ዘረኝነት፡ የዘመናችን ወጣቶች ተግዳሮት

በአዱኛ ጌታቸው

ክፍል አንድ

መግቢያ

እንደ ማኅበራዊ ሳይንስ ተመራማሪዎች የወጣትነት ዘመን የሽግግር ዘመን ነው፡፡ ይህ ሽግግር በሁለት ይመደባል፡፡ አንደኛው ከልጅነት ወደ ጎልማሳነት የሚሸገጋሩበት ሲሆን ሌላኛው ደግሞ ከቤተሰብ ጥገኝነት ራስን ወደ መቻል የሚሸጋገሩበት ዘመን ነው፡፡ ይህ የሽግግር ዘመን ወጣቶች ጊዜያቸውን በማስተዋል ከመሩት ለፍሬ የሚበቁበት በማስተዋል ካልመሩት ደግሞ ለጥፋትና ለውድቀት የሚደራጉበት ጊዜ ነው፡፡

ኢትዮጵያዊው ሊቅ ወልደ ጊዮርጊስ ወልደ ዮሐንስ ስለ ወጣትነት ዘመን ሲናገሩ “በአበባ ውስጥ የፍሬ እንቡጥ ለመያዝ መጀመሪያ የአትክልቱ አያያዝ ደንበኛ ሆኖ ሲገኝ ይጠቅማል፡፡ ወጣትም ከፍሬ ለመድረስ የሚችለው በወጣትነቱ በሠራው ሥነ ምግባር ነው፡፡ ወጣት ሰውነቱን በቆሻሻ ምግባር ያቆራመደው እንደሆነ ተስፋ ይቆርጣል፡፡ ያቀደውም ነገር ከመንገድ ይመለሳል፡፡ መንፈሳዊ ዕድል እንዲያውም አይታሰብም” ይላሉ፡፡ (ሥነ ምግባር ገጽ ፶፫)

በአጠቃላይ የወጣትነት ጊዜ ለቀጣይ የዕድሜ ዘመናት መሠረት የሚጣልበት በመሆኑ በማስተዋል መጓዝን የሚጠይቅ ነው፡፡ ወጣቶች በዘመናቸው ልዩ ልዩ አካላዊ፣ ሥነ ልቡናዊ፣ ማኅበራዊና መንፈሳዊ ተግዳሮቶች ሊገጥሟቸው ይችላል፡፡ ከእነዚህ ተግዳሮቶችም አንዱ ዘረኝት ነው፡፡

ዘረኝነት ምንድነው?

በማኅበራዊ ሳይንስ ዘርፍ ወጥነት ያለው ትርጕም ለመስጠት አስቸጋሪ ከሆኑ ቃላት አንዱ ዘር ወይም በእንግሊዝኛው (Race) የሚባለው ነው፡፡ በተለይም ዘር፣ ጎሳ፣ ነገድ፣ ብሔር ወዘተ የሚሉ ቃላት በተለያዩ አገራት የተለያየ ትርጕምና ይዘት ሊኖራቸው ስለሚችል ተመሳሳይ ግንዛቤ ለመያዝ አስቸጋሪ ያደርገዋል፡፡

ለአብነት አንዳንድ ሰዎች ከቅርብ ዐሥርት ዓመታት ወዲህ በሀገራችን የሚታየው የሕዝብ አለመረጋጋትና ቀውስ ምንጩ ተግባራዊ እየሆነ ያለው የኢትዮጵያ መንግሥታዊ አወቃቀር ዘርን ወይም ጎሳን ወይም ቋንቋን መሠረት ያደረገ በመሆኑ ነው ብለው ይሞግታሉ፡፡ ፖለቲከኞችም ይሁን የፖለቲካ ተንታኞች ይህን ይበሉ እንጂ አሁን ላይ ያለው የሃገሪቱ ሕገ መንግሥት መንግሥታዊ መዋቅሩ በዘር፣ ወይም በጎሳ፣ ወይም ደግሞ በቋንቋ ላይ የተመሠረተ ነው አይልም፡፡

የኢፌድሪ ሕገ መንግሥት አንቀጽ ፵፮ “ክልሎች የሚዋቀሩት በሕዝብ አሰፋፈር፣ ቋንቋ፣ የማንነት እና ፈቃድ ላይ በመመሥረት ነው” ይላል፡፡ ስለዚህ ከሕገ መንግሥት አንጻር ከተመለከትነው የሀገራችን ሕገ መንግሥት ለብቻው ነጥሎ በዘር፣ ወይም በቋንቋ፣ ወይም በጎሳ ላይ የተመሠረተ ነው እንደማይል አንብቦ መረዳት ይቻላል፡፡ ታዲያ መንግሥታዊ አወቃቀሩ በዘር ላይ ወይም በጎሳ ወይም በቋንቋ ላይ ነው የተመሠረተው የሚለው አባባል ምንጩ ምን ይሆን? ለሚለው መላምት ከመስጠት የዘለለ ተጨባጭ ማስረጃ ማግኘት አዳጋች ነው፡፡

እርግጥ አንዳንድ ፖለቲከኞችና የግል ጥቅማቸውን የሚያስቀድሙ ግለሰቦች ሕገ መንግሥቱን በራሳቸው አረዳድና ፍላጎት በመተረጎም ለራሳቸው ዓላማ ማስፈጸሚያ ሊያደርጉት ይችላሉ፡፡ በዚህ ምክንያት ኢትዮጵያውያን በቋንቋቸው፣ በባህላቸው፤ በሃይማኖታቸው በአጠቃላይ በማንነታቸው ምክንያት በደል ሊደርስባቸው ይችላል እንጂ የሀገራችን ሕገ መንግሥት ዘረኝነትን አያበረታታም፡፡ እንዲያውም “ማንኛውም ሰው በሕግ ፊት እኩል መሆኑንና ማንኛውም ሰው በዘር፣ በብሔር፣ በቀለም፣ በጾታ፣ በቋንቋ፣ በሃይማኖት፣ በፖለቲካ፣ በማኅበራዊ አመጣጥ፣ በሀብት፣ በትውልድ ወይም በሌላ አቋም ምክንያት ልዩነት ሳይደረግ ሰዎች ሁሉ እኩልና ተጨባጭ የሕግ ዋስትና የማግኘት መብት አላቸው” ተብሎ በአንቀጽ ፳፭ በግልጽ ተቀምጧል፡፡ ስለዚህ ሕገ መንግሥቱ የሰው ልጅ እኩልነትን ያረጋግጣል፡፡ በዚህ ጉዳይ የሕግ ባለሙያዮች የበለጠ ማብራሪያ ሊሰጡበት ይችላሉ፡፡ በግርድፉ መረዳት የምንችለው ጉዳይ ቢኖር ግለሰቦችና ልዩ ልዩ የፖለቲካ ፍላጎት ያላቸው ቡድኖች ከሕግ በአፈነገጠ መንገድ በመጓዝ ሕዝብን ከሕዝብ የሚለያዩ አጀንዳዎችን በማቀበል አፍራሽ ተግባር ላይ መሠማራታቸውን ነው፡፡

በሕገ መንግሥቱ ላይ የተጠቀሰውና ምናልባትም የዘረኝነት ምንጭ ሊሆን ይችላል ተብሎ የሚገመተው “ማንነት” የሚለው ቃል ነው፡፡ ማንነት የሚለው ቃል ደግሞ የብዙ ጥቃቅን ማንነቶች ድምር ውጤት እንጂ በቀጥታ ዘርን ብቻ አያመለክትም፡፡ ለምሳሌ ጾታ ራሱን የቻለ ማንነት ነው፣ የቆዳ ቀለም አንድ ማንነት ነው፤ሃይማኖት አንድ ማንነት ነው፣ ኢትዮጵያዊነት አንድ ማንነት ነው፣ ቋንቋ አንድ ማንነት ነው፣ ወጣትነት ወይም ጎልማሳነት ወይም እርግና ሌላኛው ማንነት ነው፣ ወዘተ፡፡ እነዚህንና የመሳሰሉት ማንነቶች በአንድ ሰው ጥቅል ማንነት ላይ ሊኖሩ ይችላሉ ማለት ነው፡፡

የማኅበራዊ ሳይንስ አጥኚዎች ዘር የሚለውን ቃል በዋናነት ሁለት መገለጫዎች እንዳሉት ይናገራሉ፡፡ አንደኛው በግልጽ የሚታይና ከሌላው ማኅበረሰብ ሊለይ የሚችል የአካል ወይም የቆዳ ቀለም ልዩነት ሊኖር ይገባል ይላሉ፡፡ ለምሳሌ በምዕራቡ ዓለም የሰው ልጅ ጥቁርና ነጭ ተብሎ እንደሚከፋፈለው ዓይነት በግልጽ ሊታይ የሚችል አካላዊ መለያ ሊኖር ይገባል ማለት ነው፡፡ ሁለተኛው ደግሞ የእገሌ ዘር አባል ነን ብለው ራሳቸውን ከሌላው ማኅበረሰብ አግልለው የራሳቸውን ማኅበረሰብ የፈጠሩና ከብዙኃኑ ማኅበረሰብ ራሳቸውን ያገለሉ ከሆነ ዘር የሚለውን መስፈርት ሊያሟሉ ይችላሉ ማለት ነው፡፡ ስለሆነም ዘር የማንነት አካል ሊሆን ይችላል እንጂ ማንነትን ሙሉ ለሙሉ ሊተካ አይችልም ማለት ነው፡፡

በአንጻሩ ጎሳ ማለት ሦስት መመዘኛዎችን የሚያሟላ ነው፡፡ የመጀመሪያው በአንድ ማኅበረሰብ ውስጥ የሚኖሩና የጋራ ማንነት ያላቸው ናቸው፡፡ ሁለተኛው ደግሞ አንደኛውን ጎሳ ከሌላው ጎሳ የሚለዩበት ማንነት በዋናነት አካላዊ ገጽታ (Phisical appearance) ሳይሆን የጋራ የሚሉት ባህላቸው፣ ታሪካቸው፣ ቋንቋቸው ነው፡፡ ሦስተኛው መመዘኛ ደግሞ ከሌላው ማኅበረሰብ በተለየ ሁኔታ በቁጥራቸው ጥቂት(Minority) ስሜት ያላቸው ናቸው፡፡ በእኛ አገር ፖለቲከኞች ጎሳ የሚለውን ትርጓሜ ብሔር ወይም ብሔረሰቦች የሚለው ቃል ጥቅም ላይ ሲውል እንመለከታለን፡፡ ይህ ግን የተሳሳተ ትርጕም እንደሆነ ብዙዎች ይስማማሉ፡፡

ስለ ማንነት፣ ስለ ዘር፣ እንዲሁም ስለ ጎሳ ይህን ካልን እገሌ ዘረኛ ነው፤ እገሊት ዘረኛ ናት፤ እነ እገሌ ዘረኞች ናቸው፣ በመካከላችን ዘረኝነት ተስፋፍቷል ወዘተ ስንል ምን ማለታችን ይሆን የሚለው መሠረታዊ ጥያቄ ነው፡፡ እውነት በሀገራችን የምናስተውለው የእርስ በርስ መገፋፋት ጎሰኝነት የወለደው ነው ወይስ ዘረኝነት የወለደው የሚለው አነጋጋሪ ጉዳይ ነው፡፡ በእርግጥ አንዳንድ የማኅበራዊ ሳይንስ አጥኝዎች ዘረኝነትን ከአካላዊ ገጽታ ባሻገር ሰፋ አድርገው ይመለከቱታል፡፡

አንድን ግለሰብ ወይም ማኅበረሰብ ወይም ተቋም የሌላ ዘር ወይም ጎሳ አባል በመሆኑ ብቻ በማንነት ላይ የተመሠረተ ጭፍን፣ ጥላቻ፣ አድልዎ ወይም ጠላትነት ማለት ነው ይላሉ፡፡ ከዚህ አንጻር በሀገራችን የምንመለከተው ጭፍን ጥላቻ፣ አድልዎ ወይም ጠላትነት የአካል ገጽታን ወይም የዘር ሐረግን መሠረት ያደረገ ሳይሆን በዋናነት ባህልን፣ ቋንቋንና ሃማኖትን መሠረት ያደረገ ነው ብንል አሳማኝ ይሆናል፡፡

እዚህ ላይ አንድ እውነታን መረዳት የግድ ይለናል፡፡ ከላይ ለመግለጽ እንደተሞከረው የሀገራችን ሕገ መንግሥት ለማንነት ትልቅ ቦታ ይሰጣል፡፡ ለሰው ልጅ እኩልነትም ትልቅ ቦታ ይሰጣል፡፡ ነገር ግን በማንነት ላይ የተመሠረተ መንግሥታዊ አስተዳደር በባሕርዩ አግላይ በመሆኑ በሕዝቦች መካከል አለመግባባትና ግጭት እንዲፈጠር ዕድል ይፈጥራል፡፡ ምንም እንኳ በሕግ ደረጃ የተቀመጠ አግላይነት ባይኖርም በመንግሥት መዋቅር ላይ የተቀመጡ አንዳንድ ፖለቲከኞች የእኔ ለሚሉት ግለሰብ ወይም ማኅበረሰብ ሊያደሉ ይችላሉ፡፡ እንዲህ ዓይነቱ አስተዳደር በሕዝቦች መካከል ማንነትን መሠረት ያደረገ ጭፍን ጥላቻና አግላይነት ሊፈጥር ይችላል፡፡ አሁን ላይ በአገራችን እየተስተዋለ ያለው የዜጎች መፈናቀል፣ ስደትና ሞት በዋናነት በማንነት ላይ የተመሠረተ ጭፍን ጥላቻና አግላይነት የወለደው እንደሆነ እሙን ነው፡፡

ይቆየን፡፡

0 replies

Leave a Reply

Want to join the discussion?
Feel free to contribute!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *