ማዘንና መጸለይ (ከባለፈው የቀጠለ)
በዲ/ን ታደለ ሲሳይ
- የቤተ ክርስቲያን ሰላም በጠፋ ጊዜ
ክርስቶስ በደሙ ዋጅቶ የመሠረታት ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ለድኅነታችን መንገድ፣ ለህልውናችን ዋስትና፣ ለሰማያዊ ቤታችን ደግሞ ተስፋ ናት፡፡ ይህንን መንገድ፣ ዋስትናና ተስፋ የምናገኘውና ተጠቃሚም የምንሆነው የኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሰላም ሲጠበቅ፣ መንጋዎቿ ፈጣሪያቸው በፈቀደላቸው መስክ ብቻ መሠማራት ሲችሉ፣ እረኞቹ ከመንጋው ባለቤት ከኢየሱስ ክርሰቶስ የተቀበሏቸውን በጎች ከቀበሮና ከሌሎች አውሬዎች መጠበቅ ሲችሉ ነው፡፡ ይህ የሚሆነው ደግሞ የቤተ ክርስቲያን ሰላም ተጠብቆ ሲቀጥል ብቻ ነው፡፡
ቤተ ክርስቲያን ሰላሟን ካጣች በጎቿ በነጣቂ ተኩላ ይበላሉ፤ እረኞቿ በጉን ትተው ቀበሮውን ያሠማራሉ፤ በዓውደ ምሕረቷ ሲመረት የነበረው የወንጌል ምርት በታሰበለት መሥፈሪያ ሳይሰፈር ይቀራል፡፡ እኛም በቤተ ክርስቲያን ማግኘት ያለብንን ሰላም እናጣለን፡፡ ምክንያቱም የቤተ ክርስቲያን ደኅንነት ደኅንነታችን፣ ሰላሟ ሰላማችን፣ ፍቅሯ ፍቅራችን ነውና፡፡
በመሆኑም «ኅሡ ሰላማ ለቤተ ክርስቲያን፤ የቤተ ክርስቲያንን ሰላም ሹ» እንዳለው ሰላሟ እንዳይናጋ ሰላሟን ልንፈልጋት ይገባል፡፡ ጠላት ዲያብሎስ በሚያጠምደው የጥፋት መረብ የቤተ ክርስቲያናችን ሰላም ቢናጋ እንኳን፣ በጸሎት፣ በሐዘንና በልቅሶ ወደ ፈጣሪያችን በመጮኽ የቤተ ክርስቲያንን ሰላም መፈለግ አለብን፡፡ በቅዳሴ ጊዜ ሁልጊዜ ዲያቆኑ «ጸልዩ በእንተ ሰላመ ቤተ ክርስቲያን፤ ስለ ቤተ ክርስቲያን ሰላም ጸልዩ» እያለ የሚያውጀው ለዚህ ነው፤ የጠላት ዲያብሎስ ሤራ የቤተ ክርስቲያንን ሰላም ለማሳጣት አርፎ አያውቅምና፡፡
አባቶቻችን ቤተ ክርስቲያን በተለያዩ መንገዶች ፈተና ሲደርስባትና ሰላሟን ስታጣ የነበረውን ሰላም የሚመልሱላት ወደ ፈጣሪያቸው በመጸለይ፣ አመድ ለብሰውና ትቢያ ነስንሰው በማልቀስና በማዘን ነበር፡፡ እኛም የአባቶቻችንን መንገድ የምንከተል የአባቶቻችን ልጆች እስከሆን ድረስ ቤተ ክርስቲያናችን ሰላሟን ባጣችበት ጊዜ መጸለይ፣ ማልቀስና ማዘን ይገባናል ማለት ነው፡፡
- የሀገር ሰላም በተናጋ ጊዜ
ሀገር ማለት የአንድ ሕዝብ ጣሪያ ናት፡፡ ሕዝቦቿ ደግሞ ግድግዳና ማገር ናቸው፡፡ በሕዝቦቿ ግድግዳና ማገርነት ጣሪያዋ ሀገር ትቆማለች፤ ታበራለች፡፡ ጣሪያ ያለ ግድግዳ መቆም እንደማይችል ሀገርም ያለ ሕዝብ መቆም አትችልም፡፡ በአንድም በሌላም መንገድ የአንድ ሀገር ሰላም ደፈረሰ የሚባለው የሕዝቦቿ ሰላም ሲደፈርስ ነው፡፡ አንዲት ሀገር ደኸየች፤ ከበረች የሚባለው ሕዝቦቿ ሲደኸዩ ሲከብሩ ነው፡፡ የሕዝቦቿ የኑሮ ደረጃ፣ የዕለት ከዕለት እንቅስቃሴና ሁለንተናዊ አቋም የአንድ ሀገር ወቅታዊ መገለጫ ነው፡፡
ሕዝቦቿ ኢአማኒ የሆኑባት ሀገር መጠሪያዋም የኢአማንያን ሀገር ነው፤ ሕዝቦቿ ክርስቲያን የሆኑላት ሀገር ደግሞ ሀገሪቱም የክርስቲያን ሀገር ትባላለች፤ ክርስትናም መገለጫዋ ይሆናል ማለት ነው፡፡ ሀገር ማለት ሰው ነው፤ ሰው ማለት ሀገር ነው፡፡ ለዚህም ነው የአባቶቻችን ብሂል «ሰብእ ይቄድሶ ለመካን ወመካን ይቄደሶ ለሰበእ፤ ሰው ቦታን ይቀድሳል ቦታም ሰውን ይቀድሳል» የሚለው፡፡ በመሆኑም የሀገር ሰላም ለአንድ ሰው አስፈላጊና ሊታሰብበት የሚገባ ጉዳይ ይሆናል ማለት ነው፡፡
አባቶቻችን የሀገራቸው ሰላም በደፈረሰ ጊዜ በሐዘንና በጸሎት ሀገራቸውን እንደሚታደጉ በታሪክ እናነባለን፤ እናያለንም፡፡ ቅድስት ቤተ ክርስቲያንም ስለ ሀገር ሰላም ትጸልያለች፤ የሚጠበቅባትንም ታደርጋለች፡፡ ለአብነት ያህል ብንጠቅስ ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን «እግዚኦ ኲነኔከ ሀባ ለሀገር ጽድቀከኒ ለቤተ ክርስቲያን አግርር ፀራ ታህተ እገሪሃ ዕቀብ ሕዝባ ወሠራዊታ ለሀገሪትነ ኢትዮጵያ፤ አቤቱ ፍርድህን ለሀገር እውነትህንም ለቤተ ክርስቲያን አድርግ፣ ጠላቶቿን ከእግሮቿ በታች አስገዛላት፣ ሕዝቧንና ሠራዊቷንም ጠብቅ» እያለች ትጸልያለች፡፡
ይህ የሚያሳየው ቤተ ክርስቲያናችን ምን ያህል ለሀገርና ለሕዝብ አደራዋን እንደምትወጣ ነው፡፡ ይህንን አብነት በማድረግ ነው፤ አባቶቻችን ለቤተ ክርስቲያንና ለሀገር ሲጸልዩ የኖሩት፡፡ ከዚያም አልፈው በሀገር ጉዳይ ለመጣ ጠላት ለሥጋቸው ሳይሳሱ እውነተኛ ኢትዮጵያዊነታቸውን እያስመሰከሩ የሞቱ ብዙዎች ናቸው፡፡ የጳጳሳቱ አቡነ ጴጥሮስና አቡነ ሚካኤል ታሪክ የሚያሳየንም ይህንኑ ነው፡፡ ከሞት ጋር ፊት ለፊት እንደተፋጠጡ ለቤተ ክርስቲያናቸውና ለሀገራቸው እየጸለዩ ለሀገራቸው ታሪክ ጥለው አልፈዋልና፡፡ በመሆኑም ክርስቲያን በክርስትና ሕይወት ሲኖር ሀገሩ ሰላም ባጣችበት ወቅት ማዘንና ማልቀስ ይጠበቅበታል ማለት ነው፡፡
ማጠቃለያ
ክርስቲያን ሕይወቱ በክርስትና መንገድ የሚመራ ነው፡፡ እያንዳንዱ ሰውም ለምንና እንዴት እንደሚኖር ማወቅ አለበት፡፡ ክርስቲያን ለደስታውም ልክ አለው፤ ለሐዘኑም መጠን አለው፡፡ ክርስቲያን ሲደሰት ሰማይን በእርግጫ ምድርን በጡጫ አይልም፤ ሲከፋም ለምን ተደፈርኩ ብሎ በኃይል አይነሣም፡፡ ክርስቲያን ሲደሰት ያመሰግናል፤ ሲከፋ ይጸለያል፡፡ የክርስቲያን መገለጫው ይህ ነው፡፡ ሁሉም ነገር መጠን አለውና፡፡
በመሆኑም በምድራዊ ኑሮ በሚደርሱ አስከፊና አሳዛኝ ጊዜያት ሁሉ ማዘን ኃጢአት ቢሆንም የሐዘንን ልክ ማበጀት ግን ብልህነት ነው፤ እግዚአብሔርም የሚወደው ነው፡፡ ከዚያ በተረፈ ግን ሐዘንን ማብዛት፣ ነገሮችን በሥጋዊ ስሌት በመመንዘር መጨነቅና እግዚአብሔርን ማስከፋት አስፈላጊ አይደለም፡፡ ብዙ ሰዎች ገደብ በሌለው ጣሪያ የነካ ሥጋዊ ፍላጎታቸው ይነሡና፣ ያ ፍላጎት ሳይሳካ ሲቀር በማዘንና በማልቀስ እግዚአብሔርን ሲያሰቀይሙ ይታያሉ፡፡ ይህ እግዚአብሔር የማይወደው ሥራ ነው፡፡
ሰዎች ሆነን በምድራዊ ኑሮ ስንኖር ጥረህ ግረህ የላብህን ብላ ተብሎ በታዘዘልን መሠረት፣ ዓለምን ንቀን ገዳም ብንገባ እንኳን ሥራ የሕይወታችን አንድ አካል መሆን እንዳለበት መጽሐፍ ያስተምረናል፡፡ በድካማችን እግዚአብሔር ባርኮ የሰጠንን ፍሬ እንድንጠቀምም እግዚአብሔር ፈቅዷል፡፡ ዳሩ ግን በማይረካ የፍላጎት ንረት ተሳፍረን ያሰብነው ባልተሳካ ቍጥር ማዘን፣ ማልቀስ፣ መከፋትና ማማረር ሥጋዊ ማንነታችንን ከመጉዳት ባለፈ እግዚአብሔርን የሚያስቀይም ነው፡፡ ልናዝንና ልንከፋ የሚገባው ከላይ እንደተጠቀሰው ለሥጋችን ስንሯሯጥ እግዚአብሔርን ባስከፋን ጊዜ፣ ሰዎች በሞት በተለዩን ጊዜ፣ ሰላመ ቤተ ክርስቲያንና ሰላመ ሀገር በጠፋ ጊዜ እንዲሁም ወገኖቻችን ከጸጋ እግዚአብሔር በተራቆቱ ወቅት ነው፡፡ ከዚያ ባለፈ ግን ሥጋችን የጋለበው የምኞት ፈረስ ከቦታው መድረስ ባልቻለ ጊዜ ሁሉ ሐዘንን ማብዛት ክርስቲያናዊ አይደለምና ልንጠነቀቅ ይገባል፡፡
ከምድራዊ ሐዘንና ልቅሶ ይልቅ በተገቢው መንገድ ማዘናችንን፣ ማልቀሳችንንና መጸለያችንን እግዚአብሔር ተመልክቶ የድካማችንን ዋጋ ይከፍለን ዘንድ ፈቃዱ ይሁን፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
kale hiwot yasemaln