ጾም ትፌውስ ቁስለ ነፍስ

ክፍል ሁለት

በዲ/ን መብራቱ ስንታየሁ (ከአዳማ ማእከል)

የጾም ዓይነቶች

የጾም ዓይነቶች ሁለት ናቸው እነርሱም የአዋጅ እና የፈቃድ በመባል ይታወቃሉ፡፡

ሀ. የዐዋጅ ጾም

የዐዋጅ ጾም የሚባሉት በዐዋጅ ለሁሉም ሰው ማለት ከሰባት ዓመት በላይ ለሆነ ሰው ሁሉ የሚታወጅ እና በይፋ ሁሉም ተባብሮ ስለሚጾማቸው ነው፡፡ “በጽዮን መለከትን ንፉ፥ ጾምንም ቀድሱ፥ ጉባኤውንም አውጁ፥” (ኢዩ ፪፥፲፭) እንደተባለ አንዴ በቤተ ክርስቲያን ታውጆ ሥርዓት ተሠርቶለት የሚጾም ስለ ሆነ የአዋጅ ጾም ይባላል፡፡ የአዋጅ ጾም በማለት ቅድስት ቤተ ክርስቲያን የምታውጃቸው እና ሁላችን በጋራ የምንጾማቸው አጽዋማት ሰባት ሲሆኑ እንደሚከተለው እንመለከታቸዋለን፡-

  1. ዓቢይ ጾም (ጾመ ሁዳድ)
  2. ጾመ ድኅነት (ዓርብ እና ረቡዕ)
  3. ጾመ ሐዋርያት (የሰኔ ጾም)
  4. ጾመ ፍልሰታ
  5. ጾመ ነቢያት (የገና ጾም)
  6. ጾመ ነነዌ
  7. ጾመ ጋድ ናቸው፡፡

ለ. የፈቃድ ጾም

የፈቃድ ጾም የሚባለው ሁሉም ሰው በዐዋጅ ሳይታዘዝ በፈቃዳችን የምንጾማቸው ናቸው፡፡ በቀኖና የሚሰጠን ጾም የሚመደበው ከዚህ ውስጥ ነው፡፡ አንዳዴም በተለየ ሁኔታ ለራሳችን የምንጾመው ጾምም የፈቃድ ይባላል፡፡ ለምሳሌ ጾመ ዮዲት (ጳጉሜን ላይ የሚጾም) እና ጾመ ጽጌ የሚጾሙ አሉ፤ እኒህም የፈቃድ አጽዋማት ናቸው፡፡

ውድ ተማሪዎች ጾም ፍቅርን ለእግዚአብሔር መግለጫ በመሆኑ ከልባችን ወደነው መጾም ይገባል፡፡ በጾም ስሜትን ራስን እንገዛበታለን፡፡ ጾም መንፈሳዊ ኃይልን ታጎናጽፋለች፤ አጋንንትን ለማራቅ እጅግ ትጠቅመናለች እንዲሁም ለመንፈሳዊ አገልግሎት የበረታን ታደርገናለች እና በአግባቡ በመጾም የምታሰጠውን ዋጋ ለማግኘት እንትጋ፡፡

እንደ ግብዞች አትጠውልጉ

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንዴት መጾም እንዳለብን የተራራውን ትምህርት ባስተማረበት ወቅት እንዲህ በማለት ተናገሮ እንመለከታለን “ስትጦሙም፥ እንደግብዞች አትጠውልጉ፤ ለሰዎች እንደጦመኛ ሊታዩ ፊታቸውን ያጠፋሉና፤ እውነት እላችኋለሁ፥ ዋጋቸውን ተቀብለዋል።” (ማቴ. ፮፥፲፮)። በዚህ ንባብ ግብዞች የሚለውን ቃል በሁለት መልኩ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ አስቀምጦት ይገኛል። እነዚህም፡-

 ፩. መጦመቸው እንዲታወቅላቸው ፊታቸውን የሚያጠፉ እንዲሁም ይጠወልጋሉ። እነዚህ ጦማቸውን ዋጋ ለሚከፍል እግዚአብሔር ከማሳየት ይልቅ ለሰዎች አድናቆት ለማግኘት ሲሉ ብቻ የጾምን ዓላማ ያጠፉታል።

፪. ሳይጾሙ እንደጾሙ የሚያስመስሉ ከንፈራቸውን የሚያደርቁ ግብዝ ተብለው ተጠርተዋል። የምንጾመው ከእግዚአብሔር ጋር ኅብረትን ለማድረግ ነው እንጂ ውዳሴ ከንቱን ለማግኘት አይደለም፤ በሁለቱም መልክ የተገለጡት ግብዞች ግን የጾምን ዓላማ የረሱና ያልተገነዘቡ ናቸው። በግብዝነት የሚገኘው ደስታ ጊዜያዊና ወዲያው የሚረሳ ነው ሆኖም ቅጣቱ ከባድ መሆኑን ዐውቆ መጠንቀቅ ይገባል።

የተወደዳችሁ ተማሪዎች በተለይ በልቶ ማስመሰል ውዳሴ ከንቱን መፈለግ ብቻ ሳይሆን ውሸትንም በውስጡ የያዘ ነውና ከግብዝነት በመራቅ በእውነት ለጾም ሕግና ሥርዓት ልንገዛ ይገባል። ለቤተሰብ ለጓደኛ ለቤተ ክርስቲያን አገልጋዮች ራሳችንን በውሸት ሕጋዊ አድርገን ለማሳየት ስንል መንግሥተ እግዚአብሔርን እንዳናጣ መጠንቀቅ ይገባል። ለሰው ጾመኛ ከመምሰል በመታቀብ ዋጋ ለሚከፍለው ጌታ ራስን ማሳየት ያስፈልጋል። ፊትን በማጥቆር ከመጾም ፊትን ከእግዚአብሔር የሚያገኙትን ዋጋ በእምነት በተስፋ በመጠበቅ ብሩህ ማድረግ በእጅጉ ይገባል። ጌታችን ጾሞ እንዴት መጾም እንዳለብን አስገንዝቦናል በዚያው መሠረት በመጾም ሥርዓትን ልንፈጽም ይገባል።

ክርስቶስ አምላካችን ዐርባ ቀንና ሌሊት በመጾም ጾም የመልካም ሥራ መጀመሪያ እንድትሆን ሰጥቶናል። እኛም የሐዋርያቱን ትውፊትና ኑሮ መሠረት በማድረግ ያማረ የጾም ሕግን ከትውልድ ትውልድ እንቀባበለዋለን። ጌታችን የጾመው በቁዔት አገኝበታለሁ ብሎ ሳይሆን አጋንንትን፣ የኃጢአት ሥሮች የተባሉ ትዕቢት፣ ስስት እና ፍቅረ ነዋይን የምናሸንፍበትን ሕግ ሊሠራልን እና ተግባሩን ሊያመለክተን ነው እንጂ ጾማችሁን ሁሉ ጾሜላችኋለሁ ከዚህ በኋላ መጾም አይጠበቅባችሁም ለማለት አይደለም።

የተወደዳችሁ ተማሪዎች በግቢ ሕይወታችሁ ከብዙ ማኅበረሰብ ጋር እንደመኖራችሁ በሃይማኖት ከማይመስሉን በተለይ ከመናፍቃን ጥያቄ ሊቀርብልን ይችላል። ለምሳሌ አጽዋማት ለድኅነት አያስፈልጉም አንዴ ክርስቶስ ጾሞልናል፤ በዚህ ጊዜ እንድትጾሙ የተጻፈው የት ነው? ወደ አፍ የሚገባ አያረክስም የሚለውን ሕግ ጥሳችኋል ሊሉን ይችላሉ።

ውድ ተማሪዎች ከመናፍቃን ጋር ያለን ልዩነት ሰፊና የመዳናችን መንገድ ላይ መሆኑን ልብ ማለት አለባችሁ ይህ ማለት ከላይ የጠቀስነው ንግግራቸው የሚመነጨው እምነት ብቻ ከሚለው አስተምሮአቸው ነው። ምግባር ለድኅነት አያስፈልግም በጸጋው ብቻ ድነናል ከሚለው አቋማቸው መሆኑን በመረዳት ከእነርሱ መራቅ ሐሳባቸውን አለመስማት ይኖርብናል። ምክንያቱም ጾም ትእዛዘ እግዚአብሔር ናት፤ ምግባር የእምነት ነፍስ ናትና “መጽሐፍም፦ አብርሃምም እግዚአብሔርን አመነ ጽድቅም ሆኖ ተቈጠረለት ያለው ተፈጸመ፤ የእግዚአብሔርም ወዳጅ ተባለ። ሰው በእምነት ብቻ ሳይሆን በሥራ እንዲጸድቅ ታያላችሁ። … ከነፍስ የተለየ ሥጋ የሞተ እንደ ሆነ እንዲሁ ደግሞ ከሥራ የተለየ እምነት የሞተ ነው።” (ያዕ. ፪፥፳፫-፳፮) እንደተባለ። እምነት ከምግባር ተዋሕዶ ሊገኝ ግድ ነው። እንግዲህ ከምግባራት ቀዳሚዋ ጾም መሆንዋ ደግሞ ሊዘነጋ አይገባውም። ጌታችን ስለ ሆድ ማሰብ ሞት እንደሆነ አስተምሮናል አስቀድመን ማሰብ የሚገባን ስለ ጽድቅ መሆኑንም አሳስቦናል “ጽድቅን የሚራቡና የሚጠሙ ብፁዓን ናቸው፥ ይጠግባሉና።” (ማቴ. ፭፥፮)። “ስለዚህ እላችኋለሁ፥ ስለ ነፍሳችሁ በምትበሉትና በምትጠጡት፥ ወይም ስለ ሰውነታችሁ በምትለብሱት አትጨነቁ፤ ነፍስ ከመብል ሰውነትም ከልብስ አይበልጥምን?” (ማቴ. ፮፥፳፭)።

ስለዚህ ክርስቶስ ጾሞልሃል የሚለውን የሰይጣን ትምህርት ትተን “ከመዝ ግበሩ፤ እንዲህ አድቡ” የሚለውን የክርስቶስን ድምጽ በመስማት የተወልንን የአርአያነት መንገድ በመከተል እውነተኛ በጎቹ ልንሆን ይገባል። “ነገር ግን አስቀድማችሁ የእግዚአብሔርን መንግሥት ጽድቁንም ፈልጉ፥ ይህም ሁሉ ይጨመርላችኋል።” (ማቴ. ፮፥፴፫) “ስትጦሙም፥ እንደ ግብዞች አትጠውልጉ፤ ለሰዎች እንደ ጦመኛ ሊታዩ ፊታቸውን ያጠፋሉና፤ እውነት እላችኋለሁ፥ ዋጋቸውን ተቀብለዋል።” (ማቴ. ፮፥፲፮።)  ‘ይህም ሁሉ’ የተባለው ምግብን እና መሰሎቹን ነው። ክርስቶስ አትጹሙ አላለም ስትጾሙ እንደ ግብዞች አትሁኑ በማለት አጿጿሙን ተናገረ እንጂ ስለዚህ ጾም ክርስቶሳዊ ትእዛዝ ነው።

ወደ አፍ የሚገባ አያረክስም በማለት ሆድን አምላክ በማድረግ ሊሾሙብን እንደ ሔዋን ራቁታችን ሆነን ገነትን መንግሥተ ሰማይን አጥተን እንዳንጠፋ መጠንቀቅ አለብን።  ውድ ተማሪዎች ተመልከቱ ጌታችን ስለ እጅ ንጽሕና ሲጨነቁ ስለ አመጋገብ ወጋቸው ከሕገ መጽሐፍ በላይ ሲያሳስባቸው ተመልክቶ የተናገራቸውን ነገር “እርሱም፦ እናንተ ደግሞ እንደዚህ የማታስተውሉ ናችሁን? ከውጭ ወደ ሰው የሚገባ ሊያረክሰው ምንም እንዳይችል አትመለከቱምን? ወደ ሆድ ገብቶ ወደ እዳሪ ይወጣል እንጂ ወደ ልብ አይገባምና አላቸው። እርሱም አለ፦ ከሰው የሚወጣው ሰውን የሚያረክስ ያ ነው። ከውስጥ ከሰው ልብ የሚወጣ ክፉ ሐሳብ፥ ዝሙት፥ መስረቅ፥ መግደል፥ ምንዝርነት፥ መጐምጀት፥ ክፋት፥ ተንኰል፥ መዳራት፥ ምቀኝነት፥ ስድብ፥ ትዕቢት፥ ስንፍና ናቸውና፤ ይህ ክፉው ሁሉ ከውስጥ ይወጣል ሰውን ያረክሰዋል።” (ማር. ፯፥፲፰-፳፫)። ተማሪዎች ተመለከታችሁን? ይህ ጾምን የሚያጸና እንጂ የሚሽር ነውን? አይደለም ምክንያቱም ጾም ማለት ከምግብና ከሚያረክሶ ነገሮች ሁሉ መራቅ ነው።

በአጠቃላይ ከመናፍቃን ራሳችንን እንጠብቅ በተዋበች የጾም ሕግ ጽድቅን እንፈልግ፤ ከተድላ ደስታ በመራቅ ከእግዚአብሔር ጋር አንድ እንሁን “ትእዛዙንም የሚጠብቅ በእርሱ ይኖራል እርሱም ይኖርበታል፤ በዚህም በእኛ እንዲኖር ከሰጠን ከመንፈሱ እናውቃለን።” (፩ኛዮሐ. ፫፥፳፬ እንደተባለ። በተጨማሪም ምሳሌውን አርአያነቱን በማስተዋል እንከተል “በእርሱ እኖራለሁ የሚል እርሱ እንደ ተመላለሰ ራሱ ደግሞ ሊመላለስ ይገባዋል።” (፩ኛዮሐ. ፪፥፮) ተብሎ እንደተጠቀሰ።

የአጽዋማትን ጊዜ የተመለከተውን ልንወዛገብበት አይገባም። ውድ ተማሪዎች የእኛ ቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ፣ ሥርዓተ አምልኮ ምንጭ መጽሐፍ ቅዱስ ብቻ አይደለም ይልቁንም የቤተ ክርስቲያን ዓለም አቀፍ ጉባኤያት፣ ትውፊትና ከሐዋርያት ጀምሮ ያሉ አበው ትምህርት ሕይወት እንደ ምንጭ የሚወሰድ በመሆኑ ከበቂ በላይ ማስረጃ አለን። በሐዲስ ኪዳን ቀኖና ውስጥ ያሉ ስምንቱ መጻሕፍት ሁሉም ላይ የጾም ጊዜ ሥርዓት በቀኖናው ተጽፎ እንደሚገኝ መዘንጋት አይገባም።  

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

0 replies

Leave a Reply

Want to join the discussion?
Feel free to contribute!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *