ንስሓ አባቶችና የግቢ ጉባኤያት አገልግሎት

ዲ/ን ኢያሱ መስፍን

የግቢ ጉባኤያት አገልግሎት ወጣቱን ወደ መንፈሳዊ ልዕልና ለማድረስ የሚደረግ ውጣ ውረድ የበዛበት ጉዞ ነው። ለዚህም የጉዞው ተሳታፊዎች እና ጉዞውን የተቃና ለማድረግ ከፊት የሚቀድሙ መሪዎች የአገልግሎት ተነሳሽነትና ቁርጠኝነት ለውጤቱ ማማር ትልቁን ድርሻ ይወስዳሉ፡፡

በየጊዜው የግቢ ጉባኤያትን አገልግሎት የሚረከቡ ወጣቶች በሚኖራቸው ዕውቀት፣ መረዳት እና ትጋት ልክ አገልግሎቱን ለማስኬድ እንዲሁም ከታለመለት ግብ ለማድረስ መጣራቸው አያጠራጥርም። እነዚህ ወጣቶች ዕቅዶቻቸውን ለማስፈጸም ከሚደረግላቸው መዋቅራዊ ድጋፍ ባለፈ ጽኑ የሆነ መንፈሳዊ እገዛ ያስፈልጋቸዋል። ይህንን እገዛ ደግሞ መስጠት የሚችሉት የንስሓ አባቶች ናቸው

ወደ አንድ ተራራ የሚወጣ ሰው መውጫ መንገዱን በሚገባ የሚያውቅ መሪ ማግኘት ግድ ይለዋል። የንስሓ አባቶችም ድርሻ ይህን የመሪነት እና የመንገድ ጠቋሚነት ሚና መጫወት ነው፡፡ ከዚህ ማስተዋል እንደሚቻለው በንስሓ አባትነት የሚሾሙ ካህናት ኑዛዜ ተቀብለው የኃጢአት ሥርየትን ከማሰጠት ባለፈ የመንፈስ ልጆቻቸውን በምግባር እና በሃይማኖት ወደ ድኅነት ጎዳና የመምራት ሥራን ይሠራሉ።

ማንኛውም መንፈሳዊ ሥራ በዕውቀትና በችሎታ ላይ በተመሠረተ የራስ መተማመን መነሻነት ብቻ ሊከወን አይችልም፡፡ “እግዚአብሔር ቢፈቅድ ብንኖርም ያን ወይም ይህን እናደርጋለን” ተብሎ የታቀደን ዕቅድ ለመፈጸም በሚደረግ ጥረት ውስጥ የእግዚአብሔርን እገዛ ትልቅ መሣሪያ አድርጎ መጠቀም ግድ ይላል። (ያዕ. ፬፥፲፭)

የንስሓ አባቶችም ይህ አገልግሎት ከእግዚአብሔር ፈቃድ ውጪ የሚፈጸም እንዳይሆን የመምራትና የማስፈጸም ትልቅ ድርሻ አላቸው። ከእነዚህም ውስጥ ጥቂቶቹን ለመቃኘት ያህል፦

. ከመንፈሳዊ ዝለት ማንቃት

የግቢ ጉባኤያት አገልግሎት ኦርቶዶክሳውያን ተማሪዎች ከትምህርታቸው ጎን ለጎን በሚኖራቸው ጊዜ በጋራ የሚፈጽሙት አገልግሎት እንደመሆኑ ትዕግሥትን እና ብዙ ጥረትን ይጠይቃል። ነገሮች በተፈለገው ልክ እና ሁኔታ ያለመሄድ ዕድላቸው ሰፊ ከመሆኑ የተነሣ በግለሰቦች ላይ በሚኖር የአገልግሎት ጫና፣ በመርሐ ግብሮች አለመሳካት፣ በቦታ፣ በጊዜ እና በመሳሰሉ ሁኔታዎች አለመመቻቸት ምክንያት በግቢ ጉባኤ አገልግሎት ተሳታፊ በሆኑ ተማሪዎች ዘንድ መባከንን ልናስተውል እንችላለን፡፡ ይህም እንደ አልዓዛር እኅት ማርታ ከአገልግሎት መብዛት የተነሣ መባከን (ሉቃ.፲፥፵) እና ከቃለ እግዚአብሔር እንዲሁም ምሥጢራትን ከመካፈል መራቅ ሊያጋጥሙ የሚችሉ ችግሮች ናቸው።

እነዚህን ችግሮች በመፍታት በኩል ከንስሓ አባት የተሻለ አቅም ያለው አካል ማግኘት አይቻልም። በግቢ ጉባኤው ውስጥ አገልግሎት በመስጠት ላይ ያሉ አባቶች የንስሓ ልጆቻቸው ያሉባቸውን ፈተናዎች ከማንም በተሻለ ያውቃሉና ችግሮቹ ላይ ያተኮሩ የመፍትሔ ሥራዎችን ለመሥራት ትልቁን ድርሻ የመወጣት አቅም አላቸው። በአገልግሎት ላይ ያሉ ተማሪዎች ተስፋ እንዳይቆርጡ በማጽናት፣ በአገልግሎት በመባከን ከሚመጣ መንፈሳዊ ዝለት ከምሥጢራት ሲርቁ እግዚአብሔርን አብነት አድርገው ‘ወዴት አለህ’ (ዘፍ. ፫፥፱) ብሎ መጥራት፣ መፈለግና ማጽናት ይጠበቅባቸዋል፡፡

. እግዚአብሔር ዘንድ ተቀባይነት ያለው አገልግሎት እንዲፈጽሙ ማስቻል

ቃየን ወንድሙን በመግደል በደል በፈጸመ ጊዜ ፈታሔ በጽድቅ ከሆነ እግዚአብሔር የተፈረደበት ፍርድ ተቅበዝባዥ መሆን ነው። (ዘፍ. ፬፥፲፪) ሊቃውንት አባቶቻችን “ምድርንም ባረስክ ጊዜ እንግዲህ ኃይሏን አትሰጥህም” የሚለውን ኃይለ ቃል መነሻ አድርገው   ተቅበዝባዥነትን በከንቱ መድከም፣ ጀምሮ አለመፈጸም፣ ዘርቶ ፍሬ ማጣት መሆኑን በትርጓሜአቸው አስረድተውናል። የግቢ ጉባኤ አገልጋዮች ድካማቸው ከንቱ አገልግሎታቸውም ፍሬ አልባ እንዳይሆን ዘወትር ራሳቸውን በጸሎት በማነጽ፣ በንስሓ ማንጻት እና ማዘጋጀት ግድ ይላቸዋል።

የንስሓ አባቶች ንስሓን የመቀበል እና የመናዘዝ አገልግሎት ደግሞ በሌላ በማንም ሊተካ የማይችል ነው። በመሆኑም በግቢ ጉባኤ አገልግሎት ተሳታፊ የሆኑ ተማሪዎችን በመናዘዝ እና ከኃጢአት እንዲነጹ በማድረግ ለአገልግሎቱ መሳካት የበኩላቸውን አባታዊ ኃላፊነት ሊወጡ  ይገባቸዋል።

. የአገልግሎቱን ቀጣይነት ማረጋገጥ

የግቢ ጉባኤ አገልጋዮች በእያንዳንዱ የአገልግሎት እርምጃቸው የንስሓ አባቶቻቸውን ተሳታፊዎች ቢያደረጓቸው ከአገልግሎታቸው መሳካት ባለፈ ከእነርሱ በተጨማሪ ሌሎች አገልጋዮች በሚመጡበት ጊዜ የግቢ ጉባኤን አገልግሎት የተረዱ እና አዲሶቹን አገልጋዮች በተሻለ ጎዳና መምራት የሚችሉ አባቶችን ማፍራት ይቻላል። ይህም የማእከላትን ጫና ከመቀነስ ባሻገር አዳዲስ አገልጋዮች አገልግሎቱን ከታች ከመጀመር ይልቅ በየአጥቢያቸው ያሉ የንስሓ አባቶቻቸውን በማማከር ከነበረበት የማስቀጠል እና የማሳደግ ዕድል እንዲያገኙ ያደርጋል።

ተግዳሮቶች

የግቢ ጉባኤያትን አገልግሎት መረዳት የሚችሉ እና ወርደው ከተማሪዎች ጋር ለመሥራት የመንፈስ ዝግጁነት ያላቸው የንስሓ አባቶች ያስፈልጉናል። የንስሓ አባቶች እና የግቢ ጉባኤያት ተማሪዎች ቁጥር አለመመጣጠን፣ እስከ አለመግባባት የሚያደርስ ሰፊ የዕድሜ ልዩነት መኖር፣ ለረጅም ጊዜ በገዳማዊ ሕይወት ያለፉ መነኮሳት ለግቢ ጉባኤ ተማሪዎች አባት ሆነው መመደባቸው፣ የቋንቋ ክፍተት መኖሩ፣ ዘመኑን ዋጅቶ በሚገባው ልክ ወጣቱን ለማስተማር እና ወደ ቤተ ክርስቲያን ለማቅረብ የሚያስችል የትምህርት ዝግጅት የሌላቸው አባቶች በንስሓ አባትነት መመደባቸው እና የመሳሰሉት ምክንያቶች የንስሓ አባቶች በሚፈለገው መጠን በግቢ ጉባኤያት አገልግሎት ውስጥ የሚጠበቅባቸውን በጎ አስተዋጽኦ እንዳያበረክቱ እንቅፋት ሆነዋል።

ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ የእረኝነት ሥራን የሚሠሩ እነዚህ ካህናት ትሩፋትን እና ትጋትን ገንዘብ ያደረጉ፣ በመንፈስ ብርታት፣ በትምህርተ ሃይማኖት ብስለት እና በተቀደሰ ሕይወት ይጠብቋቸው ዘንድ ከተሾሙላቸው ሰዎች እጅግ ተሽለው መገኘት እንዳለባቸው ሲያስረዳ “በካህኑና በምእመናኑ መካከል ሊኖር የሚገባው ልዩነት አእምሮ ባለው ሰው እና ደመ ነፍሳዊ በኾኑ እንስሳት መካከል ያለውን ያህል የሰፋ ሊሆን ይገባል። የጉዳዩ ክብደት እና አሳሳቢነት እጅግ ታላቅ ነውና” ይላል። የዚህ ዓይነት ጥንቃቄ በተለይ ዘመን በወለዳቸው አምላክ የለሽ እሳቤዎች እና ፍልስፍናዎች፣ በምንፍቅና ትምህርቶች፣ በሰፋፊ የኃጢአት ልምምዶች እና በመሳሰሉት ለመነጠቅ የሰፋ ዕድል ላላቸው የግቢ ጉባኤያት ተማሪዎች አባት ሆነው የሚሾሙ ካህናትን በተመለከተ ሲሆን ይበልጥ ምክንያታዊ ይሆናል።

የመፍትሔ ሐሳቦች

የንስሓ አባቶች ኑዛዜን ተቀብሎ ከኃጢአት እሥራት ከመፍታት ባለፈ በግቢ ጉባኤ አግልግሎት ውስጥ ጠለቅ ያለ ተሳትፎ እና የእረኝነት ድርሻ እንዳላቸው መረዳት ይገባቸዋል፡፡ በግቢ ጉባኤያት አገልግሎት ላይ ያሉ ወጣቶችም ዝግጅት ያላቸውን የንስሓ አባቶች የመንፈስ ልጆቻቸውን በተመለከተ በሚወሰኑ ውሳኔዎች እና በሚሠሩ ሥራዎች ላይ ንቁ ተሳታፊዎች እንዲሆኑ ሁኔታዎችን ማመቻቸት ያስፈልጋል። በመሆኑም በንስሓ አባቶችና በልጆቻቸው መካከል ያለውን ግንኙነት የተከሳሽ እና የዳኛ አስመስሎ የሚያሳየውን ምዕራባዊ ነጽሮት በማራቅ ኦርቶዶክሳዊ በሆነው የሐኪም እና ታካሚ ዓይነት ግንኙነት እሳቤ መነሻነት ጥብቅ የሆነ መረዳዳት እና መግባባት ላይ የተመሠረተ ግንኙነት መፍጠር መቻል ያስፈልጋል፡

ማእከላት እና የሚመለከታቸው የቤተ ክርስቲያን አካላትም ግቢ ጉባኤያቱ በያሉባቸው አካባቢዎች የሚነገሩ ቋንቋዎችን እና የአካባቢውን ባህል የተረዱ ካህናትን ከዚያው አካባቢ እንዲገኙ በማድረግ በየደረጃው ያሉ መሠረታዊ ችግሮችን ለመቅረፍ ሊሠሩ ይገባል። በተጨማሪም አገልግሎታቸው ንስሓን ከመቀበል ያለፈ እና ሁለንተናዊ የመንፈሳዊ አባትነት አገልግሎት መሆኑን ተረድተው በግቢ ጉባኤያት አገልግሎቶች ውስጥ የበኩላቸውን እንዲወጡ ማንቃትና ይህንን ማድረግ እንዲችሉ ሥልጠናዎችን እንዲያገኙ ማድረግ ተገቢ ነው፡፡

0 replies

Leave a Reply

Want to join the discussion?
Feel free to contribute!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *