እንደ ኦርቶዶክ ተዋሕዶ ሃይማኖት አማኝነት ስንኖር…

 

  ካለፈው የቀጠለ…

  ዲ/ን ታደለ ፈንታው (ዶ/ር)

 

በኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሃይማኖት በክርስትና ሕይወታችን እንድንኖር፣እንድንለማመድ፣ገንዘብም እንድናደርግ  የተፈለገው ሕይወት ውስብስብ፣ አስቸጋሪ፣ እንግዳ፣ ምናባዊ እና የማይደረስበት ሕይወትን አይደለም፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስን፣ጳውሎስን፣ዮሐንስን፣ ባስልዮስን፣ጎርጎርዮስን፣ ቄርሎስን ወይም በዘመን የከበሩ የቅድስት ቤተ ክርስቲያን ምስክርነት ያላቸውን ቅዱሳን አበውን እማትን አንዱን ወይም አንዷን መስተካከል፣ ማከል ሳይሆን መምሰል፣ የኑሮ ዱካቸውን፣ የሕይወት ዘይቤአቸውን በመከራ የተቀበሉትን ጽናታቸውን፣ በችግር መካከል ያለፈ ርጋታቸውን፣ በመከራ የተፈተነ ትሕትናቸውን ገንዘብ ማድረግ ነው፡፡

ሰሎሞን በርጋታ የምትመላለስ፣አምላኳን ለመፈለግ ጊዜ የማታባክንን የክርስቲያን ነፍስ እንዲህ በማለት ምክር ሲለግሣት እንመለከታለን፤«ያላወቅሽ እንደሆነ የመንጎችን ፍለጋ ተከትለሽ ውጪ»( መሓ ፩፡፰)

ስለምን መንጎች አላቸው? መንጋ ቁጥሩ በርካታ ነው፤ ዓላማ ሰንደቅ ይዞ እንደተሰለፈ ሠራዊት ነው፤ ከሩቁ ይታያል፡፡ መንጋውን የሚመራ አውራ ቀድሞ ከፊት ከፊት ይሄዳል፡፡ በፍየል መንጋ፣በከብቶች መንጋ በሌሎችም እንዲሁ ነው፡፡

ቅድስት ቤተ ክርስቲያን አንድስ ስንኳ ሊቆጥራቸው የማይችላቸው መንጎች የተመላለሱበት ቅድስት መካን ናት፡፡ እነዚህ መንጎች በሩቁ በሰውም በእግዚአብሔርም ዘንድ ይታያሉ፤ በትውልድ መካከል ያሸበርቃሉ፤ ያለ አጥር፣ ያለከልካይ፣ ያለመሪ፣ ያለአስተማሪ አልነበሩም፡፡ መንጋውን የሚመሩ፣ ከበጎቻቸው አስቀድሞ ራሳቸውን የሚሰጡ፣መከራን በበጎቻቸው ተገብተው የሚቀበሉ፤ እነርሱን ልቀቁአቸው እኔን ያዙ የሚሉ ድንቅ መሪዎች የነበሩአት አሁንም ያሏት የልዑል እግዚአብሔርን ክብር እያብለጨለጨች የምትኖር ቅድስት ናት፡፡

ምእመናንንም መንጎች አላቸው፤ መንጋ እውነተኛ የሆነውን እረኛ፤ መሪውን ተከትሎ የሚጓዝ ነውና፡፡ ስለዚህ አስቀድሞ ነቢያትን፣ በኋላም ሐዋርያትን ፣ከእነርሱ ቀጥሎ  ሐዋርያነ አበውን እነርሱ የወለዱአቸው ሊቃውንትን አስነሣ የእነዚህ ሁሉ መነሣት መንጋውን በተገቢው መንገድ ለመምራት ነው፡፡

እንድንመራ የተፈለገው ሕይወት

በተግባር እንድንመራ የተፈለገው ሕይወት ቀለል ያለና ለብዙዎች ቀንበር የማይሆን የፍቅር የመተሳስብ የመረዳዳት የመከባበር የመተጋገዝ ሕይወትን ነው፡፡ ሰው አብሮት የሚኖረውን በስሜት ፣ በፍላጎት፣ በአስተሳሰብ የሚመስለውን፣ በመካከሉ የሚኖረውን፤ ጎረቤቱን ጓደኛውን የማይወድ እና የሚያገልል ከሆነ የማያውቀውን አምላኩን እንዴት እወድድሃለሁ ሊለው ይችላል? እንደምንስ መውደድ ይቻለዋል፡፡

ቅዱስ የሐንስ ወንጌላዊ ወንድሙን የሚጠላ እስካሁን በጨለማ ይኖራል፤ወንድሙን የሚወድድ በብርሃን ይኖራል፤ማሰናከያም የለበትም ወንድሙን የሚጠላ ግን በጨለማ አለ፤ በጨለማም ይመላለሳል፤ የሚሄድበትንም አያውቅም ጨለማው  ዐይኖቹን አሳውሮታልና(፩ኛ ዮሐ.፪፡፫-፬) እንዳለ፡፡ ስለዚህ እንድንመራ የተጠየቅነው ሕይወት ጨለማ የተለየው ብርሃንን ማእከል ያደረገ ሕይወትን ነው፡፡ ወንጌላዊው እንዲህ በማለት ያጸናዋል፡፡ ከእርሱ የሰማናት ለእናንተም የምናወራላችሁ መልእክት እግዚአብሔር ብርሃን ነው ጨለማም በእርሱ ዘንድ ከቶ የለም የምትል ይህች ናት፡፡ (፩ኛ ዮሐ.፩፡፭)

ቀለል ያለ ሕይወት

ሌላው ቀላል ያለ ሕይወት የተባለው በመንገድ ላይ ማንም ማሰናከል የሌለበት ለማነጽ እንጂ ለማፍረስ ያይደለ፤ የሕይወት እንጂ የሞት መንገድን የማያውቅ ክርስቲያናዊ የጸሎት ሕይወት ነው፡፡ ለወንድሞቻችን ለጎረቤቶቻችን መልካም ሥራ ልንሠራላቸው፤ ወደ መልካም ሥራ እና የጸሎት ሕይወት ልንመራቸው ታዘናል፡፡

እንደ አንድ የተዋሕዶ ልጅ በጊዜ ልንነቃ፣ወገባችን ልንታጠቅ፣መብራታችንን ልናበራ በሥርዓት ልንኖር፣ በአምላካችን ፊት በኅብረት ልንቆም ታዘናል፡፡ ወንድሞች በኅብረት ቢኖሩ  እነሆ መልካም ነው፤ እነሆ ያማረ ነው”እንዲል (መዝ.፻፴፫፡፩-፪) እግዚአብሔር ኃጢአታችንን፣ በደላችንን፣ ይቅር እንዲለን ልንለምነው ይገባል፡፡

የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ እምነት ተከታይ ስንሆን ብዙ ወርቅ፣ብዙ ገንዘብ  ብዙ ጥሪት፣ መሬት፣ልብስ ሌላም ሌላ እንዲኖረን አይጠይቅም፤እነዚህ በጽናት እና በትዕግሥት ሆነን የአባቶቻችንን የእናቶቻችንን  ዐሠረ ፍኖት ተከትለን ስንጓዝ ወደእኛ የሚመጡ እንጂ እኛ ወደ እነርሱ የምንሄድባቸው ቁም ነገር ጉዳዮች አይደሉም፡፡ አስቀድማችሁ ጽድቁንና መንግሥቱን ፈልጉ ሌላው ይጨመርላችኋል የተባለው ስለዚህ ነው፡፡

ጥንቃቄያችን

እንደ ክርስቲያን መጠንቀቅ የሚኖርብን  የእግዚአብሔር የሆነውን ነገር ገንዘብ ለማድረግ በምናደርገው የዘወትር መንፈሳዊ ልምምዶች ላይ ነው፡፡ እነዚህ ልምምዶች እንድንጠነክር፣ በፈተና ተፈትነን ነጥረን እንድንወጣ፣ጸጋው እንዲበዛልን፣አእምሮአችን እንዲከፈት፣ ከእኛ በዘመን የቀደሙ አባቶቻችንና እናቶቻችን በምን አይነት መታመን እንደታመኑ የምንመለከትባቸው መነጽሮቻችን ናቸው፡፡

ቅዱስ ጳውሎስ ደቀ መዝሙሩ ጢሞቴዎስን እግዚአብሔርን ለመምሰል ራስህን አስለምድ፤ሰውነትን ለሥጋዊ ነገር ማስለመድ ለጥቂት ይጠቅማል፤ እግዚአብሔርን መምሰል ግን የአሁን እና የሚመጣውን ሕይወት  ተስፋ ስላለው ለነገር ሁሉ ይጠቅማል( ፩.ጢሞ.፬፡፯) በማለት ይመክራል፡፡ ነገር ግን በልምምድ ስፍራ ስንሆን ጠላት ወደ እኛ እንደሚመለከት፣ እንደሚያደባ፣ እንዲሚያታልል፣ እንደሚያባብል፣ እንደሚያስፈራራ ቢቻለው ሊያጠፋን ወደኋላ ገፍትሮ ሊጥለን እንደሚፈልግ  ጠንክሮም እንደሚሠራ  ማስተዋል ይገባል፡፡

ሌላው መጠንቀቅ የሚኖርብን ክርስቶስን ከሚመስል ነገር ግን ከክርስቶስ ያይደለ ሐሰተኛ አስተምህሮ ነው፡፡ ክፉ መንፈስ እና ሐሰተኛ አስተምህሮ በዓለሙ ላይ በከፍተኛ ሁኔታ ተሰራጭቷል፡፡ራሳቸውን ከፍ ከፍ የሚያደርጉ ግብዞች እና ሐሰተኛ ነቢያት ተሰማርተዋል፡፡ ከተቀበልነው፣አባቶቻችን እናቶቻችን እምነት ሊያስወጡን አጥብው እየሠሩ ነው፡፡ እንደ መልካቸው ስማቸው ልዩ ልዩ ነው፡፡

እኛ ግን ዕለት ዕለት እውነተኛ የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ተከታይ ሊያደርገው የሚገባውን መንፈሳዊ ሥራ ብቻ በመሥራት፣ የእኛ ወገኖች የሆኑትን ብቻ በመስማት፣ ከቤተ ክርስቲያናችን አስተምህሮ የሚቀዳውን ትምህርት፣ ኑሮ፣ ሕይወት፣ ሥርዓት፣ልማድ፣ ወግ ፍልስፍና እና አስተሳሰብ ከፍ አድርገን  ይዘን፤ ለመያዝም ጠንክረን እየሠራን በጽናት እና በጥንቃቄ ልንጓዝ ያስፈልጋል፡፡

ጥንካሬያችን

መምህራችን ብርሃነ ዓለም ቅዱስ ጳውሎስ ሲያስተምረን በቃልና በኑሮ በፍቅርም ፣በእምነትም፣ በንጽሕናም፣ ለሚያምኑቱ ምሳሌ ሁን እንጂ ማንም ታናሽነትህን አይናቀው፤(፩ኛ ጢሞ.፫፡፲፪) ብሎናል፡፡በንግግር፣በግብርም የሚደረግ ፍቅራችን፣ ራስን መግዛታችንን የወጣትነት ጊዜያችንንም ፍሬያማ እና የተወደደ እንደሚያደርገው አስተውሉ፡፡

ነገር ግን እነዚህን ነገሮች በማሟላት ሂደት ውስጥ ችግር ቢገጥማችሁ፣ፈተናዎች ቢደራረቡ  ጌታችን  መድኃኒታችን፣ክርስቶስ ቤዛችን፣ ክርስቶስ ነጻነታችን፣ ክርስቶስ አምላካችን የበዛውን መከራ እንደተቀበለ በእምነት አስተውሉ፡፡የለበስነው ልብስ አንዳች ሌላ ነገር ሳይሆን ራሱን ክርስቶስን እንደሆነ ልብ በሉ፡፡ ይህንን ልብስ መከራ የማያጠፋው፣ ችግር የማይበግረው ሰማያዊ ልብስ እንደሆነ በፍቅር እንመልከት፡፡

ወንድሞችንና እኅቶችን ጽናት ይሰጣቸው ዘንድ፣ በእምነት ጠንክረው ይቆሙ ዘንድ፣እግሮቻቸውን የወንጌልን መጫሚያ ይጫሙ ዘንድ አንዳችን ስለሌሎቻችን ዘወትር እንጸልይ፡፡ጥበብን፣ ሰላምን፣ ትእግሥትን፣ ትሕትናን፣ ጤንነትን፣ ማስዋልን፣ ሀብትን፣ ረጅም ዕድሜን እንዲሰጠን ዘወትር በእምነት እንጠይቀው፡፡

አስቀድመን የጠቃቀስናቸውን ነገሮች በግል ሕይወታችን በቤታችን በመኝታ ክፍላችን በግቢ ጉባኤዎቻችን፣በማኅበረሰባችን፣በአገራችን  ቢበዙልን የእግዚአብሔር የመንግሥቱ ወራሾች እንሆናለን፡፡ ስለዚህ ወጣትነታችንን እንደ ታላቅ ጥንካሬ ተጠቅመን ወደ እግዚአብሔር በእምነት፣ በትሕትና በፍቅር እና በየዋህነት እንቅረብ፡፡

ከእኛ ይልቅ በዕድሜ ለግላጋ የሆኑ ታናናሾቻችን ማስተማራችንን እርግጠኛ እንሁን፡፡ ቅዱስ ከሆነው ኦርቶዶክሳዊ ትውፊት ጋር ይተዋወቁ ዘንድ እንትጋ፡፡ በተመሳሳይ ሁኔታ ታላላቆችን እናክብር፡፡ ነገር ግን አንድ ነገር ጥንቃቄ እናድርግ ከታላላቆችን መማር የሚኖርብን በጎ የሆነውነ ነገር ብቻ ነው፡፡ ክፋትን እንጥላ እናስወግደውም፡፡ እኛም ወደ አረጋዊነት የምንሄድበት ዘመን ይመጣልና አስቀድመን በኦርቶዶክሳዊ ትውፊት ያዘጋጀናቸው ወጣቶች የሚገባንን ክብር ይሰጡናል፡፡ ስለዚህ በተቻለ መጠን ሕፃናት ላይ ጊዜን ሰጥተን ዕውቀትን ለማፍሰስ እንትጋ፡፡ልጆቻችን ወንድሞቻችን የሚገባቸው ዕድሜ ላይ ሲደርሱ በካህን ቡራኬ ወደ ተቀደሰ ጋብቻ እንዲመጡ መሠረት የምንጥልበት ጊዜ የወጣትነት ጊዜ አሁን ነው፡፡

ወጣቶቻችን ጤናቸው የተጠበቀ፣ አእምሮአቸው የተጠበቀ፣ ክፋትን የማያውቅ በጎ የሆነውን ነገር ገንዘብ ለማድረግ የሚተጉ እንዲሆኑ የምንችለውን ያህል እንርዳ፡፡ ጠንካራ የሆነ ማኅበረሰብ እና ወጣትን ለመገንባት የትኩረት አቅጣጫዎቻችን ይሁኑ፡፡

ማጠቃለያ

በሰላም ማሰሪያ የመንፈስን አንድነት ለመጠቅ(ኤፌ.፬፡፫) በምናደርገው ፍጻሜ የሌለው ተጋድሎ የቱንም ያህ  የቋንቋ፣ የአስተዳደግ የባህል ልዩነቶች ቢኖሩንም በአንድ መንፈስ በአንድ ልብ በአንድ አሳብ የክርስቶስ እንድንሆን በቅድስት ቤተ ክርስቲያን አማካኝነት ተጠርተናል፡፡

ቤተ ክርስቲያን አንዲት ቅድስት፣ ኩላዊት፣ ሐዋርያዊት እና የሁላችንም  መንፈሳዊ ሀብት ናት፡፡ እብሪተኞች አላዋቆች እና ሃይማኖት የሌላቸው ሰዎች እንደፈለጉ የሚያደርጓት አይደለችም፡፡ ስለዚህ መሠረታዊ የሆነው አስተሳሰባችንን በምድረ በዳ እንደደረቀችው የበለስ ዛፍ ሳይሆን በወንዝ ዳር እንደተተከለችው ዛፍ ነው፡፡

ኦርቶደክስ ተዋሕዶ ሃይማኖት ተከታዮች እንደመሆናችን ልዩ የአግዚአብሔር ገንዘቦች የሆንን ነን፡፡ ቤተ ክርስቲያን በሁለንተናዋ እንድታድግ አእምሯችን የፈቀደውን፣ አቅማችን የቻለውን ያህል ከማበርከት ወደኋላ አንበል፡፡

አባቶቻችንን የምንመስል፣ በተስፋ የምንጠብቅ ግዴታችንን እና መብታችንን ጠንቅቀን የምናውቅ ፣በአስተሳሰባችን ከፍ እና ላቅ ያልን ወጣቶች ሆነን ለመሥራት ዕለት ዕለት ልንተጋ ይገባል፡፡  እውነተኛ የሆነ ትጋትን እንፈልግ፤ ገንዘብም እናድርግ፡፡ በቤታችን፣ በማኅበረሰባችን፣ በግቢያችን እውነተኛ ሰላም እንድናመጣ የነገሮችን አካሂያድ በጥንቃቄ እንመርምር ፤ በእውነት ጉዳይ ደፋሮች እና ጽኑዎች እንሁን፡፡

ይቆየን!!

 

0 replies

Leave a Reply

Want to join the discussion?
Feel free to contribute!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *