መልእክተ ቅዱስ ፓትርያርክ
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!!
በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገር የምትገኙ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ምእመናንና ምእመናት እንዲሁም ኢትዮጵያውያንና ኢትዮጵያውያት በሙሉ፡- እግዚአብሔር አምላካችን በይቅርታውና በምሕረቱ እንኳን ለሁለት ሺሕ ዐሥራ አምስት ዓመተ ምሕረት የድንግል ማርያም ጾመ ፍልሰታ በሰላም አደረሳችሁ።
“ወእምኵሉሰ ዘይቀድም ተፋቀሩ በበይናቲክሙ በምልአ ልብክሙ እስመ ተፋቅሮ ይደፍኖን ወይደመስሶን ለኵሎን ኃጣውእ፤ ከሁሉ አስቀድሞ በሙሉ ልባችሁ እርስ በርሳችሁ ተፋቀሩ፣ መፋቀር ሁሉንም ዓይነተ ኃጢአት ይሸፍናልና ይደመስሳልምና” (፩ጴጥ. ፬–፰)
ሁላችንም እንደምናውቀው የቅዱስ ወንጌል አስተምህሮ መሠረትና ጣርያ ወለልና ግድግዳ በፍቅርና በፍቅር ብቻ የተገነባ ነው፤ ፍቅር እግዚአብሔር ዓለምን ያዳነበት መድኃኒት ነው፣ ፍቅር የጥላቻና የመለያየት ግንብን ንዶ ይቅርታንና አንድነትን የሚገነባ ጠንካራ ዓለት ነው፤ ፍቅር መጽናናትንና ደስታን የሚያፈራ ጣፋጭ ተክል ነው፤ በፍቅር ለፍቅር የሚደረግ ሁሉ ፍሥሐን እንጂ ጸጸትን አያስከትልም፤ በመሆኑም በሰብኣዊ ድክመት ምክንያት ሰዎች ፍቅርን ሙሉ በሙሉ በሚፈለገው ደረጃ ባንጠብቀውም በዓለማዊም ሆነ በመፈንሳዊ ሕይወት ከፍቅር የበለጠ ጠቃሚ ነገር የለም፤ ፍቅር የማይሻርና ለዘላለሙ ጸንቶ የሚኖር እንደሆነ በቅዱስ መጽሐፍ ተመዝግቦአል፤ ምክንያቱም ፍቅር ከሞት ቡኋላም ቢሆን በእግዚአብሔር መንግሥት ይቀጥላልና ነው፤ ዛሬ የሚጀመረው የድንግል ማርያም ጾመ ፍልሰታም በፍቅር ለፍቅር የተፈጸመ ነው፣ ይኸውም ቅዱሳን ሐዋርያት የድንግል ማርያምን የማረፊያ ቦታ ለማየት ሲሉ የጾሙት ጾም ነው፤ ቅዱሳን ሐዋርያት የገለፁት ፍቅረ ድንግል ማርያምን ብቻ ሳይሆን ያረፈችበትንም ቦታ ጭምር ያመለከተ ነበረ፥ ይህ ሊሆን የቻለው ከልብ የሆነ እውነተኛ ፍቅር በሐዋርያት ዘንድ ስለነበረ ነው፡፡
እኛም ዛሬ የምንጾመው ይህንን የማርያም ጾም እንደ አበው ሐዋርያት ፍቅረ ድንግል ማርያም በልባችን ውስጥ ተተክሎ ስላለ ነው፤ እግዚአብሔር በፍቅርና በሃይማኖት የሚቀርብለትን ሁሉ ይቀበላልና የሐዋርያትን ጾምና ጸሎት ተቀብሎ ጥያቄአቸውን መልሶአል፡፡ ዛሬም ይህንን ጾም የምንጾመው እግዚአብሔር ጾማችንን ተቀብሎ የልባችንን መሻት ይፈጽምልናል ብለን ነው፣ በፍቅርና በሃይማኖት እስከ ጾምን ደግሞ እግዚአብሔር ይቀበለናል።
የተወደዳችሁ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን ምእመናንና ምእመናት!
እንደ እግዚአብሔር ቃልም እንደ አባቶቻችን ትውፊትም የጾመ ፍልሰታ ጾም ሲጾም የበደለ ይቅርታ ጠይቆ፤ ተገቢውንም ካሣ ከፍሎ፣ ቂም በቀሉን አሰርዞ፣ ፍቅርን መሥርቶ ነበረ፤ የተበደለም በበኩሉ ዕርቅን አውርዶ፣ ይቅርታን ሰጥቶ የአእምሮ ማለስለሻና ማስረሻ የሆነውን ካሣውን ተቀብሎ ቂሙንና በቀሉን ከአእምሮው አውጥቶና አጽድቶ፣ ለእግዚአብሔር ስል ከልቤ ይቅር ብያለሁ ብሎ፤ ስመ እግዚአብሔርን ጠርቶ በፍቅር ይታረቃል፡፡
በዚህ ሁኔታ ፍጹምና ልባዊ ፍቅር ተይዞ ሲጾም ሁሉም ዓይነት ኃጢአት ሙሉ በሙሉ ይደመሰስለታል። እግዚአብሔርም ይቅርታ ጠያቂውንም፣ ይቅርታ ሰጪውንም አሸማጋዩንም ይባርካል ።ማኅበረ ሰቡም በዚህ ቅዱስና ሃይማኖታዊ ባህልና ትውፊት ተጠብቆ ለብዙ ዘመናት አንድነቱንና ሃይማኖቱን ወንድማማችነቱንና ነጻነቱን አስጠብቆ እስከ ዛሬ ደርሶአል፤ ይህ ለሀገራችን ታላቅ የሆነ የእግዚአብሔር በረከት ነበረ፤ ይህ እውነተኛ በረከት በአሁኑ ጊዜ ቸል በመባሉ ፈተናችን በዝቶአል፤ እንደ እውነቱ ከሆነ ሰው በኃጢአት ከወደቀበት ጊዜ ጀምሮ ጥልና መገዳደል በየትኛውም ጊዜ፣ በየትኛውም ሀገር በየትኛውም ማኅበረ ሰብ ይከሠታል፣ ዛሬም በሀገራችን በተፈጠረው አለመግባባት ከባድ ችግር ተፈጥሮአል፣ የሚያስገርመው ነገር ቢኖር እንዴት እንደ ባህላችንና እምነታችን በቀላሉ በዕርቅና በይቅርታ ማስተካከል አቃተን የሚለው ነው፤ የዘመናችን ልዩ ነገር ይህ ነው፤ ለዚህም ብዙ የተለያየ ምክንያት ሊኖረው ይችላል፤ በሃይማኖት ዓይን ሲታይ ግን ለእግዚአብሔር ቃል የምንሰጠው ክብር በእጅጉ ስለተቀነሰ ነው የሚል ሆኖ ይገኛል፤ ይህ ዝንባሌ አሁን ላለውም ሆነ ለሚመጣው ትውልድ አደገኛ ስለሆነ የኦርቶዶክስ ሕዝበ ክርስቲያንም ሆነ ሌሎቹ ኢትዮጵያውያን ሁሉ ይህንን በጥልቀት ሊያጤኑትና ሊያርሙት ይገባል፡፡
የተወደዳችሁ የመንፈስ ልጆቻችን ምእመናንና ምእመናንት!
ሽማግሌ የሀገር በረከት ነው፤ አስታራቂ ሽማግሌ የችግር ሐኪምና ፈዋሽ ነው፤ የፍቅርና የተግባቦት መሐንዲስም ነው፤ በእግዚአብሔርም “የሚያስታርቁ የእግዚአብሔር ልጆች ናቸው” ተብሎ ውዳሴ ተችሮአቸዋል፣ እነዚህን ሽማግሌዎች ተጠቅመን ችግሮቻችንን መፍታት ጊዜው የሚጠይቀው አስገዳጅ ጉዳይ ሆኖአል፤ ሁሉም ታየ፤ ሁሉም ተሞከረ፤ ዘላቂ መፍትሔ ሲያመጣ ግን አልታየም፤ እንዲያውም ችግሩ ወደ ሃይማኖት ተዛምቶ ቤተ ክርስቲያንም የገፈቱ ቀማሽ ለመሆን ተገዳለች፡፡
በተጨባጭ እንደሚታወቀው ሕዝብንና ሃይማኖትን ነጣጥሎ ሰላምን ማረጋጋጥ ከቶውኑ ሊታሰብ አይችልም፤ ምክንያቱም ሕዝብ የሃይማኖቱ ቤተሰብ ነው፣ ሃይማኖቱም በሕዝቡ መንፈስ ውስጥ ነግሦ የሚኖር መለኮታዊ ኃይል ነውና፣ ከዚህ አንጻር “ወልድ ሲነካ አብ ይነካ እንደሚባለው ሕዝቡ ሲነካ ሃይማኖቱ ይነካል፤ ሃይማኖቱ ሲነካ ደግሞ ሕዝቡ ይነካል፤ በመሆኑም በተካሄደው ግጭት ብዙ ነገሮች መመሳቀላቸው የማይካድ ቢሆንም ችግሩ በዕርቅና በካሣ በይቅርታና በመተው ካልተዘጋ ለማንም ስለማይበጅ ከባድ ጉዳት የደረሰባቸው ወገኖች ለዕርቅ ዝግጁ እንዲሆኑ፣ የበደሉም እንዲክሱ የሀገር ሽማግሌዎችም የማስታረቅ ሥራን በሐቅ በገለልተኝነትና ዕንባን በሚያደርቅ ስልት እንዲሸመግሉ መንግሥትም የበኩሉን ድጋፍ እንዲያደርግ በዚህ አጋጣሚ በእግዚአብሔር ስም ጥሪያችንን እናስተላልፋለን፡፡
በመጨረሻም
የገጠመንን ፈተና ሁሉ ሊያቀልልንና ሊያስወግድልን የሚችል እግዚአብሔር ስለሆነ በዚህ የጾመ ማርያም ወቅት ምእመናን በተመሥጦና በንሥሐ ሕይወት ለእግዚአብሔር በመንበርከክ ስለ ሰላምና ፍቅር እንዲማፀኑ፣ ካላቸውም በረከት ለተራቡትና ለተፈናቀሉት እንዲለግሱ ሁሉም ወገኖች በሆነው ነገር ይብቃን ብለው ወደ ሰላማዊ አማራጭ እንዲቀርቡ በእግዚአብሔር ስም አባታዊ መልእክታችንን እናስተላልፋለን፡፡
መልካም የጾመ ማርያም ሱባዔ ያድርግልን
እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ሕዝቦችዋን ይባርክ
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
አሜን
አባ ማትያስ ቀዳማዊ
ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም
ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት
ነሐሴ 2015 ዓ.ም.
Leave a Reply
Want to join the discussion?Feel free to contribute!