ጥምቀት

የጥምቀት ትርጉም እና ምንነት

ጥምቀት ማለት አጥመቀ(አጠመቀ) ከሚለው የግእዝ ግስ የተገኘ ሲሆን ትርጉሙም መነከር፣ መጥለቅ፣ መደፈቅ፣ በውኃ ውስጥ መጠመቅ ማለት ነው። በሌላ አገላለጽ፡- ጥምቀት አስተርእዮ ወይም መገለጥ  ማለት ነው። (ነገረ ሃይማኖት ዘተዋሕዶ ገጽ ፻፵፭)። በግሪክ ደግሞ ኤጲፋንያ ሲባል ትርጓሜውም መለኮት የተገለጠበት ማለት ነው (ስንክሳር ዘጥር ፲፩)።ይህም የእግዚአብሔር አንድነት እና ሦስትነት የተገለጠበት ታላቅ ምሥጢር መሆኑን የሚያመለክት ነው፡፡ እግዚአብሔር የሦስትነቱን ምሥጢር ገልጦበታልና አብ ከሰማይ ሆኖ “የምወደው፣ በእርሱ ደስ የሚለኝ ልጄ ይህ ነው፤ እርሱን ስሙት” (ማቴ. ፫፥፲፮-፲፯) እያለ ሲመሰክር ወልድም በዕደ ዮሐንስ በዮርዳኖስ ወንዝ ሲጠመቅ፣ መንፈስ ቅዱስም በነጭ ርግብ አምሳል በራሱ ላይ ሲቀመጥ ታየ ወይም ተገለጠ። 

ጥምቀት የሰው ልጆች ሁሉ ከአዳም ጀምሮ የወረስነውን ኃጥአት ደምስሶ በመንፈስ ቅዱስ የእግዚአብሔር ልጆች ተብለን እንጠራና ዳግም እንድንወለድ የሚያደርገን የመጀመሪያው ምሥጢር የተፈጸመበት ነው። የክብር ባለቤት ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ከምሥጢራት ሁሉ አስቀድሞ የፈጸመው ታላቅ ምሥጢር ነው። ስለዚህ ከምሥጢራት ሁሉ ጥምቀት ይቀድማል። ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሐዋርያትን ከመምረጡ በፊት፣ ወደ ገዳመ ቆሮንቶስ ሄዶ ከመጾምና ከመጸለዩ አስቀድሞ፣ ትምህርት ማስተማር እና ተዓምራት ከማድረጉ በፊት የመጀመሪያ ያደረገው በዮርዳኖስ ወንዝ በዮሐንስ እጅ በመጠመቅ ምሥጢረ ጥምቀትን መሠረተ። የመንፈስ ቅዱስ ሱታፌ የሚገኘው በምሥጢረ ጥምቀት ነውና። ሥጋዊ ልደት አንድ እንደሆነ ሁሉ መንፈሳዊ ልደትም አንድ ጊዜ የሚፈጸም ነው። ስለዚህ ጥምቀት አይደገምም። “ጌታ አንድ ነው፣ ሃይማኖትም አንዲት ናት፣ ጥምቀትም አንዲት ናት” (ኤፌ. ፬፥፭)                                                      

ጥምቀተ ክርስቶስ

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዮርዳኖስ ወንዝ በዮሐንስ እጅ መጠመቁን ሲያመለክት “ያን ጊዜ ኢየሱስ በዮሐንስ ሊጠመቅ ከገሊላ ወደ ዮርዳኖስ መጣ።” በማለት ወንጌላዊው ማቴዎስ ይነግረናል፡፡ (የማቴ. ፫፥፲፫)

ጌታችንን የሚያጠምቀው መጥምቁ ዮሐንስ እንደሆነ በትንቢትም የተገለጠ ነው። ይህንንም ከዐበይት ነቢያት መካከል ኢሳይያስ “ የአዋጅ ነጋሪ ቃል፦ የእግዚአብሔርን መንገድ ጥረጉ፥ ለአምላካችንም ጐዳና በበረሃ አስተካከሉ።” (ኢሳ. ፵፥፫) ሲል፤ ወንጌላውያንም የትንቢቱን  ፍጻሜ አስተባብረው አረጋግጠውታል። “በነቢዩ በኢሳይያስ፦ የጌታን መንገድ አዘጋጁ ጥርጊያውንም አቅኑ እያለ በምድረ በዳ የሚጮህ ሰው ድምፅ የተባለለት ይህ ነውና።” (ማቴ. ፫፥፫) በማለት ሲገልጸው፤ “እነሆ፥ መንገድህን የሚጠርግ መልክተኛዬን በፊትህ እልካለሁ፤ የጌታን መንገድ አዘጋጁ፤ ጥርጊያውንም አቅኑ፤ እያለ በምድረ በዳ የሚጮኽ ሰው ድምፅ ተብሎ በነቢዩ በኢሳይያስ እንደ ተጻፈ፥” (ማር. ፩፥፪-፫)፤ ወንጌላዊው ቅዱስ ሉቃስም “በነቢዩ በኢሳይያስ ቃል መጽሐፍ፦ የጌታን መንገድ አዘጋጁ ጥርጊያውንም አቅኑ እያለ በምድረ በዳ የሚጮኽ ሰው ድምፅ፤ ዐዘቅቱ ሁሉ ይሙላ ተራራውና ኮረብታውም ሁሉ ዝቅ ይበል፥ ጠማማውም የቀና መንገድ ይሁን፥ ሸካራውም መንገድ ትክክል ይሁን፤ ሥጋም የለበሰ ሁሉ የእግዚአብሔርን ማዳን ይይ ተብሎ እንደ ተጻፈ ለኃጢአት ስርየት የንስሐን ጥምቀት እየሰበከ በዮርዳኖስ ዙሪያ ወዳለችው አገር ሁሉ መጣ።” (ሉቃ. ፫፥፫-፮)፤ “እርሱም፦ ነቢዩ ኢሳይያስ እንዳለ፦ የጌታን መንገድ አቅኑ ብሎ በምድረ በዳ የሚጮኽ ሰው ድምፅ እኔ ነኝ አለ።” (ዮሐ. ፩፥፳፫) በዚህም መሠረት ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በ፴ ዘመኑ በዮሐንስ እጅ ተጠመቀ፡፡

ጌታችን ለምን ተጠመቀ?

ጌታችን እንደ አይሁድ የመንጻት ልማድ ከኃጢአት ለመታጠብ አይደለም። እንደ ኃጥአን መጽብሐን ከዮሐንስ ዘንድ ለንስሓ እንደተጠመቁትም ጥምቀት አይደለም። (ዘሌ. ፲፭፥፩-፲፫፤ ማቴ. ፫፥፮) “በይሁዳና በኢየሩሳሌም፣ በዮርዳኖስም ያሉ ሰዎች ወደ መጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ እየመጡ ኃጢአታቸውን እየነገሩት በዮርዳኖስ ያጠምቃቸው ነበር።” ምን እያለ ያጠመቃቸው ነበር? ቢባል “እገሌ ተጠመቅ በማየ ንስሓ ከመ ትኩን ረድኦ ለክርስቶስ፤ እገሌ ለክርስቶስ አገልጋይ ትሆን ዘንድ በንስሓ ውኃ ተጠመቅ” እያለ ያጠምቃቸው ነበር። (ትርጓሜ ወንጌል ዘማቴዎስ)።

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ  ለምን ተጠመቀ?

፩. ለእኛ ሥርዓተ ጥምቀትን ለመመስረት (ዳግም ልደትን ለመስጠት)

፪. ትሕትናን ለማስተማር፦ ዮሐንስን መጥተህ አጥምቀኝ ከማለት ወይም ባሪያ ወደ ጌታው ከመሄድ ጌታ ወደ ባሪያው ሂዶ በባሪያው እጅ መጠመቁ ትሕትናውን ያመለክታልና። ጌታችን ወደ መጥምቁ ዮሐንስ መምጣቱ ለዮሐንስ ክብር ስለሆነው ክብሩን በሚገልጽ አገላለጽ ዮሐንስ መጥምቀ መለኮት ተባለ።

፫. ለአብነት፦ ጌታችን ዮሐንስን መጥተህ አጥምቀኝ ቢለው ነገሥታትና ካህናትን ወደ እኛ መጥታችሁ አጥምቁን እንዳይሉ ሂዳችሁ ተጠመቁ ለማለት አብነት ለመሆን።

፬. ዮርዳኖስን  ብርህት ማኅፀን ለማድረግ (ውኃን ለመባረክ)፦ ለጥምቀት ኃይል ለመስጠት

፭. አንድነቱንና ሦስትነትን ለመግለጥ ጌታችን ተጠመቀ፡፡

ለምን በዮርዳኖስ ተጠመቀ

፩. ትንቢቱን ለመፈጸም፡- “ባሕርኒ ርእየት ወጎየት ወዮርዳኖስኒ ግብአ ድኅሬሁ፤ ባሕር አየች ሸሸችም ዮርዳኖስም ወደ ኋላ ተመለሰ” (መዝ. ፻፲፫፥፫)

፪. ምሳሌውን አማናዊ ለማድረግ፦ ዮርዳኖስ ከላይ ነቁ አንድ ነው፣ የሰው ሁሉ ነቁ፤ መገኛው አንድ አዳም ነው። ዝቅ ብሎ በደሴት ለሁለት ይከፈላል። እስራኤል በግዝረት፣ አሕዛብ በቁልፈት መለያየታቸውን ያሳያል፤ ወረድ ብሎ ደግሞ ይገናኛል። ይህም ጌታ በጥምቀቱ ሕዝብና አሕዛብን አንድ ሊያደርግ መምጣቱን ያመለክታል።

፫. የዕዳ ደብዳቤያችንን ሊደመስስልን፦ ዲያብሎስ መጋረጃ ጋርዶ በአዳም እና በሔዋን መከራን አጸናባቸው። ስመ ግብርናታችሁን ጽፋችሁ ብትሰጡኝ አቀልላችኋለሁ አላቸው። “አዳም ገብሩ ለዲያብሎስ፤ ሔዋን አመቱ ለዲያብሎስ” ብለው ጽፈው ሰጡት። መጻፍስ የለም ይሁንብን ማለታቸውን ለመናገር ነው እንጂ እሱ በሁለት ዕብነ ሩካም ጽፎ አንዱን በሲዖል፣ አንዱን በዮርዳኖስ ጥሎታል። በዮርዳኖስ የጣለውን ጌታ ሲጠመቅ እንደ ሰውነቱ ረግጦ፣ እንድ አምላክነቱ አቅልጦ አጥፍቶታል። በሲዖል የጣለውን በዕለተ ዓርብ በአካለ ነፍስ ወርዶ ነፍሳትን ሲያወጣ አጥፍቶላቸዋል።  በእኛ ላይ የነበረውን የሚቃወመንን በትእዛዛት የተጻፈውን የዕዳ ጽሕፈት ደመሰሰው፤ እርሱንም በመስቀል ጠርቆ ከመንገድ አስወግዶታል። (ቆላ. ፪፥፲፬) ሊቁ ቅዱስ ኤፍሬምም “ወሰጠጠ መጽሐፈ ዕዳሆሞ፤ የዕዳ ደብዳቤያቸውን ቀደደ” (ሰኞ ውዳሴ ማርያም)።   ነቢየ እግዚአብሔር  ኤርምያስ ስለ ዕዳ መጽሐፍ ሲናገር “የይሁዳ ኃጢአት በብረት ብርዕ በደንጊያ ሰሌዳ ተጽፎአል።” ይላል (ኤር. ፲፯፥፩)

ለምን በውኃ ተጠመቀ?

. ትንቢቱን ለመፈጸም፡

ሀ. “ጥሩ ውኃንም እረጫባችኋለሁ፤ እናንተም ከርኵሰታችሁ ትነፃላችሁ”  ጥሩ ውኃ የተባለ የጥምቀት ውኃ ነው፡፡ (ሕዝ. ፴፮፥፳፭)

ለ. “አቤቱ ውኖች አዩህ፤ ውሆችም አይተውህ ፈሩ” (መዝ. ፸፮፥፲፮)

ሐ.  “ድሆችና ምስኪኖች ውኃ ይሻሉ”  (ኢሳ. ፵፩፥፲፯)

መ. “ወይቤ ኩሎሙ እለ ጸምዑ ይሑር ኀበ ማይ፤ እናንተ የተጠማችሁ ሁሉ ወደ ውኃ ኑ” (ኢሳ. ፶፭፥፩)

፪ኛ. ምሳሌው ለመመሰል፡

“ለታውጽእ ባሕር ኮሎ ዘይትሐውስ ዘቦ መንፈሰ ሕይወት” ባለ ጊዜ በልብ የሚሳቡ፣ በእግር የሚሽከረከሩ፣ በደመ ነፍስ ሕያዋን ሁነው የሚኖሩ ፍጥረታት ተገኝተዋል። በረው የሄዱ አሉ፣ የኢጥሙቃን፤ በዚያው የቀሩ የጥሙቃን ምሳሌ ነው። (ዘፍ. ፩፥፳፣ አክሲማሮስ ዘሐሙስ) አንድም በልብ የሚሳቡ የሰብእ ዓለም፣ በእግር የሚሽከረከሩ ከትሩፋት ወደ ትሩፋት የሚሄዱ የባሕታዊያን፣ በክንፍ የሚበሩ ተመስጦ ያላቸው የሰማዕታት ምሳሌ ነው።

፫ኛ. ፍጻሜውና ምሥጢሩ፦

  • ውኃ በዙፋን ካለ ንጉሥ በአደባባይ እስካለ ጽኑስ ለሁሉ ተመሳሳይ ነው። የጥምቀት መሠረቱ ለሁሉ ነውና፣
  • ውኃ ከጽንፍ እስከ ጽንፍ ይፈሳል። ጥምቀትም ጽንፍ እስከ ጽንፍ ይደረጋልና፣
  • ውኃ ያነጻል፤ ጥምቀትም ያነጻናል።
  • ውኃ የወሰደው ፍለጋ የለውም። በጥምቀት የተሰረየ  ኃጢአት በፍዳ አይመረመርም፣
  • ውኃ መልክ ያሳያል፣ ያለመልማል። ጥምቀትም መልክአ ነፍስ ያሳያልና መልክአ ነፍስ ያለመልማል፡፡

፬ኛ. ውኃ ቀድሞ ሰብአ ትካትን በኋላ ግብፃውያንን አጥፍቶ ስለነበር ለመዓት እንጂ ለምሕረት አልተፈጠረም ብለው ስለነበር ለምሕረትም እንደተፈጠረ ለመጠየቅ ጥምቀቱን በውኃ አድርጓል። (ትርጓሜ ወንጌል፤ ማቴ. ፫፥፲፯)

ለምን በ ፴ ዘመኑ ተጠመቀ?

  • ሰው ሁሉ በ፴ ዘመኑ ሕገ ነፍስን ይሠራል፤ ቅስና እና ምንኩስናም በ፴ ዘመን ይገባል ሲል ነው፡፡(ዘፀ. ፬፥፫፤፩ኛዜና ፳፫፥፬፤ ፩ኛጢሞ. ፫፥፮-፲)
  •  አዳምን የ፴ ዘመን ጎልማሳ አድርጎ ፈጥሮት የሰጠውን ልጅነት አስወስዶ ነበርና የአዳምን ልጅነት ለመመለስ በ፴ ዘመኑ ተጠመቀ፡፡

ቅዱስ ዮሐንስ ጌታችንን በማን ስም አጠመቀው?

ጌታችን ዮሐንስን አጥምቀኝ ባለው ጊዜ “ሌላውን በአንተ ስም አጠምቃለሁ አንተን በማን ስም ላጥምቅህ? በአብ ስም እንዳላጠምቅህ አብ አባትህ በአንተ ሕልው ነው፣ በወልድ ስም እንዳላጠምቅህ ወልድ አንተ ነህ፣ በመንፈስ ቅዱስ ስም እንዳላጠምቅህ መንፈስ ቅዱስ ሕይወትህ በአንተ ሕልው ነው፤ ታዲያ በማን ስም ላጥምቅህ?” ብሎ ቢጠይቀው ጌታም ፦ “ወልዱ ለብሩክ ከሳቴ ብርሃን ተሣህለነ፤ አንተ ካህኑ ለዓለም በከመ ሲመቱ ለመልከ ጼዴቅ፤ እንደ መልከ ጼዴቅ ሥርዓት አንተ የዓለም ካህን ብርሃንን የምትገልጥ የአብ የባሕርይ ልጅ ሆይ ይቅር በለን”ብለህ አጥምቀኝ አለው፡፡ (ትርጓሜ ወንጌል ዘማቴ. ፫፥፲፮)

የጥምቀት አስፈላጊነት እና ጥቅም

. ለድኅነት (ለሥርየተ ኃጢአት)

አንድ ሰው መንፈሳዊ ልደትን የሚያገኘው በጥምቀት እና በእምነት ነው። ክርስቲያኖች መንፈሳዊ ልደትን ለመግኘት የግድ መጠመቅ አለባቸው። ያለ ጥምቀት ክርስትና የለም። ጥምቀት አዲስ ሕይወትን የሚያስጥና ክርስቲያናዊ ሕይወትን የሚያስገኝ ነው። ጌታችን  “ያመነ የተጠመቀ ይድናል፤ ያላመነ ግን ይፈረድበታል።” (ማር. ፲፮፥፲፮) በማለት ጥምቀት ለመዳን የግድ አስፈላጊ መሆኑን አረጋግጦልናል። ቅዱስ ጳውሎስም ጥምቀት ለመዳን አስፈላጊ መሆኑን ሲገልጽ “እንደ ምሕረቱ መጠን ለአዲስ ልደት በሚሆነው መታጠብና በመንፈስ ቅዱስ በመታደስ አዳነን እንጂ፥ እኛ ስላደረግነው በጽድቅ ስለ ነበረው ሥራ አይደለም።” (ቲቶ ፫፥) ይላል።

ቅዱስ ጴጥሮስ ለመዳን አስፈላጊ የሆነውን ጥምቀት ምሳሌውን ተርጉሞ ሲናገር “ ጥቂቶች ማለት ስምንት ነፍስ በውኃ የዳኑበት መርከብ ሲዘጋጅ፥ የእግዚአብሔር ትዕግሥት በኖኅ ዘመን በዘገየ ጊዜ ቀድሞ ክደውት ለነበሩት ሰበከላቸው፤ አሁንም እኛን በዚያው አምሳል በጥምቀት   ያድነናል፥ ሥጋን በዕድፍ በታመጠብ አይደለም፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርሰቶስ በመነሣቱ በእግዚአብሔርን መልካም ግብርን ያስተምር ዘንድ ነው እንጂ፡፡ (፩ኛጴጥ. ፫፥፳-፳፩) በማለት ጥምቀት የሰውነትን እድፍ ማስወገድ ሳይሆን ውስጣዊ እድፍን (ኃጢአትን) ማስወገጃ ምሥጢር መሆኑን ይመሰክራል።

ጴጥሮስም እንዲህ አላቸው፦ “ንስሓ ግቡ፥ ሁላችሁም በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ተጠመቁ፤ ኃጢአታችሁም ይሰረይላችኋል፡፡ የመንፈስ ቅዱስንም ስጦታ ትቀበላላችሁ።” (ሐዋ. ፪፥፴፰)  ቅዱስ ጴጥሮስ ያስተማራቸውን አይሁድ የዘለዓለም ሕይወትን እንዲወርሱ ማድረግ ያለባቸውን ሲናገር መጠመቅ እንዳለባቸው አረጋግጧል።

. ለዳግም ልደት

አንድ ሰው በሥጋው ከእናት እና አባቱ እንደሚወለድ ከመንፈስ ቅዱስም በጥምቀት አማካኝነት መንፈሳዊ ልደትን ይወለዳል። “ኢየሱስም መለሰ፥ እንዲህ ሲል፦ እውነት እውነት እልሃለሁ፥ ሰው ከውኃና ከመንፈስ ካልተወለደ በቀር ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ሊገባ አይችልም።” (ዮሐ. ፫፥፭) በጥምቀት የሚገኘው ልጅነት የማይጠፋ እና ዘለዓለማዊ የልጅነት ማረጋገጫ ነው። “ዳግመኛ የተወለዳችሁት ከሚጠፋ ዘር አይደለም፥ በሕያውና ለዘለዓለም በሚኖር በእግዚአብሔር ቃል ከማይጠፋ ዘር ነው እንጂ።” (፩ኛ የጴጥ. ፩፥፳፫)

በጥምቀት የምናገኘው የልጅነት ጸጋ የመንግሥቱ ወራሾች ያደርገናል።ልጆችም ስለ ሆናችሁ እግዚአብሔር አባ አባት ብሎ የሚጮኽ የልጁን መንፈስ በልባችሁ ውስጥ ላከ። ለዚህ ከእንግዲህ ወዲህ ልጅ ነህ እንጂ ባሪያ አይደለህም፤ ልጅም ከሆንህ ደግሞ በክርስቶስ የእግዚአብሔር ወራሽ ነህ።” (ገላ. ፬፥፮-፯) ጥምቀት ከዲያብሎስ ባርነት ወጥተን የእግዚአብሔርን ልጅነት የምናገኝበት፣ የመንግሥቱ ወርሽ የምንሆንበት ምሥጢር ነው።

. ከክርስቶስ ጋር አንድ መሆን

ጥምቀት የጌታችንን ሞቱን እና ትንሣኤውን ማመናችንን በተግባር የምንመሰክርበት እና ከሞቱ እና ከትንሣኤው የምንሳተፍበት ምሥጢር ነው።  ስንጠመቅ ወደ ውኃ ውስጥ መግባታችን የሞቱና የመቀበሩ ምሳሌ ነው። መውጣታችን ደግሞ የመነሣቱ ምሳሌ ነው። “ከክርስቶስ ኢየሱስ ጋር አንድ እንሆን ዘንድ የተጠመቅን ሁላችን ከሞቱ ጋር አንድ እንሆን ዘንድ እንደ ተጠመቅን አታውቁምን? እንግዲህ ክርስቶስ በአብ ክብር ከሙታን እንደ ተነሣ እንዲሁ እኛም በአዲስ ሕይወት እንድንመላለስ፥ ከሞቱ ጋር አንድ እንሆን ዘንድ በጥምቀት ከእርሱ ጋር ተቀበርን። ሞቱንም በሚመስል ሞት ከእርሱ ጋር ከተባበርን ትንሣኤውን በሚመስል ትንሣኤ ደግሞ ከእርሱ ጋር እንተባበራለን።” እንዲል (ሮሜ ፮፥ ፫)   

ከውኃ ውስጥ ሦስት ጊዜ ብቅ ጥልቅ ማለቱ ጌታ በመቃብር ውስጥ ሦስት ቀን እና ሌሊት መቆየቱን ያስረዳል። በሦስተኛው ከውኃ መውጣቱ ጌታ በሦስተኛው ቀን ከመቃብር ለመውጣቱ ማስረጃ ነው። ክርስቲያኖች ከክርስቶስ ጋር እንነሣለን። በመጀመሪያ የነፍስ ትንሣኤን እናገኛለን። በመጨረሻ ደግሞ ነፍስና ሥጋቸን ተዋሕደው እንነሣለን። የነፍስ ትንሣኤ የተባለው በእምነትና በጥምቀት የምናገኘው ትንሣኤ ሲሆን በነፍስ ገነት መግባትን ያመለክታል። (ትምህርተ ሃይማኖትና ክርስቲያናዊ ሕይወት ገጽ ፪፻፵፯)።

. ክርስቶስን ለመልበስ

አሮጌውን አዳማዊ ሰውነታችንን አስወግደን “አዲስ ሰው” የተባለ ዳግማዊ አዳም ኢየሱስ ክርስቶስን የምንለብሰው በጥምቀት ነው። ጥምቀት ለሕይወት የሆነ አዲስ ሰውነትን ገንዘብ የምናደርግበት ምሥጢር ነው። “ከክርስቶስ ጋር አንድ ትሆኑ ዘንድ የተጠመቃችሁ ሁሉ ክርስቶስን ለብሳችኋልና።” (ገላ. ፫፥፳፯) ያልተጠመቀ ሰው ማንም ቢሆን ክርስቶስን ሊለብስ እና አዲስ ተፈጥሮን ገንዘብ ማድረግ አይችልም። “እርስ በርሳችሁ ውሸት አትነጋገሩ፥ አሮጌውን ሰው ከሥራው ጋር ገፋችሁታልና። የፈጠረውንም ምሳሌ እንዲመስል ዕውቀትን ለማግኘት የሚታደሰውን አዲሱን ሰው ለብሳችሁታል።” (ቆላ. ፫፥፱-፲)

. መንግ ሰማያትን ለመውረስ

ጥምቀት የእግዚአብሔርን መንግሥት የምንወርስበት ነው። እግዚአብሔር የሰጠንን ጸጋ ለመቀበል በጥምቀት የእግዚአብሔር ልጆች ሆነን ካልተወለድን በስተቀር ከእናት ከአባት በተወለድነው ተፈጥሯዊና ሥጋዊ ልደት መንፈሳዊ እና ሰማያዊ የሆነውን የእግዚአብሔርን መንግሥት ለመውረስ አንችልም። “ኢየሱስም መልሶ፦ እውነት እውነት እልሃለሁ፥ ሰው ዳግመኛ ካልተወለደ በቀር የእግዚአብሔርን መንግሥት ሊያይ አይችልም” (ዮሐ. ፫፥፭) አለው።  ጥምቀት አዲስ ልደት ተብሏል። “እንደ ምሕረቱ መጠን ለአዲስ ልደት በሚሆነው መታጠብና በመንፈስ ቅዱስ በመታደስ አዳነን እንጂ፥ እኛ ስላደረግነው በጽድቅ ስለ ነበረው ሥራ አይደለም” (ቲቶ ፫፥፭)

. የቤተ ክርስቲያን አባል ለመሆን

በኦሪተ የተገረዙ ሁሉ የእግዚአብሔር ወገንነትን መብት እንደሚያገኝ ሁሉ በጥምቀት የቤተ ክርስቲያን አባልነት መብት እናገኛለን። ምክኛቱም ግዝረት በጥምቀት ተተክቷልና።

“የሥጋንም ሰውነት በመገፈፍ፥ በክርስቶስ መገረዝ፥ በእጅ ባልተደረገ መገረዝ በእርሱ ሆናችሁ ደግሞ ተገረዛችሁ፤ በጥምቀትም ከእርሱ ጋር ተቀብራችሁ፥ በጥምቀት ደግሞ፥ ከሙታን ባስነሣው በእግዚአብሔር አሠራር በማመናችሁ፥ ከእርሱ ጋር ተነሣችሁ። እናንተም በበደላችሁና ሥጋችሁን ባለመገረዝ ሙታን በሆናችሁ ጊዜ፥ ከእርሱ ጋር ሕይወትን ሰጣችሁ፤ በደላችሁን ሁሉ ይቅር አላችሁ፤ በእኛ ላይ የነበረውን የሚቃወመንንም በትእዛዛት የተጻፈውን የዕዳ ጽሕፈት ደመሰሰው፤ እርሱንም በመስቀል ጠርቆ ከመንገድ አስወግዶታል።” (ቆላ. ፫፥፲፩-፲፫)

የጥምቀት ምሳሌ በብሉይ ኪዳን

፩. አብርሃም ዮርዳኖስን ተሻግሮ ከመልከ ጼዴቅ ጋር መገናኘቱ፦ አበ ብዙኃን አብርሃም ለአምስቱ ነገሥተ ሰዶም ረድቶ አራቱን ኮሎዶጎሞርን ድል ነሥቶ ሲመለስ ዮርዳኖስን ተሻግሮ ሲሔድ መልከ ጼዴቅ ኅብስተ በረከት ጽዋዓ አኮቴት ይዞ ተቀብሎታል። አብርሃም፦ የምእመናን፣ ዮርዳኖስ፦ የጥምቀት፣ መልከ ጼዴቅ፦ የቀሳውስት፣ ኅብስተ በረከት ጽዋ አኮቴት፦ የሥጋው የደሙ ምሳሌ ነው።

፪ ኢዮብ ከዮርዳኖስ ወንዝ ተጠምቆ ከደዌው ድኗል። ኢዮብ፦ የአዳም፣ ደዌ፦ የመርገመ ሥጋ የመርገመ ነፍስ፣ ዮርዳኖስ ፦ የጥምቀት ምሳሌ ነው።

፫. እስራኤል ዮርዳኖስን ተሻግረው ምድረ ርስት እንደገቡትም እመናንም አምነው ተጠምቀው ገነት መንግሥተ ሰማያት ለመግባታችን ምሳሌ ነው።

፬. ንዕማን በዮርዳኖስ ተጠምቆ ከደዌው ተፈውሷል። ንዕማን፦ የአዳም፣ ደዌ፦ የመርገመ ሥጋ፣ የመርገመ ነፍስ፣ ዮርዳኖስ፦ የጥምቀት ምሳሌ ነው።

የጥምቀት ዓይነቶች

ጥምቀት ከሦስት ወገን ነው።

፩ኛ. መዝገበ ውሉድ ፍቁራን የምትባል የጌታ ጥምቀት

፪ኛ. ጥምቀተ ዮሐንስ

፫ኛ. ጥምቀተ አይሁድ ናቸው።

ጥምቀተ አይሁድ እና ጥምቀተ ዮሐንስ አንድ አይሆንም ሁሉም ልጅነት አያሰጥም ቢሉ አንድ አይደሉም፤ ከሰውነታቸው ሰውነቱ እንዲበልጥ ከጥምቀታቸውም ጥምቀቱ ይበልጣል። አንድም ጥምቀት ከስምንት ወገን ነው። አራቱ ምሳሌያዊ አራቱ አማናዊ ናቸው።

ምሳሌያዊ የሚባሉት

፩ኛ. አጥመቃ ለምድር በማየ አይህ፤ ምድር በማየ ዐይህ መጠመቅ

፪ኛ. ወለኩሎሙ አበዊነ አጥመቆሙ ሙሴ በደመና፤  “ወንድሞች ሆይ፥ ይህን ታውቁ ዘንድ እወዳለሁ። አባቶቻችን ሁሉ ከደመና በታች ነበሩ ሁሉም በባሕር መካከል ተሻገሩ፤ ሁሉም ሙሴን ይተባበሩ ዘንድ በደመናና በባሕር ተጠመቁ።” (፩ኛቆሮ. ፲፥፩-፪)

፫ኛ. ወተጠምቃ እገሪሆሙ ለካህናት፤ የካህናት እግሮቻቸው የዮርዳኖስን ውኃ በመርገጣቸው እንደ ጥምቀት ሆናቸው። (ኢያ. ፫፥፲፮)

፬ኛ. ጥምቀት ዮሐንስ፦ ዮሐንስ መጥምቁ ሲያጠምቃት የነበረችው ጥምቀት ናት። ዮሐንስ ለንስሓ በውኃ ብቻ እንጂ በመንፈስ ቅዱስ ስላላጠመቀ የዮሐንስ ጥምቀት የንስሓ እንጂ አማናዊ አልነበረችም።

 አማናዊ ጥምቀት

፩ኛ. መዝገበ ውሉድ ምቁራን የምትባል የጌታ ጥምቀት፦ በ፵ በ፹ ቀን ከውኃ እና ከመንፈስ የምንወለድባት አማናዊቷ ጥምቀት ነች።

. አንብዓ ንስሓ፦ ማለት በንስሓ ጊዜ የሚፈሰው የለቅሶ፣ የሐዘን ዕንባ ነው። የንስሓ ዕንባ ሥርየተ ኃጢአትን ስለሚያሰጥ እንደ ጥምቀት ይቆጠራል። (ድርሳነ ጎርጎርዮስ ፴፱፥፲)

. ደመ ሰማዕት፦ ደምን በማፍሰስ የምትፈጸም ጥምቀት ናት። ይህች ጥምቀት ክርስቶስን መምሰል የምታሰጥ እጅግ የከበረች ጥምቀት ናት፤ ዋጋዋም ከፍ ያለ ነው።

4. ባሕረ እሳት፡- እንደ ደመ ሰማዕታት በእሳት ባሕር ተጠምቆ ድኅነትን መግኘት ነው።

ጥምቀት ስንት ጊዜ ትፈጸማለች?

በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ የምትፈጸም ጥምቀት አንዲት ናት ። አንድ ጊዜ ከተፈጸመች  (ከተሰጠች) አትደገምም። ከቤተ ክርስቲያን የማይደገሙ ምሥጢራት መካከል አንዷ ነች። በካህን፣ በኢጲስ ቆጶስ እጅ የምትፈጸም ጥምቀት አንዲት ነች ። “ሊቀ ጳጳስ ወይም ኢጲስ ቆጶስ ሳይመጣ አናጠምቅም አይበሉ፤ የማጥመቅ ሥልጣን ያለው ያጥምቅ እንጂ፣ የጥምቀት ሥልጣን አንዲት ናት ።” (ፍትሃ ነገሥት አንቀጽ ፫፥፳፱)። አማናዊቱ ጥምቀት አንዲት ናት ። “አንድ ጌታ፣ አንድ ሃይማኖት፣ አንዲት ጥምቀት።” (ኤፌ. ፬፥፭)

ለምን በየዓመቱ ይከበራል?

ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን የጥምቀት በዓልን የምታከበረው የጌታችን የማዳኑን ምሥጢር ለማዘከርና  ለመመስከርም ነው፡፡ አቡነ ጎርጎርዮስ ካልዕ “የጠበሉን መረጨት አይተው  በቀድሞ ዘመን ወደ ሀገራችን መጥተው የነበሩ ኢየሱሳውያን የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን  በየዓመቱ ታጠምቃለች” ያሉትን መልስ ሲሰጡ “ይህን ምትፈጽመው ጌታችን ለእኛ ብሎ ያሳየውን ትሕትና ለመመስከር እና  ለምእመናን የጌታችን በረከተ ጥምቀት ለማሳተፍ እንጂ የተጠመቁትን ምእመናን  እየመለሰች በየዓመቱ አታጠምቅም” ብለዋል፡፡(የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ታሪክ ገጽ ፻፳፫)። ስለዚህ የጥምቀትን በዓል በየዓመቱ የምናከብረው ጌታችን ለኛ ያደረገውን የድኅነት መንገድ ለማሰብ፣ ከዲያብሎስ ቁራኝነት ነጻ የወጣንበትን ምሥጢር ለመዘከር፣ ጌታችን ከገሊላ ወደ ዮሐንስ ያደረገውን ጉዞ ለማሰብ፣ ከበዓለ ጥምቀቱ በረከተ ሥጋ በረከተ ነፍስን ለማግኘት ነው።

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

0 replies

Leave a Reply

Want to join the discussion?
Feel free to contribute!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *