የአብነት ትምህርት ለግቢ ጉባኤያት ያለው ጥቅም
በመጋቤ ሃይማኖት መ/ር ይላቅ ሻረው
(የጅማ ሐ/ኖ/ቅ/ኪ/ም/ ቤተ ክርስቲያን ስ/ወ/ክ/ ኃላፊ)
ትምህርት መንፈሳዊ ከጥቅሙ በስተቀር ጉዳት የሚባል አንዳችም የጎንዮሽ ችግር የለበትም፡፡ ለዚያውም አብነት ትምህርትን መማር የሞራልም ጥቅም አለው፡፡ ምክንያቱም ፈሊጣዊና ምሳሌአዊ ንግግሮች ከአብነት ትምህርት ማግኘት ስለሚቻል፡፡ ከቃሉ ስንነሣ እንኳን “አብነት” ማለት መሠረት፣ መነሻ፣ መጀመሪያ፣ የሚቀድመው የሌለ የሁሉም የበላይ ማለት ነው፡፡ አብነት ትምህርትን ለግቢ ጉባኤያት ተማሪዎች ማስተማር ማለት አማራጭ የሌለው ትልቁ ምርጫ ነው፡፡ በተግባርም በቆየንባቸው የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት አካባቢዎች ባሉ አብያተ ክርስቲያናት የምናገለግል አገልጋዮች ተማሪዎች የመማር ጥቅሙን አይተናል፡፡
ለዚህም የጅማ ዩኒቨርሲቲ ግቢ ጉባኤ እንደምስክርነት ሆኖ ቢቀርብ የሚያስመሰግን ነው፡፡ በቃል የማንዘረዝራቸው (ስማቸውን የማንጠራቸው) ለሀገርም፣ ለቤተክርስቲያንም ልዩ ጥቅም የሚሰጡ ከዲቁና እስከ ቅስና ድረስ፡- “ቀሲስ ዶክተር፣ ቀሲስ ኢ/ር” የምንላቸውን ውድ ልጆች አፍርቷል፡፡ “ባንድ ድንጋይ ሁለት ወፍ” የሚባለውም ይህንን ይመለከታል፡፡ በሁለት አፍ የተሳለ ሰይፍ ሆነው እንዲወጡ ከተፈለገ የከፍተኛ ትምህርት ተቋም ተማሪዎችን አብነት ትምህርት ማስተማር ላይ ከበፊቱ ይልቅ መትጋት ያስፈልጋል፡፡ ምናልባት ለጊዜው ጥቅሙን ላናውቅ እንችል ይሆናል ካለፈ በኋላ ግን ስለሚቆጨን ከወዲሁ መበርታት ይመከራል፡፡
በተለምዶ የቆሎ ትምህርት ቤት እያልን የምንጠራውን አብነት በተናጠል ለመማር ከአለንበት ተነሥተን አብነት ትምህርት ቤት ፍለጋ የምንከራተትበትን ውጣ ውረድ የሚያውቅ ያውቀዋል፡፡ ግቢ ጉባኤ ተማሪዎች ግን በአንድ የመማሪያ ተቋም ተሰብስበው ሲገኙ “ከመጣሽ ማርያም ታምጣሸ” ነውና አብነቱን አስተምሮ ሁለተኛ ጥቅማቸውን በማረጋገጥ የማኅበረ ቅዱሳን ትጋትና አስተዋፅኦ በቃላት የሚገለጥ አይደለም፡፡ ሀገራዊ ተቋማትና ቅድስት ቤተክርስቲያንም፣ ዛሬ ላይ እየተጠቀሙባቸው ያሉ ብዙ ምሁራን አብነት ትምህርት ቤት የተማሩት ናቸው፡፡ ለዚህ ግቢ ጉባኤን አብነት ትምህርት ማስተማር ከራስ አልፎ ለቤተሰብ፣ ከቤተሰብ ለአካባቢ፣ ከአካባቢ ለሀገር … ጥቅሙ በቀላሉ የሚገመት ስላልሆነ የተማሪዎች ቤተሰብም ጥቅሙን ለልጆቻቸው ቢያስተምሩ የወደፊት መልካም ዜጋ ማግኘት ይቻላል፡፡
ለግቢ ጉባኤ ተማሪዎች አብነት ትምህርት መማራቸው ምን ይጠቅማል?
ሀ. ዘመኑን ለመዋጀት
ለግቢ ጉባኤያት ተማሪዎች የአብነት ትምህርት መማር ከከንቱ አስተሳሰብና ከስንፍና እንዲርቁ በክፉዎቹም ቀናት መካከል ያለውን መንፈሳዊ ሕይወታቸውን ከክፉ ይጠብቁ ዘንድ ዘመኑን እንዲዋጁ ብርቱና ጠንካራዎችም እንዲሆኑ ይረዳቸዋል፡፡ ይህም ስንፍናቸውን እያራቀ ለጸሎትም እያተጋ ዘወትር በእግዚአብሔር ቤት እንዲኖሩ ያበረታቸዋል፡፡ “ከእንቅልፍ የምትነሡበት ሰዓት አሁን እንደደረሰ ዘመኑን ዕወቁ፣ ካመንበት ጊዜ ይልቅ መዳናችን ዛሬ ወደእኛ ቀርቦአልና” የሚለውን የቅዱስ ጳውሎስን መልእክት በተግባር የምናየው የአብነት ትምህርትን የተማሩ ተማሪዎች በግቢ ጉባኤ ቆይታቸው መገንዘብ ስለቻልን ነው፡፡ (ሮሜ 13፥11)
ለምሳሌ በቅዱሳት ሥዕላት፣ በኪነ ጥበብ፣ በሥነ ጽሑፍ በመሳሰሉት ሁሉ ብርቱና ጠንካራ ተማሪዎችን ስንመለከት የቤተ ክርስቲያን ተስፋዋ መለምለሙን ያሳየናል፡፡ ዘመኑን የሚዋጅ፣ ጥበብን የሚወድ፣ ትውልድን የሚቀርፅ፣ ዜጋ ለመፍጠር በግቢ ጉባኤያት የአብነት ትምህርት ማስተማር አማራጭ የሌለው ምርጫ ነው፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ “እንግዲህ እንደ ጥበበኞች እንጂ ጥበብ እንደ ሌላቸው ሳይሆን እንዴት እንድትመላለሱ በጥንቃቄ ተጠበቁ፤ ቀኖች ክፉዎች ናቸውና ዘመኑን ዋጁ፡፡” በማለት የመከረን መንፈሳዊ ሕይወት ለዓለም ማሳያ መስታውት፣ በጥበብም ለሚመላለሱ ብልህ ሰዎች ጥቅም መሆኑን ሲያመለክተን ነው፡፡ (ኤፌ. 5፥15)
ለ. ከክፉ የጎልማሳነት ምኞት ለመራቅ
ኦርቶዶክሳውያን ተማሪዎች በግቢ ጉባኤያት ቆይታቸው የአብነት ትምህርትን መማራቸው እግዚአብሔርን ባለመፍራት በሥጋ ፈቃድ ከሚመላለሱበት ክፉ ዘመን እንዲርቁ ይረዳቸዋል፡፡ ለምሳሌ፡- ከልዩ ልዩ ሱሶች፣ ከዝሙትና ከክፉ ሁሉ አስተሳሰብ ይጠብቃቸዋል፡፡ በመሆኑም የአብነት ትምህርትን መማሩ ጥቅሙ የጎላ ነው፡፡ ከሀገራችን ከልዩ ልዩ አካባቢዎች የመጡ ወጣቶች የአብነት ትምህርትን እንዲማሩ መደረጉ ከክፉ ልማዳዊና ጎጂ ድርጊቶች እንዲታቀቡ ከማድረጉም ባሻገር እርስ በእርስ በመንፈሳዊ ወንድማማችነት እንዲቀራረቡ፣ አንዱ ለሌላው መልካሙን እንዲያስብ ፣ ከክፉ የጎልማሳነትም ምኞት በመራቅ በትምህርታቸውና በመንፈሳዊ ሕይወታቸውም ላይ እንዲያተኩሩ፣ በአንዲት ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ጥላ ሥር እንዲከትሙም ያስችላቸዋል፡፡
ሐ. መንፈሳዊ ሰይፍን ለመታጠቅ
ቅዱስ ጴጥሮስ “በዘፈንም፣ ያለ ልክ በመጠጣት፣ ነውርም ባለበት በጣዖት ማምለክ የተመላለሳችሁበት ያለፈው ዘመን ይበቃል፡፡” በማለት እንደተናገረው (፩ኛ ጴጥ 4፥3) አብነት ትምህርትን መማር ተማሪዎች በማወቅም ባለማወቅም ያለ ልክ የኖሩበትን ዘመን በቃን ብለው ከሥጋዊ አስተሳሰብ በመለየት ጠላትን ድል የሚያደርጉበት የመንፈስን ሰይፍ እንዲታጠቁ የሚያደርጋቸው መንፈሳዊ መሣሪያ ነው፡፡ በቅዱስ መጽሐፍ፡- “የመዳንን ራስ ቁር፣ የመንፈስንም ሰይፍ ያዙ፣ እርሱም የእግዚአብሔር ቃል ነው” ተብሎ እንደተጻፈ መንፈሳዊ ሰይፍ ማለት የጾም፣ የጸሎት፣ የስግደት፣ የምጽዋት እንዲሁም የመታዘዝ፣ የመገዛትና የቅንነት በአጠቃላይ የበጎ ምገባር ትጥቅ ማለት ነው፡፡ በቅዱስ መጽሐፍ የተነገረውም ይህ ነው፡፡(ኤፌ.6፥1-12)
መ. ሃይማኖትን በሚገባ ለመረዳት
ሃይማኖታዊ ዕውቀት ስንል መንፈሳዊ ዕውቀትን ነው፡፡ መንፈሳዊ ዕውቀት ደግሞ የነፍስ ዕውቀት እንጂ የሥጋ ዕውቀት አይደለም፡፡ ስለዚህ የግቢ ጉባኤ ተማሪዎችን የአብነት ትምህርት ማስተማሩ ወይም እንዲማሩ ማድረጉ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን ሁለንተናዊ አስተምሮዋን እንዲረዱ ያስችላቸዋል፡፡ ይህም አገልግሎቷን የተሟላ እንዲሆን ያደርገዋል፡።
ከዕውቀቶች ሁሉ ታላቁ ዕውቀት የእግዚአብሔርን የባሕርይ አምላክነት የምናውቅበት መንፈሳዊ ዕውቀት ነው፡፡ “ነፍስ ዕውቀት የሌላት ትሆን ዘንድ መልካም አይደለም” እንዲል፡፡ (ምሳ.19፥2) ይህም የሚሆነው ተማሪዎች ከተለያዩ ቦታዎች ስለሚመጡ በውስጣቸው ብዙ ጥያቄዎች ይፈጠርባቸዋል፡፡ የእነዚያንም ጥያቄዎች መልስ ለማወቅ ካላቸው ጽኑ ፍላጎት የተነሣ ደጋግመው ይጠይቃሉ፡፡ በሚሰጣቸው ምላሽ በሚያውቁት ዕውቀትም ግልጽ መረዳት የሚኖራቸው በአብነት ትምህርት ማለፍ ሲችሉ ነው፡፡ በቤተ ክርስቲያናችን ወይም በተዋሕዶ ሃይማኖታችን ትልቁ ዕውቀት የሚባለው የኢየሱስ ክርስቶስን የባሕርይ አምላክነት መረዳት፣ የተረዱትንም ሳይጠራጠሩ ማመን ነውና፡፡
በመጽሐፍ እውነተኛ “አምላክ ብቻ የሆንክ አንተ የላክኸውንም ኢየሱስ ክርስቶስን ያውቁ ዘንድ ይቺ የዘለዓለም ሕይወት ናት” ተብሎ የተጻፈውን እውነት ለመረዳት መሠረቱ አብነት ትምህርት ነው፡፡ (ዮሐ.17፥3)
ሠ.ተፅዕኖ ፈጣሪ ለመሆን
የአብነት ትምህርት መማር ለግቢ ጉባኤ ተማሪዎች በሌሎች ጓደኞቻቸውም ዘንድ ሆነ በማኅበረሰቡ ዘንድ የመሰማት፣ የመደመጥ፣ የማሸነፍ፣ የሐሳብ የበላይነት እንዲኖራቸውና ተጽዕኖ መፍጠር እንዲችሉ ይረዳቸዋል፡፡ በጠቅላላው ትምህርቱ በቃል የሚያዝ ትምህርት ስለሆነ አብነት ትምህርት የተማረ ሰው ምን እናገራለሁ ብሉ አይጨነቅም፡፡ ከአንደበት ላይ ቅኔ የሚነጥቁ ምሁራን የሚፈጠሩትም በዚሁ በአብነቱ ካለፉት መምህራን መካካል ነው፡፡ ይህም ብቻ ሳይሆን ቅዱሳት መጻሕፍትን በተለይም የጸሎትና የዜማ መጻሕፍትን በአእምሮ የመወሰንና፣ ያለመርሳት ጸጋ የሚታደልበት በዚሁ በአብነት ትምህርት ቤት ነው፡፡
በጥቅሉ ብዙ ትምህርቶችን ሰብስቦ በጭንቅላት ማከማቸት፣ ለትውልድ ማድረስ፣ ለቤተሰብ ማውረስ፣ የረሱትን ማስታወስ ማለት ነው፡፡ የተፅዕኖ ፈጣሪነት ጸጋውም የሚመጣው ከማስታወስ፣ ካለመዘንጋት የተነሣ ስለሆነ የአብነት ትምህርት ለግቢ ጉባኤ ማስተማር ማለት ሙሉ ሃይማኖቱን በሰው ልቡና ወይም አእምሮ ውስጥ እንደሚቀመጥ ትልቅ መዝገብ ወይም ግምጃ ቤት ይቆጠራል፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
Leave a Reply
Want to join the discussion?Feel free to contribute!