የግቢ ጉባኤ የደረጃ ሦስት ተተኪ መምህራን ሥልጠና ተጠናቀቀ
የማኅበረ ቅዱሳን ግቢ ጉባኤያት አገልግሎት ማሰተባበሪያ ከሃያ ማእከላት ለተውጣጡ ፴፱ መምህራን የደረጃ ሦስት ሥልጠናን ከነሐሴ ፳፯ እስከ ጳጉሜን ፫ ቀን ፳፻፲፮ ዓ.ም ድረስ በመስጠት በሠርተፍኬት አስመረቀ፡፡
ሥልጠናው በሰባት የትምህርት ዓይነቶች ማለትም፡- ትምህርተ ሃይማኖት፥ አንጻራዊ ትምህርተ ሃይማኖት፥ ነገረ ድኅነት፥ የቤተ ክርስቲያን ታሪክ፥ የአንድምታ ወንጌል አጠናን ስልት፥ ነገረ አበው፥ አርአያነት ያለው የመምህራን ሕይወት በሚሉ ርእሰ ጉዳዮች ላይ ያተኮሩ ሲሆኑ በቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን በአገልግሎት በሚታወቁ መምህራን ተሰጥቷቸዋል፡፡ በተጨማሪም በማኅበረ ቅዱሳን ዋና ፀሐፊ ከሠልጣኞች የማኅበሩን አገልግሎት በተመለከተ ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ሰፋ ያለ ማብራሪያ በመስጠት ቅድስት ቤተ ክርስቲያንን የማገልግል ተልእኮአቸውን እንዲወጡ በአደራ ጭምር መልእክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡
መልአከ ታቦር ኃይለ ኢየሱስ ፋንታሁን “አርአያነት ያለው የመምህራን ሕይወት” በሚል ርእስ ማንበብን ገንዘብ እንዲያደርጉ፣ የአባቶችን ፍኖት ተከትለው እንዲጓዙ፣ በሥነ ምግባር ታንጸው የሚገጥማቸውን ፈተና በጽናት በማለፍ የተጣለባቸውን ኃላፊነት እንዲወጡ ሰፋ ባለ ሁኔታ በምክርና በተግሣጽ ላይ ያተኮረ ሕይወት ተኮር ትምህርት ተሰጥቷቸዋል፡፡
ከሠልጣኞቹ መካከል ከመቱ ማእከል የመጡት ዲ/ን ዘመኑ ለማ ሥልጠናውን በተመለከተ በሰጡት አስተያየት “ከአቀባበል ጀምሮ በመምህራኑ የተሰጠን ሥልጠና ከዚህ በፊት የነበረንን ዕውቀት የሚያሳድግ፣ እንዲሁም ያለንን የአገልግሎት ትጋት ከፍ የሚያደርግ ነው” ብለዋል፡፡ “ዕውቀትና ትግባር ተኮር ትምህርት ነው የተሰጠን፡፡ ያለብንን የዕውቀት ክፍተት ለመሙላትና በተሻለ አቅም እንድናገለግል የሚያግዘን ሥልጠና ነው” ያሉት ደግሞ ከአርሲ ግቢ ጉባኤ የመጡት ዲ/ን ቢንያም አስናቀ ናቸው፡፡
ሥልጠናውን ከተሳተፉት ውስጥ በሥልጠናው በመሳተፋቸው ያገኙትን ሲገልጹም “በመምሀራኑ የተሰጠን ሥልጠና ወደፊት አቅማችንን በማንበብ እንድናሳድግ የሚያደርገን ነው፡፡ ዕይታችንን የሚያሰፋ ሥልጠና ነውና የወሰድነው ወደፊትም ተጠናክሮ ቢቀጥል” ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡፡፡
በመጨረሻም ሥልጠናውን ካጠናቀቁ በኋላ የምሥክር ወረቀት የተሰጣቸው ሲሆን የማኅበረ ቅዱሳን ግቢ ጉባኤያት አገልግሎት ማስተባበሪያ ዋና ኃላፊ የሆኑት አቶ አበበ በዳዳ ለሠልጣኞቹ መምህራን መልእክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡ “ማኅበረ ቅዱሳን ከተሰጡት ኃላፊነቶች ውስጥ ዋነኛው የግቢ ጉባኤያት ተማሪዎችን የቅድስት ቤተ ክርስቲያንን ትምህርት ማስተማር ነው፡፡ እናንተም ይህንን ኃላፊነት እንድትሸከሙ ነው ሥልጠናውን የወሰዳችሁት፡፡ በዚህም መሠረት ለትውልዱ አርአያ የሚሆኑ ኦርቶዶክሳውያንን ማፍራት እንድትችሉ በንባብ ራሳችሁን በማሳደግ ለአግልግሎት እንድትፋጠኑ አደራ እንላለን” ብለዋል፡፡
የደረጃ ሦስት የተተኪ መምህራን ሥልጠና ሲሰጥ ይህ ለሦስተኛ ጊዜ ሲሆን ወደፊትም የሚቀጥል መሆኑን አስተባባሪዎቹ ገልጸዋል፡፡
Leave a Reply
Want to join the discussion?Feel free to contribute!