በፍቅር መኖር
…በመ/ር ኃይለ ሚካኤል ብርሃኑ…
በክርስቲያናዊ ሕይወት ለመኖር የወሰነ ሰው ሰውን ሁሉ ሊወድ ይገባል፡፡ ፍቅር ሲባል ፍትወታዊ የጾታ ፍቅር ሳይሆን ሁሉንም ሰው ሳይለያዩ መውደድ ነው፡፡ ለዚህ ነው ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከሕግጋት ሁሉ ፍቅርን ያስበለጠው፡፡ (ዮሐ. 15፥12) ቅዱስ ጳውሎስ ይህንን ሲጠቅስ በሰዎችና በመላእክት ልሳን ብናገር ፍቅር ግን ከሌለኝ እንደሚጮኽ ናስ ወይም እንደሚንሿሿ ጸናጽል ሆኛለሁ፤ ትንቢትም ቢኖረኝ ምሥጢርንም ሁሉና ዕውቀትን ሁሉ ባውቅ ተራሮችንም እስካፈርስ ድረስ እምነት ቢኖረኝ ፍቅር ግን ከሌለኝ ከንቱ ነኝ፤ ድሆችን ልመግብ ያለኝን ሁሉ ባካፍል ሥጋዬንም ለእሳት መቃጠል፤ አሳልፌ ብሰጥ ፍቅር ግን ከሌለኝ ምንም አይጠቅመኝም፡፡ ፍቅር ይታገሣል፤ ቸርነትም ያደርጋል፤ ፍቅር አይቀናም፤ ፍቅር አይመካም፤ አይታበይም፤ የማይገባውን አያደርግም…(1ኛ ቆሮ. 13፥1) በማለት አስረድቷል፡፡
በክርስቲያናዊ ሕይወታችን በእምነት መነጽርነት እግዚአብሔርን ማየት የምንችለው ፍቅርን መሠረት ያደረገ ሕይወት ሲኖረን መሆኑን «እግዚአብሔር ፍቅር ነው፤ በፍቅርም የሚኖር በእግዚአብሔር ይኖራል፤ እግዚአብሔርም በእርሱ ይኖራል» በማለት መጽሐፍ ቅዱስ ያረጋግጥልናል፡፡ (1ኛ ዮሐ. 4፥16)
ሀብተ ወልድና ስመ ክርስትና አግኝቶ በመንፈስ ቅዱስ ቅብዓ ሜሮን ተቀብቶ የከበረ ክርስቲያን ሁሉ ፍቅር ማለት እግዚአብሔርን የምናይበት የሕሊና መስታውት መሆኑን ተገንዝቦ በፍቅር ሊኖር ይገባዋል፡፡ ያለ ፍቅር ምንም ዓይነት ሥራ ቢሠራ ዋጋ የለውምና ፍቅርን ገንዘብ እናድርግ፡፡ ያለ ፍቅር ከሚሆን ብዙ ሥራ ይልቅ በፍቅር የሚሆን ትንሽ ሥራ በእግዚአብሔር ዘንድ የተወደደ ነውና ፍቅርን እናስብ፣ በፍቅር እንኑር፡፡ እግዚአብሔር የፍቅር አምላክ ነውና እርሱን እንምሰል፡፡ ስለ ፍቅር ሰው ሆኖ የተሰቀለልንን አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስን እያሰብን እኛም ለወንድሞቻችን ፍቅርን እንስጥ፡፡ በፍቅር እየኖርን የምናደርገው መንፈሳዊ ሥራ ሁሉ ፍሬ አፍርቶ የምናየው በፍቅር መኖር ስንችል ነው፡፡ አባቶቻችንን እናስብ፡፡ ገድል የፈጸሙት፣ ተኣምር ያደረጉት፣ ታሪክ የሠሩት፣ ስማቸውን በሰማይ መዝገብ ያሰፈሩት በፍቅር መኖር በመቻላቸው ነው፡፡ በፍቅር ስለ ፍቅር እንድንኖር እግዚአብሔር ይርዳን፡፡