ርእሰ ዐውደ ዓመት
እንኳን ከዘመነ ዮሐንስ ወደ ዘመነ ማቴዎስ በሰላም አሸጋገረን፡፡ መልካም አዲስ ዓመት!
በኢትዮጵያውያን ዘመን አቆጣጠር የመስከረም ወር የወራት ሁሉ መጀመሪያ ነው፡፡ ይህ ወር ዘመን መለወጫ፣ ዕንቁጣጣሽ፣ ቅዱስ ዮሐንስ እየተባለ ይጠራል፡፡ ገበሬው በክረምቱ ወራት መሬቱን አልስልሶ፣ ዘሩንም ዘርቶ ምድሪቱም አደራዋን ለመመለስ በልምላሜ የምታጌጥበት ወር ነው፡፡ በዚህም ምክንያት እንስሳት ለምለሙን ሣር ግጠው፣ የጠራውን ውኃ ጠጥተው ረክተው፣ አምረው የሚታዩበት የልምላሜ ወር ነው። ነቢየ እግዚአብሔር ዳዊት “ምድርን ጐበኘሃት አጠጣሃትም፥ ብልጥግናዋንም እጅግ አበዛህ፤ የእግዚአብሔርን ወንዝ ውኃን የተመላ ነው፤ ምግባቸውን አዘጋጀህ እንዲሁ ታሰናዳለህና። ትልምዋን ታረካለህ፥ ቦይዋንም ታስተካክላለህ፤ በነጠብጣብ ታለሰልሳታለህ፥ ቡቃያዋንም ትባርካለህ። በቸርነትህ ዓመትን ታቀዳጃለህ፥ ምድረ በዳውም ስብን ይጠግባል። የምድረ በዳ ተራሮች ይረካሉ፥ ኮረብቶችም በደስታ ይታጠቃሉ። ማሰማርያዎች መንጎችን ለበሱ፥ ሸለቆችም በእህል ተሸፈኑ፤ በደስታ ይጮኻሉ ይዘምራሉም” እንዲል። (መዝ. ፷፬፥፱-፲፫)
ቅዱስ ዮሐንስ
ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያናችንም ዓመታትን በቸርነቱ ለሚያቀዳጅ ለእግዚአብሔር ምስጋና ለማቅረብ የአዲሱን ዓመት መጀመሪያ ወይም ርእሰ ዐውደ ዓመት “ቅዱስ ዮሐንስ” በሚል ስያሜ ስታከብረው ኖራለች፣ ትኖራለችም። ይህም ሊሆን የቻለበት ምክንያት የመጥምቁ ዮሐንስ ተግባር ለዘመነ ወንጌል በር ወይም መነሻ ሆኖ መገኘቱና የቤተ ክርስቲያን አበው የበዓላትን ድንጋጌ በወሰኑበት ጊዜ የመጥምቁ ዮሐንስ መታሰቢያ በዓል የኢትዮጵያ ርእሰ ዐውደ ዓመት በሚሆን መስከረም አንድ ቀን እንዲከበር በየዓመቱ የዘመኑ መጀመሪያ በእርሱ ስም እንዲጠራ በመደንገጋቸው ነው። (ድርሳን ዘቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ)፡፡ መጽሐፈ ስንክሳር የዓመቱን መጀመሪያ የሆነውን መስከረምን ሲያትት “ይህ የመስከረም ወር የተባረከ ነው፤ እርሱም የግብጽና የኢትዮጵያ ዓመቶች መጀመሪያ ነው” በማለት ያስረዳል።
የዘመን መለወጫ
ብርሃናት (ፀሐይ፣ ጨረቃ፣ ከዋክብት) የዓመት ዑደታቸውን በጳጉሜ ወር ጨርሰው በመስከረም ወር ስለሚጀምሩ ይህ ቀን የዘመን መለወጫ ተብሎ ይጠራል። ሌሊቱ ከቀኑ ጋር ይተካከላል፡፡ ዓመቱን ጠንቅቀው ቢቆጥሩ ፫፫፷፬ ቀናት ይሆናል፡፡ መጽሐፈ ሄኖክ ይህን ሲገልጽ “ሌሊቱም ከቀኑ ጋራ ይተካከላል፡፡ ዓመቱም ጠንቅቆ ቢቆጥሩት ሦስት መቶ ስልሳ አራት ቀን ይሆናል፡፡ (ሄኖ. ፳፮፥፻፬) ነቢየ እግዚአብሔር ኤርምያስም አዲሱን ዓመት በተመለከተ ሲገልጽ “ዘመናችንን እንደ ቀድሞ አድስ” (ሰ.ኤር. ፭፥፳፩) በማለት በኃጢአት የወደቅን በንስሓ ተነሥተን፣ የቀማን መልሰን፣ በአዲስ ሰውነትና በአዲስ አስተሳሰብ ከእግዚአብሔር ጋር እርቅ የምንፈጽምበት፣ በሕይወታችንም እንድንለወጥና እንድታደስ ይመክረናል፡፡
ዕንቁጣጣሽ
ከሁለት አበይት ምክንያት መጠሪያ እንደሆነ ሊቃውንት ይናገራሉ፤ የመጀመሪያው ምክንያት የኖኅ ልጅ ካም ከወንድሞቹ ጋር ምድርን ሲከፋፈሉ በዕጣ አፍሪካ ስትደርሰው መጀመሪያ ያረፈው ኢትዮጵያ ላይ በመስከረም ወር ሲሆን በዚህ ጊዜ የምድሩንና የአበቦቹን ማማር አይቶ ደስ ብሎት”ዕንቁ ዕጣ ወጣሽል” ሲል ይህችን ወቅት እንቁጣጣሽ ብሏታል። ሁለተኛው ንጉሡ ሰሎሞን ለንግሥት ሳባ “ዕንቁ ለጣትሽ ጌጥ ይሁንልሽ” ሲል እጅግ በጣም የከበረ ዕንቁ ያበረከተላት በዚህ በመስከረም ወር ስለነበር፤ ከዚህ በመነሣት መስከረም አንድን እንቁጣጣሽ በሚለው ስያሜ እንደሚጠራ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ያስተምራሉ።
በአጠቃላይ ዘመን መለወጫ ከላይ ባየናቸው የተለያየ ስያሜ ይጠራ እንጂ ዘመኑ አዲስ እየተባለ ቢጠራም አዲስ መሆን ያለበት ወርና ወቅቱ ብቻ ሳይሆን የእኛ የክርስቲያኖች ሕይወት ነው፡፡ ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ “ወንድሞች ሆይ ሰውነታችሁን ለእግዚአብሔር ሕያውና ቅዱስ ደስ የሚያሰንም መስዋዕት አድርጋችሁ ታቀርቡ ዘንድ በእግዚአብሔር ርኅራኄ እማልዳችኋለሁ” እያለ በመዋዕለ ሥጋዌው ያስተምር ነበር፡፡ አዲስ ዓመት ሲመጣ በኃጢአት፣ በተንኮል፣ በክፋት የቆሸሸው ሰውነታችን በንስሓ፣ በቅዱስ ቊርባን፣ በመልካም ተግባር አዲስ ልናደርገው ይገባናል፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
Leave a Reply
Want to join the discussion?Feel free to contribute!