አዲስ ዓመት እና ግቢ ጉባኤያት
ጥቅምት ፳፱ ቀን ፳፪፲፯ ዓ.ም
በእንዳለ ደምስስ
እግዚአብሔር ለሰው ልጆች ከሰጣቸው በረከቶች መካከል ጊዜአቸውን ጠብቀው የሚፈራረቁ ወቅቶች ይገኙበታል፡፡ ነቢየ እግዚአብሔር ቅዱስ ዳዊት በመዝሙሩ “በቸርነትህ ዓመትን ታቀዳጃለህ” (መዝ. ፷፬፥፲፩) እንዲል የበጋውን፣ የበልጉንና ክረምቱን ወቅቶች አፈራርቆ መጸው ደግሞ ምድር በአረንጓዴና በልዩ ልዩ አበባዎች በምትደምቅበት በመስከረም ወር ሰዎችም የእግዚአብሔርን ቸርነት አድንቀውና አዲስ ተስፋን ሰንቀው “እንኳን አደረሳችሁ” በማለት ዓመቱ የተባረከ እንዲሆን የሚመኙበት ጊዜ ነው፡፡
አዲስ ዓመት ላይ ሆነን እግዚአብሔር በሰጠንና ባሳለፍነው ዓመት ምን ዐቅደን ነበር? የትኛውን አሳካን? የትኛውስ ቀረን? በሂደት ላይ ያሉትስ የትኞቹ ናቸው? በአዲሱ ዓመት ደግሞ ከደካማ ጎናችን ተምረን ራሳችንን ፈትሸን ያላጠናቀቅናቸው ዕቅዶቻችንን ጨምረን አዲስ ዕቅድ ለማውጣት ጥረት ማድረግ በብዙዎቻችን ዘንድ የተለመደ ተግባር ነው፡፡
አንዱን ስናሳካ ሌላውን መመኘት ሰዋዊ ባሕርይ እንደመሆኑ መጠን የተመኘናቸውን ሁሉ ማሳካት አንችልም፡፡ “ነገር ግን ሁሉን በአግባብና በሥርዓት አድርጉ” (፩ኛቆሮ. ፲፬፥፵) እንደተባለ ልናከናውናቸው የምንችላቸው ላይ ብቻ ትኩረት በማድረግ ዐቅደን ለመፈጸም አቅማችንን ሁሉ መጠቀም ይገባል፡፡
ከዚህ አንጻር በዚህ ጽሑፍ የግቢ ጉባኤ ተማሪዎች ላይ ትኩረት እናደርጋለን፡፡
በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በመማር ላይ የሚገኙና አዲስ ወደ ግቢዎች የሚገቡ ኦርቶዶክሳውያን ተማሪዎች ትምህርትን ፍለጋ ከቤተሰብ መራቃቸውን በመገንዘብ ለትምህርታቸው ትኩረት እንደሚሰጡ ይታወቃል፡፡ ነገር ግን እንዴት ማጥናት? መቼ ወደ ቤተ ክርስቲያን መሄድ? ኮርስ መቼ መማር፣ በተመደቡበት የአገልግሎት ክፍል ስብሰባ፣ አገልግሎት እንዴት በተቀናጀና በዕቅድ በተመራ መንገድ ማከናወን እንዳለባቸው ባለመረዳት ችግር ውስጥ ይገባሉ፡፡ በዚህም ምክንያት ውጤት ርቋቸው ሕይወታቸው ወደ አልተፈለገ አቅጣጫ ሲያመራባቸው ይታያል፡፡ ይህንን ችግር ለማስወገድና ውጤታማ ሆኖ ለመውጣት ዕቅድ አስፈላጊ ነው የምንለውም ለዚህ ነው፡፡
በዕቅዶቻቸው ውስጥ ትምህርታቸው ላይ የሚወስዱት ጊዜን፣ የሚያጠኑበት፣ መንፈሳዊ ትምህርት የሚማሩበትና የጸሎት፣ እንዲሁም ከጓደኞቻቸው ጋር መረጃ የሚለዋወጡበት፣ ጊዜ መመደብና በዕቅዳቸው ውስጥ ማካተት ይጠበቅባቸዋል፡፡ በዚህም መሠረት እነዚህን ዕቅዶች ተግባራዊ ለማድረግ ቀጥሎ ያሉትን ነጥቦች መዘንጋት አይገባም፡-
፩. እግዚአብሔርን አጋዥ ማድረግ፡-
ከሁሉም ነገር በፊት ውጤታማ ሆነው ወደ ከፍተኛ ትምህርት ተቋም እንዲገቡ ያበቃቸውን አምላካቸውን ማመስገን፣ ከእርሱም ጋር ያላቸውን ቁርኝት ማጥበቅ የዕቅዳቸው አካል ሊሆን ይገባል፡፡ “እኔ የወይን ግንድ ነኝ፤ ቅርንጫፎቹም እናንተ ናችሁ፤ በእኔ የሚኖር እኔም በእርሱ፤ ብዙ ፍሬ የሚያፈራ እርሱ ነው፤ ያለ እኔ ምንም ማድረግ አትችሉምና” ተብሎ እንደተጻፈ ያለ እግዚአብሔር ፈቃድ ምንም ሊያደርጉ እንደማይችሉ በመረዳት ሁል ጊዜ እግዚአብሔርን ማስቀደም፣ እንደ ፈቃዱም መመላለስ ይጠበቅባቸዋል፡፡ (ዮሐ. ፲፭፥፭) በትምህርታቸውም በአገልግሎታችውም ከመታከት ርቀው እግዚአብሔር በጎ ምኞታቸውንና ጥረታችውን እንዲባርክላቸው ዘወትር ሌሊት ኪዳን በማድረስ፣ ማታም በአገልግሎት በመሳተፍ ከዓላማው ሳይናወጡ መጸለይ ያስፈልጋል፡፡ “እግዚአብሔር ቅርብ ነው፤ በምንም አትጨነቁ፤ ነገር ግን በሁሉ ነገር ጸልዩ፣ ማልዱም፤ እያመሰገናችሁም ልመናችሁን ለእግዚአብሔር ግለጡ” እንዲል (ፊል. ፬፥፮)፡፡
፪. ለትምህርታቸው ትኩረት መስጠት፡-
ወደ ከፍተኛ ትምህርት ለመግባታቸው ምክንያቱ ትምህርታቸው ላይ ትኩረት አድርገው ውጤታማ ሆነው መገኘታቸው ነው፡፡ ከውጤት በኋላም ወላጅ ከእቅፉ ነጥሎ የሚልካቸው ነገ ራሳቸውን ችለው ቤተሰብን፣ ሀገርንና ቤተ ክርስቲያንን በጉልበታቸው፣ በዕውቀታቸውና በገንዘባቸው እንደሚደግፉ፣ በጎደለው በኩልም በመቆም ጎደሎን ይሞላሉ፣ ቀጥሎም የራሳቸውን ሕይወት ይመራሉ በሚል በጎ ሐሳብ ነው፡፡ ስለዚህ ወደ ከፍተኛ ትምህርት ተቋም የገቡበት ዋነኛ ዓላማ ጊዜአቸውን ለትምህርታቸው ቅድሚያ በመስጠት ውጤታማ ሆነው መገኘታቸው ነው፡፡ በግቢ ቆይታቸውም ክፍል ውስጥ መገኘት፣ በማስተዋል ትምህርታቸውን መከታተል፣ የሚሰጣቸውን የክፍል፣ የቤት ወይም የቡድን ሥራ ንቁ ተሳታፊዎች ሆነው በጥራት በመሥራት ለሌሎች አርአያ መሆን ይጠበቅባቸዋል፡፡
፪. የጥናት ጊዜን መመደብ፡-
አንድ ተማሪ በየትኛውም የትምህርት ደረጃ ላይ ይገኝ የጥናት ጊዜ ሊኖረው ይገባል፡፡ በቀን ውስጥ ለጥናት የሚሆን ጊዜ መመደብ፣ ለዚያም ታማኝ በመሆን ከሌሎች ጉዳዮች በመራቅ የመደበውን ሰዓት በአግባቡ መጠቀም ያስፈልጋል፡፡ በከፍተኛ ትምህርት ተቋም ውስጥ እስካለ ድረስ ማጥናት ግዴታው መሆኑን፣ ይህንንም በሥርዓትና በኃላፊነት መወጣት እንዳለበት ራሱን ማሳመን አለበት፡፡ እርሱ ጥናቱን አጠናቅቆ ሌሎች ጉዳዮችን ለማከናወን በሚዘጋጅበት ጊዜ ሌሎች ጓደኞቹ የራሳቸውን ጉዳዮች አጠናቀው መጥተው እናጥና ስላሉት፣ ወይም እንዝናና ቢሉት በይሉኝታ ታስሮ ከዐቀዳቸው ዕቅዶች ውጪ ማከናወን ወይም መጓዝ የለበትም፡፡ ለመደበው ጊዜና ላቀደው ዕቅድ ታማኝ መሆን አለበት፡፡ ስለዚህ ለጥናት ልዩ ትኩረት በመስጠት ጊዜውን በአግባቡ መጠቀም ይገባል፡፡
፫. የጸሎት ጊዜ፡-
ክርስቲያን ከጸሎት የተለየ ሕይወት ሊኖረው አይገባም፡፡ በተለይም በግቢ ጉባኤ ውስጥ የሚሳተፉ ወንድሞችና እኅቶች በጸሎት የታገዘ ሕይወት ሊኖራቸው ይገባል፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ለኤፌሶን ሰዎች በላከው መልእክቱ “በጸሎትና በምልጃ ሁሉ ዘወትር በመንፈስ ጸልዩ፤ ከዚህም ጋር ስለ ቅዱሳን ሁሉ ለመጸለይ ሁል ጊዜ ትጉ” በማለት ክርስቲያን ጸሎት መጸለይ እንደሚገባው ይናገራል፡፡ በጋራም ሆነ በግል ጸሎት ላይ በቅድስት ቤተ ክርስቲያን በመገኘት መንፈሳዊ ሕይወትን ማሳደግ ያስፈልጋል፡፡ (ኤፌ. ፮፥፲፰)
ጸሎት በንጽሕና ሆነን ከእግዚአብሔር ጋር የምንገናኝበት መንፈሳዊ የሕይወት መንገድ ነው፡፡ ያለ ጸሎት መንፈሳዊ ሰው መሆን፣ በአገልግሎት መትጋት፣ መንፈሳዊ ፍሬዎችንም ማፍራት አይቻልም፡፡ ከጸሎት የተለየ ሕይወት የአጋንንትና የሠራዊቱ ማኅደር እስከ መሆን ያደርሳልና ዘወትር በጸሎት መትጋት ከአንድ ክርስቲያን ይጠበቃል፡፡
በግቢ ጉባኤ ውስጥ ትምህርታቸውን የሚከታተሉ ወጣቶችም ይህንን ከግንዛቤ በማስገባት የጸሎት ጊዜ በመመደብ የሚገጥማቸውን ፈተና ሁሉ እግዚአብሔርን አጋዥ በማድረግ በተጋድሎ ሊጸኑ ይገባል፡፡ ይህም በሥጋም በነፍስም ተረጋግተው ውጤታማ ሕይወት እንዲመሩ ያስችላቸዋል፡፡
፬. ለመንፈሳዊ አገልግሎት ጊዜ መስጠት፡-
አንድ በግቢ ጉባኤ ውስጥ የሚሳተፍ ተማሪ ለትምህርቱ ቅድሚያ ከሰጠ፣ የጥናት ጊዜውን መድቦ ተግባራዊ ካደረገ፣ ለጸሎት ልዩ ትኩረት ሰጥቶ ከተጋ ቀሪው በመንፈሳዊ አገልግሎት ውስጥ በመሳተፍ በተሰጠው ጸጋ ማገልገል ነው፡፡ አገልግሎትን በግቢ ውስጥ በአገልግሎት ላይ ልምድ ካካበቱ ወንድሞች ጋር በመሆን ከእነርሱም በመማርና ልምድ በመቅሰም ክርስቲያናዊ ግዴታውን መወጣትይገባዋል፡፡
ብዙውን ጊዜ በአንዳንድ የግቢ ጉባኤ ወንድሞችና እኅቶች ችግር ሆኖ የሚታየው ጊዜአቸውን ሁሉ ለአገልግሎት በማዋል በትምህርታቸው ሲደክሙ ማየት የተለመደ ነው፡፡ ይህ የሚመነጨውም ጊዜአቸውን በአግባቡ ዐቅደው ባለመጠቀማቸው ምክንያት ስለሆነ በትምህርት ጊዜ ለትምህርታቸው፣ በጥናት ጊዜም ጥናታቸውን፣ በአገልግሎት ጊዜም አገልግሎታቸው ላይ ትኩረት በማድረግ ሳይጨናነቁ ሁሉንም አጣጥመው መጓዝ ይገባቸዋል፡፡
በአጠቃላይ የግቢ ጉባኤ ተማሪዎች ውጤታማ ሆነው ለመውጣት በዕቅድ መመራትን ልምድ እንዲያደርጉና ለዐቀዱት ዕቅድ ደግሞ ታማኝ ሆነው በመገኘት ወደ ተግባር በመለወጥ በሥጋም በነፍስም ሊያተርፉ ይገባል፡፡ በዚህ አዲስ ዓመትም ካለፈው ስሕተት በመማር ስኬታማ የትምህርት ዘመንን ለማሳለፍ ዕቅድ በማውጣትና ተግባራዊ በማድረግ ሊጓዙ ይገባል፡፡ ከላይ የጠቀስናቸው ነጥቦች ከብዙ በጥቂቱ ቢሆኑም እነዚህን ተግባራዊ በማድረግ ስኬታማ ሆነው መውጣት ይችላሉና፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
Leave a Reply
Want to join the discussion?Feel free to contribute!