“ለግቢ ጉባኤ ትምህርቴ የመደበኛው ትምህርቴን ያህል ትኩረት ስሰጠው ነበር፡፡” (ዲ/ን ፕ/ር እንግዳ አበበ)

ክፍል አንድ                                             

በእንዳለ ደምስስ

ዲ/ን ፕ/ር እንግዳ አበበ በ፲፱፻፹፯ ዓ.ም ከኮልፌ አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የ፲፪ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተናን ፬ ነጥብ በማምጣት በ፲፱፻፹፰-፲፱፻፺፬ ዓ.ም በጅማ ዩኒቨርስቲ የሕክምና ትምህርታቸውን ተከታትለዋል፡፡ በሰባት ዓመታት የሕክምና ትምህርት ቆይታቸው ከትምህርት ክፍሉ እና ከአጠቃላይ የዩኒቨርሲቲው ተመራቂዎች በከፍተኛ ማዕረግ የሜዳልያ ተሸላሚ በመሆን የሕክምና ትምህርታቸውን አጠናቀዋል፡፡ ባስመዘገቡት ውጤት መሠረትም በዩኒቨርሲቲው ለሁለት ዓመታት በመምህርነት ተመድበው አገልግለዋል፡፡

ለሰባት ዓመታት በዩኒቨርሲቲው ትምህርታቸውን ሲከታተሉ በየዓመቱ ዩኒቨርሰቲው የሚያዘጋጃቸውን ሽልማቶች በተደጋጋሚ ለመቀበል ችለዋል፡፡ እንዲሁም በዩኒቨርሲቲው በቆዩባቸው ጊዜያት በግቢ ጉባኤ ውስጥ በንቃት ከሚሳተፉ ወንድሞችና እኅቶች መካከል ነበሩ፡፡

ፕ/ር እንግዳ በሙያቸው በተለያዩ ሆስፒታሎች ውስጥ ያገለገሉና በቅዱስ ጳውሎስ ሚሊኒየም ሆስፒታል ውስጥ በሚገኘው የሕክምና ኮሌጅ ውስጥ በኃላፊነትና በመምህርነት እያገለገሉ ይገኛሉ፡፡ በሙያቸው ባበረከቱት አስተዋጽኦም ከተለያዩ ተቋማት ሽልማቶችን ለማግኘት የቻሉ ባለሙያ ናቸው፡፡

በዚህም መሠረት የካቲት ፲ ቀን ፳፻፲፬ ዓ.ም የቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሊኒየም ሕክምና ኮሌጅ የማኔጅመንት ቦርድ የዶ/ር እንግዳ አበበን መረጃዎች ከገመገመ በኋላ የሙሉ ፕሮፌሰርነት ማዕረግ ለመጀመሪያ ጊዜ ሰጥቷል፡፡ ፕሮፌሰር እንግዳ አበበ ገላን የሕክምና ዲግሪያቸውን (MD) ከጅማ ዩኒቨርሲቲ ፣ የቀዶ ሕክምና ስፔሻሊቲ ዲግሪያቸውን ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በቀዶ ሕክምና እንዲሁም የሰብ-ስፔሻሊቲ ዲግሪያቸውን በኩላሊት ንቅለ ተከላ ከቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሊኒየም የሕክምና ኮሌጅ ያገኙ ሲሆን፤ የተለያዩ አጫጭር የሞያ ሥልጠናዎችን በአገር ውስጥ እና በውጭ አገር መከታተላቸውን የሕክምና ኮሌጁ አስታውቋል፡፡

ፕሮፌሰር እንግዳ አበበ ገላን በግላቸውና ከሙያ አጋሮቻቸው ጋር ከ፵ በላይ በምርምር የተደገፉ ጥናታዊ ፅሁፎችን በታወቁ አገራዊና ዓለም አቀፋዊ መጽሔቶች ላይ ለኅትመት አብቅተዋል፡፡ በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሕክምና ኮሌጅ በሚገኘው የሕክምና ትምህርት ቤት ውስጥ የቀዶ ሕክምና ትምህርት ክፍል ኃላፊ ሆነው በማገልገል ላይ ይገኛሉ።

ወደ ቃለ ምልልሳችን ከመግባታችን በፊት አብረዋቸው የሚሠሩ ባለሙያዎች ስለ ዲ/ን ፕ/ር እንግዳ አበበ የሰጡትን የምስክርነት ቃል በጥቂቱ እነሆ፡-

“እጅግ በጣም ታታሪ እና ትሁት ስለሆነው ፕ/ር እንግዳ አበበ ሳወራ በኩራት ነው፡፡ ወደ ቀዶ ጥገና ክፍል የሚሄድ ሁሉ ያውቀዋል፡፡ ጠዋት ታካሚዎችን ስንጎበኝ ለአንድ ቀን የተኛ ታካሚ እንኳን በእርሱ መታየት ይፈልጋል፡፡ በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል የሚማሩ ተማሪዎች ሁሉ እንደ እርሱ መሆን ይፈልጋሉ፡፡ በሆስፒታል ውስጥ በሚሠሩ ሰዎች ሁሉ የተከበረ ነው፡፡ የቀዶ ጥገና ፕሮፌሰርና የኩላሊት ንቅለ ተከላ ሐኪም የሆነው ፕ/ር እንግዳ አበበ ለእኛ ልዩ አርአያችን ነው፡፡” (ዶ/ር ፍራኦል)

“በእርሱ መማር መቻሌ ታላቅ ዕድል ነው፡፡ ሰው አክባሪ፣ ትሁት፣ እግዚአብሔርን የሚፈራ ሰው ነው፡፡”(ምሕረት ተዘራ)

“የተባረኩ እጆች፣ የሚደንቅ ዕውቀት ያለው ሰው ነው፡፡ ከእርሱ ጋር ቀዶ ጥገና ከገባህ የሚያሳስብህ አይኖርም፡፡”(ቶሌ ካን ያደቴ)

“በሀገራችን ካሉ ምርጥ የቀዶ ጥገና ሐኪሞች አንዱ ነው፡፡ ትህትናው፣ ዕውቀቱ እና ታማኝነቱ ሁሉም ተስማምተው ስለ እርሱ መልካምነት እንዲያወሩ አድርጎታል፡፡”(አዲስ ዓለም ገንታ)

“ፕ/ር እንግዳ እጅግ የምትደነቅ ትሁት እና ሥራ ወዳድ ሰው ነህ፡፡ አብሬህ በመሥራቴ ዕድለኛ እንደሆንኩ ይሰማኛል፡፡” (ቤላ ሮማን)

“እርሱ በጣም የሚደንቅና ታላቅ ሰብእና ያለው ሰርጀን ነው፤ በጣም ትሁት፣ ታታሪና ጠንካራ ሠራተኛ እንዲሁም ለታካሚዎች አክብሮት የሚሰጥ ሰው ነው፡፡ እርሱን በቃላት መግለጽ አይቻልም፡፡ በእርሱ በመማሬ በጣም ደስተኛ ነኝ፡፡” (አያንቱ ተስፋዬ)

ከላይ የቀረበው ምሥክርነት “Hakim 2011 Nominee” በተሰኝ ድረ ገጽ ላይ ያገኘነው መረጃ ሲሆን ከዲ/ን ፕ/ር እንግዳ አበበ ጋር በሕክምናው ዘርፍ የሠሩ እና የተማሩ ባለሙያዎች ናቸው፡፡ ለመሆኑ ዲ/ን ፕ/ር እንግዳ አበበ ማን ናቸው? በየጊዜው የግቢ ጉባኤያት ተማሪዎችን ታሳቢ በማድረግ በምናሳትማቸው የጉባኤ ቃና መጽሔት እትሞቻችን በግቢ ጉባኤያት ውስጥ ያለፉና የሕይወት ተሞክሯቸው ሌሎችን ያስተምራል ያልናቸውን ወንድሞችና እኅቶችን በቃና እንግዳ ዓምዳችን እናቀርባለን፡ እኛም በዚህ ዝግጅታችንም የግቢ ጉባኤ ቆይታቸውን መሠረት አድርገን ከሕይወት ተሞክሯቸው ያካፍሉን ዘንድ ዲ/ን ፕ/ር እንግዳ አበበን እንግዳችን አድርገናቸዋል፡፡ መልካም ቆይታ ይሁንላችሁ፡፡

ጉባኤ ቃና፡- ወደ ከፍተኛ ትምህርት ተቋም ከመግባትዎ በፊት ለቤተ ክርስቲያን የነበረዎትን ቅርበት ቢገልጹልን?

ዲ/ን ፕ/ር እንግዳ፡- ተወልጄ ያደግሁት አዲስ አበባ ነው፡፡ ልጅ ሆኜ እንደማንኛውም ሕፃን እናቴ ወደ ቤተ ክርስቲያን ትወስደኝና ታስቆርበኝ ነበር፡፡ በዕድሜ ከፍ ስል ከሌላ ጊዜ በተለየ ሁኔታ የፍልሰታ ለማርያም ጾምን በጉጉት እጠብቀው ስለነበር ከሰፈር ጓደኞቼ ጋር ወደ ቤተ ክርስቲያን በመሄድ እቆርብ ነበር፡፡ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቴን ስከታተልም ቅዱስ ራጉኤል ቤተ ክርስቲያን የረቡዕ ሠርክ እና እሑድ ከቅዳሴ በኋላ ልዩ ጉባኤ በየዐሥራ አምስት ቀኑ ይካሄድ ስለነበር ያለማቋረጥ እሳተፍ ነበር፡፡ በሠርክ ጉባኤም እየተገኘሁ በመማር ስለ እምነቴና ስለ ቤተ ክርስቲያን ለማወቅ ጥረት ከማድረግ ወደ ኋላ አላልኩም፡፡ በተለይም በወቅቱ ያስተምሩን የነበሩት መምህራን በዘመኑ ላለነው ወጣቶችና ኦርቶዶክሳውያን አርአያ ነበሩ ማለት ይቻላል፡፡ ስለዚህ ከልጅነቴ ጀምሮ ቤተ ክርስቲያንን ለማወቅና ስለ እምነቴ ለመረዳት የቻልኩትን አድርጌያለሁ ማለት እችላለሁ፡፡ ይህም በወጣትነት ዘመኔ ራሴን እንድገዛና በፈሪሃ እግዚአብሔር እንድታነጽ አድርጎኛል፡፡

ጉባኤ ቃና፡- የከፍተኛ ትምህርትን ለመከታተል ከቤተሰብ ርቆ መሄድ እንዴት ይገልጹታል?

ዲ/ን ፕ/ር እንግዳ፡- ከቤተሰብ መራቅ በራሱ አስፈሪ ያደርገዋል፡፡ ለአንዲት ቀን ከቤተሰብ ተለይቶ የማያውቅ ተማሪ በአንድ ጊዜ ወደተመደበበት ለመሄድ ሲታሰብ ከራስ አልፎ ቤተሰብ ውስጥ የሚፈጥረው ስጋት ቀላል አይደለም፡፡ በቤተሰብ በኩል ምክሮችና መመሪያዎች ይበዙብሃል፤ “እንዲህ አድርግ፣ እንዲህ ደግሞ አታደርግ” ትባላለህ፡፡ በዚህ ላይ ወጣትነት በራሱ አዲስ ነገር ለማየትና ለመሞከር ፍጥነት የሚታይበት ጊዜ ነው፡፡ ለተወሰኑ ቀናት አካባቢውን ለማጥናትና ለመልመድ ሲባል ቁጥብነት በተማሪው ዘንድ ይታያል፡፡

እኔ የተመደብኩት ጅማ ዩኒቨርሲቲ ነበር፡፡ እንደማንኛውም ተማሪ ፍርሃት ይኖራል፡፡ ነገር ግን ብዙ አልተቸገርኩም፡፡ ከእኛ ቀድመው ወደ ዩኒቨርሲቲው የገቡና የግቢ ጉባኤ ተሳታፊ የነበሩ ወንድሞችና እኅቶች አውቶቡስ ተራ ሄደው ነው የተቀበሉን፡፡ ቦርሳችንን ተሸክመው እየተንከባከቡ እግራችንን በሽሚያ አጥበው፣ አስመዘግበውን፣ ማደሪያ ክፍላችን ድረስ ወስደው ነው ያስገቡን፡፡ በዚህ እንክብካቤ ውስጥ ፍርሃት ይጠፋል፡፡ በጣም ደስ የሚል አቀባበል ነበር፡፡ አንዳንዶች ቶሎ ለመልመድ ቢቸገሩም በአብዛኛው ግን ቶሎ ይለምዳል፡፡ ስለዚህ እኔ አልተቸገርኩም ማለት እችላለሁ፡፡

ጉባኤ ቃና፡- ግቢ ጉባኤ ውስጥ መሳተፍ እንዴት ጀመሩ?

ዲ/ን ፕ/ር እንግዳ፡- ቀድሞ መርካቶ ቅዱስ ራጉኤል ቤተ ክርስቲያን ሠርክ ላይ ይሰጥ የነበረው የወንጌል ትምህርትና አገልግሎት በጣም ረድቶኛል፡፡ በተለይ በወቅቱ ያገለግሉ የነበሩ መምህራን እግር ሥር ቁጭ ብለን እንማር ስለነበር እኔም አንድ ቀን ወደ አገልግሎት እንደምገባና እንደ እነርሱ ባይሆንም የአቅሜን አበረክታለሁ የሚል ሕልም ነበረኝ፡፡ በወቅቱ በሚያገለግሉ ወንድሞቻችን ላይ በጣም መንፈሳዊ ቅናት እቀና ነበር፡፡ ጅማ ዩኒቨርሲቲ ስገባ የነበረው ግቢ ጉባኤ በጣም ጠንካራና የተደራጀ ነበር፡፡ አስተባባሪዎቹም የሚመጣውን ተማሪ የሚንከባከቡበት መንገድ አስደሳች ስለነበር ገብተን መንፈሳዊውን ማዕድ ለመካፈል አልተቸገርንም፡፡ ቤተ ክርስቲያን መሄድ የምትፈልጉ ኑ እናሳያችሁ እያሉም ይወስዱን ስለነበር እኔም ከፍተኛ ፍላጎት ስለነበረኝ ለመግባት ችያለሁ፡፡  እኛን ለማቅረብና ግቢ ጉባኤ ውስጥ እንድንማር የሚያደርጉት ጥረት፣ በዚያውም እንደ አቅማችን በአገልግሎት እንድንሳተፍ ያበረታቱን ነበር:: የመጀመሪያ ዓመት ላይ በግቢ ጉባኤው አማካይነት ይሰጥ የነበረውን መንፈሳዊ ትምህርት በመማር ነው ያሳለፍኩት፡፡ መምህራኖቻችንም ቤተ ክርስቲያንን እንድንወድ፣ የጸሎት ሕይወት እንዲኖረን፣ ጊዜያችንን አጣጥመን ውጤታማ ሆነን እንድንወጣ ዘወትር ይመክሩን ነበር፡፡

ይቆየን

0 replies

Leave a Reply

Want to join the discussion?
Feel free to contribute!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *