“ፋሲካችን ክርስቶስ ተሠውቶ የለምን?”( ፩ኛቆሮ.፭፥፯)
በቀሲስ ኃይለ ሚካኤል ብርሃኑ
ፋሲካ ማለት ማለፍ፣ መሻገር፣ ደስታ ሲሆን በዕብራይስጥ “ፓሳሕ” ይለዋል፡፡ ይህም ዐለፈ ማለት ነው፡፡ ቅዱስ ያሬድም በትንሣኤ በዓል የሚዘመረውን የመዝሙር ክፍል “ፋሲካ” በማለት ሰይሞታል፡፡ ይኸውም “ወምድርኒ ትገብር ፋሲካ ተሐፂባ በደመ ክርስቶስ፤ ምድርም በክርስቶስ ደም ታጥባ ፋሲካን ታደርጋለች” በማለት እንደተናገረው እኛም እርሱን አብነት አድርገን በእርሱ ዜማ እያመሰገንን ትንሣኤውን እየመሰከርን በትንሣኤውም ያገኘነውን ትንሣኤ ዘለ ክብር(የክብር ትንሣኤ) እያሰብን እናከብራለን፡፡
የፋሲካ በዓል የሚከበረው የክርስትና እምነት ተከታዮች ሁሉ ባሉበት በኅብረት ወይም በጋራ ነው፡፡ ምክንያቱም በዓሉ የሁሉ ነውና፡፡ ብርሃነ ዓለም ቅዱስ ጳውሎስ እንደጠቀሰው “የክርስቶስ ፍቅር በዚህ ሐሳብ እንድንጸና ያስገድደናል ሁሉ ፈጽመው ስለ ሞቱ አንዱ ስለ ሁሉ ቤዛ ሆኖ ሞቶአልና በሕወት የሚኖሩትም ስለ እነርሱ ቤዛ ሆኖ ለሞተውና ለተነሣውም እንጂ ወደፊት ለራሳቸው የሚኖሩ እንዳይሆኑ እርሱ ስለ ሁሉ ቤዛ ሆኖ ሞተ” (፪ኛቆሮ.፭፥፲፬) በማለት የብዙኀን በዓል መሆኑን ያስረዳል፡፡
ለአማናዊው ፋሲካችን ምሳሌ የነበረው ኦሪታዊው የፋሲካ በዓል አከባበር የሚጀምረው የእስራኤል ከግብጽ መውጣት ጋር ተያይዞ ነው፡፡ የእስራኤል ልጆች በግብጽ ሀገር ሲኖሩ መከራው ቢጸናባቸው የእግዚአብሔርን ክንድ ደጅ መጥናታቸውን ተከትሎ ከግብጽ እንዲወጡ ሙሴን መሪ(መስፍን)፣ አሮንን አፍ (ካህን) አድርጎ እግዚአብሔር ቢያዛቸውም ፈርዖን እግዚአብሔርን አላውቅም እስራኤልንም አለቅም በማለቱ በዘጠኝ መቅሠፍት ግብፃውያን ተመተው እግዚአብሔርን መስማት እስራኤልንም መልቀቅ ስላልፈቀዱ በዐሥረኛ ሞተ በኵር ተቀጡ፡፡
መቅሠፍቱ በእግዚአብሔር ላይ ያመፀውን ፈርዖንንና ግብጻውያንን የሚቀጣ በመሆኑ የእስራኤል ልጆች መቅሰፍቱ እንዳያገኛቸው ብሎም ለእግዚአብሔር የተለዩ መሆናቸው እንዲታወቅ ለሙሴ በተነገረው መሠረት በየወገናቸው የአንድ ዓመት ጠቦት አርደው ደሙን በቤታቸው በሁለቱ መቃኖችና በጉበኑ ላይ በመርጨት ምልክት አደረጉ፡፡ የእግዚአብሔር መልአክ ያንን የደም ምልክት እያየ የእስራኤልን ልጆች እያለፈ የግብጻውያንን በኵር ሁሉ በሞት ቀጣቸው፡፡ ያ ስለ እስራኤላውያን ደኅንነት የታረደ በግ በደሙ ምልክት አማካይነት የእስራኤን ልጆች ከግብጻውያን ጋር በሞት ከመቀጣት ያመለጡበት ሥርዓት ነው፡፡ የእስራኤል ልጆች ከግብጽ ባርነት ተላቀው ከፈርዖን እጅ አምልጠው ወደ ተስፋዪቱ ምድር ለመግባት ጉዞ ለመጀመራቸው ሳይወድ በግድ የፈርዖንን እሺታ ያስገኘ ዐሥረኛው መቅሠፍት ሞተ በኵር ነው፡፡
ለፋሲካ የሚታረደውም በግ ፋሲካ ይባል ነበር (ዘፀ.፲፪፥፩-፲፫)፡፡በግብጻውያን ቤት ልቅሶ ሲሰማ በእስራኤላውያን ቤት ከበጉ ደም የተነሣ መጠበቅ (የቀሳፊው ሞት ማለፍ) ሆኖላቸው ደስታ የተሰማበት፣ የእግዚአብሔር ትድግና የታየበት ስለሆነ ፋሲካ ተባለ፡፡፡
የእስራኤል ልጆች ከእግዚአብሔር በታዘዙት መሠረት በመጀመሪያ ወራቸው በዐሥራ አራተኛው ቀን የፋሲካን በዓል ያከብራሉ፡፡ ከዚያም ምሽት እስከ አንድ ሳምንት ድረስ የቦካውን ነገር ለመብላት ስላልተፈቀደላቸው ሙሉ ሳምንቱ የቂጣ በዓል ተባለ፡፡ እስራኤል ከግብጽ ሲወጡ በችኮላ ስለነበር ያልቦካ ቂጣ መብላታቸውን የሚያስቡበት ነው፡፡ እስራኤል ከግብጽ ወጥተው ወደ ተስፋዪቱ ምድር መግባታቸው የሰው ልጅ ከሲዖል ወደ ገነት፣ ከጨለማ ወደ ብርሃን፣ ከሞት ወደ ሕይወት፣ ከመገዛት ወደ ነጻነት፣ ከባርነት ወደ ልጅነት ለመግባታችን(ለመሻገራችን) ምሳሌ ነው፡፡
የእስራኤል ልጆች በታረደው በግ ደም አማካኝነት ከሞት ማምለጣቸው በአማናዊው በግ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ደም ከዲያብሎስ ቁራኝነት ከሲዖል ባርነት ተላቀን ሞታችን በሞቱ ተወግዶልን ሕይወትን የማግኘታችን ምሳሌ ነው፡፡ ለዚህም ነው ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ የቆሮንቶስ ክርስቲያኖችን በመከረበት ትምህርቱ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን “ፋሲካችን” እያለ ሲገልጸው የምናየው፡፡
“እንግዲያስ መታበያችሁ መልካም አይደለም ጥቂቱ እርሾ ብዙውን ሊጥ እንደሚያመጥ አታውቁምን እንግዲህ ለአዲስ ቡሆ ትሆኑ ዘንድ አሮጌውን እርሾ ከእናንተ አርቁ፤ ገና ቂጣ ናችሁና ፋሲካችን ክርስቶስ ተሠውቶ የለምን? አሁንም በዓላችሁን አድርጉ ነገር ግን እውነትና ንጽሕና ባለው እርሾ ነው እንጂ በአሮጌው እርሾ በኃጢአትና በክፋት እርሾም አይደለም”(፩ኛ ቆሮ.፭፥፮) በማለት ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ፋሲካችን ይለዋል፡፡
በመከራው መከራችንን አስወግዶ፣ በሞቱ ሞታችንን ሽሮ፣ በትንሣኤው ትንሣኤያችንን አውጆልናልና ፋሲካችን ክርስቶስ ነው፡፡ ለዚህም ነው ሊቁ ቅዱስ ያሬድ ድጓ በተሰኘው ድርሰቱ በዕለቱ ማለትም በበዓለ ፋሲካ (በትንሣኤ ዕለት) በሚቆመው የመዝሙር ክፍል “ይትፌሣሕ ሰማይ ወትትሐሠይ ምድር…፣ ሰማይ ይደሰታል፣ ምድርም ሐሤት ታደርጋለች” ይልና ዝቅ ብሎ “ወምድርኒ ትገብር ፋሲካ ተሐፂባ በደመ ክርስቶስ፣ ምድር በክርስቶስ ደም ታጥባ ፋሲካን አደረገች” በማለት ያመሰገነው፡፡
በዓለ ፋሲካ አንዱ ክርስቶስ ስለ ሁሉ የሞተበት፣ ሕዝብና አሕዛብ አንድ የሆኑበት ሰማያውያንና ምድራውያን የተደሰቱበት፣ የራቁት የቀረቡበት፣ የአዳም ተስፋ የተፈጸመበት ታላቅ በዓል ነው፡፡ በዚህ በዓል የተጣላ ታርቆ፣ የበደለ ክሶ፣ የተበደለ ይቅር ብሎ እግዚአብሔር ለሰው ያደረገውን በአንድያ ልጁ ቤዛነት ያሳየንን ፍጹም ፍቅሩን እያደነቅን እርስ በእርሳችን በፍቅር ተሳስረን ያለን ለሌላቸው አካፍለን፣ ድሃ ሀብታም ሳንል፣ ብሔር፣ ቋንቋ፣ ፆታ ሳንለይ ሁላችን የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ልጆች መሆናችንን ላፍታም ሳንዘነጋ መሆን አለበት፡፡
በዓለ ፋሲካ ወይም በዓለ ትንሣኤ ከመጀመሪያው የትንሣኤ ቀን አንሥቶ እስከ በዓለ ኀምሳ ማለትም እስከ ኀምሳኛው ቀን ድረስ ትንሣኤ ሕይወትን እያሰብን ደስ ብሎን የምናከብረው የደስታ በዓላችን ነው፡፡ ይህ ማለት ግን ትንሣኤ የሚታሰበው በዚህ ቀን ብቻ ነው ማለት ሳይሆን በልዩ የአምልኮ ሥርዓት ትንሣኤ ክርስቶስን እያሰብን እኛም እንዲሁ ትንሣኤ ዘለ ክብር እንዳገኘን በምልዓት የምንመሰክርበት ወቅት በመሆኑ ነው፡፡ ደስታችንም ከወገኖቻችን ጋር ባለን ነገር እየተሳሰብን መሆን ይኖርበታል፡፡ ምክንያቱም ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለዓለሙ ሁሉ ድኅነት በመስቀል ላይ ዋለ እንጂ ለአንድ ጎሳ ወይም ለአንድ ሀገር ወይም ለአንድ ቋንቋ ተናጋሪ አይደለም፡፡
ወንጌላዊው ቅዱስ ዮሐንስ እንደ ጻፈው “በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘለዓለም ሕወት እንዲያገኝ እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን ቤዛ አድርጎ እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን እንዲህ ወዶታልና” ይላል፡፡(ዮሐ.፫፥፲፮)፡፡ በዚህ ገጸ ንባብ ላይ ዓለም የተባለ ሰው ነው፡፡ እግዚአብሔር ሰውን የወደደውና የባህርይ ልጁን ቤዛ አድርጎ እስከ መስጠት ያደረሰው ፍቅር ነው፡፡ የክርስትና ሃማኖት የተመሠረተውም በፍቅር ነው፡፡ አንድ ክርስቲያን በሚኖርበት አካባቢም ሆነ በተገኘበት ቦታ ሁሉ በወንድሞቹ መካከል በፍቅር ሊመላለስ ይገባዋል፡፡
ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ በመልእክቱ “ወንድሞቻችን ሆይ እንግዲህ ደስ ይበላችሁ ጽኑ ታገሡ በአንድ ልብም ሁኑ በሰላም ኑሩ፤ የሰላምና የፍቅር አምላክም ከእናንተ ጋር ይሁን በተቀደሰ ሰላምታ እርስ በርሳችሁ ሰላም ተባባሉ” (፪ኛቆሮ.፲፫፥፲፩) በማለት እንዳስተማረን ሆነን ልንኖር ተጠርተናል፡፡ ሞትን በሞቱ ሽሮ ሙስና መቃብርን አጥፍቶ በኃይልና በሥልጣን የተነሣውን አምላካችንን እንደ ቅዱስ ያሬድ በዝማሬ ስናመሰግነውም “ትንሣኤከ ለእለ አመነ ብርሃነከ ፈኑ ዲቤነ፤ ለእኛ ትንሣኤህን ለምናምን ብርሃንህን በላያችን ላክልን” በማለት የትንሣኤውን ብርሃን እንዲልክልን ስንለምነው ያደፈ ማንነታችን መቀደስ የመጀመሪያ ሥራችን አድርገን ነው፡፡
እግዚአብሔር ንጹሓ ባሕርይ ነውና በንጹሕ ሰውነታችን ላይ ስለሚያድር ከወደቅንበት ኃጢአት በንስሓ ዕንባ ታጥበን መነሣት እና ቤተ መቅደስ ሰውነታችን ንጹሕ ማድረግ ይኖርብናል፡፡ የእግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ማደሪያዎች ለመሆን ዳግም በክርስቶስ ተሠርተናልና እርሱን የጽድቅ ልብሳችን አድርገነዋል፡፡ በእርሱ ልብስነት የተሸፈነ /ያጌጠ/ ማንነታችን ደግሞ ለሁሉ ፍቅርን የሚያደርግ ይሆናል፡፡
ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ለሮሜ ክርስቲያኖች በላከላቸው መልእክቱ “እንግዲህ የጨለማን ሥራ ከእኛ እናርቅ፣ የብርሃንንም ጋሻ ጦር እንልበስ በቀን እንደሚሆን በጽድቅ ሥራ እንመላለስ፤ በዘፈንና በስካር፣ በዝሙትና በመዳራትም አይሁን በክርክርና በቅናትም አይሁን ነገር ግን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ልበሱት የሥጋችሁንም ምኞት አታስቡ” እንዲል፡፡(ሮሜ ፲፫፥፲፪)
ቅዱስ ጳውሎስ እንዳስተማረን በዓለ ትንሣኤውን ስናከብር የጨለማን ሥራዎች ከእኛ ማራቅ ይጠበቅብናል፡፡ እነርሱም ትዕቢት፣ አመጽ፣ ክፋት፣ ስግብግብነት፣ ፍቅረ ንዋይ፣ ዘረኝነት፣ ቁጣ፣ ቅንዓት፣ ዝሙት፣ ነፍሰ ገዳይነት፣ ሐሜት፣ ዘፋኝነት ወዘተ ሲሆኑ እነዚህን ክፉ ሥራዎች ከእኛ በማራቅና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ያሳየንን ፍጹም ፍቅር ተገንዝበን እርሱን ልንለብስ ይገባናል፡፡
ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ልበሱት ካለ በኋላ በሌላው ክፍል ደግሞ “እንግዲህ እግዚአብሔር እንደመረጣቸው ቅዱሳንና ወዳጆች ምሕረትንና ርኅራኄን፣ ቸርነትንና ትሕትናን፣ የውሀትንና ትዕግሥትን ልበሱት ባልንጀሮቻችሁን ታገሡአቸው እርስ በእርሳችሁ ይቅር ተባባሉ፤ ባልንጀሮቻችሁን የነቀፋችሁበትን ሥራ ተዉ፣ ክርስቶስ ይቅር እንዳላችሁ እናንተም እንዲሁ አድርጉ፤ ከዚህም ሁሉ ጋር ዘወትር ተፋቀሩ የመጨረሻው ማሠሪያ እርሱ ነውና” በማለት እንደመከረን መንፈሳዊ ፍሬ የምናፈራ መሆን እንዳለብን ይመክረናል፡፡(ቆላ.፫፥፲፪)
እንግዲህ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መራራውን ሞት የተጎነጨ፣ ሕማማተ መስቀሉን በፍቅር የተቀበለ እኛን ከሞት ወደ ሕይወት፣ ከባርነት ወደ ነፃነት፣ ከጨለማ ወደ ብርሃን ለመመለስ እርሱ ሁሉን ፈጽሞ ስለ እኛ ነፍሱን ለሞት አሳልፎ ሰጥቷልና፡፡ በከበረ ደሙ ፈሳሽነት ከኃጢታችን ሁሉ ነጽተናል፡፡ ስለሆነም ንጽሕናን ቅድስናን እንደ ልብስ ተጎናጽፈን እንድንኖር አዲሱን ልብስ ክርስቶስን እንልበስ፡፡
የቅዱሳን አምላክ እግዚአብሔር የትንሣኤውን ብርሃን ለሁላችን ያድለን አሜን፡፡
Leave a Reply
Want to join the discussion?Feel free to contribute!