ወቅታዊ ጉዳዮችን በማስመልከት ከማኅበረ ቅዱሳን የተሰጠ መግለጫ
የቤተ ክርስቲያናችን ስደት የሚቆመው ሁላችንም ድርሻችንን ስንወጣ ነው!!!
“ለቅዱሳን አንድ ጊዜ ስለተሰጠ ሃይማኖት እንድትጋደሉ እየመከርኳችሁ እጽፍላችሁ ዘንድ ግድ ሆነብኝ፡፡” (ይሁዳ ፩፥፫)
ማኅበረ ቅዱሳን ከሦስት ዓመት በፊት ግንቦት ወር 2013 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ እንደገለጸው ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ከ1950ዎቹ ጀምሮ ሁለንተናዊ የአስተሳሰብ ውጊያ ሲደረግባት ቆይቷል፡፡ ይህ የአስተሳሰብ ውጊያ በጊዜ ሂደት መዋቅራዊና ስልታዊ ሆኖ ቀጥሎ ይኸው ዛሬም ቤተ ክርስቲያን ከስደት አልተመለሰችም፡፡ ይልቁንም የቤተ ክርስቲያን መከራና ስደት በዓይነቱ ተለይቶ፣ ድግግሞሹ በዝቶ፣ በመጠኑም ጨምሮ ቀጥሏል፡፡ ለዚህም ባሳለፍናቸው ሦስት ዓመታት ውስጥ በቤተ ክርስቲያንና በልጆቿ ላይ ተጠናክረው የተፈጸሙ ድርጊቶች በቂ ማሳያዎች ናቸው፡፡ በተለያዩ ቦታዎች በተከታታይ ካህናት፣ መነኮሳትና ምእመናን በሃይማኖታቸው ተለይተው ተገድለዋል፣ ተሰደዋል፣ አብያተ ክርስቲያናትና ገዳማት ተቃጥለዋል፡፡ በተጨማሪም ንብረታቸውንም እንዲያጡ ተደርገዋል፡፡ የቤተ ክርስቲያን መዋቅርም እንዲናጋ ከፍተኛ ጥረት ተደርጓል፡፡
በአጠቃላይ በውስጥና በውጭ ባሉ የቤተ ክርስቲያን ጠላቶች ቅንጅት የቤተ ክርስቲያንን አንድነት የሚፈታተኑ ተግባራት በድፍረትና በማን አለብኝነት ተፈጽመዋል፡፡ በቅርቡም የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ ወደ ሀገር ውስጥ እንዳገቡ መደረጋቸው፣ በተመሳሳይ በዝቋላ ገዳም መናኝ አባቶች ላይ የተፈጸመው የግፍ ግድያ በቤተ ክርስቲያን ላይ የተፈጸመ መዋቅራዊ ጥቃት ማሳያ ነው፡፡
ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት በነነዌ ጾም መልእክታቸው ላይ እንዳስተላለፉት፡፡
“ይህንን የነነዌ ጾም ልንቀበል ዋዜማ ላይ ባለንበት በዚህ ጊዜ በቤተ ክርስቲያናችን ጥንታዊ ከሆኑት ገዳማት አንዱ በሆነው በዝቋላ ደብረ ከዋክብት አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ገዳም የሚገኙ፣ ዓለሙን ትተው በፈቃዳቸው ረኃብተኛ እና ጥማተኛ ሆነው ሀገርን በጸሎት የሚጠብቁ መነኮሳት ጫካው መኖሪያችሁ፣ ዳዋው ልብሳችሁ፣ ቅጠሉ ምግባችሁ መሆን አይችልም ተብለው የሰማዕትነት ጽዋ ተጎንጭተዋል፡፡ እነርሱ በሥጋ እየሞቱ እኛም በየቀኑ ሟቾችን እየቆጠርን በኀዘን ለመኖር የተፈረደብን ሆኗል” ብለዋል፡፡
በሀገራችን ውስጥ የሕግ የበላይነት እስካልሰፈነና ጠያቂና ተጠያቂ እስካልኖረ ድረስ ወደፊትም በባሰ ሁኔታ ሊቀጥል ይችላል፡፡ በመሆኑም የቤተ ክርስቲያን ስደት ይቆም ዘንድ የቤተ ክርስቲያን ልዕልና ይከበር ዘንድ ሁላችንም የድርሻችንን ለመወጣት በያለንበትም ሆነ በጋራ በመናበብ ከሕጻን እስከ አዋቂ፣ ከሊቅ እስከ ደቂቅ የሥጋ ጥቅምን፣ ምድራዊ ሥልጣንና የግል ፍላጎትን አስወግደን በቤተ ክርስቲያን ጉዳይ ሁላችንም ቁርጥ መንፈሳዊ አቋም በመያዝ ለሃማኖታችን ዘብ ልንቆምና የድርሻችንን በትጋት ልንወጣ እንደሚገባ ማኅበረ ቅዱሳን እያሳሰበ ለቤተ ክርስቲያን አካላት ሁሉ ጥሪውን ያስተላልፋል፤
- የተከበራችሁ አበው ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ሆይ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ በመልእክቱ “በገዛ ደሙ የዋጃትን የእግዚአብሔርን ቤተ ክርስቲያን ትጠብቁ ዘንድ መንፈስ ቅዱስ እናንተን ጳጳሳት አድሮ ለሾመባት ለመንጋው ሁሉና ለራሳችሁ ተጠንቀቁ” እንዳለ በዚህ ታላቅ የፈተና ወቅት የቤተ ክርስቲያንን አንድነት ለማስጠበቅ፤ ቅዱስ ሲኖዶስ የሰጣችሁን ኃላፊነት ለመወጣት ምእመናንን አቅጣጫ በመስጠት የቀደሙ አባቶቻችሁን ፈለግ በመከተል ዛሬም በጽናት እንድትተጉ፤ ያከበረቻችሁን ቤተ ክርስቲያን በአንድነት ሆናችሁ እንድትጠብቁ በልጅነት መንፈስ በትሕትና እንጠይቃለን፡፡ በተጨማሪም የአባትነት የዋህ ልቡናችሁን በመጠቀም ያዘኑ፣ የጠቀሙ፣ የተቆረቆሩ መስለው ቀርበው የግል ፍላጎታቸውን ለመፈጸም የሚጥሩ ስለሚኖሩ ሁሉንም በጥንቃቄ እንድትመረምሩ፣፤ ቀኖች ክፉዎች ናቸውና ዘመኑን በመዋጀት አንድነታችሁን እንድታጠነክሩና በቤተ ክርስቲያን ዙሪያ ለሚፈጠሩ ችግሮች በጥልቀት እንድትወያዩና እንድትመካከሩ እናሳስባለን፡፡
- ከዚህ ውጭ ቤተ ክርስቲያንን በማይጠቅማት ጉዳይ የግል ፍላጎትንና ምድራዊ ዓላማን መሠረት አድርጋችሁ ከቤተ ክርስቲያን ሕግ ቀኖና ውጭ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊን ለመተካት፣ ፓትርያርክ ለመሾምና የመሳሰሉትን ለመፈጸም የምትንቀሳቀሱ አንዳንድ አባቶች ከድርጊታችሁ እንድትታቀቡ ለማሰብ እንወዳለን፡፡ ማኅበራችን ይህንን ጉዳይ እየተከታተለ መረጃውን ለምእመናን የሚያደርስ መሆኑንም በዚሁ አጋጣሚ እንገልጻለን፡፡
- ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን፣ መምህራነ ወንጌል፣ ካህናት ሆይ በጸሎትና በትምህርት ምእመናንን በማጽናናት፤ ከእውነት ጋር በመቆም እውነታውን በማሳየት ምእመናን ለቤተ ክርስቲያን ዘብ እንዲቆሙ በማድረግ ድርሻችሁን እንድትወጡ እናሳስባለን፡፡
- ውድ ምእመናንና የማኅበራችን አባላት የታሪክ አጋጣሚ ሆኖ በዚህ ዘመን ቤተ ክርስቲያንን ከአሳዳጆቿ የመጠበቁ ዋነኛ ኃላፊነት በዘመኑ ባለን ብፁዓን አባቶች፣ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን፣ ካህናትና ምእመናን ሁላችን እጅ ላይ ወድቆአል፡፡ የቤተ ክርስቲያንን ጉዳይ ለአባቶችና ለካህናት ትተን “እኔ አያገባኝም፣ አይመለከተኝም” ልንል አይገባም፡፡ ሁሉም በየድርሻው ቤተ ክርስቲያኑን ለመጠበቅ መትጋት አለበት፡፡ በቤተ ክርስቲያን ላይ የደረሰውን ጥፋትና ሊመጣ ያለውን ፈተና አስቀድሞ በመረዳት ቅዱስ ሲኖዶስ ቀደም ሲል በወሰነው መሠረት በየአጥቢያችን፤ በተለያየ መልኩ በመደራጀት፤ በቤተ ክርስቲያን ላይ ጥፋት ለማድረስ የሚመጡትን በመከላከል የቤተ ክርስቲያንን ስደት ለማስቆም መንፈሳዊ ግዴታችን እንድንወጣ እንጠይቃለን፡፡
- በቤተ ክርስቲያን ውስጥ በልዩ ልዩ አገልግሎት እየተሳተፋችሁ ያላችሁ ሰንበት ትምህርት ቤቶች፣ ማኅበራትና ሌሎችም ሁላችንም አንድነታችንን በመጠበቅ በጋራ አገልግሎቶችን በመፈጸም ድርሻችንን እንድንወጣ ለተግባራዊነቱ ጥሪ እናቀርባለን፡፡
- ገዳም ድረስ ገብቶ መሳሪያ ያልያዙና ራሳቸውን እንደ ሞቱ ቆጥረው እየኖሩ ያሉ መነኮሳት ላይ ግድያ የፈጸመ ማንኛውም የታጠቀ ኃይል (መደበኛም ይሁን ኢመደበኛ፣ በግልም ይሁን በቡድን፣ አማኝም ይሁን ኢአማኝ) ድርጊቱ ከሰውነት ተፈጥሮ የወጣ ነው፡፡ ምናኔንና የክህነት ክብርን በተቃረነ መልኩ ሰብእና የጎደለው ጥቃት ማድረስ ኢትዮጵያዊ ባህልም አይደለም፡፡ ጥቅም የሌለው ከንቱ ተግባር ነው፡፡ በዚህ የሚገኝ የፖለቲካ ትርፍ ይኖራል ብለን አናምንም፡፡ ጤነኛ በሆነ አእምሮ ታስቦ የተፈጸመ ነው ማለትም አይቻልም፡፡ ማስተዋል ተወስዶባቸው እውቀት ተሰውሮባቸው እንጂ ይህንን ማድረግ ቀርቶ ማሰቡም የሙት ሐሳብ ነው፡፡ ቀድሞ የሞተው ሟቹ ሳይሆን ገዳዩ ነው፡፡ በዚህ መንገድ የቤተ ክርስቲያን አማኞች ሲበዙ እንጂ ሲያንሱ በታሪክ አልታየም፡፡ ይህ ድርጊት ክርስቲያኖችን ሲያጠነክር እንጂ ሲያዳክም ታይቶ አይታወቅም፡፡ መጽሐፍ ጎርፍም መጣ፣ ነፋስም ነፈሰ፣ ያንን ቤት ገፋው፤ በዐለት ላይ ስለተመሠረተ አልወደቀም” ባለው መሠረት ቤተ ክርስቲያን በጽኑ ዐለት ላይ የተመሠረተች ስለሆነ አታሸንፏትም፡፡ ዲዮቅልጥያኖስም አላጠፋትም፤ ዲያብሎስም ዝናሩን እንዲሁ ጨረሰ፡፡ ስለዚህ አትድከሙ፤ አትሳቱም፡ እናንተ ሳትወለዱም የነበረች ቤተ ክርስቲያን እናንተም አልፋችሁም እንደ እናንተ ላሉት በስሑት መንገድ ለሚጓዙት ሁሉ እየጸለየች ትቀጥላለች፡፡ ሐሳቧም፣ ሥራዋም፣ ዓላማዋም፣ ግቧም ሰማያዊ ነውና፡፡
በመጨረሻም ማኅበረ ቅዱሳን ከቤተ ክርስቲያን ሕልውና በላይ የሚያስቀድመው የሌለ በመሆኑ ቤተ ክርስቲያን የገጠማትን ፈተና ለማለፍ ከሚመለከታቸው የቤተ ክርስቲያን አካላት ጋር በመናበብ የሚጠበቅበትን መንፈሳዊ ግዴታ ለመወጣት ዝግጁ መሆኑን በዚሁ አጋጣሚ እያሳወቅን የሁላችንም መሰባሰብና የአገልግሎት ማእከል ቤተ ክርስቲያን በመሆኗ ከሁሉም ነገር በፊት ቅድሚያ ሰጥተን ሊመጣ ካለው አደጋ ቤተ ክርስቲያናችንን የመጠበቅ ኀላፊነት በትጋት እንወጣ ሲል ማኅበረ ቅዱሳን በአክብሮት ጥሪውን ያቀርባል፡፡
ረድኤተ እግዚአብሔር አይለየን!!!
Leave a Reply
Want to join the discussion?Feel free to contribute!