የነቢያት ሀገራቸው ቤተ ልሔም ደስ ይበልሽ
ክፍል አንድ
ዲ/ን ዐቢይ ሙሉቀን
የቃሉ ተናጋሪ የሶርያው ኤጲስ ቆጶስ ቅዱስ ኤፍሬም ነው፡፡ በአበው የተመሰለው ምሳሌ፣ በነቢያት የተነገረው ትንቢት ፍጻሜውን ያገኘው በድንግል ማርያም እና ለአዳም የገባውን ቃል ኪዳንና ትንቢተ ነቢያትን ሊፈጽም ወደዚህ ዓለም በመጣው በጌታችን በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ ስለዚህ የትንቢተ ነቢያት መፈጸሚያ የሆነችውን ድንግል ማርያምን ባመሰገነበት ድርሰቱ ተናግሮታል፡፡
ቅዱስ ኤፍሬም በሰኞ ውዳሴ ማርያም ድንግል ማርያምን በቀጥታ ስሟን አልጠራም፡፡ የድርሰት ትኩረቱም መከራ አዳምና ድኅነተ አዳም (ነገረ ድኅነት) ላይ ነበር፡፡ በመሆኑም ይህ ነገረ ድኅነት በደጋግ አባቶችም፣ በነቢያትም፣ በብዙ ቅዱሳንም እንዳልተፈጸመ በድንግል ማርያም ብቻ እንደተፈጸመ ይገልጻል፡፡ እንዲያውም አዳምንና ሔዋንን አስከትላ መጥታ ነበርና ቢያያቸው አነሣቸው፡፡ እንዲህ በማለት “ጌታ ልቡ ያዘነና የተከዘ አዳምን ነጻ ያወጣውና ወደ ቀድሞ ክብሩ ይመልሰው ዘንድ ወደደ፡፡” በማለት፤ አዳምን እንዳነሣ ሁሉ “ሠምረ ልቡ ኀበ ፍቅረ ሰብእ ወአግዓዛ፤ ሰውን ወደደና ነጻ አደረጋት” በማለት ደግሞ ሔዋንን ጠቀሰ፡፡
ሊቁ ቅዱስ ኤፍሬም አመስግነኝ ባለችው ጊዜ እሷን ከማመስገን አስቀድሞ ልጇ አዳምንና ሔዋንን ነጻ እንዳወጣ ይህንም ነጻ የማውጣት ሥራ ለመሥራት በራሱ ፈቃድ እንደሆነ እንዲህ ያለው ድንቅ ምሥጢር የተፈጸመባት ምሥጢራዊት ሀገር ደግሞ ድንግል ማርያም እንደሆነች ያስረዳል፡፡ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርቶስ አዳምንና ሔዋንን ነጻ ለማውጣት በወደደ ጊዜ ነቢያት በመሰሉት ምሳሌ፣ በተናገሩት ትንቢት፣ ስማቸው የተጠቀሰውን ቅዱስ ኤፍሬም እያነሣሣ ሲያመሰግን ቤተ ልሔምንም አነሣት፡፡
ይህች ቤተ ልሔም ሙሴ፣ ኢያሱና ካሌብን ምድረ ርስትን ሰልላችሁ ኑ ብሎ በላካቸው ጊዜ ቤተ ልሔምን የእርሱ እንድትሆን ካሌብ ኢያሱን ለምኖት ነበር፡፡ ምድረ ርስትን ከወረሱ በኋላ ለካሌብ ሆናለች፡፡ በዚህ ጊዜ ከብታ የምትባል ሚስት አግብቶ በሚስቱ ስም ከብታ ተብላለች፡፡ ከብታ ልጅ ሳትወልድለት ቀረች፡፡ ኤፍራታ የምትባል ሚስት አግብቶ በሚስቱ ስም ኤፍራታ ብሎ አስጠርቷታል፡፡ ይህች ኤፍራታ ልጅ ወለደችለት፡፡ ሀብታቸው በዝቶላቸው ነበርና ልሔም አለው፡፡ ልሔም ማለት፡- ኅብስት፣ እንጀራ፣ ሀብት ማለት ነው፡፡ ልጁ አድጎ ፍርድ የሚጠነቅቅ፣ አስተዋይና ለተራበ የሚያበላ አዛኝ ሆነ፡፡ በእርሱም ቤተ ልሔም ተብላ ተጠርታለች፡፡ ይህም ስም ጸንቶላት ኖሯል፡፡
ከብታ፡- ከብታ ማለት ቤተ ስብሐት፤ የምስጋና ቤት ማለት ነው፡፡ ቤት የእመቤታችን፣ ስብሐት የጌታ ምሳሌ ነው፡፡ ምስጋና የባሕርዩ የሆነ አምላክ ዘጠኝ ወር ከአምስት ቀን ማሕፀኗን ዙፋን አድርጎ ተወልዷና የምስጋና ቤት ተባለች፡፡ ጌታን ፀንሳ ሳለ መላእክት በማሕፀኗ ያለውን ፈጣሪ ያመሰግኑት ነበርና የምስጋና ቤት ተባለች፡፡ እሷም ገና በሦስት ዓመቷ ቤተ መቅደስ ገብታ የመላእክትን ምስጋና ገንዘብ አድርጋ ዐሥራ ሁለት ዓመት ከመላእክት ጋር ፈጣሪዋን እያመሰገነች ኖራለችና የምስጋና ቤት ተብላለች፡፡ “ኦ መቅደስ ዘኮነ ባቲ እግዚአብሔር ካህነ፤ እግዚአብሔር ካህን ሆኖ ላገለገለባት መቅደስ አንክሮ ይገባል፡፡” (ሃ/አበው ፵፰፥፲፯) በማለት ሊቁ ኤራቅሊስ እንዳመሰገናት ሊቀ ካህናት ኢየሱስ ክርስቶስ ተገልጦባታልና የምስጋና ቤት ተብላለች፡፡
ሊቁ አባ ሕርያቆስም “ኦ ድንግል አኮ ወራዙት ስፉጣን ዘናዘዙኪ አላ መላእክተ ሰማይ ሐወጹኪ በከመ ተብህለ ካህናት ወሊቃነ ካህናት ወደሱኪ፤ ድንግል ሆይ የሚያታልሉ ጎልማሶች ያረጋጉሽ አይደለም፣ የሰማይ መላእክት ጎበኙሽ እንጂ፣ እንደተነገረ ካህናትና የካህናት አለቆች አመሰገኑሽ እንጂ፡፡” /ቅዳሴ ማርያም/ በማለት ምስጋና ያልተለያት፣ የምስጋና ቤት እንደሆነች አስረድቷል፡፡
ኤፍራታ፡- ኤፍራታ ማለት ጸዋሪተ ፍሬ፤ ፍሬን የተሸከምሽ ማለት ነው፡፡ ጸዋሪት የእመቤታችን ፍሬ የጌታ ምሳሌ መልካም ፍሬ ከመልካም እንጨት ይገኛል፡፡ ባለቤቱ መድኅነ ዓለም ኢየሱስ ክርስቶስ “መልካም ዛፍ ሁሉ መልካም ፍሬን ያፈራል፤ ክፉ ዛፍም ክፉ ፍሬን ያፈራል፡፡” (ማቴ ፯፥፲፯) በማለት እንዳስተማረን መልካም ፍሬ የሚገኘው ከመልካም ዛፍ ነው፡፡ በመሆኑም ንጽሕተ ንጹሓት፣ ቅድስተ ቅዱሳት ኅጥዕተ አምሳላት ድንግል ማርያም የሕይወት ፍሬን ተሸክማ ለዓለም አድላለች፡፡ ስለሆነም ኤፍራታ፣ ጸዋሪተ ፍሬ ተብላ ትጠራለች፡፡
“አብርሂ፣ አብርሂ ናዝሬት ሀገሩ ንጉሥኪ በጽሐ ዘምስለ ማርያም መጾሩ፤ አንቺ ናዝሬት ሀገሩ አብሪ፣ አብሪ ንጉሥሽ ክርስቶስ ከመጾሩ (ተሸካሚው) ማርያም ጋር ደርሷልና” በማለት የፍሬ ሕይወት ጌታ ዙፋን የተባለች ድንግል ማርያም መሆኗን አባ ጽጌ ድንግል ነግሮናል፡፡ “ይጸውር ድደ ወይነብር ጠፈረ አኃዜ ዓለም በእራኁ ኲሉ እኁዝ ውስተ እዴሁ፤ በሰማያት ተቀምጦ መሠረትን ይሸከማል፤ ዓለምን በመሐል እጁ የሚይዝ ሁሉ በእጁ ያለ” /ቅዳሴ ዲዮስቆሮስ/ የተባለለት ጌታ በአንዲት ብላቴና በድንግል ማርያም ማኅፀን ተወሰነ፡፡ እርሷም ጌታን ተሸከመችው ተባለ፡፡ ይህ ሁሉ ያስደነቀው ቅዱስ ያሬድም በድጓው “ሰማይ ወምድር ዘኢያገምሮ እፎ እንጋ ማኅፀነ ድንግል ጾሮ፤ ሰማይና ምድር የማይችለውን እንዴት የድንግል ማርያም ማኅፀን ቻለው” እያለ በአድናቆት ይነግረናል፡፡
እንዲሁም ሊቁ ቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅ በሃይማኖተ አበው “መኑ ርእየ ወመኑ ሰምዐ እስመ እግዚአብሔር ዘኢይትገመር ተገምረ በከርሠ ብእሲ ዘኢይጸውርዎ ሰማያት ኢያጽዐቆ ከርሣ ለድንግል አላ ተወልደ እምኔሃ እንዘ ኢይትዌለጥ መለኮቱ ወኢኮነ ዕሩቀ እመለኮቱ፤ የማይወሰን እግዚአብሔር በድንግል ማሕፀን እንደተወሰነ ማን አየ? ማን ሰማ? ሰማያት ለማይወስኑት እርሱ የድንግል ማሕፀን አልጠበበውም፣ ባሕርዩ ሳይለወጥ ከእርሷ ተወለደ እንጂ ከመለኮቱ የተለየ ዕሩቅ ብእሲ አይደለም፡፡” /ሃ.አበ.፷፮፥፭/ በማለት ማሕፀኗን ዙፋን አድርጎ ከሥጋዋ ሥጋ ከነፍሷ ነፍስ ነስቶ እንደ ተወለደ ዙፋኑ ማደሪያው እንደ ተባለች ያስረዳናል፡፡
ፍሬ የተባለው ጌታ ነው፣ ያውም የሕይወት ፍሬ፡፡ ሊቁ ቅዱስ ያሬድ በአንቀጸ ብርሃን ድርሰቱ እንዲህ ይለናል፡፡ “አንቲ ውእቱ ዕፅ ቡሩክ ዕፀ ሕይወት ወዕፀ መድኃኒት ህየንተ ዕፀ ሕይወት ዘውስተ ገነት ዘኮንኪ ዕፀ ሕይወት በዲበ ምድር ፍሬኪኒ ፍሬ ሕይወት ውእቱ ወዘበልዐ እምኔሁ ሕይወተ ዘለዓለም የሐዩ፤ አንቺ የተባረክሽ ዕፅ ነሽ፣ የሕይወትና የደኅንነት ዕፅ ነሽ፣ በገነት ውስጥ ባለው ዕፀ ሕይወት ፈንታ በዚህ ዓለም የሕይወት ዕፅ ሆንሽ፣ ፍሬሽም የሕይወት ፍሬ ነው፤ ከእርሱም የሚበላ ለዘለዓለም ይኖራል፡፡” እንዲል፡፡
ቤተ ልሔም፡- ቤተ ልሔም ማለት ቤተ ኅብስት ማለት ነው፡፡ ቤት የእመቤታችን፣ ኅብስት የጌታ ምሳሌ ነው፡፡ በቤት ብዙ ነገር ይገኛል፣ እርሷም ሁሉን ለሚችል ጌታ መገኛ ናትና፡፡ በቤት ውስጥ ከሚገኙት መካከል ምግብ አንዱ ነው፡፡ ድንግል ማርያምም የምግበ ሕይወት ጌታ መገኛ ናት፡፡ ሊቁ አባ ሕርያቆስ “ኦ ማርያም በእንተ ዝ ናፈቅረኪ ወናዐብየኪ እስመ ወለድኪ ለነ መብልዐ ጽድቅ ዘበአማን ወስቴ ሕይወት ዘበአማን፤ ማርያም ሆይ ስለዚህ እንወድሻለን፣ ከፍ ከፍም እናደርግሻለን፣ እውነተኛውን መብል፣ እውነተኛውን መጠጥ አስገኝተሽልናልና፡፡” በማለት በቅዳሴው ያመሰግናታል፡፡
ኅብስት የተባለ ጌታ ነው፡፡ “ከሰማይ የወረደ ኅብስት እኔ ነኝ፤ ከዚህ ኅብስት የሚበላ ለዘለዓለም ይኖራል፤ ስለ ዓለም ሕይወት የምሰጠው ይህ ኅብስት ሥጋዬ ነው፡፡” (ዮሐ.፮፥፶፩) በማለት ራሱ ባለቤቱ መድኅነ ዓለም ኢየሱስ ክርስቶስ በመዋዕለ ስብከቱ እንደነገረን፤ ኅብስት ያውም ሰማያዊ ኅብስት፣ ያውም ዘለዓለማዊ ሕይወትን የሚያድለው ኅብስት ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ ይህ ኅብስት ደግሞ ከድንግል ማርያም የነሣው ሥጋ ስለሆነ ድንግል ማርያም ቤተ ኅብስት ተብላለች፡፡ ሊቁ ቅዱስ ኤፍሬምም “አንቲ ውእቱ መሶበ ወርቅ ንጹሕ እንተ ውስቴታ መና ኅቡእ ኅብስት ዘወረደ እምሰማያት፤ የተሠወረ መና ያለብሽ ንጹሕ የወርቅ መሶብ አንቺ ነሽ፣ መናም ከሰማይ የወረደው ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡” (ውዳሴ ማርያም ዘእሑድ) በማለት እንደተረጎመልን የተሠወረ መና የተባለው ባሕርዩ የማይመረመር ኢየሱስ ክርስቶስ፣ መሶበ ወርቅ የተባለች ደግሞ ድንግል ማርያም ናት፡፡ ስለዚህ ለዚህ ለተሠወረው መና መገኛ ቤተ ኅብስት ድንግል ማርያም ናት፡፡
ይቆየን፡፡
Leave a Reply
Want to join the discussion?Feel free to contribute!