“ጾም ትፌውስ ቁስላ ለነፍስ” (ጾመ ድጓ)
ጾም ሥጋ ለነባቢት ነፍስ ትገዛ ዘንድ የተሠራ ሕግ ነው፡፡ ልዑለ ባሕርይ ቅዱስ እግዚአብሔር በጥንተ ልደት ሰውን /አዳምን/ እንዲህ ብሎ አዘዘው፡፡ “ከገነት ዛፍ ሁሉ ትበላለህ፣ ነገር ግን መልካሙንና ክፉውን ከምታስታውቀው ዛፍ አትብላ፡፡ ከእርሱ በበላህ ቀን የሞት ሞትን ትሞታለህና፡፡” (ዘፍ.፪፤፲፮) ሲል የጾምን ሕግ ሲያስተምረው እናያለን፡፡ ከዐራቱ ባሕርያተ ሥጋና ከሦስቱ ባሕርያተ ነፍስ የተፈጠረው ሰው ለራሱ ሁለት ባሕርያት አሉት፡፡ እነዚህም ባሕርይ እንስሳዊና ባሕርይ መልአካዊ ይባላሉ፡፡
ባሕርይ እንስሳዊ ልብላ፣ ልጠጣ፣ ልደሰት፣ ይድላኝ ይላል፡፡ “ቀዳሜ ሕይወቱ ለሰብእ እክል ወማይ፣ አስቀድሞ የሰው ሕይወቱ እህልና ውኃ ነው፡፡” እንዲል መጽሐፈ ሲራክ፡፡ ዳዊትም “እክል ያጸንዕ ኃይለ ሰብእ፣ እህል የሰውን ኃይል ያጸናል” ይላልና፡፡ ባሕርይ መልአካዊ ደግሞ ልጹም፣ ልጸልይ፣ ልስገድ፣ ልመጽውት ይላል፡፡ “ዓይነ ኵሉ ነፍስ ይሴፎ ኪያከ፣ የሁሉ ሰውነት ዓይን አንተን ተስፋ ያደርጋል” እንዲል (መዝ.፻፵፬፤፲፭)፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጻውሎስም “በነገር ሁሉ፣ በጸሎትና በምልጃ ከምስጋና ጋር በእግዚአብሔር ዘንድ ልመናችሁን አስታውቁ እንጂ በአንዳች አትጨነቁ፡፡” (ፊል.፬፤፮) በማለት አበክሮ ያስገንዝባል፡፡ እንግዲህ የእግዚአብሔርን አገልግሎት በሚገባ ማከናወን የሚቻለው በጸሎት በመትጋት፣ በመጾም፣ በመስገድና ንጽሕናን በመጠበቅ እንደሆነ ከአበው የሕይወት ልምድ እንረዳለን፡፡
ጾም በኃጢአት ጦር ተወግታ ለቆሰለች ነፍስ ዓይነተኛ ፈውስ መሆኑና ከገቢረ ኃጢአት ወደ ገቢረ ጽድቅ ተመልሶ ከፈጣሪ ጋር ለመታረቅ የሚያስችል መሣሪያ መሆኑን በትንቢተ ኢዩኤል ተጽፎ እናገኛለን፡፡ እንዲህ ሲል ”አሁንስ ይላል እግዚአብሔር በፍጹም ልባችሁ በጾም፣ በልቅሶ፣ በዋይታ ወደ እኔ ተመለሱ” ይለናል፡፡ (ኢዩ.፪፤፲፪)፡፡ ሥጋ ደካማ ነው በምኞት ወጥመድ ይጠመዳል፣ በዚህ ዓለም ፍትወት ተተብትቦ ይወድቃል፡፡ ነገር ግን የሥጋን ምቾትና ፍላጎት በመግታት ለምግብና ለመጠጥ ምርኮኛ ከመሆን ርቀንና ተለይተን ሥጋችንን የምንቀጣበት መሣሪያ ጾም ነው፡፡ የመልካም ሥነ ምግባርም መፍለቂያ ምንጭ ነው፡፡
በመጽሐፈ መነኮሳት “ጾም ለጸሎት እናቷ፣ ለአርምሞ እህቷ፣ ለእንባ መፍለቂያው፣ ለበጎ ሥራ ሁሉ ጥንተ መሠረት ናት፡፡” ይላል፡፡ ስለዚህ ጾም ከጽሉላት ምግብ ብቻ የምንታቀብበት ብቻ ሳይሆን በጠቅላላው ሕዋሳተ ሥጋችንን የምንገታበት ልጓም ነው፡፡ ቅዱስ ያሬድ ጾመ ድጓ በተባለው የዜማ ድርሰቱ ላይ ይህንኑ ሲገልጽ እንዲህ ይላል፡- “ዓይን ክፉ ከማየት ይጹም፣ ልሣንም ክፉ ከመናገር ይጹም፣ ጆሮም ክፉ ከመስማት ይጹም ፍቅርንም በመያዝ” ይላል፡፡ ይህ ማለት በጾም ወራት በዓይናችን ቅዱሳት መጻሕፍትን እንድንመለከትበት፣ በአንደበታችን ቃለ እግዚአብሔርን እንድንናገርበት፣ በጆሮአችን መልካሙን ዜና ትምህርተ ወንጌል እንድናደምጥበት፣ ፍቅረ እግዚአብሔርና ፍቅረ ቢጽን ገንዘብ አድርገን በነፍስ በሥጋ እንደንጠቀምበት ያስገነዝበናል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ጾም በመንፈሳዊ የሕይወት ጉዞአችን መሰናክል ከሚሆኑን ርኩሳን መናፍስትና ረቂቃን አጋንንት ጋር በምናደርግው ውጊያና ተጋድሎ ላይ ኃይል እንድናገኝና ከፈተና እንድንድን ይረዳናል፡፡
ጾም እግዚአብሔር የማይወደውን ሥራ እየሠሩ ቢጾሙት ወይም በሰው ዘንድ ጿሚ መስሎ ለመታየትና ውዳሴ ከንቱን በመሻት ቢጾሙት ቅጣትን ያመጣል፡፡ ነገር ግን ከቂም ርቆ፣ ፍቅርን ይዞ የሠሩትን በማወቅም ባለማወቅ የፈጸሙትን ኃጢአት እያሰቡ በመጸጸት በዐንብዓ ንስሐ እያዘኑ እየተከዙ ቢጾሙት ሰማያዊ ዋጋ ያሰጣል፣ የኃጢአት ሥርየትን ያስገኛል፡፡
ሀገር በወራሪ ጠላት በተከበበች ጊዜ በኃጢአት አባር፣ ቸነፈር፣ በሽታና ረሓብ በታዘዘ ጊዜ ሕዝቡ ራሳቸውን ዝቅ አድርገው በንስሐ ተመልሰው ስለ ችግራቸው ከእግዚአብሔር እርዳታን ምሕረትን፣ ይቅርታን በተማጸኑ ጊዜ ምዓቱን በምሕረቱ፣ ቁጣውን በትዕግሥቱ መልስ አስገኝቶላቸው ከመከራ ሥጋ ይድናሉ፡፡ ይህም የጸሎት፣ የጾምና የጸሎት ውጤት ነው፡፡ ምእመናንም ይህን የመሰለ የጾምን ጠቃሚ መሣሪያነት በመረዳት በጾሙ ወራት ቅዱስ ዳዊት ”ብፁዕ ዘይሌቡ ላዕለ ነዳይ ወምስኪን፤ ለችግረኛና ለምስኪን የሚያስብ ምስጉን ነው፡፡” (መዝ.፵፤፩) ያለውን በማሰብ ለተራቡ ከእንጀራ ቆርሶ፣ ለተጠሙት ከማይ ቀድቶ፣ ለታረዙት አልብሶ ሌባ ግንቡን አፍርሶ ግድግዳውን ምሶ ከማይወስዱበት ከሰማያዊው ቤት መዝገብን ማኖር ያስፈልጋል፡፡ ለዚህም በዝናብ አብቅሎ፣ በፀሐይ አብስሎ ከሚመግብ ፈጣሪ ተስፋ በረከትን በመሻት መጾም ይገባል፡፡ ጾመን፣ ጸልየን በረከት እንድናገኝ አምላካችን እግዚአብሔር ይርዳን፡፡ አሜን፡፡
Leave a Reply
Want to join the discussion?Feel free to contribute!