ዘመነ ጽጌ
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የወቅቶች አቆጣጠር መሠረት ከመስከረም ፳፮ እስከ ኅዳር ፭ ቀን ያለው ወቅት “ዘመነ ጽጌ” ተብሎ ይጠራል፡፡ በግእዝ ቋንቋ “ጸገየ” ማለት “አበበ፤ አፈራ፤ በውበት ተንቆጠቆጠ፤ አጌጠ፤ የፍሬ ምልክት አሣየ” ማለት ነው፡፡
ዘመነ ጽጌ ምድር በልምላሜ የምትንቆጠቆጥበት ወቅት ሲሆን በቅድስት ቤተ ክርስቲያን እመቤታችን ቅድስት ድንግል ልጇን ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ሊገድለው ከሚሻው ከሄሮድስና ከጭፍሮቹ ለማዳን ወደ ምድረ ግብጽ የተሰደደችበት ወቅት የሚታሰብበት ነው፡፡ ይህንንም መሠረት በማድረግ ካህናት፣ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያንና ምእመናን በየሳምንቱ እሑድ ከምሽቱ ጀምሮ ማኅሌተ ጽጌ ይቆማሉ፤ ሰዓታት ያደርሳሉ፡፡ በዚህ ጊዜ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምን በአበባ፣ በትርንጎ፣ በሮማን፣ … እየመሰሉ ለፈጣሪ መዝሙርና ምስጋና ያቀርባሉ፡፡
በይሁዳ ክፍል በቤተ ልሔም ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በተወለደ ጊዜ ሰብአ ሰገል ከምሥራቅ ወደ ኢየሩሳሌም “ኮከቡን ከምሥራቅ አይተን እንሰግድለት ዘንድ መጥተናልና የተወለደው የአይሁድ ንጉስ ወዴት ነው?” እያሉ መጡ፡፡ በዘመኑ ንጉሡ ሄሮድስ ከእርሱ ሌላ እስራኤልን የሚገዛ እንደሌለ ይመካ ነበርና የጌታችን መድኀኒታችን ኢያሱስ ክርስቶስ መወለድ በሰማ ጊዜ ደነገጠ፤ ኢየሩሳሌምም በመላዋ ከእርሱ ጋር ደነገጠች፡፡” (ማቴ. ፪፥፩-፫)
“አንቺ የኤፍራታ ምድር ቤተ ልሔም ሆይ! አንቺ በይሁዳ አእላፋት መካከል ትሆኚ ዘንድ ታናሽ ነሽ፤ ነገር ግን አወጣጡ ከቀድሞ ጀምሮ ከዘላለም የሆነ በእስራኤል ላይ ገዢ የሚሆን ከአንቺ ይወለዳል፡፡” የሚለው የነቢያት ትንቢት ሄሮድስን አስጨነቀው፡፡ ስለዚህም ጌታችንን ሊገድለው ወደደ፡፡ (ማቴ. ፪፥፩-፪) እውነቱንም ሲረዳ ሰብአ ሰገልን በስውር አስጠርቶ “ኮከቡ የታየበትን ዘመን ከእነርሱ ተረዳ፡፡ “ሄዳችሁ የዚያን ሕፃን ነገር ርግጡን መርምሩ፤ ያገኛችሁትም እንደሆነ እኔም መጥቼ እሰግድለት ዘንድ በእኔ በኩል ተመልሳችሁ ንገሩኝ ብሎ ወደ ቤተ ልሔም ሰደዳቸው፡፡” (ማቴ. ፪፥፬-፰)
ሰብአ ሰገልም ወደ ቤተልሔም ሲሄዱ በምሥራቅ ያዩት ኮከብ ሕፃኑ ባለበት ቦታ ላይ ደርሶ እስኪቆም ድረስ ይመራቸው ነበር፡፡ በከብቶች ማደሪያ ግርግም እንስሳት በትንፋቸው እያሟሟቁት ሕፃኑን ከእናቱ ከቅድስት ድንግል ማርያም ጋር አገኙት፤ ወድቀውም ሰገዱለት፡፡ ሳጥኖቻቸውንም ከፍተው ወርቅና ዕጣን፣ ከርቤም እጅ መንሻ አቀረቡለት፡፡
ከዚህ በኋላ መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል በሕልም ለአረጋዊው ዮሴፍ ተገልጦ “ሕፃኑንና እናቱን ይዘህ ወደ ምድረ ግብጽ ሽሽ፤ ሄሮድስ ሕፃኑን ለመግደል ይፈልጋልና” ብሎ ነገረው፤ ሕፃኑንና እናቱን እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምን ይዞ በሌሊት ወደ ግብጽ ምድር ተሰደደ፡፡ (ማቴ.፪፥፲፫)
እመቤታችን ልጇን አዝላ ከአረጋዊው ዮሴፍ እና ከሰሎሜ ጋር የአሥራ አምስት ዓመት ብላቴና ስትሆን ረሃቡንና ጥሙን ተቋቁማ ልጇን ከሄሮድስ እጅ ለማዳን ወደ ግብጽ በረሃ ለመሰደድ ተገደደች፡፡
እግዚአብሔር በነቢዩ ሆሴዕ ላይ አድሮ “ልጄን ከግብጽ ጠራሁት” እንዲል አስቀድሞ እንደ ተናገረው ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በልጅነቱ ወደ ምድረ ግብጽ የተሰደደው የተነገረው የነቢያት ትንቢት ይፈጽም ዘንድ ነው፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ አምላካችን ክርስቶስ ያለ ጊዜው (ዕለተ ዓርብ) ደሙ አይፈስምና ሊገድለው ከሚፈልገው ክፉ ንጉሥ ከሄሮድስ ለማምለጥ ነው፡፡ (ሆሴ. ፲፩፥ ፩-፪)፡፡
ሰብአ ሰገል ለጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወርቅ ዕጣን እና ከርቤ አቅርበው ወደ ሀገራቸው ሲመለሱ ንጉሡ ሄሮድስ ወደ እርሱ መጥተው ሕፃኑ ያለበትን እንዲነግሩት ባሳሰባቸው አልተመለሱም፡፡ መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል በሕልም ነግሯቸው ስለነበር በሌላ መንገድ ወደ ሀገራቸው ተመለሱ፡፡
ሄሮድስም ሰብአ ሰገል ወደ እርሱ እንዳልተመለሱና እንደዘበቱበት በተረዳ ጊዜ እጅግ ተቆጣቶ በቤተ ልሔምና በአውራጃዎችዋ ያሉትን ከሁለት ዓመት እና ከዚያም በታች የሆናቸውን ሕፃናት አስገደለ፡፡ ያን ጊዜ በነቢዩ ኤርምያስ የተነገረው ትንቢት ተፈጸመ፡፡ እንዲህ ሲል፡- “ራሔል ስለ ልጆችዋ ስታለቅስ ብዙ ልቅሶና ዋይታ በራማ ተሰማ፤ መጽናናትንም እንቢ አለች፣ ልጆችዋ የሉምና፡፡” እንዲል፡፡ (ማቴ. ፪፥፩-፲፰)
ከሦስት ዓመት ከመንፈቅ የግብጽ ስደት በኋላም ሄሮድስ በመሞቱ የእግዚአብሔር መልአክ ለአረጋዊው ዮሴፍ በግብጽ ሀገር በሕልም ታየው፡፡ እንዲህ ሲል፡- “የሕፃኑን ነፍስ የሚሹ ሙተዋልና ተነሥተህ ሕፃኑንና እናቱን ይዘህ ወደ እስራኤል ሀገር ሂድ” አለው፡፡ እርሱም ተነሥቶ ሕፃኑንና እናቱን ይዞ ወደ እስራኤል ምድር ገባ፡፡ (ማቴ. ፪፥፲፱-፳፩)
የቅድስት ቤተ ክርሰቲያናችን ሊቃውንት ይህንን መሠረት አድርገው “ተመየጢ ማርያም ሀገረኪ ናዝሬተ፣ በላዕሌኪ አልቦ ዘያበጽሕ ሁከተ፣ ወኢትጎንድዪ በግብጽ ከመ ዘአልብኪ ቤተ፣ ዘየኀሥሦ ለወልድኪ ይእዜሰ ሞተ፣ በከመ ነገሮ መልአክ ለዮሴፍ ብሥራተ፤ ማርያም ሆይ! ወደ ሀገርሽ ወደ ናዝሬት ተመለሺ፤ በአንቺ ላይ ሁከት የሚያመጣ ማንም የለም፡፡ ቤት እንደሌለሽ ሁሉ በግብጽ አትቆይ፡፡ ለዮሴፍ በሕልሙ መልአክ እንደ ነገረው የሕፃኑን ነፍስ የፈለገው (ጠላት ሄሮድስ) ሞቷልና” በማለት ሊቃውንቱ በማሕሌት ሲያመሰግኑ ያድራሉ፡፡
በአጠቃላይ በዘመነ ጽጌ ዘወትር እሑድ፣ እሑድ በመላው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ አብያተ ክርስቲያናት ማኅሌት በመቆም ታላቅ በዓል ይደረጋል፡፡ እመቤታችን ልጇን ይዛ ከሰሎሜና ከዮሴፍ ጋር ወደ ምድረ ግብጽ በተሰደዱ ጊዜ የደረሰባትን ጭንቅና ውኃ ጥም፤ ግፍና እንግልት ለማስታወስና ከግብጽ ወደ ሀገሯ ናዝሬት መመለስዋን ለመዘከር ሲባል በዘመነ ጽጌ የደመቀ አገልግሎት ይከናወናል፡፡
በዚህ ወቅት የሚቆመው የሰንበት ማኅሌቱ፣ መዝሙሩና ቅዳሴው እንደዚሁም የሚቀርበው የክብር ይእቲና የዕጣነ ሞገር ቅኔ ሁሉ በዘመነ ጽጌ ላይ የተመሠረተ ነው፡፡ እመቤታችን ስደት በረከት ያገኙ ዘንድ የፈቃድ ጾም የሚጾሙ ምእመናንም ብዙዎች ናቸው፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
Leave a Reply
Want to join the discussion?Feel free to contribute!