ቆይታ ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ኦርቶዶክሳውያን ተመራቂዎች ጋር
ክፍል ሁለት
በእንዳለ ደምስስ
“ግቢ ጉባኤ ባይኖርና ወደ ቤተ ክርስቲያን ባንመላለስ በዓለም ጠፍተን እንቀር ነበር”
(ዶ/ር ምንተስኖት መንግሥቱ)
የተከበራችሁ የማኅበረ ቅዱሳን የግቢ ጉባኤያት አገልግሎት ማስተባበሪያ ድረ ገጽ ተከታታዮች፡- “ቆይታ ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ኦርቶዶክሳውያን ተመራቂዎች ጋር” በሚል ርእስ በክፍል አንድ ዝግጅታችን ከቦንጋ ዩኒቨርሲቲ ግቢ ጉባኤያት ከዩኒቨርሲቲው አጠቃላይ ተመራቂዎች 3.99 ከፍተኛ ነጥብ በማምጣት የዋንጫና የሜዳልያ ተሸላሚ ከሆነችው እኅታችን ውብነሽ ለማ ጋር ያደረግነውን አጭር ቆይታ አቅርበንላችኋል፡፡ በክፍል ሁለት ዝግጅታችን ደግሞ ከሌሎች ተመራቂዎች ጋር የምናደርገውን ቆይታ ትከታተሉ ዘንድ እነሆ፡-
ዶ/ር ምንተስኖት መንግሥቱ በ፳፻፲፭ ዓ.ም ከጅግጅጋ ዩኒቨርሲቲ ሕክምና ትምህርት ክፍል በእንስሳት ሕክምና ትምህርቱን አጠናቋል፡፡ በሦስት ነጥብ ዘጠኝ ስምንት (3.98) አጠቃላይ ውጤት ዩኒቨርሲቲው ያዘጋጀውን ዋንጫና ሜዳሊያ ተሸላሚ ለመሆን በቅቷል፡፡ በዩኒቨርሲቲው እና ስለ ግቢ ጉባኤ ቆይታው ጠይቀነዋል፡-
ዶ/ር ምንተስኖት እንዲህ ይገልጸዋል፡- “በዩኒቨርስቲ ቆይታዬ የምችለውን ያህል ጥረት ማድረጌ እንዳለ ሆኖ የእግዚአብሔር እገዛና ቸርነት አልተለየኝም፡፡ በሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት ሳለሁም በቅድመ ግቢ ጉባኤ እሳተፍ ስለነበር ዩኒቨርሲቲ ስገባ ቀጥታ ያመራሁት ወደ ግቢ ጉባኤ ነው፡፡ እንዲያውም እኔና ጓደኞቼ ወደ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ስንሄድ በአባቶች ቡራኬ ነበር የተሸኘነው፡፡ በተጨማሪም በቅድመ ግቢ ጉባኤ ውስጥ ከእኛ ቀድመው ዩኒቨርሲቲ ትምህርታቸውን ያጠናቀቁ ወንድሞችና እኅቶች ተጋብዘው ተሞክሯቸውን ያካፍሉን ነበር፡፡ ወንደሞችና እኅቶችም በጥሩ ሁኔታ ነው የተቀበሉኝ፡፡ በዙሪያዬም መልካም ኦርቶዶክሳውያን ቤተሰቦችና ዩኒቨርሲቲ ስገባም ያጋጠሙኝ ጓደኞቼ ለቤተ ክርስቲያንና ለትምህርታቸው ትኩረት የሚሰጡ ስለነበሩ ለውጤታማነቴ አስተዋጽኦ አድርገዋል ማለት እችላለሁ፡፡ በቆይታዬም ለትምህርቴና ለቤተ ክርስቲያን ቅድሚያ በመስጠቴ ለውጤት በቅቻለሁ” ሲል ይገልጻል፡፡
ጓደኛን በተመለከተም “በዩኒቨርሲቲ ቆይታችን ውስጥ ጓደኛ ትልቁን ድርሻ ይወስዳል፡፡ ተመሳሳይ ዓላማ ከሌላቸው ተማሪዎች ራስን ማራቅም ይገባል፡፡ ወደ ዩኒቨርሲቲ ስሄድ ዓላማዬ መማር ነው፡፡ መማር ብቻም ሳይሆን ወደፊት ለሚኖረኝ ሕይወት መሠረት የምጥልበት ስለሆነ ከሌሎች የተሻለ ሆኜ ለመገኘት መሥራት እንዳለብኝ ራሴን አሳምኜ ነው የገባሁት፡፡ ስለዚህ ከማይመቹ እና የሕይወት አቅጣጫዬን ከሚያስቱ ተማሪዎች መራቅ ነበረብኝ፤ ይህንንም አድርጌዋለሁ፡፡ ጓደኞቼ ጥሩዎች ስለነበሩ ጅግጅጋ ቅድስት ኪዳነ ምሕረት ቤተ ክርስቲያን እንሄዳለን፤ መርሐ ግብሮች አያመልጡንም፣ ቅዳሜና እሑድ ደግሞ በግቢ ጉባኤያችን የተዘጋጀውን ጉባኤ እና ተከታታይ ትምህርት እንሳተፋለን፤ ቀሪውን ጊዜ ደግሞ ለትምህርት እናውለዋለን፡፡ በቃ የእኔ ሕይወት በዩኒቨርሲቲ ውስጥ ይህ ነበር ማለት እችላለሁ” በማለት ቆይታውን ይገልጻል፡፡
ከጊዜ ጋር የነበረውን አጠቃቀምም በተመለከተ “አንድም ደቂቃ ትሁን ዋጋ አላት” ይላል ዶ/ር ምንተስኖት፡፡ አያይዞም “የገባሁበት ትምህርት ክፍል ከፍተኛ ንባብ የሚጠይቅ ክፍል ነው፡፡ ስለዚህ አብዛኛውን ጊዜዬን የማሳልፈው በማንበብ ነው፡፡ ይህንንም በእቅድ መምራት ያስፈልጋል፡፡ አንድ ጊዜ ካቀድከው እቅድ ከተደናቀፍህ ወደ ትክክለኛው አቅጣጫ ለመምጣት ያስቸግራልና ከፍተኛ ጥንቃቄ አደርግ ነበር፡፡ ለዚህም ነው ውጤታማ መሆን የቻልኩት” በማለት ተሞክሮውን አጋርቶናል፡፡
ግቢ ጉባኤን በተመለከተ ሲገልጽም “በግቢ ጉባኤ ውስጥ መቆየቴ አንዱ የውጤታማነቴ ምሥጢር ነው፡፡ በግቢ ጉባኤ ያገኘሁት ትምህርት በመንፈሳዊ ሕይወቴም ብቻ ሳይሆን ዓለም ውጣ እንዳታስቀረኝ ትልቅ ትጥቅ ሆኖኛል፡፡ የሚገጥሙኝን ፈተናዎች ለመወጣትና ራሴም በትክክለኛው መንገድ መራመድ እንድችል ትልቅ አቅም ፈጥሮልኛል፡፡ ግቢ ጉባኤ ባይኖርና ወደ ቤተ ክርስቲያን ባንመላለስ ኖሮ በዓለም ጠፍተን እንቀር ነበር፡፡ በግቢ ጉባኤ መታቀፋችን ዋጋው ብዙ ነው” ብሏል፡፡
በዩኒቨርሲቲ ውስጥ ትምህርታቸውን በመከታተል ላይ ለሚገኙ ወንድሞችና እኅቶች ባስተላለፈው መልእክትም “ዋናው ዩኒቨርሲቲ ገብቻለሁ ማለት ሳይሆን ለትምህርታቸው ልዩ ትኩረት መስጠት አለባቸው፡፡ በመንፈሳዊ ሕይወታቸውም እየበረቱ እግዚአብሔር እንዲያግዛቸው ራሳቸውን ከቅድስት ቤተ ክርስቲያን ጋር ማቆራኘት ይጠበቅባቸዋል፡፡ ነገ ነገ እያሉ መዘናጋት ብዙ ዋጋ ስለሚያስከፍል የውሳኔ ሰው መሆን፣ ከቤተ ክርስቲያን ውጪ ያለው ሕይወት ለውጤት እንደማያበቃ መረዳት ያስፈልጋል፡፡ ፈተና ቢገጥም እንኳን እግዚአብሔር ፈተናውን አሳልፎ እንደሚያሻግር መረዳት መልካም ነው፡፡ ይህን ካደረግን እግዚአብሔር አብዝቶ ይባርከናል” ሲል ምክሩን ለግሷል፡፡
የተከበራችሁ የግቢ ጉባኤያት አገልግሎት ማስተባበሪያ ድረ ገጽ ተከታታዮች በክፍል ሦስት ዝግጅታችን ደግሞ ከሌሎች ውጤታማ ተመራቂዎች ጋር ያደረግነውን ቆይታ ይዘን እንቀርባለን፡፡ ይቆየን፡፡
Leave a Reply
Want to join the discussion?Feel free to contribute!