ወርኃ ጳጉሜን
ወርኃ ጳጉሜን
የጳጕሜን ወር አሥራ ሦስተኛዋ ወር በማለት እንጠራታለን፡፡ አሥራ ሁለቱ ወራት እያንዳንዳቸው ሠላሳ ቀናት ያሏቸው ሲሆን የጳጕሜን ወር ግን ያሏት አምስት (በዘመነ ማቴዎስ፣ በዘመነ ማርቆስ፣ በዘመነ ሉቃስ) እና በየአራት ዓመቱ በዘመነ ዮሐንስ ደግሞ ስድስት ቀናትን ትይዛለች፡፡ በቤተ ክርስቲያናችን አስትምህሮም የጳጕሜን ወር የዓመት ተጨማሪ ወር ትባላለች፡፡
ጳጕሜን “ኤፓጉሜኔ” ከሚለው የግሪክ ቃል የመጣ ሲሆን ትርጉሙም “ጭማሪ” ማለት ነው፡፡ በግእዝ “ወሰከ፤ ጨመረ” ከሚለው የግእዝ ግስ የወጣ ተውሳክ (ተጨማሪ) ማለት ነው፡፡ (አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ፤ መዝገበ መጽሐፈ ሰዋስው ወግስ ወመዝገብ ቃላት፤ ገጽ ፱፻፭)
የጳጕሜን ወር በየዓመቱ የክረምትን ወር አሳልፈን ወደ ጸደይ ወቅት የምንሸጋገርባት እንደሆነች ሁሉ በኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የጳጕሜን ወር የዓለም ፍጻሜ መታሰቢያ ተደርጋም ትታሰባለች፡፡ ጌታችን መድኃኒታችን ኢያሱስ ክርስቶስ ይህቺን ምድር ያሳልፋት ዘንድ በክበበ ትስብዕት፣ በግርማ መለኮት በቅዱሳን መላእክት ታጅቦ የሚመጣበት፣ የዓለም መከራና ችግር እንዲሁም ሥቃይ የሚያበቃበት መሆኑን የርስት መንግሥተ ሰማያት ማሳያ ናት ጳጕሜን፡፡
ወደ አዲስ ዘመን ስንሸጋገር አዲስ ተስፋና በጎ ምኞትም ይዘን “ኑ የአባቴ ብሩካን ዓለም ሳይፈጠር የተዘጋጀላችሁን መንግሥት ውረሱ” የሚባሉባት እንደ መሆኑ ጳጕሜን ወር አዲሱን ዓመት ለመቀበል የምንዘጋጅበት ጊዜ ነው፡፡ (ማቴ. ፳፭፥፴፬) በዚህች በተሰጠን የጭማሪ ወር ተጠቅመን ለነፍሳችን ድኅነት የሚሆነን ስንቅ በመያዝ አዲሱን ዘመን ልንቀበል ያስፈልጋል፡፡
ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ገዳመ ቆሮንቶስ በፈቃዱ በሄደ ጊዜ ከቆመ ሳይቀመጥ፣ ከዘረጋ ሳያጥፍ ለአርባ ቀንና ሌሊት በዲያብሎስ ቢፈተንም ዲያብሎስን ድል ነሥቶ ከፊቱ አሰወግዶታል፡፡ ከጾሙም በኋላ የሥራው መጀመሪያ ያደረገው በኢየሩሳሌም እየተዘዋወረ አስተምሯል፣ ድውያንን ፈውሷል፣ ለምጻሙን አንጽቷል፣ ሺባውን ተርትሯል፣ የተራቡትን አብልቷል፣ የተጠሙትንም አጠጥቷል፣ ልዩ ልዩ ተአምራትንም አድርጓል፡፡
ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከትንሣኤው በኋላ ቅዱሳን ሐዋርያትን ከኢየሩሳሌም እንዳይወጡ አስጠንቅቋቸው ለአርባ ቀናት መጽሐፈ ኪዳንን እያስተማራቸው ቆይቷል፡፡ ከዚያም “ሂዱና አሕዛብን በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም እያስተማራችኋቸውና እያጠመቃችኋቸው ክርስቲያን አድርጓቸው” ብሏቸዋል፡፡ ሀገረ ስብከታቸውን ተከፋፍለው ለአገልግሎት ከመሰማራታቸው በፊት ግን መምህራቸውን አብነት አድርገው በጾም በጸሎት ተወስነው ቆተዋል፡፡ ይህንንም ጾም ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ከሰባቱ የአዋጅ አጽዋማት አንዱ አድርጋ ሥርዓት ሠርታለች፡፡ የአገልግሎት መጀመሪያ በጾም ጸሎት መወሰን፣ ፈቃደ እግዚአብሔርን መጠየቅ ዋጋ ያሰጣልና ኦርቶዶክሳውያን ምእመናን ይህንን የጳጉሜን ወር በፈቃድ ጾም ተወስነው ዓመቱ በሃይማኖት የሚጸኑበት፣ በጎ ሐሳባቸው ይፈጸም ዘንድ የሚተጉበት ይሆን ዘንድ ይጾሙታል፡፡
እኛም አዲሱን ዓመት ከመቀበላችን በፊት የበደልን ንስሓ ገብተን፣ ዓመቱን ሙሉ አቅደናቸው ያልሠራናቸውን ሥራዎች ዕቅድ የምናወጣበት፣ ከሁሉም በላይ መንፈሳዊ ሕይወታችንን በማጠንከር ከእግዚአብሔር ጋር እርቅ የምንፈጽምበት ጊዜ መሆኑን ተረድተን በአዲስ ማንነትና ሰውነት ታድሰን አዲሱን ዓመት ለመቀበል መዘጋጀት ይጠበቅብናል፡፡
ወርኃ ጳጉሜን የዮዲት ጾም ተብሎም በቤተ ክርስቲያናችን ይጠራል፡፡ ዮዲት በጾምና በጸሎት ተወስና በሕገ እግዚአብሔር በምትኖርበት ጊዜ በእርሷና በሕዝቡ ላይ የመጣውን መከራና ችግር አምላክ እንዲፈታላት የያዘችው ሱባኤ ከእግዚብሔር ዘንድ ምላሽና መፍትሔ እንዳሰጣት ሁሉ እኛም የችግራችን ቋጠሮ እንዲፈታልንና ካለንበት የመከራ አረንቋ አውጥቶ ወደ በጎ ዘመን እንዲያሸጋግረን ተስፋ በማድረግ ልንጾም እና በጸሎት ልንማጸን ይገባል፡፡
እምነት ኃይልን ታደርጋለችና አምላካችን እግዚአብሔር ችግራችን እንደሚፈታልን በማመን በጾምና በጸሎት ብትንጋ ምላሽ እናገኛለን፡፡ በጾምና በጸሎት የተጋችው ዮዲት ጠላቶቿን ድል ማድረግ እንደምትችል በማመን ካሉበት ድረስ በመሄድ የተፈጥሮ ውበቷን ተጠቅማ አሸንፋለች፡፡
ከዚያ ሁሉ አስቀድማ ግን ማድረግ ስላሰበችው ነገር የአምላኳን ርዳት በሱባኤ ጠይቃ ስለነበር ያለ ምንም ፍራቻ ለምታምንበት ነገር ሽንፈትም ሆነ ውድቀትን ሳታሳብ ያለ ጥርጣሬ ጠላቷን ተጋፍጣ አሸንፋዋለች፡፡ በዚህም ከራሷ አልፎ ለሀገሯ ሕዝብ መዳንና የሀገር ሰላም መገኛ ሆናለች፡፡ እኛም ይህን ያለ ጥርጣሬ በማመን በዚህ በከፋ ወቅት በአንድነት ሆነን አምላካችን እንለምን፤ ኅብረት ጥንካሬ ነውና፡፡ የተሰጠንን የጊዜ ጭማሪ በመጠቀምም በጾም ተወስነን አብዝተን እንማጸን፡፡ እንደ ዮዲት ማቅ ለብሰን፣ አመድ ነስንሰንና ድንጋይ ተንተርሰን አብዝተን ልንጾምና ልንጸልይ ይገባል፡፡ ከመከራና ሥቃይ እንዲሰውረን፣ የእርስ በእርሱን ጦርነት እንዲገታልን፣ ያጣነውን ሰላም፣ ፍቅርና አንድነትን እንዲመልስልን መጸለይና መጾም ያስፈልጋል፡፡
Leave a Reply
Want to join the discussion?Feel free to contribute!