“የእግዚአብሔር ልጅ ተገለጠ” (፩ኛዮሐ. ፫፥፰)
ክፍል ሦስት
በመ/ር ኃይለ ሚካኤል ብርሃኑ
ቀደም ብለን በክፍል ሁለት በተመለከትነው ዳሰሳችን ላይ የሰይጣንን ሥራ ያፈርስ ዘንድ የእግዚአብሔር ልጅ ተገለጠ የሚለውን ተመልክተን የሰይጣን ሥራ ምን እንደሆነና ሰይጣን በባሕርዩ የሚታወቅባቸው የክፋት ሥራዎቹ ምን ምን እንደሆኑ ተመልክተናል፡፡ በዚህ በክፍል ሦስት ደግሞ ቀጣዩን እነሆ ብለናል፡፡
አዳምን ወደ ቀደመ ክብሩ ይመልሰው ዘንድ
አምላካችን ልዑል እግዚአብሔር ሰው የሆነበት ዋናው ዓላማ አዳምን ወደ ቀደመ ክብሩ ይመልሰው ዘንድ ነው፡፡ አባታችን አዳም የቀድሞ ክብሩ የእግዚአብሔር ልጅነት ሲሆን ልጅነቱን በበደል ምክንያት በማጣቱ ኃጢአት ሰልጥኖበት ነበር፡፡ በዚህም ምክንያት በሞተ ሥጋ ሞተ ነፍስ በርደተ መቃብር ርደተ ሲኦል ተፈረደበት፡፡ እግዚአብሔር ቸርና መሓሪ ነውና ከዚህ ኩነኔ ያድነው ዘንድ ከሦስቱ አካል አንዱ ወልድ በተለየ አካሉ ሰው ሆነ፡፡ በዚህም የማይታየው ታየ፣ የማይዳሰሰው ተዳሰሰ የማይወሰነው ባጭር ቁመት በጠባብ ደረት ተወሰነ፣ ልዑል የሆነው አምላክ ከክብሩ ሳይጎድል በትሕትና በሥጋ ተገለጠ፡፡
ለዚህም ነው ሐዋርያው ቅዱስ ዮሐንስ በመልእክቱ “የእግዚአብሔር ልጅ ተገለጠ” በማለት የመሰከረለት፡፡ መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በሥጋ ማርያም ተገልጧልና፡፡ እርሱ የእግዚአብሔር ልጅ እግዚአብሔር ሲሆን ከዓለም (ከዘመን በፊት) አስቀድሞ በጌትነቱ የነበረ፣ከዘመን በኋላ ባሕርየ ሰብእን ገንዘቡ አድርጎ በሥጋ የተገለጠ (ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም የተወለደ) ዓለሙን ለማዳን ነው፡፡ ለዚህም ነው ሊቁ ቅዱስ ኤፍሬም በውዳሴ ማርያም ድርሰቱ፡-
“የነበረው የሚኖረው የመጣው ዳግመኛ የሚመጣውም ቃል ኢየሱስ ክርስቶስ ያለመለወጥ ፍጹም ሰው ሆነ አንዱ ወልድ በሥራው ሁሉ አልተለየም የእግዚአብሔር ቃል መለኮት አንድ ነው እንጂ”(ውዳሴ ማርያም ዘሰኑይ) በማለት ቅድምናውን ከገለጠ በኋላ የዓለሙን ሁሉ ኃጢአት ይቅር ይልዘንድ ሰው መሆኑን መሰከረ፡፡
ይህም ሊቅ በሌላው ክፍል እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምን እያመሰገነ ምሥጢረ ሥጋዌውን በመመስከር ሰውን ያድን ዘንድ መወለዱን(በሥጋ መገለጡን) ሲያስረዳ፡- “የተባረክሽና ንጽሕት የሆንሽ አዳራሽ ሆይ እነሆ ጌታ የፈጠረውን ዓለም ሁሉ በይቅርታው ብዛት ያድን ዘንድ ካንቺ ወጣ (ተወለደ) ፈጽመን እናመስግነው፡፡ ቸርና ሰውን ወዳጅ ነውና”(ውዳሴ ማርያም ዘቀዳሚት)በማለት ቅዱስ ኤፍሬም እንደ መሰከረው አዳም የልጅነት ክብሩን ያጣው በኃጢአት ነውና በይቅርታው ብዛት የሰውን የቀድሞ በደል ይቅር ብሎ በአዲስ ተፈጥሮ ዳግም ከማይጠፋ ዘር በእግዚአብሔር ቃል ተወልዶ የእግዚአብሔርን ልጅነት የሰው ልጅ ያገኝ ዘንድ አምላክ በሥጋ ተገለጠ፡፡
ኃጢአት ሰውን ከክብሩ ታጎድለዋለች ከእግዚአብሔርም ትለየዋለች፤ ሰው ደግሞ ከእግዚአብሔር ከተለየ ምንም አይነት ክብር የለውም፡፡ ሕይወትንም ያጣል፡፡ ሰው እግዚአብሔር በጸጋ የሰጠውን ክብር በኃጢአት ያጣል፡፡ ከክብር ወደ ጉስቁልና፣ ከነጻነት ወደ መገዛት፣ከልጅነት ወደ ባርነት፣ከከፍታ ወደ ተዋረደ ማንነት፣ ከሕይወት ወደ ሞት ይጓዛል፡፡ ይህም ሰው ከእግዚአብሔር ተለይቶ በሕይወትና በክብር መኖር የማይችል ስለሆነ ነው፡፡ “ሞታ ለነፍስ ርኂቅ እም እግዚአብሔር፤ የነፍስ ሞቷ ከእግዚአብሔር መለየት ነው” እንዲል፡፡ አዳም አትብላ የተባለውን ዕፀ በለስን በበላ ሰዓት ወዲያውኑ በሥጋ አልሞተም በመንፈስ ግን ሞተ፡፡ ለዚህም ነው ሞት ከእግዚአብሔር መለየት እንደሆነ ቅዱሳት መጻሕፍት የሚያስረዱት፡፡ ለአዳም የተሰጠውን ትእዛዝ አለመጠበቅን ስንመለከትና ውጤቱን ስናይ የምናስተውለው ሞት የኃጢአት ውጤት መሆኑን ነው፡፡
“እግዚአብሔር አምላክም አዳምን እንዲህ ብሎ አዘዘው በገነት ካለው ዛፍ ሁሉ ብላ ነገር ግን መልካምንና ክፉን ከሚያሳየውና ከሚያስታውቀው ዛፍ አትብላ ከእርሱ በበላህ ቀን ሞትን ትሞታለህ”(ዘፍ.፪፥፲፮)፡፡ አዳም ግን ከእግዚአብሔር የተማረውን ትምህርት (የታዘዘውን) ወደ ጎን በመተው የሰይጣንን ምክር በተቀበለች በሔዋን አማካኝነት ትእዛዘ እግዚአብሔርን በመተላለፍ ዕፀ በለስን በላ፡፡ በዚህን ጊዜ “ከእርሱ በበላህ ቀን ሞትን ትሞታለህ” እንደተባለው በሥጋም በነፍስም ሞተ፤ ክብሩን አጣ፣ጎሰቆለ፣ከጸጋ እግዚአብሔር ተራቆተ፡፡
አዳም ከጸጋ እግዚአብሔር ስለተራቆተ በነፍስ ብቻ ሳይሆን በሥጋውም መፍረስና ወደ መሬት መመለስ ዕጣ ፈንታው ሆነ፡፡ በሞተ ሥጋ ሞተ ነፍስ በርደተ መቃብር ርደተ ሲኦል ተፈረደበት፡፡ ከዚህ ፍርድ ነጻ ያወጣው ዘንድ ወደ ቀደመ ክብሩም ይመልሰው ዘንድ አምላክ ሰው ሆነ፡፡
ለዚህም ነው ቅዱስ ኤፍሬም በድርሰቱ “ጌታ ልቡ ያዘነና የተከዘ አዳምን ነጻ ያወጣውና ወደ ቀድሞ ቦታው ይመልሰው ዘንድ ወደደ”(ውዳሴ ማርያም ዘሰኑይ)፡፡ የአዳምና የሔዋን የልጆቻቸውም የልቡናቸው ሐዘን ስለ ሚበላ እንጀራና ስለ ሚጠጣ ውሃ ወይም ስለ ሚለብሱት ልብስና ስለሚያድሩበት ቤት ሳሆን እግዚአብሔርን ያህል ጌታ ገነትን ታህል ቦታ አጥቶ መኖር እጅግ የከፋ የሞት ሞት ስለ ሆነ ነው፡፡
እግዚአብሔር አምላክም ቸርነቱ ብዙ ምህረቱ ሰፊ ስለሆነ የአባቶቻችንን የልባቸውን መጸጸት ተመልክቶ ሰውን ከሞት ወደ ሕይወት ከጨለማ ወደ ብርሃን ከባርነት ወደ ነጻነት ይመልሰው ዘንድ በሥጋ ማርያም ተገለጠ፡፡ ሊቁ ቅዱስ ኤፍሬም የምሥጢረ ሥጋዌን ነገር ባብራራበት ክፍል ጌታችን መድኃታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም የተወለደበትን ምክንያት ሲጠቅስ “ የነቢያት ሀገራቸው ቤተ ልሔም ሆይ ደስ በልሽ ሁለተኛው አዳም ክርስቶስ በአንቺ ዘንድ ተወልዷልና፡፡ የቀድሞውን ሰው አዳምን ከምድር(ከሲዖል) ወደ ገነት ይመልሰው ዘንድ፤አዳም ሆይ መሬት ነበርክና ወደ መሬት ትመለሳለህ ብሎ የፈረደበትንም የሞት ፍርድ ያጠፋለት ዘንድ ብዙ ኃጢአት ባለችበት የእግዚአብሔር ጸጋ ትበዛለች”(ውዳሴ ማርያም ዘሰኑይ) በማለት ያስረዳል፡፡
ቅዱስ ዮሐንስ በመልእክቱ “የእግዚአብሔር ልጅ ተገለጠ” በማለት የመሰከረው የማይታየው መታየቱ የማይወሰነው መወሰኑ አምላክ በባሕርዩ የማይመረመር፣የማይወሰን፣የማይሞት፣የማይታመም ሲሆን የሥጋን ባሕርይ ባሕርዩ አድርጎ የሥጋን ገንዘብ ገንዘቡ በማድረጉ ነው፡፡ ሰውንም ያዳነውና ወደ ቀድሞ ክብሩ የመለሰው ፍጹም አምላክ ሲሆን ፍጹም ሰው ሆኖ ነው፡፤ መገለጡም በሥጋ ማርያም ነው፡፡ ሰው ሆኖ ያዳነን የተዋረድነውንና የተናቅነውን ወደ ቀደመው ክብራችን የመለሰው አምላካችን ልዑል እግዚአብሔር ምስጋና ይድረሰው፡፡ ይቆየን…
Leave a Reply
Want to join the discussion?Feel free to contribute!