“በጽዮን መለከትን ንፉ፤ ጾምንም ቀድሱ፤ ጉባኤውንም ዐውጁ” (ኢዩ. ፪ ÷፲፭)
ክፍል አንድ
በኃይለ ኢየሱስ ዘጼዴንያ
ጾም የሥጋን ምኞት እስከ መሻቱ ቆርጦ የሚጥል፣ ለመንፈስ ልዕልና የሚያበቃውን መሣሪያ የሚያስታጥቅ ነው፡፡ ክርስቲያን ይህን መሰል መንፈሳዊ የጦር ዕቃ እንዳይለየው አጥብቆ ይለምናል፡፡ የጦር ልምድ እንደሌለው ወታደር ጠላቱን የሚቋቋምበት የጦር ትጥቅ ሳይዝ አውላላ ሜዳ ላይ ባዶውን አይቆምም፡፡ መንፈሳዊ ውጊያን በሥጋዊ ጥበብ ማሸነፍ ስለማንችል ነው አበው አጽዋማትን በአስተምህሮአቸውና በሕይወታቸው የሰበኩልን፡፡
አጽዋማት ሲደርሱ ክርስቲያኖች የሚደሰቱት ጾም የሥጋ ፈቃድ እንዳይሰለጥንባቸው፣ ቁስለ ሥጋን በማከም፣ ቁስለ ነፍስን ስለሚፈውስላቸው ነው፡፡ ጾም የቁስል መፈወሻ ኃይለ መዊዕም (ድል ማድረጊያ) ይሆናል፡፡ ከሥጋም ከመንፈስም ተቆራኝቶ ሰውን ወደ ጥፋት የሚወስድን ክፉ መንፈስ ለማራቅም ይጠቅማል፡፡
ጾም እነዚህንና መሰል መንፈሳዊ በረከትን ስለሚያስገኝ ክርስቲያኖች ይመጣላቸው ዘንድ ይናፍቁታል፡፡ ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችንም መጽሐፍ ቅዱስን መሠረት አድርጋ በዓመት ውስጥ የሚጾሙ አጽዋማትን ደንግጋ ኦርቶዶክሳውያን ክርስቲያኖች ከዲያብሎስ ፈተናና ወጥመድ ያመልጡ ዘንድ አበርክታለች፡፡ እነዚህም ሰባቱ አጽዋማት በመባል ይታወቃሉ፡፡ ጾመ ነቢያት (የገና ጾም)፣ ጾመ ገሀድ(ጋድ)፣ ጾመ ነነዌ፣ ዐቢይ ጾም፣ ጾመ ሐዋርያት፣ ጾመ ድኅነት (ረቡዕ እና ዐርብ) እና ጾመ ፍልሰታ ናቸው፡፡
በዚህ ዝግጅታችን ከእነዚህ የዐዋጅ አጽዋማት መካከል አንዱ የሆነውን ጾመ ነቢያትን በተከታታይ በሁለት ክፍል እናቀርብላችኋለን፡፡
ጾመ ነቢያት (የገና ጾም)
ጾመ ነቢያት ለአዳም የተነገረው ትንቢት ማለትም፡- አዳም ስለ በደሉ በማልቀሱና ንስሓ በመግባቱ ምሕረቱ ወሰን የሌለው አምላካችን ቅዱስ እግዚአብሔር “አምስት ሺህ አምስት መቶ ዘመን ሲፈጸም ከልጅ ልጅህ ተወልጄ አድንሃለሁ” ተብሎ የተናገረውን የተስፋ ቃል በማሰብ ነቢያት የጾሙት ጾም ነው፡፡ በየዘመናቱ የተነሡ ነቢያት የእግዚአብሔር ወልድ መውረድ፣ መወለድ በትንቢት መነጽርነት እየተመለከቱ፣ እንዲሁም እግዚአብሔር ወደፊት ሊያደርግ ያሰበው ምሥጢር ተገልጦላቸው የራቀው ቀርቦ፣ የረቀቀው ገዝፎ እየተመለከቱ፤ ምሥጢረ ሥጋዌ እውን ሊሆን መቃረቡን በማሰብ ነቢያት ጾመውታል፡፡
ይህንንም ቅዱሳን ነቢያት የተስፋው ቃል በዘመናቸው ተፈጽሞ በዓይነ ሥጋ ለማየት ባይችሉም እግዚአብሔር “የማያደርገውን አይናገር፣ የተናገረውንም አያስቀርም” ብለው አምነው ከወዲሁ ተደሰቱ፡፡ (ኢሳ. ፶፰÷፫-፲፬)
ቅዱሳን ነቢያት ስለ እግዚአብሔር ወልድ መወለድ፣ ወደ ግብፅ መሰደድ፣ በባሕረ ዮርዳኖስ መጠመቅ፣ በትምህርተ ወንጌል ጨለማውን ዓለም ስለ ማብራቱ፣ ለሰው ልጆች ድኅነት ጸዋትወ መከራ ስለ መቀበሉና ስለ መሰቀሉ፣ ስለ ትንሣኤው፣ ስለ ዕርገቱና ስለ ዳግም ምጽአቱ ትንቢት ተናግረው አላቆሙም፤ ለአዳም የተሰጠው ተስፋ ተገልጦላቸው ለተናገሩት ትንቢትም ፍፃሜ ይደርስላቸው ዘንድ ፈጣሪያቸውን ተማጽነዋል፡፡
ነቢያት “ይወርዳል ይወለዳል” ብለው ከጾሙ እኛ እርሱ ወርዶ፣ ተወልዶ ተሰቅሎ ካዳነን በኋላ ያለን የሐዲስ ኪዳን ክርስቲያኖች ስለምን የነቢያትን ጾም እንጾማለን? ቢሉ እንደቀደሙት ነቢያት ይወርዳል ይወለዳል እያልን ሳይሆን እነርሱ የጾሙትን ጾም በማሰብ መጾማችን ድኅነተ ሥጋ፣ ድኅነተ ነፍስ፣ በረከተ ሥጋ፣ በረከተ ነፍስ እንድናገኝበት ነው፡፡
ጾመ ነቢያት ከኅዳር ፲፭ ጀምሮ እስከ ታኅሳስ ፳፱ ቀን ድረስ ለ፵፬ ቀናት ይጾማል፡፡ በዘመነ ዮሐንስ ደግሞ እስከ ታኅሳስ ፳፰ ቀን ለ፵፫ ቀናት ይጾማል፡፡ ከእነዚህም መካከል ፵ ቀናት ጾመ ነቢያት፣ ፫ ቀናት ጾመ አብርሃም ሶርያዊ፣ እንዲሁም አርድእተ ፊልጶስ የጾሙት ጾም ሲሆን የቀረው ፩ ቀን ደግሞ የገሃድ ጾም ነው፡፡ (ፍትሐ ነገሥት አንቀጽ ፲፭ ቁጥር ፭፻፷፭፣ ፭፻፷፯)፡፡
የጾመ ነቢያት ስያሜዎች
ጾመ ነቢያት በተለያዩ ስሞች ይጠራል፡፡ እነዚህም።-
ጾመ አዳም፡- ለአዳም የተነገረው የድኅት ተስፋ ስለ ተፈጸመበት ጾመ አዳም ይባላል፡፡ አዳም በገነት ያለውን ሁሉ ይገዛ ይነዳ ዘንድ እግዚአብሔር ፈቃድ ሲሰጠው አንድ ነገር ግን ከልክሎታል፡፡ በገነት ካሉት ዛፎች ዕፀ በለስን እንዳይበላ አዘዘው፡፡ ይህንንም ተላልፎ ቢገኝ የሞት ሞትን እንደሚሞት ነገርሮታል፡፡ ነገር ግን አዳም የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ጠብቆ መኖር የቻለው ለሰባት ዓመታት ከሁለት ወር ከአሥራ ሰባት ቀናት ብቻ ነው፡፡ አትብላ የተባለውንም ዕፀ በለስ በላ፤ ራቁቱንም መሆኑን ተረዳ፣ ጸጋውም ተገፈፈ፡፡ በተድላ በደስታ ከሚኖርበት ገነትም ወደ ምድረ ፋይድ ተባረረ፡፡ (ኩፋ. ፫፥፲፯-፳፬)
አዳም የእግዚአብሔርን ትእዛዝ መተላለፉን የሞት ሞትም እንደሚሞት በተረዳ ጊዜ ከእግዚአብሔር የተነገረውን ቃል አሰበ፤ የፀፀት ዕንባን እያነባ ይቅርታን ከአምላኩ ዘንድ ለመነ፡፡ እግዚአብሔር ቸርነቱ ወሰን የለውምና ለአዳም “አምስት ቀን ተኩል (አምስት ሺህ አምስት መቶ ዘመን) ሲፈጸም ከልጅ ልጅህ ተወልጄ አድንሃለሁ ሲል ቃል ኪዳን ገባለት፡፡ (ቀሌ. ፫፥፲፯-፲፱) አዳምም ቃል ኪዳኑ ይፈጸምለት ዘንድ ጾመ ጸለየ፡፡
ይህንንም ጾም ከአዳም ጀምሮ እስከ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መወለድ ድረስ የነበሩት ነቢያት ጾመውታል፡፡ ነቢያት ለምን ጾሙት ብንል፤- ለአዳም የተገባውን ቃል ኪዳን ይፈጸም ዘንድ እየናፈቁ ከድንግል ማርያም ይወለዳል፣ በሞቱም ሞት የተፈረደበትን የሰው ልጅ ነፃ ያወጣዋል ሲሉ ነው፡፡ ለመጥቀስ ያህል ሊቀ ነቢያት ሙሴ ፵ ቀን ጾሟል (ዘፀ ፴፬÷፳፯)፤ በተጨማሪም ነቢዩ ዕዝራ፣ ሌሎችም ነቢያት ጾመውታል፡፡
ጾመ ማርያም፡- እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ወልደ አብን ፀንሼ ምን ሠርቼ እወልደዋለሁ በማለት ጾማዋለችና ጾመ ማርያም ይባላል፡፡ ይህን ያለችው በመደነቅ፣ በትሕትና እና ቀደምት አባቶቿ ነቢያት ሲጾሙት አይታ ጾማዋለች፡፡ እንዴት ፀንሼ እወልደዋለሁ ማለት ጥርጥር ሳይሆን ተደምሞ፣ መደነቅ የነገረ ልደቱን አይመረመሬነት ይገልጻል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ትሕትና ነው፡፡
እግዚእሔር ወልድ በነቢያት ምሳሌ እየተመሰለ፣ ትንቢት እያናገረ አምስት ሺህ አምስት መቶው ዘመን ሲፈጸም ንጽሕት ቅድስት ከምትሆን ከእመቤታችን ድንግል ማርያም ከሥጋዋ ሥጋ፣ ከነፍሷ ነፍስ ነሥቶ ተወልዷል፡፡ የነቢያትም ትንቢት ተፈጽሟልና የጾሙ መጨረሻ (መፍቻ) በዓለ ልደት በመኾኑም የልደት ጾም ተብሏል፡፡
ዘመነ አስተምሕሮ(አስተምህሮ)
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የዘመን አከፋፈል ሥርዓት መሠረት ከኅዳር ፮ ጀምሮ እስከ ታኅሣሥ ፯ ቀን ድረስ ያለው ወቅት ዘመነ አስተምህሮ ይባላል፡፡
አስተምህሮ፡- ቃሉ በሀሌታው “ሀ” ሲጻፍ የቃለ እግዚአብሔር ማስተማሪያ (የትምህርተ ወንጌል) ዘመን ማለት ነው፡፡ ሥርወ ቃሉም “መሀረ – አስተማረ፤ ለመምህር ሰጠ፤ መራ፤ አሳየ፤ መከረ፤ አለመደ” ወይም “ተምህረ – ተማረ፤ ለመደ” የሚለው የግእዝ ግስ ሲሆን፣ ይኸውም የእግዚአብሔር ቸርነቱ፣ ርኅራኄው፣ ትዕግሥቱና የማዳን ሥራው በቤተ ክርስቲያን በስፋት የሚሰበክበት ጊዜ ነው፡፡
አስተምሕሮ፡- ስንል ደግሞ ቃሉ በሐመሩ “ሐ” ሲጻፍ ደግሞ የምሕረት፣ የይቅርታ ዘመን ማለት ነው፡፡ ሥርወ ቃሉም “መሐረ – ይቅር አለ፣ ዕዳ በደልን ተወ” ወይም “አምሐረ – አስማረ፤ ይቅር አሰኘ፤ አራራ፤ አሳዘነ” የሚለው የግእዝ ግስ ነው፡፡ ዘመነ አስተምሕሮ ስለ እግዚአብሔር ቸርነትና ርኅራኄ፤ እርሱ በደላችንን ሁሉ ይቅር እንደሚለን እኛ ምእመናንም እርስ በእርስ ይቅር መባባል እንደሚገባን ትምህርት የሚሰጥበት ወቅት ነው፡፡
ይህ ዘመነ አስተምሕሮ ቤተ ክርስቲያን ስለ ልጆቿ ይቅርታ የምትጠይቅበት፤ ምእመናንንም በጾም በጸሎት ተወስነው ስለ በደላቸው ይቅርታ የሚጠይቁበት፣ እግዚአብሔርንም የሚማጸኑበት ጊዜ ነው፡፡ የእግዚአብሔር ምሕረትና ይቅር ባይነትም በስፋት ትምህርት የሚሰጥበት ዘመን ነው፡፡
በዘመነ አስተምሕሮ የሚገኙ ሰንበታት፡- በቅዱስ ያሬድ የዜማ መጻሕፍት እንደተቀመጠው በዘመነ አስተምሕሮ ውስጥ የሚገኙ ሰንበታት (ዕሑዶች) አስተምሕሮ፣ ቅድስት፣ ምኵራብ፣ መጻጉዕ እና ደብረ ዘይት ተብለው ይጠራሉ፡፡ ሳምንታቱን በዚህ መልክ የከፋፈለውም ሊቁ ቅዱስ ያሬድ ነው፡፡ (ድጓ ዘአስተምህሮ)፡፡ ከመጀመሪያው ሳምንት (ከአስተምሕሮ) በቀር የአራቱ እሑዶቹ ስያሜ ከዐቢይ ጾም ሰንበታት ጋር አንድ ዓይነት ነው፡፡
የዘመነ አስተምህሮ ሰንበታት (እሑዶች) ስያሜ ከዐቢይ ጾም ሰንበታት ስያሜ ጋር ተመሳሳይ ይሁን እንጂ በእነዚህ ሳምንታት ሌሊት የሚዘመሩ መዝሙራት፣ በቅዳሴ ጊዜ የሚነበቡ ምንባባትና የሚቀርቡ ትምህርቶች ግን በይዘትና በምሥጢር ይለያያሉ፡፡ ትምህርቶቹ በምስጢር ይለያያሉ ስንልም በዚህ ወቅት የሚነገረው ምስጢርና ይዘት በወቅቱ ላይ የሚያተኩር መሆኑን ለመግለጽ ነው፡፡
ይቆየን
Leave a Reply
Want to join the discussion?Feel free to contribute!