«ታገኙ ዘንድ ሩጡ» (፩ኛቆሮ.፱፥፳፬)

በመ/ር ተርቢኖስ ቶሎሳ 

ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ በግሪክ ከነበሩ አውራጃዎች አንዷ ከሆነችው አካይያ መዲና ቆሮንቶስ ከተማ ገብቶ ለሕዝቡ ጌታ ከፅንሰቱ ጀምሮ ያደረገውን ተአምራት፣ ያስተማረውን ትምህርት፣ ቢነግራቸው ብዙዎቹ ከጣዖት አምልኮ እግዚአብሔርን ወደ ማምለክ፣ ኃጢአትን ከመሥራት ጽድቅን ወደ ማድረግ ተመለሰው፤ አምነው ተጠመቁ፡፡ (ሐዋ.፲፰፥፩–፲)

ቅዱስ ጳውሎስ የቆሮንቶስ ከተማን ሕዝብ አስተምሮ፣ አሳምኖና አጥምቆ ካቆረባቸው በኋላ ከዚያ ወጥቶ ወደ ኤፌሶን ሄደ፡፡ ነገር ግን በቆሮንቶስ ያሉ ምእመናን «አስተምሮ ዋጋ ይቀበላል (ገንዘብ ይበላል)» ብለው አሙት፡፡ ይህንን ሐሜታቸውን ሰምቶ ተስፋ ሳይቆርጥ የወንጌል አገልግሎቱን፣ ማለትም መንፈሳዊውን ትምህርት በሰፊው ቀጥሎበት ለቁመተ ሥጋ ያህል በምእመናን ገንዘብ መመገብ ምንም ቁም ነገር እንዳልሆነ፣ ምንም ሥጋዊ ጥቅም እንደማይፈልግና ገንዘብም እንዳልተቀበላቸው በትምህርቱ ውስጥ ይገልጥ ነበር፡፡ ይልቁንም ቅዱስ ጳውሎስ ይተጋ የነበረው ወንጌልን ስለማስተማር፣ ሰዎችንም ለድኅነት ለማብቃት እንደ ሕጋቸው፣ እንደ አኗኗራቸው ሁሉ እየኖረ ወንጌልን በመስበክ በዓለም በሚደረግ ሰልፍ፣ ሩጫና ሽልማት እየመሰለ ከክርስትና የሚገኘውን ክብር አስተምሯቸዋል፡፡

ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ «በእሽቅድምድም ሥፍራ የሚሽቀዳደሙ ሁሉ እንደሚፋጠኑ አታውቁምን? ለቀደመው የሚደረግለት ዋጋ አለ፤ እንዲሁ እናንተም እንድታገኙ ፈጽማችሁ ሩጡ» ይላል፡፡ (፩ኛቆሮ. ፱፥፳፬) በጦር ሜዳ ተሰልፎ እየፎከረ፣ ጠላቱን ድል የሚያደርግ አርበኛ (ጦረኛ) ከጌታው ዘንድ ሹመት፣ ሽልማት እንዲያገኝ እንዲሁ መንፈሳዊ አርበኛ የሚሆኑ ምእመናንም በምግባር በትሩፋት እየተሸቀዳደሙ ዋጋቸውን (ክብራቸውን) ያገኙ ዘንድ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ አጥብቆ ይመክራቸዋል፡፡

መሮጥና ማግኘት የሚሉትን ፀንሰ ሐሳቦች ሐሳብ በሁለት መንገድ ማየት እንችላለን፡፡ አንደኛው፡- በዚህ ዓለም በሚደረግ የሩጫ ውድድር አንጻር በክርስትና የሚደረግ የሕይወት ዕድገትና መንፈሳዊ ፉክርክር ነው፡፡ አትሌቶች ሀገራቸውን ወክለው በሩጫ ተወዳድረው አሸናፊ ሆነው ተሸልመው የራሳቸውንም የሀገራቸውንም ስም በዓለም ያስጠራሉ፤ ሥጋውያን ሯጮጭም ሲሮጡ በመንገዳቸው ላይ የሚደርስባቸውን ድካም የሚገጥማቸውንም መሰናክል ተቋቁመው የሚያልፉትና ለአሸናፊነት የሚበቁት በአሸናፊነታቸው የሚያገኙትን ክብርና ሽልማት ተስፋ በማድረግ ነው፡፡ ይህንንም ተስፋ ሳይጠራጠሩ እስከ መጨረሻው ድረስ በጽናት ይሮጣሉ፡፡

መንፈሳውያን ሯጮች የሆኑ ምእመናንም እንዲሁ በኅሊናቸው ከዚህ ዓለም ድካምና ፃዕር በኋላ ያለውን የዘለዓለም ሕይወትና የማያልፍ ተድላ ደስታን እያሰቡ ወደ መንግሥተ ሰማያት በእግረ ኃሊናቸው በጽናት ይሮጣሉ፡፡ በሕይወት መንገዳቸው ላይ ከፈቃደ ሥጋቸው፣ ከአጋንንትና ከዐላውያን ነገሥታት ሁሉ የሚደርስባቸውን የቅድስና ሕይወት የመንግሥተ ሰማያት ሩጫ መሰናክሎችን በፍጹም እምነትና በጽናት አሸንፈው በእግዚአብሔር ዘንድ የዘለዓለማዊው ሕይወት የመንግሥተ ሰማያት ተሸላሚ ይሆናሉ፡፡

ክርስቲያን ሁል ጊዜም በምግባረ ክርስትና የሚሮጥ (የሚያድግ) ነው፤ ምግባረ ክርስትና እግዚአብሔርን የምንመስልበት ሕይወት ነው፡፡ ሐዋርያው «እኔ ክርስቶስን እንድመስለው እናንተም እኔን ምሰሉ» እንዳለ፡፡ (፪ኛቆሮ.፲፩፥፩) በጥንተ ፍጥረትም አምላካችን ቅዱስ እግዚአብሔር «ሰውን በአርአያችን እንደ ምሳሌያችን እንፍጠር>> ብሎ እርሱን የመምሰል ሕይወት በሰው እንደሚገለጥ ተናግሯል፡፡ (ዘፍ.፩፥፳፮) እግዚአብሔር ደግሞ በባሕርዩ መልካም ነው፤ ለመልካምነቱም ገደብ የለውም፡፡

ምግባረ ክርስትና ገደብ የለውም፤ ሁል ጊዜም ማደግ ነው፡፡ እስከ አሁን የጾምኩት፣ የጸለይሁት፣ ያስቀደስኩት፣ የቈረብኩት ይበቃኛል፣ … አይባልም፡፡ ምክንያቱም የምንነሣበት እንጂ የምንደረስበት ምግባር የለምና፣ በጎነት መጨረሻ የለውም፡፡ ስለዚህ የክርስቲያን ኑሮው ሁል ጊዜ በሩጫ (በበጎ ምግባር መገሥገሥ) ነው፡፡

ቅዱስ ጳውሎስ «በኋላዬ ያለውን እየረሳሁ በፊቴ ያለውን ለመያዝ እጄን እዘረጋለሁ» ያለውም ለዚህ ነው፡፡ (ፊል.፫፥፲፫) ተክል እንደተተከለ ብቻ ከቀረ ይደርቃል እንጂ አያድግም፡፡ ስለዚህ አድጎ ፍሬ እንዲያፈራ ይኮተኮታል፤ ከአፈር፣ ከአየር እና ከውኃ ይመገባል፡፡  ከዚህም የተነሣ አድጎ፣ ለምልሞና አብቦ ያፈራል፤ ክርስቲያናዊ ሰውም እንዲሁ ነው፡፡ በሃይማኖትና በጥምቀት፣ ይተከላል፤ በመንፈስ ቅዱስ ጸጋ ይመገባል፤ በምግባር ለምልሞ፣ በትሩፋት አብቦ የክብር ፍሬ ያፈራል፡፡ ስለዚህ በክርስትና ሁል ጊዜም ማደግ ነው፡፡

በክርስትና ሕይወት ውስጥ ምግባር ሃይማኖት «እዚህ ጋር ይበቃኛል» ብለን የምናቆመው ሳይሆን ዕለት ዕለት መሽቀዳደም፣ ለፍቅር፣ ለየዋሀት፣ ለቅንነት፣ ለለጋሥነት፣ ለርኅራኄ … መፎካከር ነው፡፡ ሐዋርያው «ፍቅርን ተከተሏት>» በማለት እንዳስተማረን፡፡ (፩ኛቆሮ.፲፬፥፩) እንዲህ ከሆነ በሰማይ የሚገኘው ክብር ታላቅ ነው፡፡ ክብር ሁሉ በሥራ መጠን ነውና ለሁሉም እንደ ዋጋው እከፍለዋለሁ እንዳለው አምላካችን ጥቂት የሠራ ጥቂት ክብር ይቀበላል፤ አብዝቶ የሠራም አብዝቶ ይቀበላልና፡፡ (ራእ.፳፪፥፲፪)

ሁለተኛው በጦር ሰልፍ በሚደረግ ሩጫ አንጻር በተጋድሎ የሚገኝ ጸጋን ለማመልከት ነው፡፡ ከላይ እንዳየነው የጦር ሰልፍ ሩጫ ጠላትን ድል አድርጎ ነፃነትን ማወጅ፣ ከድል በኋላ የሚገኝን ሹመትንና ሽልማትን ገንዘብ ማድረግ፣ ክብርንና አዎንታዊ የታሪክ ባለቤት መሆንን መቀዳጀት ነው፡፡ ስለዚህ ሥጋውያን ጦረኞች እግራቸውን ለጠጠር፣ ግንባራቸውን ለጦር ሰጥተው ከድል በኋላ ስለሚያገኙት ሽልማት እኔ ልዝመት እኔ ልዝመት ብለው ይሽቀዳደማሉ፡፡

ከተጋድሎ በኋላ የሚያገኘውን ክብር የሚያስብ ክርስቲያንም እንደዚሁ ዲያብሎስ ያሰለፈውን ጦር ድል ለመንሣት ይሰለፋል፣ ሞትንም አይፈራም፡፡ «ብእሲ ዘይሬኢ አክሊላቲሁ ኢይሜምእ፤ አክሊሉን የሚያይ ሰው ወደ ኋላ አያፈገፍግም» በማለት እንዳስተማረን፡፡ (ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ተግሣጽ) ከፊቱ የሚጠብቀውን ክብርና ሽልማት የሚያስብ ተጋዳይ በአሁናዊ መከራው አይማረርም፡፡ መዝሙረኛው ዳዊት እንዲህ ይላል «እለ ይዘርዑ በአንብዕ ወበሐሴት የዐርሩ፤ ሶበሰ የሐውሩ ወፈሩ እንዘ ይበክዩ ወጾሩ ዘርዖሙ ወሶበ የአትዉ መጽኡ እንዘ ይትፌሥሑ ወጾሩ ከላስስቲሆሙ፤ በልቅሶ(በዕንባ) የሚዘሩ በደስታ ይሰበስባሉ፤ በሄዱጊዜ ዘራቸውን ተሸክመው እያለቀሱ ተሰማሩ፤ በተመለሱ ጊዜ ግን ነዷቸውን ተሸክመው ደስ እያላቸው ይመጣሉ» እንዲል፡፡ (መዝ.፻፳፭፥፮-፰)

በክረምት የሚዘራ ገበሬ ጠዋት ሲወጣ በላይ ዝናቡ ይወርድበታል፤ በታች ቅዝቃዜው፣ ጭቃውና ጎርፉ ይፈራረቁበታል፤ ስለዚህ በመከራ ይዘራል፡፡ የዘራው አፍርቶ አጭዶ ሲከምረው ግን መከራውን ረስቶ ጨምሬ ዘርቼ ቢሆን ኖሮ ይላል፤ እሸቱን እየበላ ነዶውን ሲሰበስብም ደስ ይለዋል፡፡ እንዲሁ በክርስትና ሕይወታቸው የጸኑ ሰማዕታት ከተሳለ ስለት፣ ከነደደ እሳት ሲገቡ መከራው ይሰማቸዋል፤ ጻድቃን ፍትወታት እኩያት ኃጣውእ ርኵሳት ሕሊናቸውን ያስጨንቃቸዋል፣ ድል ከነሡ በኋላ ግን ሰማያዊ አክሊልን ተቀዳጅተው በተድላ በደስታ ይኖራሉ፡፡

ንጉሡ ቆስጠንጢኖስ በአካለ ነፍስ ሆኖ መነኮሳት በአክናፈ እሳት ወደ ኢየሩሳሌም ሲገቡ አይቶ አንድን አባት «ሰላም ለክሙ ብፁዓን መነኮሳት፤ ንዑዳን ክቡራን መነኮሳት ሆይ ሰላም ለእናንተ ይሁን»  አለው፡፡ መነኮሱም «አንተም እንጂ ንዑድ ክቡር ነህ በዘመንህ ቀርነ ሃይማኖት ቆሞልሀልና» አለው፡፡ ቆስጠንጢኖስም «ይህንን አውቄስ ቢሆን መንግሥቴን ትቼ እንደ እናንተ በምናኔ በኖርሁ ነበር» ብሎታል፡፡ (ፊልክስዩስ) ስለዚህ የዚህን ዓለም መከራና ሥቃይ የወዲያኛውን ክብር ያስረሳዋል፡፡ በዚህ ዓለም ሴት ልጅ በጭንቅና በምጥ ስትወልድ ታዝናለች ከወለደች በኋላ ግን ደስ ይላታል፤ ከወደለች በኋላ ግን ጭንቋንና ምጧን አታስበውም፤ ምክንያቱም ጨንቋንና ምጧን በልጇ ስለምትረሳው፡፡ (ዮሐ.፲፮፥፳፩) ስለዚህ ክርስቲያኖችም የዚህን ዓለም ውጣ ውረድ በተጋድሎና በትዕግሥት ሊያልፉት ይገባል፡፡ እንዲህም ከሆነ በሰው ኅሊና የማይተረጎም ሰማያዊ ክብርን ያገኛሉ፡፡

ወንጌላዊው ቅዱስ ዮሐንስ በራእዩ «እስከ ሞት ድረስ የታመንህ ሁን፤ የሕይወት አክሊልንም እሰጥሀለሁ» እንዲል፡፡ (ራእ.፫፥፲) ቅዱሳን፣ ጻድቃን፣ ሰማዕታት በተጋድሏቸውና በአሸናፊነታቸው ከሚቀበሉት ክብር አንጻር አሁን የሚያገኛቸው መከራ ኢምንት ነው፡፡ ስለዚህ ሰማያዊውን ክብር ለማግኘት መንፈሳዊውን ሩጫ መሮጥ ከኦርቶዶክሳውያን ይጠበቃል፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር፣ ወለወላዲቱ ድንግል፣ ወለመስቀሉ ክቡር፡፡

0 replies

Leave a Reply

Want to join the discussion?
Feel free to contribute!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *