ወጣትነት እና እጮኝነት
በዲ/ን ኢያሱ መስፍን
ክፍል ሦስት
የእጮኝነት ጊዜ
ተገቢውን ዝግጅት እና ጥንቃቄ አድርጎ እጮኛውን የመረጠ ሰው እስከሚያገባበት ቀን ድረስ እጮኛ መሆኑ የሚሰጠው ብዙ የተለየ መብት አይኖርም። የትዳር ተስፋ ያላቸው ከመሆኑ ባሻገር ከልብ ጓደኛና፣ የተለየ አካላዊ ግንኙነት እንዲኖራቸው ለእጮኛሞች አይፈቀድም። ከጋብቻ በፊት የሚደረግ ሩካቤ ዝሙት ነው። ሩካቤ ሳይፈጸም ጾታዊ ደስታን ለማግኘት የሚፈጸሙ እንደ መሳሳም፣ መተቃቀፍ፣ መነካካት ያሉ ድርጊቶች መጽሐፍ ቅዱስ መዳራት ብሎ የሚጠራቸውና ያልተፈቀዱ የኃጢአት ሥራዎች ናቸው። መጽሐፍ ቅዱስ ይዞ መማማል፣ በንስሓ አባቶች ፊት ቃል መገባባት፣ ያለ ቤተ ክርስቲያን ዕውቅና አብሮ ሄዶ መቁረብ፣ ያለ ቤተ ክርስቲያን ዕውቅና ቀለበት መተሳሰር እና የመሳሰሉት ድርጊቶች እጮኛሞች አካላዊ ግንኙነት እንዲኖራቸው መብት የሚሰጡ አይደሉም። መሓላ በራሱ ኃጢአት ከመሆኑም በተጨማሪ (ማቴ 5፡34) ጋብቻን ሊተካ የሚችል አይደለም። አንዳንድ ንስሓ አባቶች ልጆቻቸው አንዳቸው ሌላኛውን እንዳይበድሉ በማሰብ እርሳቸው ባሉበት ቃል እንዲገባቡ የሚያደርጉ ሲሆን ይህ የማይበረታታ እና ብዙ ችግር ይዞ ሊመጣ የሚችል ድርጊት ነው። አንደኛ ይህንን ቃል እንደ ጋብቻ ቆጥረው ወደ ሩካቤ የሚገቡ ጥንዶች ይኖራሉ፡፡
እንዲሁም እጮኝነት የትውውቅ ጊዜ እንደመሆኑ የእጮኞቻቸውን ክፉ አልያም ሊሻሻል የማይችል እና ከነርሱ ፈቃድ ጋር የማይሄድ ነገር ያዩ ሰዎች ሐሳባቸውን እንዳይቀይሩና ተገቢውን ጥንቃቄ እንዳያደርጉ የገቡት ቃል የሚያስጨንቅ እስራት ይሆንባቸዋል። ይህን እና ይህን የመሰለውን ፈተና ይዞ ስለሚመጣ ቤተ ክርስቲያን በሠርጋችን ዕለት ቃል እስክታስገባን ድረስ እንደዚህ ዓይነት ቃል ኪዳኖች ውስጥ ላለመግባት መጠንቀቅ ያስፈልጋል። በንስሓ አባቶች ግፊት የምንገባ ከሆነ ያ ቃል ኪዳን አጋራችንን ላለመበደል እና ክፉ ላለማድረግ የገባነው እንጂ የጋብቻ እንዳልሆነ ማወቅ ያስፈልጋል። ከትዳር በፊት ሩካቤን እና አብሮ መኖርን የሚያበረታቱ ንስሓ አባቶችንም እንቢ ማለት ነውር አይደለም። ቤተ ክርስቲያን በሰው እና በእግዚአብሔር ፊት ዐውጃ፣ ተገቢውን ጸሎት አድርጋ በጋራ እስካላቆረበችን ድረስ ተስማምቶ መቁረብ፣ በአንድ ቀን መቁረብ እንጂ አብሮ መቁረብ ሊባል አይችልም። የዚያን ቀን ከእኛ ጋር ተሰልፈው ከቆረቡት ሰዎች የተለየ አንዳንች ኅብረት አይኖረንም ስለዚህ ይህም ጋብቻን የሚተካ ድርጊት አይደለም። ቅድስት ቤተ ክርስቲያን በሰርጉ ቀን በቅብዓ ሜሮን አክብራ ከምታደርገው ቀለበት ውጪ ሌላ የቀለበት ሥርዓት የላትም፡፡ ስለዚህ በግል አልያም ቤተሰብ ባለበት የሚደረግ ቀለበት የመደራረግ ሥርዓት መንፈሳዊውን ጋብቻ የሚተካ ስላልሆነ የተለየ መብት አይሰጥም።
ስለዚህ ኦርቶዶክሳውያን ወጣቶች በዝሙት ፈተና ወድቀው እግዚአብሔርን እንዳያሳዝኑ ለዚህ ፈተና ከሚዳርጉ ሁኔታዎች ራሳቸውን አርቀው ከዝሙት በመሸሸ (1ቆሮ 6፣18) አካላቸውን እና ሐሳባቸውን በመቀደስ፣ በጋራ ቃለ እግዚአብሔርን በመማር፣ ምክረ ካህን በመቀበል፣ የንስሓ እና የቅዱስ ቁርባን ሕይወትን በመለማመድ የእጮኝነት ጊዜያቸውን ሊያሳልፉ ይገባል።
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
Leave a Reply
Want to join the discussion?Feel free to contribute!