የቴክኖሎጂ ጥቅም በኦርቶዶክሳዊ ክርስትና እይታ
በዲ/ን በረከት አዝመራው
የሰው ልጆች በምድራውያኑ ፍጥረታት ውስጥ ካሉት ድርሻዎች ውስጥ መሪነት እና ገዢነት ይጠቀሳሉ፡፡ “ምድርን ሙሏት … ግዟትም” የሚለው ቃል ለሰው ልጅ የተሰጠውን ኃይል፣ ዕውቀትና ሥልጣን የሚገልጥ ነው፡፡ (ዘፍ. ፩፥፳፰)፡፡ ይህ ገዢነትና በእነዚህ ፍጥረታት ላይ የተሰጠው ሥልጣን በምን ገለጣል? ሰው ይህን ለማድረግ የሚያበቃ ምን ነገር አለው? እንዲገዛቸውና እንዲጠቀምባቸው ከተፈጠሩት ፍጥረታት መካከል ከእርሱ የሚበረቱ፣ የሚፈጥኑ እና የሚገዝፉ ፍጥረታት እንዴት ከበታቹ ሊሆኑ ይችላሉ? የሚል ጥያቄ ልናነሣ እንችላለን፡፡
ለእነዚህ ጥያቄዎች መልስ የምናገኘው የሰውን ጥንት ተፈጥሮ በማስተዋል ነው፡፡ ሰውን ይህን ክብር ያቀዳጀው የሰው በእግዚአብሔር አርአያና አምሳል መፈጠሩ ነው፡፡ (ዘፍ. ፩፥፳፮-፳፯)፡፡ ሰው በእግዚአብሔር አርአያ እና አምሳል ተፈጠረ ስንል የእግዚአብሔር የባሕርይው መገለጫዎች ወሰን የሌላቸው እና ከማንም ያልተቀበላቸው ናቸው፤ ባሕርይውን ደግሞ ለሰው ልጅ በፀጋ ሰጥቶታል ለማለት ነው፡፡ እግዚአብሔር በባሕርይው አዋቂ እንደሆነ ሁሉ ሰውም የፀጋ አዋቂነት ተሰጥቶታል፤ እግዚአብሔር በባሕርይው ገዥ(ንጉሥ) እንደሆነ ሁሉ ለሰውም በፀጋ በምድራዊው ሁሉ ገዥነት ተሰጥቶታል፡፡ እግዚአብሔር የባሕርይ አምላክ በመሆኑ ሁሉም ፍጥረታት በፍርሃት እና በአክብሮት ሆነው በፊቱ እንደሚቆሙ ሁሉ ሰውም እግዚአብሔር ከሰጠው የፀጋ አምላክነት እና ግርማ የተነሣ በኃጢአት ከመጎስቆሉ በፊት ምድራውያን ፍጥረታት በአክብሮትና በፍርሃት ይታዘዙት ነበር፡፡ ይህም የሚታወቀው አስፈሪ የሆኑ አራዊት እንኳን ሳይቀሩ ለቅዱሳን በሚያሳዩት አክብሮትና መታዘዝ ነው(ዘፍ. ፪፥፳)፡፡
ለሰው ልጅ ከእግዚአብሔር የተሰጠው ዕወቀት፣ ጥበብ እና ማስተዋል አለው፡፡ ሰው ቢበድለውም እንኳን የሰጠውን ዕውቀት፣ ጥበብ እና ማስተዋል አለመግፈፉ ከቸርነቱ የተነሣ ነውና ይህ የእግዚአብሔርን ቸርነት፣ ለሰው ያለውን ርኅራኄ እና መግቦት ያሳያል፡፡ በዓለማችን በዘመናት የምናያቸው ዕውቀቶች፣ ጥበቦች እና በማስተዋል የተገኙ ግኝቶች ሁሉ ከዚህ ከእግዚአብሔር ሥጦታ ምንጭ እንደ ወንዝ የሚፈሱ የፀጋ ሥጦታዎች ናቸው፡፡
በዘመናችን ተስፋፍትው የምናያቸው የሳይንስና የቴክኖሎጂ ግኝቶችም የዚሁ አካል ናቸው፡፡ የሰው ልጅ ይህ በተፈጥሮ የተሰጠውን አዋቂነት እና ጥበብ ተጠቅሞ በየዘመኑ ሕይወቱን ያሳልጥበታል፤ የየዘመኑን ፈተናዎች ይቋቋምበታል፤ በአጠቃላይ ሕይወቱን በአግባቡ ለመምራት ይጠቀምበታል፡፡
ጠለቅ ብለን ስናየው የሳይንስና የቴክኖሎጂ ዕድገት እግዚአብሔር በሰው ውስጥ ያስቀመጠው መግቦት ነው፡፡ ይህን በጥንት ተፈጥሮ የሰጠውን ፀጋ በበደለው ጊዜ እንኳን አልነሳውም፤ ይህም ከላይ እንዳልነው የቸርነቱ ውጤት ነው፡፡
ልዑል እግዚአብሔር ለሰው የመግቦት አካል ይሆን ዘንድ፣ በኑሮው የሕይወቱን ውጣ ውረድ እንዲያቀልለት ዕውቀትንና ጥበብን በመስጠቱ ሰው በአእምሮው የዕውቀት ምጥቀትና በጥበቡ እየታገዘ እግዚአብሔር የፈጠራቸውን ፍጥረታት በመጠቀም ብዙ ድንቅ የሆኑ የቴክኖሎጂ ውጤቶችን አስገኝቷል፡፡ ይህ መልካም ነገር ነው፤ እግዚአብሔርንም የምናመሰግንበት አንድ ትልቅ ምክንያትም ነው፡፡ በመልካም ልቡና ስናስተውለው የእግዚአብሔርን ቸርነት እና ኃያልነት የምናስብበት ሥጦታ ነው! የፈጠረው ሰው ይህን ያህል ጥበብና ኃይል እንዲኖረው ያደረገ እግዚአብሔር ይመስገን፡፡
ነገር ግን ቴክኖሎጂ መልካም የሚሆነው ለመልካም ነገር ስንጠቀምበት ነው፡፡ ዕውቀቱንና ማስተዋሉ ሲሰጠን ለመልካም እንድንጠቀምበት ቢሆንም ለክፉም ልንጠቀምበት እንችላለን፡፡ ይህም ከነፃ ፈቃድ የተነሣ ነው፤ እግዚአብሔር ለሰው የሰጠው ዕውቀትን ብቻ ሳይሆን ወደ ፈለገው የሚሄድበትን ነጻ ፈቃድም ጭምር ነውና፤ ለመልካም ብንጠቀምበት እግዚአብሔርንም ሰውንም እናስደስታለን፤ ለበለጠ ሰማያዊ እና ዘለዓለማዊ ዕወቅትም የተገባን ሆነን እንገኛለን፡፡ ለኃጢአት ብንጠቀምበት ግን እንኳን የሠራነው ቴክኖሎጂ ቀርቶ የገዛ ሰውነቶቻችንም ይረክሳሉ፤ ከሰማያዊው ርስት ዕድል ፈንታ አይኖረንም፡፡ ስለዚህ ቴክኖሎጂ በመልካም ኅሊና ሊመራ ይገባዋል ማለት ነው፡፡
አሁን የምናየው የቴክኖሎጂ ዕድገት የሚመራው በምን ኅሊና ነው? ይህ በተለይ በክርስቲያኖች ዘንድ ሊስተዋል የሚገባው ጠቃሚ ጥያቄ ነው፡፡ ቴክኖሎጂን የሚመራው የሰው ኅሊና ለመልካምነቱ ወሳኝ ነው፤ ኅሊና ጤናማ ከሆነ ቴክኖሎጂም ጤናማ አገልግሎት ይሰጣል፤ ካልሆነ ግን ወደ ሞት ይዞን ሊወርድ ይችላል፡፡
ይህን የተክኖሎጂ ጤነኛነት ቢያንስ በሁለት መንገድ ልንመዝነው እንችላለን፡፡ የመጀመሪያው ለስንፍና፣ ለኃጢአት፣ ለትዕቢት እና ለአምባገነንነት መሣሪያ ከሆነ ጤናማ አይደለም፡፡ ሰው ቴክኖሎጂን ተጠቅሞ ኃጢአት የሚሠራ እና ሌሎችን የሚበድል ከሆነ ለራሱ መጥፊያ እየተጠቀመበት ነው ማለት ነው፡፡ በቴክኖሎጂ ብዛት የማይዳንባት የእግዚአብሔር ፍርዱም የኋለ ኋላ ታጠፋዋለች፡፡
ሁለተኛው ችግር ደግሞ ቴክኖሎጂን ከመጠን በላይ ቦታ ሰጥቶ እንደ አምላክ ማየት ነው፡፡ የሕይወት መጨረሻ መንግሥተ ሰማዯትን ወርሶ ከእግዚአብሔር ጋር መኖር እንጂ ቴክኖሎጂን እንደ ምኞት መዳረሻ ቆጥሮ በዚህ ምኞት ውስጥ ራስን አስክሮ መኖር አይደለም፡፡ “በሰለጠነው ዓለም” ሰዎች ለራሳቸው ለፈጠሯቸው ለሳይንስና ለቴክኖሎጂ ሥራዎች ለፈጣሪ የሚሰጠውን ዓይነት አክብሮትና ምስጋና ሲቸሯቸው እናስተውላለን፡፡ ቴክኖሎጂ ጣዖታችን ከሆነ መሞቻችን ሆኗል ማለት ነው፡፡
እኛ ክርስቲያኖች ግን ቴክኖሎጂን መጠቀም ያለብን የምኞታችን ሁሉ መዳረሻ አድርገን ሳይሆን በዚህ ምድር ለምንኖረው ኑሮ ለመልካም ሥራ መሣሪያ እንዲሆነን እንጂ በራሱ ግብ ስለሆነ አይደለም፡፡
ይህች ዓለም በቴክኖሎጂ ሳይሆን በእግዚአብሔር ኃይል እና መግቦት እንደምትኖር ያለ ግብዝነት ልናምን ይገባል፡፡ ቴክኖሎጂ ራሱ እግዚአብሔር ለሰው ከሰጠው ዕውቀት የተነሣ እንደሆነና በአግባቡ ከተጠቀምንበት ለመልካም ነገር መሣሪያ የሚሆን የሰው ልጅ ሀብት እንደሆነ ሁል ጊዜ ማሰብ ማሰላሰል ይኖርብናል፡፡ ካልሆነ ግን መልካም ሥጦታነቱ ቀርቶ ለሰው ልጅ የከንቱነት ምክንያት እንዲሁም ለጥፋቱ መሣሪያ ሊሆን እንደሚችል እናውቃለን፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
Leave a Reply
Want to join the discussion?Feel free to contribute!