ሰሙነ ሕማማት ዕለተ ረቡዕ
በሰሙነ ሕማማት ሰኞ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መራቡንና ከቅጠል በስተቀር ፍሬ ያልተገኘባትን በለስ አግኝቶ ፍሬ አልባ ቅጠል ብቻ ሆና አግኝቷታልና “እንግዲህ ወዲህ ለዘለዓለም ፍሬ አይኑርብሽ” በማለት እንደ ረገማትና ወዲያውኑ በለሲቱ እንደ ደረቀች የሚታሰብበት ቀን እንደሆነ ባለፉት ክፍሎች ተመልክተናል፡፡ (ማቴ. ፳፩፥፲፰-፲፱)
በሰሙነ ሕማማት ዕለተ ማክሰኞ (ሁለተኛ ቀን) ደግሞ የጥያቄ ቀን በመባል እንደሚታወቅ ተገልጿል፡፡ ሹመትን ወይም ሥልጣንን ለሰው ልጅ የሰጠ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሰኞ ዕለት አንጽሖተ ቤተ መቅደስን ከፈጸመ በኋላ በዕለተ ሠሉስ ወደ ቤተ መቅደስ ገብቶ ሲያስተምር የካህናት አለቆችና የሕዝቡ ሽማግሌዎች ወደ እርሱ መጥተው “በማን ሥልጣን ይህ ታደርጋለህ? ይህንስ ሥልጣን ማን ሰጠህ?” በማለት ጠይቀውታልና የጥያቄ ቀን በመባል ይታወቃል፡፡ እንዲሁም ዕለተ ሠሉስ የትምህርት ቀን በመባልም ይጠራል፡፡ ጌታችን ከፍቅረ እግዚአብሔር የተለዩትን አስተምሮ ማቅረብና መክሮ መመለስ እንደሚገባን በቤተ መቅደስ ውስጥ ሆኖ ረጅም ትምህርት በማስተማሩ የተሰጠው ስያሜ ነው፡፡
በዕለተ ረቡዕ የሚከተሉት ሦስት ነገሮች ተፈጽመዋል፡-
ምክረ አይሁድ፡- የካህናት አለቆች፣ የሕዝብ ሽማግሌዎችና ጸሐፍት ፈሪሳውያን በጌታችን ላይ ተማክረዋል፡፡ “ፋሲካም የሚባለው የቂጣ በዓል ቀረበ፡፡ የካህናት አለቆችና ጻፎችም ሊገድሉት ይሹ ነበር፤ ነገር ግን ሕዝቡን ይፈሩአቸው ነበር፡፡ ቁጥሩ ከዐሥራ ሁለቱ በነበረው በስቆርቱ ይሁዳ ልብ ሰይጣን አደረ፡፡ ሄዶም ከካህናት አለቆችና ከታላላቆች ጋር እርሱን አሳልፎ እንዲሰጣቸው ተነጋገረ” እንዲል፡፡ (ሉቃ. ፳፪፥፩)
በዚህም መሠረት ይህቺ ዕለት የአይሁድ ሊቃነ ካህናትና ጸሐፍት ፈሪሳውያን ጌታ ኢየሱስን እንዴት መያዝ እንዳለባቸው ምክር የመከሩበት፣ ምክራቸውንም ያጸኑበትና ሰቅለው ይገድሉት ዘንድ የወሰኑበት ቀን በመሆኑ የአይሁድ የምክር ቀን ተብላ ትጠራለች፡፡ በዚሁ ምክራቸው ወቅት ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን እንዴት አድርገው እንደሚይዙት በጣም ይጨነቁ ነበር፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ወቅቱ የፋሲካ በዓላቸውን የሚያከብሩበት ወቅት በመሆኑ በጌታችን ትምህርት የተማረኩ ብዙ ሕዝብ ትምህርቱን ያደንቁ ስለነበር ሁከት እንዳይፈጠር ከመፍራታቸው የተነሣ ነው፡፡ በዚህ ጭንቀት ሳሉ ከደቀ መዛሙርቱ መካከል አንዱ የሆነው የአስቆሮቱ ይሁዳ በመካከላቸው ተገኝቶ ጌታችንን በመሳም አሳልፎ እንደሚሰጣቸው ለዚህ ተግባሩም ሠላሳ ብር ወረታውን እንዲከፍሉት ከእነርሱ ጋር በመስማማቱና የምክራቸው ተባባሪ በመሆኑ ጭንቀታቸውን አስወግዶላቸዋል፡፡ (ማር. ፲፬፥፲)
የመልካም መዓዛ ቀን፡- ጌታችን በስምዖን ዘለምጽ ቤት ሳለ ራስዋን በዝሙት አስገዝታ ትኖር የነበረችው ማርያም እንተ ዕፍረት (ባለ ሽቱዋ ማርያም) ሽቱ ቀብታዋለች፡፡ “እርሱም በቢታንያ በለምጻሙ በስምዖን ቤት በማዕድ ተቀምጦ ሳለ አንዲት ሴት ዋጋው የከበረ ጥሩ የናርዶስ ሽቱ የሞላበት የአልባስጥሮስ ብልቃጥ ይዛ መጣች፤ ብልቃጡንም ከፍታ በራሱ ላይ አፈሰሰችው” (ማር. ፲፬፥፫) በዚህም ምክንያት ዕለቱ የመልካም መዓዛ ቀን ተብሏል፡፡
የዕንባ ቀን፡– ማርያም እንተ ዕፍረት በጌታችን እግር ላይ ተደፍታ መላ ኃጢአቷን ይቅር እንዲላት በዕንባዋ እግሩን እያጠበች በፀጉሯም እግሩን እያበሰች ስለ ኃጢአቷ ሥርየት ተማጽናዋለችና የዕንባ ቀን በመባልም ተሰይሟል፡፡ (ማቴ.፳፮፥፮-፲፫፣ ማር.፲፬፥፫-፱፣ዮሐ.፲፪፥፩-፰)
Leave a Reply
Want to join the discussion?Feel free to contribute!