‹‹ሁሉ በአግባቡ እና በሥርዓቱ ይሁን›› ፩ኛ ቆሮ.፲፬፥፵ (የመጨረሻ ክፍል)
በዲ/ን ታደለ ሲሳይ
ማኅበራዊ የመገናኛ ብዙኀንን ስንጠቀም መልካሙን ከክፉ መለየት፣ ከአስተምህሮአችን ጋር ከሚቃረነው መራቅ ይኖርብናል፡፡ ስለዚህ መንፈሳዊ እና ሃይማኖታዊ መልእክቶችን በማኅበራዊ የመረጃ መረቦች በምናስተላልፍበት ወቅት የሚከተሉትን ሥርዓታዊ አካሄዶች መከተል አለብን፡፡
- መሠረታዊ የቤተ ክርስቲያንን አስተምህሮ የማይጻረር እና ከትምህርተ ሃይማኖት እንከኖች የጸዳ ሊሆን ይገባል፡፡ ይኸውም የጌታችንና የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ የባህርይ አምላክነትን፤ የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያምን ወላዲተ አምላክነት ፤ የቅዱሳንን ምልጃ የማይጋፋ፣ የማይጻረር መሆን አለበት፡፡ የጥንቱ የአባቶቻችን አስተምህሮ ሳይበረዝ እና ሳይከለስ ለቀጣዩ ትውልድ ለማስተላለፍ እንዲያስችል በተማሩት ትምህርት መጽናት እና ሥርዓትን መጠበቅ አማራጭ የሌለው መፍትሔ ነው፡፡ በመሆኑም የምንጠቀመው የዘመናዊነት መገለጫ ሕገ እግዚአብሔርን የማያፋልስ መሆን አለበት፡፡
- በምንም ዓይነት መንገድ፣ ዘርን፣ ቋንቋን፣ የትውልድ ቦታን መሠረት ያላደረገ እና ዓለም እየጠፋችበት ያለውን ዘረኝነት የማያበረታታ መሆን አለበት፡፡ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ሁሉንም የሰው ዘር በእኩል የምትመለከት እና ከአድልዎ ነጻ የሆነች መንገድ ነው፡፡ አስተምህሮዋም የሰው ዘር ሁሉ እርስ በርሱ እንዲከባበር እና እንዲዋደድ ነው እንጂ እንዲለያይ አይደለም፡፡ ‹‹ወዳጆች ሆይ እግዚአብሔር እንዲህ አድርጎ ከወደደን እኛ ደግሞ እርስ በርሳችን ልንዋደድ ይገባናል›› እንዲል ከፍቅር ውጭ ጥላቻንና ክፍፍልን አያስተምርም፡፡ ፩ኛ ዮሐ. ፬፤፲፩ ዘረኝነትም ሆነ ሌሎች ሥጋዊ የመለያያ መንገዶች በቅድስት ቤተ ክርስቲያን የማይወደዱና ያልተፈቀዱ ተግባራት ስለሆኑ፣ ወጣቱ ዘመናዊነትን ለፍቅር እንጂ ለልዩነት መጠቀም የለበትም፡፡
ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም «በወንድማማች መዋደድ እርስ በርሳችሁ ተዋደዱ፤ እርስ በርሳችሁ ተከባበሩ፡፡» ያለው የኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ አስተምህሮ መከባበርንና መዋደድን የሚሰብክ፣ ዘረኝነትን የሚነቅፍ፣ አንድነትነም የሚያጸና በመሆኑ ነው፡፡ ሮሜ ፲፪፤፲
የሰው ልጆች፣ ይልቁንም ክርስቲያኖች በቋንቋ፣ በባህል እና በአስተሳሰብ ቢለያዩም በእግዚአብሔር ግን አንድ ቤተሰብ ናቸው፡፡ አባታችን እግዚአብሔር፣ እናታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ናትና በኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ጥላ ሥር እየኖረን ዘረኝነትን መስበክና በዘር መመካት እግዚአብሔርን የሚያስቀይም ከባድ በደል ነው፡፡ ለዚህም ነው ቅዱስ መጽሐፍ ‹‹በእምነት በኩል ሁላችሁ በክርስቶስ ኢየሱስ የእግዚአብሔር ልጆች ናችሁና፤ ከክርስቶስ ጋር አንድ ትሆኑ ዘንድ የተጠመቃችሁ ሁሉ ክርስቶስን ለብሳችዃልና፡፡ አይሁዳዊ ወይም አረማዊ የለም፣ ገዥ ወይም ተገዥ የለም፣ ወንድም ሴትም የለም፣ ሁላችሁም በክርስቶስ ኢየሱስ አንድ ናችሁ›› ያለው፡፡ (ገላ. ፫፥፳፮-፳፰)፡፡ የሰው ዘር ሁሉ ምንጩ፣ ከአንድ አዳም ነውና ሁላችንም በእግዚአብሔር እጅ ተፈጥረን፣ ለአንድ አዳምና ከአንዲት ሄዋን መገኘታችንን መዘንጋት የለብንም፤ አዳምንና ሄዋንን ብዙ ተባዙ ብሎ እንጂ በየነገዳችን ለእያንዳንዳችን ሌላ አዳምና ሌላ ሄዋን ፈጥሮ አይደለም እንድንበዛ ያደረገን፡፡ በመሆኑም፣ ልዩነታችን በወቅታዊ ጉዳይ፣ በመልክአ ምድር አቀማመጥ፣ ከሰው ልጅ የረዘመ የትውልድ ሐረግ የተነሳ መሆኑን ልብ ብለን ዘራችን አንድ አዳም መሆኑን መዘንጋት የለብንም፡፡
በአጠቃላይ ዓለማችን እየሄደችበት ያለውን የሥልጣኔና የዘመናዊነት መንገድ በሩቁ መመልከት ሳይሆን፣ በመጽሐፍ እንደተጻፈልን ዘመኑን በመዋጀት በአግባቡና በሥርዓቱ ልንጠቀም ይገባል፡፡ ሥልጣኔ ስለሆነ ብቻ በገፍ መቀበል ዋጋን ያስከፍላል፤ መመርመር ግን ከመልካም ጎዳና ያደርሳል፡፡ በመሆኑም እግዚአብሔር አምላክ በሰጠን አስተዋይ ልቡና፣ በአካለ ሥጋ ያየነውን በዐይነ ሕሊና በመመልከት፤ በዕዝነ ሥጋ የሰማነውን በዕዝነ ሕሊና በመመርመር፣ ለሥጋችን ብቻ ሳይሆን ለነፍሳችንም የሚጠቅመንን መልካሙን ነገር መያዝ አለብንና የዘመናዊነት መረዳታችን የተስተካከለ፣ የማኅበራዊ ሚዲያ አጠቃቀማችንም ዘመኑን የዋጀ፣ የቅድስት ቤተ ክርስቲያን አስተምህሮን የጠበቀ መሆን አለበት፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
Leave a Reply
Want to join the discussion?Feel free to contribute!