እግዚአብሐርን ማመስገን

በዳዊት አብርሃም

ክፍል ሁለት

ላለማመስገን የሚቀርቡ ምክንያቶች

ለራሳችን መልካም የሆነውን ስለማናውቅ፡-

ጥሩ ነው ይበጀናል ብለን የምናስበው ነገር ይኖርና በእርግጥም ያንን ነገር ማግኘት የሚጠቅመን ሊመስለን ይችላል፡፡ እውነታው ደግሞ የሐሳባችን ተቃራኒ ሆኖ ሊገኝ ይችላል፡፡ ለእኛ የሚያስፈልገን በትክክል የሚያውቀው እግዚአብሔር ብቻ ነው፡፡ ሰለሆነም በእኛ ላይ ሊሆን ያለውን በሙሉ ለእርሱ ልንተው፣ እርሱ ለእኛ ያለውን ፈቃድ ልናምን ይገባናል፡፡ እመቤታችንና ጻድቁ ዮሴፍ ወደ ግብጽ እንዲሸሹ ሲታዘዙ ተቀብለው ፈጸሙት እንጂ አላቅማሙም፤ ወይም አላማረሩም፡፡ ሁል ጊዜ የእግዚአብሔር የሆነው አማራጭ እንዲበልጥ ማመን ካልቻልን እርሱ በፈቃዱ እንዲሆን በሚያደርገው ነገር ተደስተን ምስጋና ልናቀርብ አንችልም፡፡

የወደፊቱን ማሰብ አለመቻል፡-

ሳናመሰግን ስንቀር ያላመሰገንነው ባለፉት ጊዜያት ወይም በዚህ አሁን ባለንበት ጊዜ የገጠመንን ችግር በማስብ ብቻ ተወስነናል ማለት ነው፡፡ ይህ ሁኔታ በሚመጡት ዘመናት ሊቀየር ወይም ሊሻሻል አይችልም ብለን አስበናል፡፡ ውጤቱን ደርሶ ካላየነው በስተቀር ለማመስገን አንፈቅድም፡፡ ለምሳሌ ዕውር ሆኖ የተወለደውን ሰው ሁኔታ እንይ፡- ደቀ መዛሙርቱ ይህ ሰው በኃጢአቱ ነው እንዱህ የሆነው ብለው ደምድመው ጨርሰዋል፡፡ ጥያቄአቸው ውስጥ ድምዳሜአቸው ይሰማል፡፡ “ደቀ መዛሙርቱም መምህር ሆይ ይህ ሰው ዕውር ሆኖ እንዲወለድ ኃጢአት የሠራ ማነው? እርሱ ወይስ ወላጆቹ? ብለው ጠየቁት” (ዮሐ. ፱፥፪) ጥያቄአቸው የሚነግረን የአሕዛብ ተጽእኖ በከፍተኛ ደረጃ እንዳረፈባቸው ነው፡፡ ጌታ ግን ምስጋና የሚገባውን መለኮታዊ እቅዱን ገልጦ ነገሩ እነርሱ በክፉ እንዳሰቡት እንዳልሆነ አሳያቸው፡፡ “ኢየሱስም እንዲህ ብሎ መለሰ፡፡ የእግዚአብሔር ሥራ በእርሱ እንዲገለጥ ነው እንጂ እርሱ ወይም ወላጆቹ ኃጢአት አልሠሩም፡፡” (ዮሐ. ፱፥፫) ይህ ሰው ሲወለድ ጀምሮ ዕውር ባይሆን ኖሮ በእግዚአብሔር ለማመንም ሆነ ስለ ክርሰቶስ ለመመስከር አይችልም ነበር፡፡ ስለዚህ ያለፈውና ነባሩ ሁኔታው ለወደፊቱ መጥፎ ሆኖ አልቀጠለም፡፡ መጥፎ የነበረው ሁኔታው በጊዜው የሚያስከፋው ቢሆንም ለኋላው ግን ወደ አዲስ ሕይወት የሚያሸጋግር  ሆነለት፡፡ በታሪክ ውስጥ የሚወሳ፤   የእግዚአብሔርም ሥራ የሚገለጥበት ለመሆን በቃ፤ ለብዙዎች ማመንም ምክንያት ሆነ፡፡

ሌላው ለምሳሌ የአልአዛር ሞት ነው፡፡ የአልአዛር እኅት ማርያም እንዲህ ብላ ነበር፡፡ “ማርያምም ኢየሱስ ወዳለበት መጥታ ባየቸው ጊዜ በእግሩ ላይ ወድቃ ጌታ ሆይ አንተ በዚህ ኖረህ ብትሆን ወንድሜ ባልሞተም ነበር አለችው፡፡” (ዮሐ. ፲፩፥፴፪) ሆኖም የአልአዛር ሞት የላቀ ዓላማ ነበረው፡፡ የእርሱ ሞት እግዚአብሔር የሚከብርበት ነው፡፡ ኢየሱስም ሰምቶ ይህ ሕመም የእግዚአብሔር ልጅ በእርሱ ይከብር ዘንድ ስለ እግዚአብሔር ክብር ነው እንጂ ለሞት አይደለም አለ፡፡” (፲፩፥፬)

እግዚአብሔር የሰጠንን ነገር ሳናስብ ስንቀር፡-

የማያመሰግን ሰው ሁል ጊዜ የእግዚአብሔርን ውለታ ይረሳል፤ በረከቶቹ ላይ አያተኩርም፤ ሁል ጊዜ ሌላውን ብቻ ያስባል፡፡ ያጠውን፣ የጎደለበትን ወይም መጥፎ የሚለውን ገጠመኝ ብቻ ያስባል፡፡ በዚህም የተነሣ ያለፈው ዘመን ክፉ ብቻ ያመጣበት ይመስላል፡፡ ነቢዩ ዳዊት ግን ከእግዚአብሔር የተቀበለውን መልካምነት እያሰበ እንዲህ ይላል፡፡ “ነፍሴ ሆይ እግዚአብሔርን ባርኪ፣ ምስጋናውንም ሁሉ አትርሺ፡፡” (መዝ. ፻፫፥፪)

ትዕቢተኝነት፡-

በሥራችን ሁሉ ዋጋ የምንሰጠው ለራሳችንና ለገዛ ጥረታችን ብቻ ነው፡፡ እግዚአብሔር እንዳከናወነልን አንገነዘብም፡፡ በራስ መመካት ደግሞ ወደ ትዕቢት ይወስዳልና እግዚአብሔርን እንረሳለን፡፡ “እርስ በእርሳችሁ በአንድ ሐሳብ ተስማሙ የትዕቢትን ነገር አታስቡነገር ግን የትሕትናን ነገር ለመሥራት ትጉ” በማለት ቅዱስ ጳውሎስ ይመክረናል፡፡ (ሮሜ. ፲፪፥፲፮)

ከመልካም ገጠመኞች ይልቅ ክፉ ገጠመኞቻችን ላይ ይበልጡን በማተኮር ባሉበት መቆም፡-

የማያመሰግን ሰው ሁል ጊዜ ትኩረቱ አሉታዊ በሆኑ ያለፉ ነገሮች ላይ ብቻ የተወሰነ ነው፡፡ ባለፉት መጥፎ ገጠመኞች ላይ ተመሥርቶ የነገሮችን ከባድነት የበለጠ ያስባል፡፡ ስላለፉትም ሆነ አሁን ስላሉብን አሉታዊ ሐሳቦች ማሰብ እንደማይገባን ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ሲመሰክር “ወንድሞች ሆይ እኔ ገና እንዳልያዝኩት እቆጥራለሁ፤ ነገር ግን አንድ ነገር አደርጋለሁ፤ በኋላዬ ያለውን እየረሳሁ በፊቴ ያለውን ለመያዝ እዘረጋለሁ፡፡” (ሉቃ. ፫፥፲፫) እንዲል፡፡ ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም  “ኢየሱስ ግን ማንም እርፍ በእጁ ይዞ ወደኋላ የሚመለከት ለእግዚአብሔር መንግሥት የተገባ አይደለም አለው፡፡” (ሉቃ. ፱፥፷፪)

አለመርካት፡-

የማይረካ ሰው እግዚአብሔር የቱንም ያህል መልካሙን ሁሉ ቢሰጠው መርካት ይሳነዋል፡፡ አለመርካት ከራስ ወዳድነትና ከስስታምነት ይመነጫል፡፡ ሐዋርያው ከዚህ የተለየውን ሐሳብ ይዞ መገኘት እንደሚገባ ራሱን አርአያ አድርጎ ሲያስተምር እንዲህ ይላል፡፡ “ይህን ስል ስለ ጉድለት አልልም፤ የምኖርበት ኑሮ ይበቃኛል ማለትን ተምሬአለሁና፡፡” (ፊል. ፬፥፲፩)

አማራሪነት፡-

የሚያማርር ሰው  አመስጋኝ መሆን አይችልም፡፡ እንዲያውም አንዳንድ የማማረር ዝንባሌዎች ሥር እየሰደዱ የሥነ ልቡና ችግሮች ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ይህ ችግር የተጠናወተው ሰው ሲያማርር፣ ሲወቅስ፣ ሲቃወም ብቻ ይሰማል፡፡ ምንም ነገር ቢሆን አይጥመውም፤ አያስደስተውም፡፡ ይህ ችግር ሥነ ልቡናዊ ብቻ ሆኖ አይቀርም፤ ማኅበራዊ በሽታ ወደ መሆን ይዛመታል፡፡ እንዲሁም መንፈሳዊ ደዌም ነው፡፡

ራስ ወዳድነት፡-

ራስ ወዳድነት የሚያጠቃው ሰው ዘወትር ሐሳቡ እንዴት በቁሳዊ ነገሮች ራሱን ማርካት እንደሚችል ብቻ ነው፡፡ አንዱን ሲያገኝ ሌላው ስለሚያስፈልገው ለምስጋና የሚሆን ፋታ የለውም፡፡

ስለ ዓለማዊ ሀብት ብቻ ማሰብ፡-

ፍላጎታቸውና ግባቸው በሙሉ ገንዘብ፣ ዓለማዊ ደስታ፣ ዝና፣ ቁሳዊ ሀብት የሆኑ ሰዎች ሊረኩ፣ የምስጋና ሕይወት ሊኖራቸው አይችልም፡፡ በሆነ አጋጣሚ ከእነዚህ ሀብቶቻቸው መካከል አንዱን ቢያጡ ሕይወታቸው መራራይሆንባቸዋል፡፡ እጦታቸው ጊዜያዊ ብቻ እንኳ ቢሆን ትዕግሥት አይኖራቸውም፡፡

የእግዚአብሔርን ፈቃድ መተውና በራስ ፈቃድ ብቻ መመራት፡-

በራሱ ፈቃድ እየተመራ የእግዚአብሔርን ፈቃድ የሚዘነጋ ሰው የምስጋና ሕይወት አይኖረውም፡፡ ራሱ የሚሻውን እንጂ የእግዚአብሔርን ፈቃድ  አይጠይቅም፡፡ ያሰበውን ሁሉ ጥሩም ይሁን መጥፎ ሳይመዝን፣ ይጥቀመው ወይም ይጉዳው ሳይረዳ ጉዞውን ይቀጥላል፡፡ በዚህም ምክንያት ይሰናከላል፡፡

ኃጢአትን መርሳት፡-

የማያመሰግን ሰው ኃጠአቱን ለማሰብ ያልቻለ ሰው ነው፡፡ የኃጢአታችንን ብዛትና የእግዚአብሔርን ቸርነት የምናስታውስ ከሆነ በምስጋና መኖር ለእኛ በጣም ቀላል መሆኑ አይቀርም፡፡

በመከራ ውስጥ ያለንን በረከት ለመመልከት አለመቻል፡-

ስንፈተንና በመከራ ውስጥ ለማለፍ ስንገደድ ምላሻችን ማማረርና ሳይመሰግኑ መቅረት ይሆናል፡፡ በመከራ ውስጥ የእግዚአብሔርን ክብር ማየትና እርሱ የሚሰጠንን በረከት እንዳለ አምነን ማመስገን ተስኖናል ማለት ነው፡፡ የእግዚአብሔር ቃል ግን “ይህ ስለ ክርስቶስ ተሰጥቷችኋልና ስለ እርሱ መከራ ደግሞ ልትቀበሉ እንጂ በእርሱ ልታምኑ ብቻ አይደለም” ሲል ያስተምረናል፡፡ (ፊል.፩፥፳፱)፤ እንዲሁም “ልጆች ከሆንን ወራሾች ደግሞ ነን፣ ማለት የእግዚአብሔር ወራሾች ነን፤ አብረንም ደግሞ እንድንከብር አብረን መከራ ብንቀበል ከክርስቶስ ጋር አብረን ወራሾችን ነን፡፡” (ሮሜ. ፰፥፲፯) እንዲል፡፡

መቅረት የሌለበትና ሊቀርም እንደማይችል አድርጎ ማሰብ፡-

ምግብ፣ ውኃ፣ ልብስ፣ መጠለያና የመሳሰሉት ነገሮች ስለተሰጡን ልናመሰግን ቀርቶ እስከ ጭራሹም መኖራቸው ትዝ አይለንም፡፡ እነዚህ ነገሮች ተራና ሊኖሩንም ግድ የሆኑ የመስለናል፡፡ ስለዚህም ምስጋና ማቅረብ አስፈላጊ መስሎ አይታየንም፡፡ የእነዚህ አምላካዊ በረከቶች ምንነት የምንገነዘበው ስናጣቸው ነውና ብዙ ጊዜ ለምስጋና ምክንያት ሳናደርጋቸው እንዘነጋቸዋለን፡፡

  ይቆየን 

0 replies

Leave a Reply

Want to join the discussion?
Feel free to contribute!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *