የክርስቶስ ሞትና ትንሣኤ

ክፍል አንድ

መ/ር ሕሊና በለጠ

የክርስቶስ ሞቶ መነሣት ለትንሣኤያችን መጀመሪያ ነው፡፡ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በሞቱና በትንሣኤው ትንሣኤያችንን ባያረጋግጥልን ኖሮ ሃይማኖት ዋጋ አያሰጥም ነበር፡፡ የአማኞችም ሕይወታቸው በክርስቶስ ሞትና በትንሣኤው በተገኘ ሕይወት ላይ የተመሠረተ ነው፡፡ ለዚህም ነው የጥንት ክርስቲያኖች “ማራናታ” እያሉ ሰላምታ ይለዋወጡ የነበሩት፡፡ “ማራናታ” ማለት “ክርስቶስ የተነሣው፣ ያረገውና ዳግም የሚመጣው” ማለት ነው፡፡ በቤተ ክርስቲያናችንም ይህ ትውፊት ቀጥሎ በሰሙነ ትንሣኤና በበዓለ ሃምሳ “ክርስቶስ ተንሥአ እሙታን፣ በዐቢይ ኃይል ወሥልጣን…፤ክርስቶስ በታላቅ ኃይልና ሥልጣን ከሙታን ተለይጦ ተነሣ” እያልን ሰላምታ እንለዋወጣለን፡፡

ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ የክርስቶስ ትንሣኤ ለክርስትና መኖርና በክርስትናችን ጸንተን ለምናገኘው ትንሣኤ የግድ አስፈላጊ እንደ ነበር “ክርስቶስ ከሙታን ተለይቶ ተነሥቷል ብለን ለሌላው የምናስተምር ከሆነ እንግዲህ ከመካከላችሁ ሙታን አይነሡም የሚሉ እንዴት ይኖራሉ? ሙታን የማይነሱ ከሆነ  ክርስቶስም ከሙታን ተለይቶ አልተነሣማ፤ ክርስቶስም ካልተነሣ እንግዲያስ ትምህርታችን ከንቱ ነው፤ የእናንተም እምነታችሁ ከንቱ ነው፤ …በዚህ ዓለም ሕይወት ብቻ ክርስቶስን ተስፋ ከአደረግነው፥ ከሰው ሁሉ ይልቅ ጉዳተኖች ነን” (፩ቆሮ.፲፭፥፲፪-፲፱)፡፡ በማለት በአጽንዖት አስተምሯል፡፡

በመስቀል ላይ ሞቶ ሞትን ድል መንሣቱ

“እግዚአብሔር ወልድ ለምን ሰው ሆነ?” የሚለውን ጥያቄ ሲመልሱ ቅዱሳን አበው “ወልደ እግዚአብሔር ሰው የሆነው ለሰው ሁሉ ሕይወትን ለመስጠት ነው” ይላሉ፡፡ እግዚአብሔር ብቻውን ሕያው ነው፡፡ “እርሱ ብቻ የማይሞት ነው” (፩ጢሞ.፮፥፲፮)፡፡ ስለዚህ መዋቲ የሆነው ሰው ጽድቅንና ሕይወትን የሚያገኘው በጸጋ ነው፡፡ “ያዳነን በቅዱስ አጠራሩም የጠራን እርሱ ነውና፤ ዓለም ሳይፈጠር በኢየሱስ ክርስቶስ እንደ ተሰጠን እንደ ፈቃዱና እንደ ጸጋው እንጂ እንደ ሥራችንም አይደለም፤ ይህም ሞትን በሻረው ሕይወትንም በገለጣት በወንጌሉም ትምህርት ጥፋትን ባራቀ በጌታችንና በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ መምጣት ዛሬ ተገለጠ።” (፪ጢሞ. ፩፥፱-፲) በማለት ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ለደቀ መዝሙሩ ጢሞቴዎስ በጻፈው መልእክቱ እንደገለጠለት የእርሱን ዘለዓለማዊነት (ሕያውነት) በጸጋ አድሎ የፈጠረው የሰው ልጅ የተሰጠውን ሀብት በማጣቱ፣ ያጣውን ሀብት ይመልስለት ዘንድ አምላክ ሰው ሆነ በመስቀልም መከራ መስቀልን ተቀበለ፡፡

ሞተን የነበርን እኛ ሕይወትን አግኝተን የማንሞት እንሆን ዘንድ ሞት ራሱ መሞት አለበት፡፡ ይህ ይሆን ዘንድ በመለኮቱ የማይሞት እግዚአብሔር ወልድ በሥጋ ሞተና ሞትን ድል አደረገ፡፡ ይህንን ቅዱስ ጳውሎስ ሲገልጽልን “ይህ የሚፈርሰው የማይፈርሰውን በለበሰ ጊዜ፣ የሚሞተውም የማሞተውን በለበሰ ጊዜ፣ “ሞት በመሸነፍ ተዋጠ” ተብሎ የተጻፈው ያን ጊዜ ይፈጸማል፡፡ ሞት ሆይ እንግዲህ መውጊያህ ወዴት አለ? መቃብር ሆይ አሸናፊነትህ ወዴት አለ? የሞት መውጊያ ኃጢአት ናት፣ የኃጢአትም ኃይልዋ ኦሪት ናት፡፡” (፩ቆሮ.፲፭፥፶፬-፶፮) በማለት ሞት በመስቀለ ክርስቶስ ድል መነሳቱን ገልጾልናል፡፡ ከዚያም ሞት በመስቀለ ክርስቶስ ድል በመሆኑ አዲስ ሕይወትን በትንሣኤው አገኘን፡፡ “በኢየሱስ ክርስቶስ ዘንድ አዲስ ፍጥረት መሆን ነው እንጂ መገዘር አይጠቅምም፣ አለመገዘርም ግዳጅ አይፈጽምም” እንዲል (ገላ.፮፥፲፭)፡፡

በሌላ አገላለጽ “አሮጌው ሰውነታችን” በሞትና በኃጢአት ከእግዚአብሔር የተለየ ሆነ፡፡ አዳም ሲበድል የሰብእና ባሕርዪ በሞላ በሞት ተበከለ፡፡ የመጀመሪያዎቹ ወላጆቻችን የእግዚአብሔር ሕግና ትእዛዝ በመተላለፍ እነርሱንም ሆነ ልጆቻቸውን ለሞት አሳልፈው ሰጡ፡፡ በመሆኑም ሁላችን ሞተን ነበር፤ ኃጢአትን በመፈጸምም የምንሞት ሆንን፡፡ “የኃጢአት ደመወዝ ሞት ነውና፤ የእግዚአብሔር የጸጋ ስጦታ ግን በክርስቶስ ኢየሱስ በጌታችን የዘለዓለም ሕይወት ነው” እንዲል፡፡(ሮሜ.፮፥፳፫)፡፡

ስለዚህ ለዚህ ጥፋት ዋናው መፍትሔ ሞትን ማጥፋት ነበር፡፡ ሞትን ማጥፋት ደግሞ ለፍጥረታት የሚቻል አይደለም፡፡ ቅዱስ አቡሊዲስ ዘሮም “ሙሴም ሞትን ያጠፋ ዘንድ አልቻለም፤ እርሱንም ይዞ ገዛው እንጂ፡፡ ከእርሱም በኋላ የተነሡ ነቢያትንም ሁሉ ሞት ገዛቸው እንጂ፡፡ ክርስቶስ ግን በቸርነቱ ለሁሉ ሕይወትን ሰጠ” ብሏል፡፡ ሞት ከጠፋ፣ ሰው የማይሞት ከመሆኑም ባለፈ የሞት መንገድ ከሆነው ከኃጢአትም ነጻ መውጣት ይችላል፡፡ በክርስቶስ ሕያው የሆነ ሰው ኃጢአትን አይሠራም፤ በሥጋ ቢሞትም ፈርሶ በስብሶ አይቀርም፤  በትንሣኤ ዘጉባኤ ይነሣል፡፡ ሰው የማይሞት ከሆነ ከእግዚአብሔር ባሕርይ በጸጋ ለመሳተፍ (ሱታፌ አምላክ) የሚቻለው ይሆናል፡፡ በመሆኑም በሞቱ ሞትን ለማጥፋት “የሰውን ልጅ ሊያገለግል፣ ነፍሱንም ለብዙዎች ቤዛ ሊሰጥ” በፈቃዱ ወደ መስቀሉ ሔደ፡፡ (ማቴ.፳፥፳፰፤ማር.፲፥፵፭)፡፡ እንዲል በበደሉ ምክንያት ስለጠፋው የሰው ልጅ ሲል የማይሞተው ሞተ፤ በዓለም ላይ ሠልጥኖ የነበረውንም ባለሥልጣን ሻረ፤ ነጻነቱን አጥቶ በጽኑ ግዞት የነበረው የሰው ልጅ የአጣውን ነጻነት ተጎናጸፈ፡፡

ከኃጢአት ብቻ በቀር እንደኛ ሰው ሆኗልና ቅድስት ነፍሱን ከቅዱስ ሥጋው በፈቃዱ ለየ፣ ማለት በሥጋ ሞተ፤ ከሙታንም ተለይቶ ተነሣ፡፡ በእውነትም መለኮት በሥጋ ሞቶ ሞትን ድል አድርጎ ተነሣ፡፡ “ምትሐት ያይደለ በእውነት ተራበ፣ ተጠማ እንጂ፡፡ ዳግመኛም ከኃጥአን ከመጸብሓን ጋር በላ፣ ጠጣ፤ ራሱን አሳልፎ ለመስቀል ሰጠ፤ እጁን እግሩን ተቸነከረ፤ ጎኑን በጦር ተወጋ፤ ከእርሱም ቅዱስ ምሥጢር የተገለጠበት ደምና ውኃ ፈሰሰ /ወጣ/” በማለት ታላቁ ቅዱስ ባስልዮስ ዘቂሣርያ ተናገረ፡፡ የእኛን በደል ሳይሠራ በእኛ ላይ ሊደርስ የሚገባውን ሁሉ ተቀበለ፡፡

ይህ ሁሉ መከራ የደረሰበት ግን ሥጋን ተዋሕዶ ነው፡፡ በመለኮቱ እንዲህ ሆነ እንዳንል አበው ያስጠነቅቃሉ፡፡ ታላቁ ቅዱስ ጎርጎርዮስ ይህንን ሲያስተምር “እጆቹን፣ እግሮቹን በተቸነከረባቸው ችንካሮች መወጋቱንም እናምናለን፡፡ ነቢዩ ኢሳይያስ እርሱ ደዌያችንን ወሰደ ሕማማችንንም ተሸከመ፤ እኛን ለማዳን ኃጢአታችንንም ይቅር ለማለት መከራ ተቀበለ እንዳለ፡ በባሕርዩ ሕማም የሌለበት ሲሆን በሥጋ የታመመ ነው፤ በእርሱ ከመከራ ሥጋ ከመከራ ነፍስ ድነናል አለ፡፡ መለኮት ሥጋን ተዋሕዶ በተገረፈና በተቸነከረም ጊዜ በመከራው ሁሉ መለኮትን ሕማም ተሰማው የሚል ሰው ቢኖር የተለየ የተወገዘ ይሁን” ብሎ ገልጧል፡፡ አምላክ በባሕርዩ የማይራብ፣የማይጠማ፣ የማይደክም፣የማይታመም፣ የማይሞት ነው፡፡ ነገር ግን  በሥጋ ተራበ፤ ተጠማ፤ ተሰደደ፤ ደከመ፤ ታመመ፤ ሞተ፡፡ በዚህም አስተምህሮ ጸንቶ መኖር ያስፈልጋል፡፡

ይህ ማለት ግን መለኮቱን ከትስብእቱ መለየት እንዳልሆነ ማስተዋል ተገቢ ነው፡፡ ቅዱስ አዮክንድዮስ ዘሮም “በመስቀል በሥጋ ተሰቅሎ ሳለ ለመለኮት ከሥጋ መለየት የለበትም፡፡ አንዲት ሰዓትም ቢሆን የዐይን ጥቅሻ ያህል ስንኳ ቢሆንም መለኮት ከትስብእት አልተለየም፤ በመቃብር ውስጥ ሳለም መለኮት ከትስብእት አልተለየም” ያለው ይህንን በደንብ እንገነዘብ ዘንድ ነው፡፡

ቅዱስ ዲዮናስዮስ ዘአንጾኪያ ይህንንም በጥንቃቄ ሲያስረዳ “እርሱ መቼም መች ከመለኮቱ ሳይለይ የሰውነትን ሥራ ሁሉ ገንዘቡ አደረገ፡፡ ይኸውም መራብ፣ መጠማት፣ መንገድ በመሔድ መድከም፣ በመስቀል ላይ መሰቀል፤ በብረት ችንካር መቸንከር ነው፡፡ በሰውነቱ መቼም መች ሰው ነው፤ በአምላክነቱ ሰውን የፈጠረ ነው፤ ግን ከማይከፈል ተዋሕዶ በኋላ መከፈል የለበትም፡፡ ሰው እንደ መሆኑ ስለ እኛ የታመመውና የሞተው እርሱ ነው፡፡ በመለኮቱ ግን መቼም መች አይታመምም፤ አይሞትም፤ ሕማምንና ሞትንም አይቀበልም፡፡ በሞቱ ሞትን ያጠፋው እርሱ ነው፡፡ ሲኦልንም የበዘበዘው እርሱ ነው” ብሏል፡፡ ይህ ሁሉ የሆነው ማለትም በሥጋ የታመመ፣ የሞተ፣ ነፍሱም ከሥጋው በተለየ ጊዜ ሥጋውን ገንዘው የቀበሩት እኛን ከሲኦል ለማዳን ወደ ጥንተ ክብራችን ልጅነት፣ ወደ ጥንተ ቦታችን ገነት ለማስገባት እንደሆነ ልብ ልንል ይገባል፡፡

ነገር ግን ስለ ድል መንሣቱ ሌላ የምንናገረውም ምሥጢር አለ፤ በሞት ላይ ሥልጣን የነበረውን ዲያብሎስን ደምስሶታልና፡፡ እግዚአብሔር ሰው የሆነውና የሚያሳፍር የመስቀልን ሞት ሳይቀር የሞተው ለዚሁ ነው፡፡ “መልአከ ሞትን በሞቱ ይሽረው ዘንድ ይኸውም ሰይጣን ነው” (ዕብ.፪፥፲፬)፡፡ በማለት ሐዋርያው እንደተናገረ ጥንተ ጠላት ዲያብሎስ ተሻረ፡፡ “ከሲኦል እጅ እታደጋቸዋለሁ፥ ከሞትም እቤዣቸዋለሁ ሞት ሆይ፥ መውጊያህ ወዴት አለ? ሲኦል ሆይ ድል መንሣትህ  ወዴት አለ? ደስታህ ከዓይኖችህ ተሰወረች።” (ሆሴ.፲፫፤፲፬) በማለት ነቢዩ ሆሴዕ እንደተነበየው፡፡

ጌታችን ሞትን በማጥፋት የዲያብሎስን ሥልጣን አስወገደበት፡፡ የታሠሩትን ነጻ ለማውጣት ራሱን ለሕማምና ለለሞት አሳልፎ ሰጠ፡፡ “ቅዱስ” እና “ፍጹም” በመሆን እግዚአብሔርን እንድንመስለው ጸጋ ተሰጥቶናል፡፡ ዲያብሎስ ሊሳለቅብንና ሊፈትነን ዘወትር እረፍት ባይኖረውም አዛዣችን መሆን ግን አይችልም፡፡ ለኃጢአት መንበርከክ፣ ለኃጢአት ተገዢ መሆን አብቅቷል፡፡ ግብጻዊው ቅዱስ መቃርዮስም “የመድኃኒታችን (የአዳኛችን) ንጽሕት ፈቃድ ከፍትወታትና ከኃጢአት ነጻ አውጥታናለች” ብሏል፡፡

በክርስቶስ የተፈጸመ ዕርቅ

የሥግው ቃል ክርስቶስ ሰው የመሆኑ ውጤት የእግዚአብሔርና የሰው ዕርቅ ነው፡፡ ነባቤ መለኮት ቅዱስ ጎርጎርዮስ ይህንን ሲያስረዳ “እግዚአብሔር ጨካኙን ገዢ ድል በመንሣት እኛን ነጻ አውጥቶ በልጁ በኩል ከራሱ ጋር አስታረቀን” ብሏል፡፡ በኃጢአት ምክንያት ሰዎች የእግዚአብሔር ጠላት ሆኑ፤ በሥርየተ ኃጢአትና ይቅርታን በማግኘት ወይም በክርስቶስ ቤዛነት ግን ወዳጆቹ ከመሆንም ባለፈ ልጆቹ ሆኑ፡፡

ፍጹም ሰው ፍጹም አምላክ በመሆን በሰውና በእግዚአብሔር መካከል መካከለኛ የሆነ እርሱ ሰላምን አወረደ፡፡ “ሁሉንም በእርሱ ይቅር ይለው ዘንድ በመስቀሉ ባፈሰሰው ደም በምድርና በሰማያት ላሉ ሰላምን አደረገ፡፡ እናንተንም ቀድሞ በሐሳባችሁና በክፉ ሥራችሁ ከእግዚአብሔር የተለያችሁና ጠላቶች ነበራችሁ፡፡ አሁን ግን በፊቱ ለመቆም የተመረጣችሁና ንጹሓን፣ ቅዱሳንም ያደርጋችሁ ዘንድ፣ በእርሱም ፊት ያቀርባችሁ ዘንድ በሥጋው ሰውነት በሞቱ ይቅር አላችሁ።” (ቆላ.፩፥፳-፳፪) በማለት በሰውና በእግዚአብሔር መካከል ዕርቅ መፈጸሙን ይነግረናል፡፡ ይህ ሲባል በሰው በደል ምክንያት ለሰው ልጅ የተፈጠሩ ፍጥረታት ከሰው ጋር ተጣልተውና ተለያይተው ነበር፡፡ በክርስቶስ ሰው መሆንም በዋናነት በነፍስና በሥጋ፣ በሰውና በመላእክት፣ በሰውና በእግዚአብሔር መካከል የነበረው የጥል ግድግዳ ፈርሶ ለሁሉም ሰላምን አደረገ፡፡

ቅዱስ ጎርጎርዮስ ዘኑሲስ በምን ዓይነት መሥዋዕት እንደ ታረቀን ሲገልጽ “የሚሠዋ በግ እርሱ ነው፤ የሚሠዋ ካህን እርሱ ነው፡፡ ከባሕርይ አባቱ ከአብ፣ ከባሕርይ ሕይወቱ ከመንፈስ ቅዱስ ጋርም መሥዋዕት የሚቀበል እርሱ ነው፡፡ በፈቃዱ መከራን በሥጋው የተቀበለ፣ መከራንም ሁሉ የታገሰ እርሱ ነው፡፡ እንደ በግ ሊሠዋ መጣ፤ በግ በሚሸልተው ሰው ፊት እንዳይናገር አልተናገረም፤ በአንደበቱ ሐሰት አልተገኘበትም” በማለት እንዲሁ ወዶንና ሁሉንም መንገድ እርሱ ተጉዞ እንደ ታረቀን አስተምሯል፡፡ እርሱ ስለ እኛ ሞቶ፣ ሞትንም ድል አድርጎ በመነሣቱ ለኃጢአታችን ካሣ ተከፈለልን፤ ወይም ይቅር ተባልን፣ ዓለም በደሙ ነጻች፣ ዘለዓለማዊነት ተሰጠን፣ ቤተ ክርስቲያን በመንፈስ ቅዱስ ምሪት ተመሠረተች፡፡ በክርስቶስ ተቤዥተው በመንፈስ ቅዱስ የተቀደሱት ፍጥረታት ዘወትር ለእግዚአብሔር የምስጋናን መሥዋዕት የሚያቀርቡና የመሥዋዕታቸውንና የአምልኮአቸውን ዋጋ የሚያገኙ ሆኑ፡፡

ክርስቶስ በመስቀል ላይ ያደረገልንን እናውቀዋለን፤ በደሙ ተቤዥቶናልና፡፡ ነገር ግን ቅዱስ ጳውሎስ “ስለ ኃጢአታችን  የተሰቀለውን፣ ሊያስነሣንና ሊያጸድቀን የተነሣውን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ከሙታን ተለይቶ በአስነሣው ስለምናምን ስለ እኟም ነው እንጂ” ብሎ ገለጸው፡፡ (ሮሜ.፬፥፳፭)፡፡ “ሊያስነሣንና ሊያጸድቀን የተነሣውን” ሲል ምን ማለቱ ነው? እርሱ ባይሞትልንና ስለ ብዙዎች ለኃጢአት ይቅርታ የሚፈስ የአዲስ ኪዳን ደሙን ባያፈስልን ኖሮ አሁንም ድረስ በዲያብሎስ ሥር ተገዢዎች እንሆን ነበር፡፡ (ማቴ.፳፮፥፳፰)፡፡ እርሱ በተዋሐደው ሥጋ ሞቶ ተነሣ፤ ሞትንም ድል አደረገ፡፡ ይህ ባይሆን ኖሮ ግን ጽድቅ አይኖርም፤ ዕርቅ አይኖርም፤ ቅድስና አይኖርም፡፡ ሁሉም የኖሩት በሞቱና በትንሣኤው መሠረትነት ላይ ነው፡፡ እርሱ ሰው ሆኖ ወደዚህ ዓለም ባይመጣና ልጅነትን ባይመልስልን በሞቱ ትንሣኤያችንን ባያውጅልን ኖሮ የአካለ ክርስቶስ ብልቶች አንሆንም፤ ድኅነትም የለም፡፡ “አካልም አንድ እንደ ሆነ ብዙም ብልቶች እንዳሉበት ነገር ግን የአካል ብልቶች ሁሉ ብዙዎች ሳሉ አንድ አካል እንደ ሆኑ፥ ክርስቶስ ደግሞ እንዲሁ ነው፤ … እኛ ሁላችን በአንድ መንፈስ አንድ አካል እንድንሆን ተጠምቀናልና።” (፩ቆሮ.፲፪፥፲፪-፲፫) እንዲል፡፡ በጥምቀት አንድ ስለመሆናችንም ሲገልጽ “ከክርስቶስ ጋር አንድ ትሆኑ ዘንድ የተጠመቃችሁ ሁሉ ክርስቶስን ለብሳችኋል” ተብለናል፡፡ (ገላ.፫፥፳፯)፡፡

እኛ የክርስቶስ ነን፤ የእርሱ አካል ብልቶች ነን፡፡ የምንጠመቀው መጠመቅም ከእርሱ ሞትና ትንሣኤ የሚያሳትፍ ነው፡፡ (ሮሜ፮፥፫-፲፩)፡፡ በዚህም ምክንያት በጥምቀት ሦስት ጊዜ ብቅ ጥልቅ ብለን ረቂቅ ልብሰ ብርሃን ለብሰን እንወጣለን፡፡ (ለሞቱ ምሳሌ እንዲሆን) ከጠለቅንበት ውኃ በመውጣት ቀና እንላለን፤ ይህም በእግዚአብሔር የሚኖረንን አዲስ ሕይወት የሚጠቁም ነው፡፡

መጽደቅ ማለት ከወልደ እግዚአብሔር ጋር መታረቅ፣ ከዚያም የእግዚአብሔርን ልጅነት ማግኘት ነው፡፡ “አባ አባት ብለን የምንጮህበትን የልጅነት መንፈስ ተቀበላችሁ እንጂ እንደገና ለፍርሃት የባርነትን መንፈስ አልተቀበላችሁምና። የእግዚአብሔር ልጆች መሆናችንን ያ መንፈስ ራሱ ከመንፈሳችን ጋር ይመሰክራል። ልጆች ከሆንን ወራሾች ደግሞ ነን፤ ማለት የእግዚአብሔር ወራሾች ነን፥ አብረንም ደግሞ እንድንከብር አብረን መከራ ብንቀበል ከክርስቶስ ጋር አብረን ወራሾች ነን።” (ሮሜ.፰፥፲፭-፲፯)፡፡ ክርስቶስ ሰው ሆኖ  የተወሰደብንን ክብር ልጅነት ሰጠን፣ ወደ ጥንተ ርስታችን ወደ ገነት መለሰን፤ ይህ ሁሉ የሆነውና የታየው በሞቱና በትንሣኤው ነውና የክርስቶስን ትንሣኤ የትንሣኤያችን ማረጋገጫ ማኅተም እንለዋለን፡፡

ይቆየን፡፡

0 replies

Leave a Reply

Want to join the discussion?
Feel free to contribute!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *