ጾመ ነቢያት

ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ሰባት የዐዋጅ አጽዋማትን በቀናት፣ በሳምንታትና በወራት ቀምራ ኦርቶዶክሳውያን ሁሉ እንጠቀምበት ዘንድ ደንግጋ አበርክታለች፡፡ ከእነዚህ አጽዋማት መካከል ደግሞ ጾመ ነቢያት አንዱ ሲሆን ኦርቶዶክሳውያን ከኅዳር ፲፭ እስከ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ልደት ዋዜማ ድረስ የምንጾመው ጾም ነው፡፡  

እግዚአብሔር ለአዳም አባታችን በገባው ቃል ኪዳን መሠረት ይህንን ዓለም ያድን ዘንድ የሰውን ሥጋ ለብሶ እንደሚወለድ ነቢያት በትንቢት መነጽርነት ተመልክተው ተናግረዋል፡፡ ነቢየ እግዚአብሔር ኢሳይያስ “ስለዚህ ጌታ ራሱ ምልክት ይሰጣችኋል፤ እነሆ ድንግል ትፀንሳለች፣ ወንድ ልጅም ትወልዳለች፤ ስሙንም አማኑኤል ብላ ትጠራዋለች” (ኢሳ. ፯፥፥፲፬) እንዲል፡፡ ይህም ብቻ አይደለም ነቢየ እግዚአብሔር ቅዱስ ዳዊት በመዝሙሩ “ከአጥቢያ ኮከብ አስቀድሞ ከሆድ ወለድሁህ” ተብሎ እንደተጻፈው፡፡ (መዝ. ፻፱፥፫)፣ በተጨማሪም “እነሆ በኤፍራታ ሰማነው፤ ዛፍ በበዛበትም ቦታ አገኘነው፤ እንግዲህስ ወደ እግዚአብሔር ማደሪያዎች እንገባለን፤ የጌታችን እግሮቹ በሚቆሙበት ቦታ እንሰግዳለን” (መዝ. ፻፴፩፥፮-፯) በማለት “ይወርዳል፣ ይወለዳል” የሚለውን የጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ይህን ዓለም ለማዳን በሥጋ መምጣት ተናግረዋል፡፡ ነቢያት በዚህ ብቻ ሳያበቁ ስለ ስደቱ፣ ስለ ጥምቀቱ፣ ወንጌልን ስለመስበኩ፣ መከራ ስለ መቀበሉ፣ ስለ ሞቱ፣ ስለ ትንሣኤው፣ ዕርገቱና ዳግም ምጽዓቱ በትንቢት ተናግረዋል፡፡ በዚህ ምክንያት ነቢያት የጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን መወለድ እየናፈቁ ጾመውታልና ጾመ ነቢያት ተብሏል፡፡

የነቢያት ትንቢት ፍጻሜውን አግኝቶ ጌታችን መድኃኒታችን ኢያሱስ ክርስቶስ ከእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በተወለደ ጊዜም የአዳም ተስፋው ተፈጽሟልና “ጾመ አዳም” እየተባለም ይጠራል፡፡ የጾሙ መጨረሻም በዓለ ልደት በመሆኑ “ጾመ ልደት” ይባላል፡፡ የነቢያት ትንቢት ተፈጽሞ ጨለማውን ዓለም በወንጌል ብርሃንነት (በስብከት) አጣፍጧልና “ጾመ ስብከት” ተብሎ ይጠራል፡፡

እንደዚሁም ሐዋርያት በዓለ ልደቱን እንዴት ዝም ብለን እናከብረዋለን? ነቢያት አባቶቻችን “ይወርዳል ይወለዳል” ብለው በተስፋ እየናፈቁ ጾመውታል፤ በዓለ ትንሣኤውን ዐቢይ ጾምን ጾመን እናከብረዋለን፤ በዓለ ልደቱንም ጾመን በረከት እናገኝበታለን ሲሉ ጾመውታልና “ጾመ ሐዋርያት” ይባላል፡፡ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል በግብረ መንፈስ ቅዱስ አምላክን እንደምትፀንስ ካበሠራት በኋላ “ሰማይና ምድር የማይወስኑትን አምላክ ፀንሼ ምን ሠርቼ እወልደዋለሁ?” በማለት ጌታችንን ከመውለዷ አስቀድማ ጾማዋለችና ይህ ጾም “ጾመ ማርያም” እየተባለም ይጠራል፡፡

በአጠቃላይ በዚህ በነቢያት ጾም ነቢያት፣ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም፣ ሐዋርያት፣ ጻድቃን ሰማዕታት ጾመው በረከት አግኝተውበታልና እኛ ምእመናንም በረከትን እናገኝ ዘንድ መጾም እንደሚገባን የቤተ ክርስቲያን አባቶች ሥርዓት ሠርተውልናል፡፡ ጾመን፣ ጸልየን የበረከቱ ተሳታፊዎች ያድርገን፡፡ አሜን፡፡  

ምንጭ፡-

ፍትሐ ነገሥት ንባቡና ትርጓሜው፣ አንቀጽ ፲፭፡፡

ጾምና ምጽዋት፣ ዲያቆን ቃኘው ወልዴ፤ ገጽ ፵፯ -፶፡፡

0 replies

Leave a Reply

Want to join the discussion?
Feel free to contribute!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *