ትንሣኤ ምንድን ነው?

ክርስቶስ ተንሥአ እሙታን…….በዐቢይ ኃይል ወሥልጣን

አሰሮ ለሰይጣን……..አግዓዞ ለአዳም

ሰላም….….እምይእዜሰ

ኮነ…….ፍሥሓ ወሰላም

እንኳን ለብርሃነ ትንሣኤው በሰላም አደረሳችሁ

ትንሣኤ፡– ትንሣኤ ተንሥአ ተነሣ ከሚለው የግእዝ ቃል የወጣ ሲሆን ትርጉሙ መነሣት ማለት ነው፡፡ ይኸውም የሰው ልጅ ሞቶ ሥጋው ፈርሶ በስብሶ እንደማይቀር እና በዳግም ምጽአት ጊዜ እንደሚነሣ የሚያመለክት ነው፡፡ የሰው ልጅ ከፈጣሪ የተሰጠውን ትእዛዝ ባለመጠበቁ ምክንያት የሞት ሞት ተፈርዶበት ነበረ፡፡ “እንዳትሞቱ ከእርሱ አትብሉ፣ አትንኩትም” ተብሎ ነበርና፡፡ (ዘፍ.፫፣፫) በዚህም ምክንያት ከአቤል ጀምሮ እስከ እለተ ምጽአት ድረስ የሰው ልጅ በሥጋ የሚሞት ሆኗል፡፡ ነገር ግን እንደሞትን አንቀርም፡፡ ሁላችንም ትንሳኤ አለን፡፡ ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከሙታን ተለይቶ በመነሣት የትንሣኤያችን በኩር ሆኖናልና፡፡(፩ኛ ቆሮ.፲፭፣፳፩)፡፡

“ሞት በሰው በኩል ስለመጣ ትንሳኤ ሙታን በሰው በኩል ሆኗል›› እንዲል፡፡ ዘለዓለማዊ ሞታችን እና ፈርሶ በስብሶ መቅረት የቀረልን አካላዊ ቃል ሥጋችን ተዋሕዶ ሰው ሆኖ ሞትን በሞቱ ድል ከነሣልን በኋላ ነው፡፡ ሊቁ ሱኑትዩ በሃይማኖተ አበው “ሞተ ክርስቶስ በሞተ ዚኣነ ከመ ይቅትሎ ለሞት በሞቱ፤ ሞትን በሞቱ ያጠፋልን ዘንድ ክርስቶስ በተዋሐደው ሥጋ የእኛን ሞት ሞተ ብሎ እንደገለጠው፡፡ (ዮሐ.፲፩፣፳፭)

“ትንሣኤና ሕይወት እኔ ነኝ” ያለ ጌታ በጥንተ ትንሣኤ መጋቢት ፳፱ ቀን በዕለተ እሑድ ከሙታን ተለይቶ ተነሣ፡፡ ማር.(፲፮፣፮) መልአኩም “አትደንግጡ የተሰቀለውን የናዝሬቱን ኢየሱስ ትሻላችሁን? ተነሥቷል” ብሎ ለቅዱሳት አንስት ነግሯቸዋል፡፡ (ሉቃ.፳፬፣፮)፡፡

የክርስቶስ ትንሣኤ ከአልዓዛር ትንሣኤ የተለየ ነው፡፡ አልዓዛርን ያስነሣው ራሱ ክርስቶስ ሲሆን ትንሣኤውም መልሶ ሞት ነበረበት፡፡ ክርስቶስ ግን የተነሣው በራሱ ሥልጣን ነው፡፡ ዳግመኛ ሞትም የለበትም፡፡(ዮሐ.፪፥፲፱፤ ፲፥ ፲፰)”ይህን ቤተ መቅደስ አፍርሱት በሦስት ቀንም አነሧዋለሁ” ካለ በኋላ እርሱ ግን ይህንን የተናገረው ቤተ መቅደስ ስለተባለ ሰውነቱ ነበር ይለዋል፡፡ በሌላም የወንጌል ክፍል “እናንተ በሰቀላችሁት እግዚአብሔርም ከሙታን ባስነሣው በናዝሬቱ ኢየሱስ ክርስቶስ ሥም… ይላል፡፡(ሐዋ.፬፣፲) በሃይማኖተ አበው ደግሞ መንፈስ ቅዱስ አስነሳው የሚል ይገኛል፡፡ ይህን ቢል ሦስቱ አካላት አንዲት ግብረ ባሕርይ ስላላቸው ያችን ለእያንዳንዱ አካላት አድሎ መናገሩ ነው፡፡ አብ አምላክ፣ ወልድ አምላክ፣ መንፈስ ቅዱስ አምላክ ቢል ሦስት አምላክ አንልም፡፡ አንድ አምላክ እንላለን እንጂ፡፡ (ዮሐ.፲፥፴) “እኔና አብ አንድ ነን”(ዮሐ.፲፥፱) እንዲል፡፡ ማስነሣት ሦስቱ አካላት አንድ የሚሆኑበት ግብር ስለሆነ አብ አስነሣው፣ በራሴ ሥልጣን ተነሣሁ፣ መንፈስቅዱስ አስነሣው ቢል አንድ ነው፡፡

የትንሣኤ ዓይነቶች

በዳግም ምጽአት ጊዜ ሙታን ሲነሡ ሁለት ዓይነት ትንሣኤ ይነሣሉ፡፡ አንደኛው ትንሣኤ ዘለክብር ሲሆን ሁለተኛው ትንሣኤ ዘለኀሣር ነው፡፡ ትንሣኤ ዘለክብርን የሚነሡ የእግዚአብሔርን ትእዛዝ የፈጸሙ ቅዱሳን ናቸው፡፡ ትንሣኤ ዘለኀሣርን የሚነሡት ደግሞ የእግዚአብሔርን ሕግ ያልፈጸሙ ኃጥአን ናቸው፡፡ (ማቴ.፳፭፥፵፮) “እነዚያም (ኃጥአን) ወደ ዘለዓለም ቅጣት ጻድቃን ግን ወደ ዘለዓለም ሕይወት ይሄዳሉ” ተብሎ እንደተገለጠ፡፡ ትንሣኤ ዘለክብርን የተነሡ ጻድቃን ለዘለዓለም በመንግሥተ ሰማያት በተድላ በደስታ ይኖራሉ፡፡ ትንሣኤ ዘለኀሣርን የተነሡ ኃጥአን ደግሞ ለዘለዓለም በገሃነመ እሳት በሥቃይ በሰቆቃ ይኖራሉ፡፡

የትንሣኤ ምሳሌዎች

. ፀሐይ፡-

ፀሐይ የመውጣቷ የመወለዳችን ምሳሌ ነው፡፡ ፀሐይ ጠዋት ወጥታ ስታበራ እንድትውል እኛም ተወልደን በዚች ምድር ለመኖራችን ምሳሌ ነው፡፡ በሠርክ ፀሐይ መግባቷ የመሞታችን ምሳሌ ነው፡፡ መልሳ ጠዋት መውጣቷ የትንሣኤያችን ምሳሌ ናት፡፡ (ሃይ.አበ.፶፰፥፭)

. ዖፈ ፊንክስ፡-

ይህ ወፍ የሚሞትበት ቀን እንደደረሰ ባወቀ ጊዜ ብዙ ጭቃ ሰብስቦ ወደ ግብጽ ይሄዳል፡፡ በጭቃው ላይ ቆሞ ክንፉን በደረቱ ባማታው ጊዜ ከአካሉ እሳት ወጥቶ ሥጋውን አጥንቱን ሁሉ ያቃጥለዋል፡፡ በእግዚአብሔር ትእዛዝ ዝናም የያዘ ደመና መጥቶ ዝናም ይዘንማል፡፡ እሳቱንም ያጠፋዋል፡፡ ከዚያ ከአመዱ ትንኝ ይገኛል፡፡ክንፍም ይበቅልለታል፡፡ ቡላል አህሎ ያድራል፡፡ በሦስተኛው ቀን እንደቀደመ አካሉ ይመለስለታል፡፡

የራሳችን ፀጉርም ከተላጨ በኋላ መልሶ ሌላ አዲስ ፀጉር ይበቅልልናል፡፡ የእጅ ጥፍርም እንዲሁ ከተቆረጠ በኋላ አዲስ ጥፍር ይወጣል፡፡ ይህ ሁሉ ምሳሌ ዘየሐጽጽ ነው፡፡ እኛ በምንነሣበት ጊዜ ይዘነው የምንነሣው ሥጋ የማይራብ የማይጠማ ሥጋን ነው፡፡ በምስጋና እና በጸጋ ላይ ጸጋ እየተጨመረለት የሚሄድ ሥጋን ይዘን ነው የምንነሣው፡፡ ሌላው እና ዋናው ግን በኃጢአት የወደቅን ሰዎች በንስሓ ተነሥተን አዲስ ልብን ገንዘብ ማድረግ ይገባናል፡፡ ይህም ትንሣኤ ልቡና ይባላል፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

0 replies

Leave a Reply

Want to join the discussion?
Feel free to contribute!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *