‹‹ሰላምን የሚሹ ሰላምን ያደርጋሉ››
ለሜሣ ጉተታ
ከእናንተ ጥበበኛና አስተዋይ ማን ነው? በመልካም አንዋዋሩ ሥራውን በጥበብ የዋህነት ያሳይ፡፡ ነገር ግን መራራ ቅንዓትና አድመኛነት በልባችሁ ቢኖርባችሁ አትመኩ፤ በእውነትም ላይ አትዋሹ፡፡ ይህ ጥበብ ከላይ የሚወርድ አይደለም ፤ ነገር ግን የምድር ነው ፤ የሥጋም ነው፤ የአጋንንነትም ነው ፤ቅንዓትና አድመኛነት ባሉበት ስፍራ በዚያ ሁከትና ክፉ ሥራ ሁሉ አሉና፡፡ ላይኛይቱ ጥበብ ግን በመጀመሪያ ንጽሕት ናት ፤ በኋላም ታራቂ ገር እሺ ባይ ምሕረትና በጎ ፍሬ የሞላባት ጥርጥርና ግብዝነት የሌለባት ናት፡፡ የጽድቅም ፍሬ ስላምን ለሚያደርጉት ሰዎች በሰላም ይዘራል፡፡ ያዕ 3፡ 13-18
ሰላም የመንፈስ ቅዱስ ፍሬ ነው፡፡ ሰላምን ለማግኘት እግዚአብሔርን መፍራት በሕጉና በትእዛዙ መሠረት መሔድ፣ ከክፋት ከተንኮል መራቅ በጎነትን መሥራት ያስፈልጋል፡፡ ሰላም በስብሰባ ፣ በሥልጠና፣ በውይይትና በሰላማዊ ሰልፍ የሚመጣ አይደለም፤ ሰላማዊ በመሆንና በጎነትን በመሥራት ክፋትን በመጠየፍ እንጂ፡፡ በእውነት ከልብ ሰላማዊ ሰው በመሆን የሚገኝ ነው ሰላም፡፡ መጽሐፍም “ሰላምን አጥብቀህ ተከተል፤ “ሰላምን እሻ ተከተላትም” (2ኛ ጢሞ 2፡22፣ መዝ 34፤14) ይለናል፡፡
ክርስቲያን የሰላም ሰው መሆን አለበት፡፡ ሰላምን አንድነትንና ፍቅርን ከሚያደፈርሱ ነገሮች ተግባርና ሐሳብም ጭምር መራቅ አለበት፡፡ ሁል ጊዜም ስለ ሰላም፣ ስለ ፍቅር፣ ስለአንድነት መለመን አለበት፡፡ ሰላምን ከሚያደፈርሱ ነገሮች ከመራቅ በተጨማሪም ሰዎችን መምከር፣ ማስተማር መገሰጽ አለበት፡፡ ክርስትና የሰላምና የፍቅር ሕይወት ነውና ፡፡ ይህን ለማድረግ ግን የግል ፍላጎትን መተው አለብን ፡፡ ዕብ 12፡14 ላይም “ከሰው ሁሉ ጋር ሰላምን ተከታተሉ፤ ትቀደሱም ዘንድ ፈልጉ፤ ያለ እርሱ ጌታን ሊያይ የሚችል የለምና“ መባሉም ለዚህ ነው ፡፡ ስለ ፍቅር፣ ስለ ሕዝብ፣ ስለ ወገን ሰላም የሚመኝ ሰው በቃሉ ሰላማዊ በልቡና በተግባሩ ግን ተቃራኒ ሆኖ መገኘት የለበትም፡፡ የአብዘኞች የዘመናችን ግለሰቦች ችግር ግን ይህ ነው ፡፡ በቃል እና በአፋቸው ሰላምን ይሰብኩሉ፤ ከመጋረጃ ጀርባ ያለው ተግባራቸው ግን እጅግ በጣም አሰከፊ እና አጸያፊም ነው፡፡ አብዘኞቻቸው ሰላምን በሚያደፈርስ ተግባር ውስጥ ናቸውና፡፡
ሰላም ለሰው ልጅ ሕይወት መሠረታዊ ጉዳይ ነው፡፡ ሰላም የሁሉም ነገር መሠረት ነው፡፡ ያለ ሰላም እንኳን ልማትን ማልማት፣ መማርና ሠርቶ መለወጥ ይቅርና ተኝቶ መነሳት፣ ወጥቶ መግባት እንኳን አይቻልም፡፡ ፈጣሪን ለማምለክ፣ ለመማር፣ ለማደግ ለመለወጥ፣ ቤተሰብን ለመመሥረት ሰላም ያስፈልጋል፡፡ ሰላም ከግል ሕይወትና ከቤተሰብ የሚጀምር የሕይወት መሠረት ነው፡፡ የሰው እድሜው በምድር እጅግ አጭር ነው፡፡ በዚህ አጭር የሕይወት ዘመን የተረጋጋ ሕይወትን በመኖር መልካም ሥራን ሠርቶ ማለፍ አለበት፤ ለዚህ ደግሞ ሰላም ያስፈልጋል፡፡ ሰላም ከሌለ የማይጎዳ የሕብረተሰብ ክፍል የለም ፡፡ ከጦርነት፤ ከጥል፤ ከሁከት የሚገኝ አንድም ነገር የለም ፡፡ ሰላም ስታጣ ሕይወት ይጠፋል፤ መረጋጋትም አይኖርም፡፡ መተማመን ይጠፋል፡፡ በመካከለችንም ጥርጣሬ ይሰፋል፡፡ በዚህ መሐል እርሰ በእርስ መተላለቅም ይመጣል፡፡
Leave a Reply
Want to join the discussion?Feel free to contribute!