በነጻነት ልንኖር ክርስቶስ ነጻነት አወጣን (ገላ. 5÷1)
በዲ/ን ታደለ ፈንታው
ይህ መልእክት ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ለገላትያ ሰዎች በጻፈው መልእክቱ በምዕራፍ አምስት ቁጥር አንድ ላይ የተቀመጠ ኀይለ ቃል ነው፡፡ የገላትያ ሰዎች አስቀድመው እግዚአብሔርን ያወቁ፣ ክፉ ከሆነው ከዚህ ዓለም የሥጋ ዐሳብ ያመለጡ፣ በሃይማኖት የሚኖሩ፣ ከክፋት የራቁ፣ መልካም የሆነውን ነገር ፈትነው የተቀበሉ፣ ለማፍረስ ያይደለ ለማነጽ የተጠሩ፣ ፍጹማን ይሆኑ ዘንድ ደፋ ቀና የሚሉ፣ ሌትና ቀን በቤተ መቅደሱ በጸሎት ሁሉ የሚተጉ ክርስቲያኖች ነበሩ፡፡ አስቀድመው በተጠሩበት መጠራት መመላለስ ሲያቅታቸው ከመንፈሳዊው ነገር ይልቅ ትኩረታቸው ጉጉታቸውና አላማቸው ሥጋዊ ነገር ላይ ሲያርፍ ትውክልታቸው እግዚአብሔር መሆኑ ቀርቶ ምድራዊ ነገር ሲሆን የሚፈሩት ነፍስንና ሥጋን አንድ አድርጎ በገሀነም የሚቀጣውን እግዚአብሔርን ሳይሆን ጊዜ የሰጣቸውን ወገኖች ሆኖ ቢያገኛቸው እንዲህ የሚል መልእክት ጻፈላቸው፡፡ ‹‹በክርስቶስ እናንተን ከጠራች ከእርሱ ወደልዩ ወንጌል እንዲህ ፈጥናችሁ እንዳለፋችሁ እደነቃለሁ እርሱ ግን ሌላ አይደለም የሚያናውጧችሁ የክርስቶስን ወንጌል ሊያጣምሙ የሚወዱ አንዳንድ ወገኖች አሉ እንጂ›› (ገላ.1፥6) በማለት ይጽፍላቸዋል፡፡ ክርስቲያኖችን ሁል ጊዜ በሚያባብል ቃል መቅረብ አስፈላጊ አይደለም፡፡ ተግሣጽ በሚያስፈልግበት ጊዜ አቀራረባችን መለየት ይኖርበታል እንጂ፡፡ የወንጌል መንገድ እንዲሁ ነው፡፡ ተግሣጽ በሚያስፈልግበት ጊዜ በሚያባብል ቃል መናገር የጠላት እንጂ የእውነተኛ ክርስቲያኖች ጠባይ አይደለም፡፡ ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አብዛኛውን ጊዜ ደቀ መዛሙርቱን የሚያናግራቸው በቀስታና በለዘበ አነጋገር ነበር፤ ነገር ግን ተግሣጽ በሚያስፈልግበት ጊዜ ገስጿቸዋል፡ ፡ በምስጋና ጊዜ ስምዖንን “አንተ ብፁዕ ነህ›› / ማቴ.16፥17/ እንዳለው በአንተ ቃል መሠረትነት ላይ ቤተ ክርስቲያኔን እመሠርታለሁ ብሎ ቃል እንደገባለት በተግሣጽ ጊዜ ‹‹አንተ ሰይጣን ከፊቴ ዘወር በል የሰውን እንጂ የእግዚአብሔርን አትመለከትምና›› /ማቴ.16፥23/ በማለት ሲናገር እናደምጠዋለን፡፡
የዚህ ትምህርት ዋና ማጠንጠኛ ዐሳብም የግቢ ጉባኤ ተማሪዎቻችን የእግዚአብሔርን እንጂ የሰውን ሳይመለከቱ በቤተ ክርስቲያናችን ትምህርት ሥርዓት፣ ሕግና ቀኖና፣ መሠረት እንዲጓዙ እንጂ ልማዳዊ በሆነ ወይም ሰው ሠራሽ በሆነ መንገድ ተጉዘው ለእግዚአብሔር ያላቸውን መታመን እንዳያጡ ወንዶች በ4ዐ ቀን ሴቶች በ8ዐ ቀን በጥምቀት ከቅድስት ሥላሴ ያገኙትን ልጅነት ጠብቀው እግዚአብሔር በወሰነላቸውና ባዘጋጀላቸው መንገድ እንዲጓዙ እንዲመላለሱ በማሰብ የተጻፈ ነው፡፡ ስለዚህ በዚህ ጽሑፍ አስቀድመን የግቢ ጉባኤያት ሊገጥሟቸው የሚችሉ ፈተናዎችን በማንሣት ለችግሮችም መፍትሔ የሚሆኑ ነገሮችን በመጠቆም ጽሑፋችንን እንቋጫለን፡፡ ከነዚህም አንዱ በዕድሜ ምክንያት የሚመጣ ፈተና ነው።
ይህ ፈተና ሴቷ ለአቅመ ሔዋን ወንዱ ለአቅመ አዳም ሲደርሱ ከዚህ በፊት አይቶት የማያውቀው የስሜት መነሣሣት፣ ወደ ተቃራኒ ጾታ የመሳብ፣ በዐሳብ ጭልጥ ብሎ የመጓዝ፣ የማያውቁትን ወደ መናፈቅ ለአለባበስ መጠንቀቅና ሌሎችም ቆጥረን ልንጨርሳቸው የማንችላቸው ክስተቶች የሚታዩበት የፈተና ዓይነት ነው፡፡ ይህ ፈተና በራሱ የሚጎዳ አይደለም፣ በስሜታችን ውስጥ የሚቀሰቀስ የሚለወጥ ፈጥነው መፍትሔ ካልወሰዱለት የሚያድግ ውጤቱ አውዳሚ የሆነ ፈተና ነው፡፡ በቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ የመጀመሪያው ስሜትን የማሰብ ደረጃ ነቅዐ ሀልዮ በመባል ይታወቃል፡፡ በዚህ ደረጃ የሚፈጠርን ፈተና በጸሎት፣ በጾም፣ በስግደት፣ ቅዱሳት መጻሕፍትን በማንበብ፣ ራስን ከአልባሌ ቦታዎች በመጠበቅ ጸበል አዘውትሮ በመጠመቅና በመጠጣት ማራቅ ይቻላል፡ ፡ አለበለዚያ የወደድነውን የፈቀድነውን ነገር ለማግኘት ወደ መጓጓትና ለመፈጸም ወደ መትጋት ያሸጋግረናል፡፡ ይህ ሁኔታ ቁርጥ ሀልዮ ይባላል፡፡ ይህንን ሁኔታ ተከትሎ የሚመጣው ገቢር /ድርጊት/ ወይም ኀጢአት ነው፡፡ አስቀድመን ላነሣነው ነጥብ ማሳያ የሚሆን መጽሐፍ ቅዱሳዊ ታሪክ አለን፡፡
ለዳዊት ልጅ ለአቤሴሎም አንዲት የተዋበች እኅት ነበረችው፤ ስምዋም ትዕማር ነበር። ወንድሟ አምኖን ወደዳት ከትዕማር የተነሣ እጅግ ስለተከዘ ታመመ ድንግልም ስለነበረች አንዳች ያደርጋት ዘንድ በዐይኑ ፊት ጭንቅ ሆነበት፣ ታምሜአለሁ ብሎ ተኛ፣ እኅቱ መብል እንድታዘጋጅለት ወደ አምኖን ቤት ሄደች፣ ዱቄትም ወሰደች፣ ለወሰች ዐይኑ እያየ እንጎቻ አደረገች ጋገረችም፡፡ ምጣዱንም ወስዳ በፊቱ ገለበጠች ነገር ግን የአምኖን ምኞት ሌላ ነበርና ካዘጋጀችለት አልተመገበም መብሉን ባቀረበች ጊዜ ያዛትና ከእኔ ጋር ተኚ አላት፤ አይሆንም አለችው አስገድዶ አስነወራት፡፡ ከዚያም በኋላ አምኖን ፈጽሞ ጠላት፤ አስቀድሞ ይወዳት ከነበረው ውድ ይልቅ በኋላ የጠላት ጥል በለጠ በራስዋ ላይ አመድ ነስንሳ ብዙ ኅብር ያለውን ልብሷን ተርትራ እጅዋን በራስዋ ላይ ጭና እየጮኸች ሄደች፡፡ (2ኛ ሳሙ.13፥1-19) በወጣትነት ዕድሜ ላሉ ጾታዊ ግንኙነታቸው ገደቡን አልፎ ወደ አልሆነ ቅጣጫ ለሚጓዙ ወጣቶች ይህ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ታሪክ አስተማሪነቱ የጎላ ነው፡፡ እንዲህ ዓይነት ስሜት የሚፈጠረው ተዘልሎ ከመቀመጥ እንደ ክርስቲያን ካለመመላለስ ነው፡፡ ክርስቲያን ፈጽሞ ዝንጋኤ ልቡና አያድርበትም በአዋዋሉ በአነጋገሩ በሚያደርገው ሥራ በሚወስደው ርምጃ ሁሉ ጥንቃቄና ማስተዋል ከእርሱ ጋር አብረውት ይሆናሉ እንጂ፡፡ በግቢ ጉባኤ በተቃራኒ ጾታዎች መካከል የሚደረጉ አላስፈላጊ መቀራረቦች አጀማመራቸው መልካም ይሆንና ፍጻሜአቸው ግን አሳዛኝ ይሆናል፡፡