የክርስቶስ ሞትና ትንሣኤ

መ/ር ሕሊና በለጠ
ክፍል ሁለት
የሞቱና የትንሣኤው ፍሬ ነገሮች
ጌታችን በመስቀል ላይ ሲሞት ድኅነታችን ተከናወነ፣ ሞትን ድል አድርጎ ሲነሣ ደግሞ ትንሣኤያችን እውን ሆኖ ተገለጠ፡፡ ለቤተ ክርስቲያን የማይቋረጥ አገልግሎት መሠረት የሆነ ድል፣ የምድርም የደስታዋ ምንጭ ሆነ፡፡ “ወምድርኒ ትገብር ፋሲካ ተሐፂባ በደመ ክርስቶስ፤ በክርስቶስ ደም ታጥባ ምድርም ደስታን ታደርጋለች” በማለት ሊቁ ቅዱስ ያሬድ እንደገለጸልን እኛም ደስታችንን ለመግለጽ እናመሰግናለን፡፡
ከነገረ ድኅነት አንጻር የክርስቶስ ሞትና ትንሣኤ ያመጣውን ውጤት በሦስት ከፍለን እንመልከት፡
ሀ. በሲኦልና በሞት ላይ የተገኘ ድል
የሰው ልጅ ገነትን ካጣ በኋላ ኑሮው በሁለት የተከፈለ ነበር፡፡ የምድር ሕይወቱ እና ከሞት በኋላ የሚኖረው ሕይወቱ፡፡
የምድር ሕይወቱ ነፍሱ ከሥጋው ስትለይና የሥጋ ሞትን ሲሞት ያበቃል፡፡ ከዚያም ገነት የተዘጋች ናትና ነፍሱ ወደ ሲኦል ትሔዳለች፡፡ ሲኦል ደግሞ በጽልመትና በስቃይ የተሞላ፣ እንዲሁም የጨለማው ገዢ ዲያቢሎስ የሠለጠነበት ሥፍራ ነው፡፡ መዝሙረኛው ቅዱስ ዳዊት “በሞት የሚያስብህ የለምና፥ በሲኦልም የሚያመሰግንህ ማን ነው?” (መዝ.፮፥፭) ሁሉም የጌታችንን መምጣት፣ መሞትና መነሣትን በታላቅ ተስፋ የሚጠብቅ ነበር፡፡ ቅዱስ ጳውሎስም ይህንን ሲገልጽ “እነዚህም ሁሉ በእምነታቸው ተመስክሮላቸው ሳሉ የተሰጠውን የተስፋ ቃል አላገኙም፥ ያለ እኛ ፍጹማን እንዳይሆኑ እግዚአብሔር ስለ እኛ አንዳች የሚበልጥ ነገርን አስቀድሞ በይኗልና” ብሏል፡፡ (ዕብ.፲፩፥፴፱-፵)፡፡
ጌታችን፣ መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመስቀል ላይ ለእኛ ሲል ከሞተ በኋላ በአካለ ሥጋ ወደ መቃብር ሲወርድ፣ በአካለ ነፍስ ደግሞ ወደ ሲኦል ወርዶ ነበር፡፡ ቅዱስ አትናቴዎስ ሐዋርያዊ ይህንን ምሥጢር እንዲህ ይዘክረዋል፡- “ነፍሱን ከሥጋው በለየ ጊዜ፡ ያን ጊዜ በሲኦል ፈጥኖ ብርሃን ታየ፡፡ ጌታችን በአካለ ነፍስ ወደ ሲኦል ሔደ፡፡ ሲኦል ተነዋወጠች፤ መሠረቶቿም እፈርስ እፈርስ አሉ፤ ምድርን ያለ ጊዜዋ እንዳታልፍ አጸናት፤ ደሙን በምድር ላይ አፈሰሰ፡፡ ከኅልፈት ጠበቃት፤ በርሷ ያለውንም ሁሉ ጠበቀ፡፡ ስለ ፍጥረት ሁሉ ሥጋውን በመስቀል እንደተሰቀለ ተወው፡፡ ነፍሱ ግን ወደ ሲኦል ወረደች፤ ከዚያ ተግዘው የነበሩ ነፍሳትን አዳነች፤ ሲኦልንም በዘበዘች፤ ፍጥረትንም ሁሉ ገንዘብ አደረገች፡፡ ሥጋውም በመቃብር ያሉ ሙታንን አስነሣ፤ ነፍሱም በሲኦል ተግዘው የነበሩ ነፍሳትን ፈታች፡፡” እያለ በዕለተ ዐርብ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አዳምና ልጆቹን ለማዳን በመስቀል ላይ የከፈለውን ዋጋ ያሳየናል፡፡
ለዘመናት በሞት ጥላ ውስጥ ሆነው በተስፋ ሲጠብቁት ለነበሩት ነፍሳት ሁሉ በሲኦል ውስጥ ድኅነትንና ሰላምን ሰበከላቸው፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስ ይህን ሲነግረን “ክርስቶስ ደግሞ ወደ እግዚአብሔር እንዲያቀርበን እርሱ ጻድቅ ሆኖ ስለ ዓመፀኞች አንድ ጊዜ በኃጢአት ምክንያት ሞቶአልና፤ በሥጋ ሞተ፣ በመንፈስ ግን ሕያው ሆነ፥ በእርሱም ደግሞ ሄዶ በወኅኒ ለነበሩ ነፍሳት ሰበከላቸው” (፩ጴጥ.፫፥፲፰-፲፱) አለ፡፡ ቅዱስ ጳውሎስም ስለዚሁ ጉዳይ ሲናገር “ምርኮን ማርከህ ወደ ሰማይ ወጣህ፤ ጸጋህንም ለሰው ልጅ ሰጠህ” ይላልና ከምድር በታች (ሲኦል) ካልወረደ መውጣቱ ምንድን ነው? የወረደው እርሱ ነው፤ ሁሉንም ይመላ ዘንድ ከሰማያት ሁሉ በላይ የወጣው ደግሞ እርሱ ነው” ሲል ገልጾታል፡፡ (ኤፌ.፬፥፰-፲)፡፡
ቅዱስ ኤጲፋንዮስ ዘቆጵሮስ የዘመነ ብሉይ ሰዎችን ጩኸት እግዚአብሔርም እንደሰማቸውና፣ መለኮት ከሥጋ ጋር በመቃብር ከነፍስም ጋር በሲኦል በተዋሕዶ እንደ ነበር ሲያስረዳ “ነቢይ ዳዊትም ነፍሴን በሲኦል አትተዋትም፤ የባሕርይ ልጅህንም ሙስና መቃብርን ያይ ዘንድ አሳልፈህ አትሰጠውም አለ፡፡ ይህም ጌታ በተዋሐደው አካል ያለውን የነፍስና የሥጋ ተዋሕዶ ያስረዳል፤ የቀና ልቡና ዕውቀት በእርሱ ጸንቶ ይኖር ዘንድ፡፡ ዳዊት እንደተናገረው እውነት ሆነ፤ ነፍስ መለኮትን ተዋሕዳ ወደ ሲዖል ወርዳለችና፤ ሥጋም ሦስት መዓልት ሦስት ሌሊት በመቃብር ሳለ መለኮት ከሥጋ አልተለየም” ብሏል፡፡
ይህ ሁሉ የሚያስረዳው በማኅፀነ ማርያም መለኮት ከትስብእት፣ ትስብእት ከመለኮት ጋር ከተዋሐደ በኋላ ምንም ዓይነት መለያየት ሳይኖር መለኮት በሥጋ እየተሰደደ፣ እየደከመ፣ እየተራበ፣ እየተጠማ፣ እየታመመ፣ እንዲሁም በመስቀል ተሰቅሎ በሞቱ ዓለምን ያዳነ መሆኑን ነው፡፡ ከላይ የሆኑት ሁሉ መለኮት በሥጋ ብለን የምንገልጸው ሲሆን እንዲሁ ሥጋም በመለኮት ሕሙማንን እየፈወሰ፣ ዕውራንን እያበራ፣ የተራበ እያበላ፣ ሙት እያነሣ፣ የተፈጸመ የነገረ ድኅነት ጉዳይ እንደሆነ ነው፡፡
ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅም በትንሣኤ በዓል ድርሳኑ “ሲኦል ወደዚያ በወረደው በክርስቶስ ምርኮ ሥር ሆነ፤ ተበረበረ” ሲል ገልጾታል፡፡
ሲኦልን መበዝበዙን ቅዱስ ቄርሎስ ዓምደ ሃይማኖት “ታመመ፤ ሞትን ከተቀበለበት ከሥጋ ጋር ተዋሕዶ በመስቀል ላይ በፈቃዱ ለሥጋውያን ሞተ፤ ባሕርየ መለኮት ሥጋን ተዋሕዶ በማኅፀን ካደረ ጀምሮ ሥጋ ገንዘቡ እንደ መሆኑ በሥጋ ይኸንን ሥርዓት ፈጸመ፡፡ ለማይመረመር ለመለኮቱ ባሕርይ እንደሚገባ ደግሞ እርሱ ኅብስት አበርክቶ ሁሉን ያጠግባል፤ አይራብም፤ አይጠማም፤ አይደክምም፤ አያንቀላፋም፤ አይታመምም፤ አይሞትም፤ ሕይወትን ለሁሉ ይሰጣል፡፡ ዳግመኛ በዚያ በሲኦል ተገዝተው ያሉ ነፍሳትን ያድን ዘንድ በአካለ ነፍስ ወደ ሲኦል ወረደ፤ በመለኮቱም ሲኦልን በዘበዘ” ብሎ አስተምሯል፡፡
አስቀድመን በሰፊው እንዳየነው ከክርስቶስ ትንሣኤ በኋላ ሞት አስፈሪነቱ ጠፋ፡፡ ሞት ከምድራዊው ሕይወት የሚያርፉበት ዕረፍት፣ ወደ ሰማያዊው ሕይወት መሸጋገሪያ ሆነ፡፡ በክርስቶስ ትንሣኤ ባገኘነው ክብር በትንሣኤ ዘጉባኤ እስክንነሣ ድረስ ብቻ ነፍስ ከሥጋ የሚለያዩበት ሆነ፡፡ “አሁንም ክርስቶስ ከሞቱ ሰዎች አስቀድሞ ተነስቷል።” እንዲል ሐዋርያው (፩ቆሮ.፲፭፥፳)፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ ይበልጥ ሲያብራራውም “ሁሉ በአዳም እንደሚሞቱ እንዲሁ ሁሉ በክርስቶስ ደግሞ ሕያዋን ይሆናሉና። ነገር ግን እያንዳንዱ በራሱ ተራ ይሆናል፤ ክርስቶስ እንደ በኩራት ነው፥ በኋላም በመምጣቱ ለክርስቶስ የሆኑት ናቸው ብሏል፡፡ (፩ቆሮ.፲፭፥፳፪-፳፫)፡፡ በመቀጠልም የሞትን በክርስቶስ ሞት ፍጹም መሻርና መደምሰስ ሲገልጽልን “የኋለኛው ጠላት ይሻራል፣ ይኸውም ሞት ነው” ሲል አስተምሯል፡፡ (፩ቆሮ. ፲፭፥፳፮)፡፡ በዚህም ሃይማኖቱን አጽንቶ፣ ምግባሩን አቅንቶ በክርስቶስ የባሕርይ አምላክነት አምኖ የሚኖር ሰው ሁሉ ይህን ሞት የሚናፍቀው እንጂ የሚፈራውና የሚጠላው አይደለም፡፡
ለ. የቅዱሳን በገነት መክበር፣ የድል አድራጊዋ ቤተ ክርስቲያን ወይም የክርስቶስ መንግሥት መገለጥ
ጌታችን ከማረጉ በፊት ለሐዋርያት “በአባቴ ቤት ብዙ ማደሪያና ማረፊያ አለ፤ እንዲህስ ባይሆን ኖሮ ቦታ ላዘጋጅላችሁ እሄዳለሁ እላችሁ ነበር፤ ከሄድሁና ቦታ ከአዘጋጀሁላችሁም ዳግመኛ እመጣለሁ፤ እናንተም እኔ ባለሁበት ትኖሩ ዘንድ ወደ እኔ እወስዳችኋለሁ” (ዮሐ.፲፬፥፪-፫) ብሏቸው ነበር፡፡ በጸለየ ጊዜም “አባት ሆይ፥ ዓለም ሳይፈጠር ስለ ወደድኸኝ የሰጠኸኝን ክብሬን እንዲያዩ እኔ ባለሁበት የሰጠኸኝ እነርሱ ደግሞ ከእኔ ጋር ይሆኑ ዘንድ እወዳለሁ” ማለቱም ከዚሁ ጋር የተያያዘ ነው፡፡ (ዮሐ.፲፯፥፳፬)፡፡ በእርግጥ ሐዋርያቱም “ልሄድ ከክርስቶስም ጋር ልኖር እናፍቃለሁ፥ ከሁሉ ይልቅ እጅግ የሚሻል ነውና” (ፊል.፩፥፳፫) ብሎ ቅዱስ ጳውሎስ እንደመሰከረው ከምድር ሕይወት ተለይተው ከእርሱ ጋር ለመሆን ይናፍቁ ነበር:: “በሰማይ ያለ በእጅ ያልተሠራ የዘለዓለም ቤት የሚሆን ከእግዚአብሔር የተሠራ ሕንጻ” እንዳላቸው ያውቃሉና፡፡ (፪ቆሮ. ፭፥፩)፡፡ እንዳለው ውጣ ውረድ፣ ድካም፣ ረኀብ፣ ጥም፣ ኃጢአት፣ ወዘተ ከአለበት ዓለም ይህ ሁሉ ችግር በሌለባት ዓለመ ነፍስ በሆነችው በገነት መኖር የተቻለው በክርስቶስ ሞትና ትንሣኤ ነው፡፡
በገነት ያለውን የቅዱሳን ሕይወት እንዴት እንደ ሆነ ቅዱስ ዮሐንስ በራእዩ ገልጾታል፡፡ “በዙፋኑ ዙሪያም ሃያ አራት ዙፋኖች ነበሩ፥ በዙፋኖቹም ላይ ነጭ ልብስ ለብሰው በራሳቸውም የወርቅ አክሊል ደፍተው ሃያ አራት ሽማግሌዎች ተቀምጠው ነበር” (ራእ.፬፥፬)፡፡ “… ስለ እግዚአብሔር ቃልና ስለ ጠበቁት ምስክር የታረዱትን የሰዎች ነፍሳት ከመሠዊያ በታች” አየ፡፡ (ራእ.፮፥፱)፡፡ ከዚህ በኋላ በራእዩ ምን እንዳየ ሲነግረንም “…አንድ እንኳ ሊቆጥራቸው የማይችል ከሕዝብና ከነገድ ከወገንም ከቋንቋም ሁሉ እጅግ ብዙ ሰዎች ነበሩ፤ ነጭ ልብስም ለብሰው የዘንባባንም ዝንጣፊዎች በእጆቻቸው ይዘው በዙፋኑና በበጉ ፊት ቆሙ፤ በታላቅም ድምፅ እየጮሁ- በዙፋኑ ላይ ለተቀመጠው ለአምላካችንና ለበጉ ማዳን ነው አሉ” ሲል ጽፎልናል፡፡ ከክርስቶስ ሞትና ትንሣኤ በፊት ይህ ሁሉ አልነበረም፡፡ በእንዲህ ያለ ሕይወት መኖር የተቻለው ደግሞ በክርስቶስ ሞትና ትንሣኤ የሞት ሥልጣን ከተሻረ በኋላ ነውና ይህን ክብር ለማግኘት ሁሉም ቅዱሳን ከዚህ ዓለም መሄድን ይመርጣሉ፡፡
በሰማይ ለቅዱሳን የተዘጋጁት ብርሃናማ መኖሪያዎች በቅዱሳት መጻሕፍት “የእግዚአብሔር ከተማ” (ዕብ.፲፪፥፳፪)፤ “የንጉሥ ከተማ”፤ “የጽዮን ተራራ” (መዝ.፵፯፥፪)፤ ፵፯፥፲፩)፤ “ሰማያዊት ኢየሩሳሌም”፣ (ቅድስት ማርያም)፣ “ላይኛይቱ ኢየሩሳሌም” (ገላ.፬፥፳፮)፤ “አዲሲቱ ኢየሩሳሌም” (ራእ.፳፩፥፪) ተብለዋል፡፡ ስለዚህ ከትንሣኤው በኋላ በሰማይ ያለች የክርስቶስ መንግሥት ለቅዱሳን ተገለጠች፡፡ በብሉይ ኪዳን የነበሩት ሁሉ ወደ ውስጧ ገቡ፡፡
እንደ ቅዱሳት መጻሕፍት አስተምህሮ፣ የቅዱሳን ሰዎች በገነት መክበር ስንል ፩ኛ. ከድካማቸው ማረፋቸውን፣ ፪ኛ. ከኀዘንና ከስቃይ እንግልት መለየታቸውን (ራእ.፲፬፥፲፫፤ ፥፲፮)፣ ፫ኛ. ከአበውና ከሌሎች ቅዱሳን ጋር ፍጹም የሆነ አንድነትን ማግኘታቸውን፣ ፬ኛ. እርስ በራሳቸውም ሆነ ከአዕላፍ መላእክት ጋር አንድ መሆናቸውን፣ ፭ኛ. ከበጉ ዙፋን ፊት ቆመው ማመስገናቸውንና እርሱን ማገልገላቸውን ነው፡፡
ሐ. ርደተ መንፈስ ቅዱስ
ጌታችን ከሕማማቱና ከስቅለቱ በፊት ለሐዋርያት ከእነርሱ ጋር እስከ ዘለዓለም ድረስ አብሮ የሚቆየውንና የሚያስተምራቸውን እንዲሁም እርሱ ያስተማራቸውን በማጽናት የሚመራቸውን ሌላኛውን አጽናኝ ከአብ የሚወጣ መንፈስ ቅዱስን እንደሚልክላቸው ቃል ገብቶላቸው ነበር፡፡ (ዮሐ.፲፭፥፳፮)፡፡ ከትንሣኤው በኋላም ለደቀ መዛሙርቱ ተገልጦላቸው የመንፈስ ቅዱስን ጸጋ ሲያድላቸው ይህንም ብሎ እፍ አለባቸውና መንፈስ ቅዱስን ተቀበሉ። “ኃጢአታቸውን ይቅር ያላችኋቸው ሁሉ ይቀርላቸዋል፤ የያዛችሁባቸው ተይዞባቸዋል አላቸው”፡፡ (ዮሐ.፳፥፳፪-፳፫)፡፡ ከዕርገቱ በዐሥረኛው ቀንም በበዓለ አምሳ መንፈስ ቅዱስን “እንደ እሳት በተከፋፈሉ ልሳኖች” ላከላቸው፡፡ (ሐዋ. ፪፥፫)፡፡
የመንፈስ ቅዱስ መውረድ በመጀመሪያ ለሐዋርያት በተሰጡት የመፈወስ፣ በልሣን የመናገርና በመሳሰሉት አስደናቂ ስጦታዎች የተገለጸ ሲሆን፣ በመቀጠልም በክርስቶስ የሚያምኑትን ሁሉ ወደ ፍጹምነትና ወደ ድኅነት በመውሰዱ የታወቀ፣ የተረዳ ሆኗል፡፡
“የመለኮቱ ኃይል፥ … ለሕይወትና እግዚአብሔርን ለመምሰል የሚሆነውን ነገር ሁሉ ሰጥቶናል፡፡ (፩ጴጥ. ፩፥፫)፡፡ እነዚህ የጸጋ ስጦታዎች ሁሉ ጌታችን በመሠረታት ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ይገኛሉ፡፡ የቅድስናችንንና የድኅነታችንን ምሥጢር ሁሉ የያዙ ናቸው፡፡
በአጠቃላይ ዋናው የክርስቶስ ሰው መሆን፣ መሰደድ፣ መራብ፣ መጠማት፣ መሰቀል፣ መነሣት በሰው ልጅ ላይ ሠልጥኖ የነበረውን ሞት ድል አድርጎ ሰውን ለማዳን ነው፡፡ እንደ ሰው ድንቅ ውለታ የተዋለለት ፍጥረት የለም፡፡ በአባቱ ሞት የዳነ፣ ጠላቱን ያሸነፈ፣ ሠልጥኖበት ከነበረው ጠላት ነጻ የወጣ የሰው ልጅ ብቻ ነው፡፡ በሰው ሰውኛው አንድ ሰው እናት አባት ሲሞትበት አሳዳጊ ያጣል፤ የሚያለብሰው፣ የሚያጎርሰው፣ የሚያስተምረው፣ ርስት ጉልቱን የሚያወርሰው እና ከድኅነት የሚያወጣው ያጣል፡፡ በአባታችን በክርስቶስ ሞት ግን ያጣነውን ሁሉ አግኝተናል፡፡ ባለጸጎች ሆነናል፤ ወደ ርስታችን ተመልሰናል፡፡ አሁንም በክርስቶስ የባሕርይ አምላክነት አምነን፣ የተከፈለልንን ውለታ እያሰብን በሃይማኖት ጸንተን እንድንኖር፣ እንዲሁ ከበዓለ ስቅለቱና ከበዓለ ትንሣኤው በረከት ያድለን ዘንድ አምላከ ቅዱሳን ፈቃዱ ይሁንልን፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር!

0 replies

Leave a Reply

Want to join the discussion?
Feel free to contribute!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *