ጌታችን ኢየሱስ ተወለደ
ዲያቆን አለልኝ ጥሩዬ
ለአምስት ሺሕ አምስት መቶ ዘመን በዓለም ላይ ሠልጥኖ የነበረውን ጨለማ ያስወግድ ዘንድ እግዚአብሔር አምላክ ሰው ሆነ፡፡ ከቅድስት ድንግል ማርያም የተወለደው አማናዊው ብርሃን ፀሐየ ጽድቅ ክርስቶስ በሥጋ ተገለጠ፡፡ ቅዱስ ኤፍሬም በውዳሴው እንዳለው ‹‹ብርሃን ዘበአማን ዘያበርህ ለኵሉ ሰብእ ለእለ ይነብሩ ውስተ ዓለም፤ በጨለማ ውስጥ ለሚኖር ሕዝብ ታላቅ ብርሃን ወጣላቸው›› (ኢሳ. ፱፥፪)፡፡ ቀዳሚ ቃል ኢየሱስ ክርስቶስ ከእመቤታችን ከሥጋዋ ሥጋ፣ ከነፍሷ ነፍስ ነስቶ ሰው በሆነ ጊዜም ቅዱሳን መላእክት በቤተ ልሔም ተገኝተዋል፡፡ ይህንም ቅዱስ ሉቃስ ‹‹ወግብተ መጽኡ ብዙኃን ሐራ ሰማይ፤ የሰማይ መላእክት በድንገት መጡ›› በማለት ገልጾታል (ሉቃ. ፪፥፲፫)፡፡ በድንገት መባሉም አመጣጣቸው ግሩም በመሆኑ ነው፤ ቅዱሳን መላእክት ቀድሞ አመጣጣቸው ጻድቃንን ለመርዳት፣ ሰማዕታትን ከስለት ለመታደግ፣ የተቸገረውን ለማጽናት ነበር፡፡
ዛሬ ግን ስለ ሰው ፍቅር ከሰማይ የወረደውን፣ በጎል (በበረት) የተጣለውን፣ በጨርቅ የተጠቀለለውን አምላክ ከሰው ልጅ ጋር በአንድነት ለማመስገን መጡ፡፡ ‹‹ዮም አሐደ መርዔተ ኮኑ መላእክት ወሰብእ ከመ ይሰብሕዎ ለክርስቶስ ንጉሥ፤ ሰውና መላእክት፣ ንጉሥ ክርስቶስን ያመሰግኑ ዘንድ ተባበሩ›› እንዲል፡፡ መላእክት በተፈጥሯቸው የማይሞቱ (ሕያዋን) ሲሆኑ ሰው ደግሞ ሟች ነው፤ ሞት ይስማማዋል፡፡ በጌታችን ልደት ግን መላእክትና የሰው ልጆች በአንድ ማኅበር፣ በአንድ ቃል ‹‹ስብሐት ለእግዚአብሔር›› እያሉ እግዚአብሔርን አመስግነዋል፡፡ በአዳም ኀጢአት ምክንያት ፈርሶ የነበረው የመላእክትና የሰው ልጆች ማኅበር ከተቋረጠ ከብዙ ዘመን በኋላ በኢየሱስ ክርስቶስ ልደት እንደ ገና ተጀመረ፡፡ ይህ የምስጋና ኅብረትም ምድር እንደ ልብስ ተጠቅልላ ስታልፍ ወደ ፊት በምትመጣዋ በአዲሲቷ ዓለም፣ በአዲሱ ሰማይ፣ በአዲሱ ቤተ መቅደስ ይቀጥላል፡፡ (ራእ. ፳፩፥፩-፬)
አንድነታችን እንደማያቋርጥና በሰማይም እንደሚቀጥል አረጋዊ መንፈሳዊ ሲገልጥም ‹‹እሉሂ ወእልክቱሂ በአሐዱ ኁባሬ አልቦ ማዕከሌነ ወማዕከሌሆሙ፤ በእኛ በደቂቀ አዳም እና በቅዱሳን መላእክት መካከል ልዩነት የለም›› ይላል፡፡ ይህም የሆነው በጌታችን መወለድ ምክንያት ነው፡፡ በጌታችን ልደት ምክንያት እኛም ዳግመኛ ተወለድን፡፡ የጌታችን ልደት የእኛም የክርስቲያኖች ሁሉ ልደት ነው፡፡ ከሦስቱ የቀጰዶቅያ አባቶች አንዱ፣ ታላቁ የቤተ ክርስቲያን አባት ሊቁ ቅዱስ ባስልዮስ ዘቂሣርያ ይህን ምሥጢር ሲገልጥ ‹‹የክርስቶስ ልደት የመላው ሰው የልደት ቀን ነው›› ሲል መስክሯል፡፡
ሊቃውንት እንዳስተማሩን እግዚአብሔር አምላክ ዓለምን ከፈጠረበት ጥበቡ ይልቅ ዓለምን ያዳነበት ጥበቡ ይበልጣል፡፡ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተወለደበት እና ዓለምን ያዳነበት ምሥጢር ከምሥጢራት ሁሉ በላይ ነው፡፡ ይህን ምሥጢር ከማድነቅ ሌላ ሊናገሩት አይቻልም፡፡ ሊቁ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅም በመገረም ይህን ጥበብ እንዲህ ሲል ይገልጸዋል፤ ‹‹ምን እላለሁ? ምንስ እናገራለሁ? ከዘመን አስቀድሞ የነበረው እርሱ ሕፃን ሆኗልና፡፡ እኔ ፈጽሜ አደንቃለሁ፡፡ ከሰማየ ሰማያት በላይ የሚሆን፣ በዘለዓለማዊ ዙፋን የሚኖር እርሱ በበረት ተጣለ፡፡ ከሥጋዌ አስቀድሞ አይዳሰስ የነበረ አንዱ እርሱ በምድራውያን እጅ ተዳሰሰ፡፡ ኀጢአትን የሚያስተሰርይ እርሱን በጨርቅ ጠቀለሉት፡፡ ይህን ወዷልና፤›› (ሃይማኖተ አበው ዘዮሐንስ አፈ ወርቅ፣ ፷፮፥፲፯)፡፡ ቅዱስ ዲዮስቆሮስም በቅዳሴው የእግዚአብሔርን ሰው የመሆን ምሥጢር እንዲህ በማለት ገልጾታል፤ ‹‹በጐለ እንስሳ ተወድየ አሞኀ ንግሡ ተወፈየ ወከመ ሕፃናት በከየ እንዘ ይስእል እምአጥባተ እሙ ሲሳየ፤ በእንስሳት በረት ተጨመረ፤ የንጉሡንም እጅ መንሻ ተቀበለ፤ ከእናቱ ጡቶች ምግብን እየለመነ እንደ ሕፃናት አለቀሰ፤›› (ቅዳሴ ዲዮስቆሮስ ቍ. ፲፯)፡፡
በዚህ ታላቅ በዓላችን የምናደንቀው ሌላው ምሥጢር እግዚአብሔር ወልድ በቅድስት ድንግል ማርያም ማኅፀን፣ በኅቱም ድንግልና ተፀንሶ በኅቱም ድንግልና የመወለዱ ረቂቅ ምሥጢር ነው፡፡ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ይህን ድንቅ የሥጋዌ ምሥጢር ግሩም፣ ዕፁብ እያሉ ያደንቁታል፡፡ ሐዋርያውያን አበውን ተከትለው ከተነሡ የቤተ ክርስቲያን ጠባቆች መካከል አንዱ ቅዱስ ሄሬኔዎስም ፩ኛ የእመቤታችን ዘለዓለማዊ ድንግልና፣ ፪ኛ ድንግል ማርያም አማኑኤል ጌታን መውለዷ እና ፫ኛ የማይሞተው አምላክ መሞት በእግዚአብሔር የዝምታ ሸማ የተጠቀለሉ ሦስት ምሥጢሮች መሆናቸውን ይናገራል፡፡ ኢትዮጵያዊው ቄርሎስ የተባለው አባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫም በመጸሐፈ አርጋኖን ድርሰቱ ይህን ድንቅ የተዋሕዶ ምሥጢር በሚከተለው መልኩ ይገልጠዋል፤
‹‹ሦስቱን ደጆች ያልከፈተ የአብን ልጅ ጥበብ አደንቃለሁ፤ ያለ መለወጥ በኅቱም ድንግልና በመወለዱ፣ የመቃብሩን ደጅ ሳይከፍት በመነሣቱ፣ ደቀ መዝሙርቱ ተሰብስበው ወዳሉበት ቤት በተዘጋ ቤት በመግባቱ እና በሩን ሳይከፍት በመውጣቱ ስለነዚህም ሦስት ደጆች ልቤ አደነቀች፡፡ ከሁለቱ ይልቅ የመጀመሪያው እጅግ ያስደንቀኛል፡፡ ምክንያቱም ሁለቱን ከዚህ በፊት በመጽሐፍ ቅዱስ አውቃቸዋለሁ፡፡ የመቃብሩን ደጅ የሚመስለው ነገር አለ (ዮሐ. ፳፥፲፱)፡፡ ብልጣሶር የተባለ ዳንኤልን በአንበሶች ጕድጓድ ውስጥ በጣሉት ጊዜ ጕድጓዱን በታላቅ መዝጊያ ዘጉት፡፡ ዳንኤልም በረሃብ እንደ ተጨነቀ ልዑል እግዚአብሔር ባየ ጊዜ መልአኩን ወደ ነቢዩ ዕንባቆም ላከ (ዳን. ፮፥፲፮–፲፯)፡፡ በራሱም ፀጕር አንሥቶ ተሸክሞ ወስዶ ዳንኤል ወዳለበት ጕድጓድ አገባው፡፡ ዳንኤልና ዕንባቆም እንጀራውንና ንፍሮውን በልተው እግዚአብሔርን አመሰገኑ፡፡ ዕንባቆምም ደጅ ተዘግቶ ሳለ ወጣ፡፡ ስለ ቤቱ ደጅም የሚመስል ነገር አለ፡፡ የእግዚአብሔር መልአክ ከሰማይ ወርዶ ጴጥሮስን ከግዞት ቤት እንዳወጣው በሐዋርያት ሥራ ተጽፏል፡፡ ጴጥሮስንም ካወጣው በኋላ ደጁ ተቈልፎ ዘበኞች በሁሉ ወገን ይጠብቁ ነበር፡፡ (ሐዋ. ፲፪፥፮) ለእነዚህ ለሁለቱ ደጆች ለቅዱሳን የተገኘውን ምክንያት አገኘሁ፡፡ ስለ ድንግልናሽ ደጅ እጠናለሁ፤ ግን ምክንያት አላገኘሁም፡፡ በድንግልና የኖረች ሴትም አላየሁም፡፡ እንደዚህ ዓይነት ነገር ሆኖ አያውቅም፡፡ ኢኮነ እምቅድመ ዝ ወኢኮነ እምድኅረ ዝ፤ ከዚህ በፊት አልተደረገም፤ ከዚህ በኋላም አይደረግም›› (አርጋኖን ዘቀዳሚት)፡፡
በዓለ ልደት፣ በሰውና በእግዚአብሔር መካከል እርቅ የተፈጸመበት በዓላችን ነው፡፡ ለሞት ከመገዛት የዳንበት፤ ጨለማው ተወግዶልን የብርሃን ልጆች የሆንበት፤ የእባብ ራስ የተቀጠቀጠበት፤ ከምድር ወደ ሰማይ ያረግንበትና ከመላእክት ጋር ሆነን ለእግዚአብሔር ምስጋና ያቀረብንበት፤ ከነቢያት ኅብረት ጋር አንድ የሆንበት በዓል ነው፡፡ ድንቅ የተዋሕዶ ምሥጢር የተፈጸመበትን ይህን ልዩ በዓል በመንፈሳዊ ሥርዓት ማክበር ይገባናል፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር ወለወላዲቱ ድንግል ወለመስቀሉ ክቡር
Leave a Reply
Want to join the discussion?Feel free to contribute!