መንፈሳዊ ብስለት ማለት አንድ ክርስቲያን በመንፈሳዊ ሕይወት ውስጥ የሚያመጣው መንፈሳዊ እድገት ነው። መንፈሳዊ እድገት (ብስለት) የሚመጣው ደግሞ ከአካላዊ ተግባር፣ ከልቡናዊ የሐሳብ ጽርየት (ልቡናን ከክፉ ነገር ከማንጻት)፣ ከዐቂበ ርእስ እም ኃጢአት (ራስን ከገቢረ ኃጢአት መጠበቅ) ወዘተ … ነው ።
ሰው መንፈሳዊ እድገት ጀመረ የሚባለው ሃይማኖቱን ተረድቶት፣ ፍቅረ እግዚአብሔር ገብቶት ሁሉንም ጉዳይ ስለ ፍቅረ እግዚአብሔር ብሎ ማድረግ ሲጀምር ነው። መንፈሳዊ እድገት ማምጣት የሚፈልግ ሰው መጀመር ያለበት ከትንሿ ተግባር እንጂ ከትልቁ ተግባር አይደለም። ምክንያቱም ትንሹን ትቶ ከትልቁ ከጀመረ መንፈሳዊ ተግባራቱን ማከናወን ሲከብደው ተስፋ ወደ መቁረጥ ይደርሳልና፤ ስለዚህም ማር ይስሐቅ “በትልቁ እንዳትወድቅ ከትንሹ ተጠንቀቅ” አለ።
መንፈሳዊ እድገት ማምጣት የሚፈልግ ሰው ከታች የተዘረዘሩትን ዋና ዋና ጉዳዮችን ማወቅ (መረዳት) ይኖርበታል፡፡ እነዚህም፡-
➾ መንፈሳዊ እድገት ማምጣት ለምን እንዳስፈለገው?
➾ መንፈሳዊ እድገት የሚጀምሩት እንጂ የሚጨርሱት እንዳልሆነ፣
➾ መንፈሳዊ እድገት የፍቅር ድካም እንዳለው ማወቅ፣
➾ ትሕትና ያለው መሆን
➾ የሚኖርለትን የመንፈሳዊ ሕይወት ዓላማ መረዳት
➾ መንፈሳዊ ፈለጥ ማወቅ አለበት
ፍቅር እንዴት ያደክማል የሚል ሰው ቢኖር፡- የፍቅር ድካም ማለት ክርስቶስ ለቤተ ክርስቲያን ሲል ራሱን ለመከራ አሳልፎ እንደሰጠ፤ ስለ ክርስቶስ መከራ መቀበል ነው። ለዚህ ነው “እስመ ከመዝ አፍቀሮ እግዚአብሔር ለዓለም እስከ ወልዶ ዋሕደ መጠወ ወወሀበ ቤዛ ኩሉ፤ አንድ ልጁን እስከ መስጠት ድረስ አግዚአብሄር ዓለሙን ወዶታልና” በማለት የገለጸው ።”(ዮሐ. ፫÷፲፮)
ክርስቲያን የፍቅር ድካም ደከመ የሚባለው ከክርስቶስ ፍቅር የሚለየውን ሥጋዊ ፍትወት፣ ሥጋዊ ሐሳብ፣ ምድራዊ ሥልጣን፣ ጊዜያዊ ቅንጦት፣ ዓላማዊ ማሸብረቂያዎች የማያታልሉት ሲሆንና ሥጋዊ ግብርን ቆርጦ ሲጥል ነው፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ወደ ሮሜ ሰዎች በላከው መልእክቱ “ከክርስቶስ ፍቅር ማን ይለየናል? መከራ ነውን? ኀዘን ነውን? ስደት ነውን? ራብ ነውን? መራቆት ነውን? ጭንቀት ነውን? ሾተል ነውን?” (ሮሜ. ፰፥፴፭) እንዲል እስከ መጨረሻዋ እስትንፋስ መከራ ለመቀበል ዝግጁ መሆን ሲቻል ነው።
ሰው መንፈሳዊ እድገት ሲጀምር በጓደኞቹም ሆነ በተለያዩ ሰዎች መንፈሳዊ አኗኗሩም ሆነ አስተሳሰቡ ሊነቀፍበት ይችላል። ነገር ግን ክርስቲያናዊ ሕይወቱና መንፈሳዊ አኗኗሩ ትክክለኛ ከሆነ መንፈሳዊ እድገቱን መተው የለበትም።
የመንፈሳዊ ዕድገት መገለጫዎች
መልካም ልጅ የአባቱን የፍቅር መግለጫ ደብዳቤ ከናፍቆቱ የተነሣ በስስት ዘወትር እንደሚያነብ በመንፈሳዊ እድገት ላይ ያለ ሰውም እግዚአብሔር ለመንፈሳዊ ልጆቹ በቅዱሳን በኩል የጻፋቸውን መንፈሳዊ መጻሕፍትን የሚያነብ፣ መልእክቱን ተረድቶ ትእዛዙን የሚፈጸምና መንፈሳዊ ትምህርት በሚነገርባቸው ቅዱሳት መካናት የሚገኝ ነው። ልጅ አባቱን እንደሚወድ የሚታወቀው የአባቱን ትእዛዝ መፈጸም ሲችል ነው። በመንፈሳዊ እድገት ውስጥ ያለ ክርስቲያንም እንዲሁ ነው።
ክርስቶስ ለእኛ ያለውን ፍቅሩን ለመግለጽ ራሱን አሳልፎ እንደሰጠ ሁሉ በመንፈሳዊ ሕይወት እድገት ላይ የሚገኝ ክርስቲያንም በኑሮው ሁሉ ራሱን ለእግዚአብሔር በማስገዛት በጾም፣ በጸሎት በመትጋት ከጊዜ ወደ ጊዜ መንፈሳዊ ለውጥ ማምጣት የሚችል መሆን ይገባዋል፡፡ መንፈሳዊ ኃይልን በመታጠቅ ከአጋንንት የሚመጡ ፈተናዎችን በመቋቋም፣ በንስሓ ሕይወት እየተመላለሰ የክርስቶስን ሥጋና ደም በመቀበል መኖር ይጠበቅበታል፡፡
ለሕይወት መዛል ምክንያት የሚሆኑ ፍልስፍናዊና ዓለማዊ ሐሳቦችን መለየትና ዐቂበ ሕይወትን (ሕይወትን መጠበቅ) መያዝ የቻለ ሰው መንፈሳዊ እድገት ጀምሯል ይባላል። አትክልቶች በየጊዜው ውኃ መጠጣት እንደሚያስፈልጋቸው ለመንፈሳዊ ሰውም ሁልጊዜ የእግዚአብሔርን ቃል ነፍሱን ማጠጣት አለበት፡፡
ሰው የውቅያኖስን ውኃ ጠጥቶ ባይጨርስም እንኳ ለጥም ያህል እንደሚጠጣ መንፈሳዊ ሰውም ባሕርየ እግዚአብሔርን መርምሮ ባይጨርስም ለሃይማኖት ያህል እግዚአብሔር የገለጠውን ማወቅ ከእግዚአብሔር ሱታፌ ጸጋ (የጸጋ ተሳትፎ) እንዲኖረው መጋደል አለበት፡፡◊
Leave a Reply
Want to join the discussion?Feel free to contribute!