ጾመ ፍልሰታ ለማርያም
እንኳን ለፍልሰታ ለማርያም ጾም በሰላም አደረሳችሁ!
ጾመ ፍልሰታ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ከደነገገቻቸው ሰባቱ የዐዋጅ አጽዋማት አንዱ ነው፡፡ ይህንንም ጾም ከነሐሴ ፩-፲፮ ቀን ድረስ ለሁለት ሱባኤ ከሰባት ዓመት ሕፃናት ጀምሮ ኦርቶዶክሳውያን ሁሉ የሚጾሙትና በናፍቆት የሚጠበቅ ጾም ነው፡፡
ቤተ ክርስቲያን ሐዋርያትን አብነት አድርጋ የምትጾመው ጾም እንደመሆኑ ምእመናን በየገዳማቱና አድባራት በመገኘት ራሳቸውን ለእግዚአብሔር በማስገዛት በሱባኤ በጾም፣ በጸሎት፣ በስግደትና በምሕላ ከእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በረከት ያገኙ ዘንድ በፍጹም ፍቅርና ትጋት ይጾሙታል፡፡
ፍልሰታ የሚለው ቃል “ፈለሰ” ከሚለው የግእዝ ቃል የተገኘ ሲሆን ትርጉሙም “መለየት፣ ማረግ፣ ወደ ላይ መውጣት፣ ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ መሄድ” ማለት ነው፡፡ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በ፷፬ ዓመቷ ከዚህ ዓለም ድካም ጥር ፳፩ ቀን ፵፱ ዓ.ም በማረፏ ሐዋርያት ሥጋዋን በጌቴሴማኒ ለማሳረፍ ሲወስዷት አይሁድ “እንደ ልጇ ተነሣች፤ ዐረገች እያሉ እንዳያውኩን በእሳት እናቃጥላት” ብለው በዓመፃ ተነሡ፡፡ ታውፋንያ የሚባል አይሁዳዊም በክፋት ተነሣስቶ አጎበሩን ይዞ ሊያወርዳት ሲል የእግዚአብሔር መልአክ ሁለት እጆቹን ቆረጠው፡፡ እግዚአብሔርም ሐዋርያው ቅዱስ ዮሐንስን ጨምሮ እመቤታችንን በደመና ነጥቆ ወስዶ በገነት ከዕፀ ሕይወት ሥር አስቀመጣት፡፡ ዮሐንስም በዕፀ ሕይወት ላሉት ነፍሳት “ዛቲ ይእቲ ሕይወትክሙ ኪያሃ ሰብሑ፤” ብሎ ሰጣቸው፡፡ እነርሱም ተቀብለው “ብፅዒት ከርስ እንተፆረትኪ ወብፅዓት ዓይንት እለእርያ ኪያኪ ፤ ሕይወታችሁ ይህቺ ናት፤ እርሷን አመስግኑ፣ አንቺን የተሸከመች ማኅፀን የተባረከች ናት፤ አንቺን ያዩ ዓይኖችም የተባረኩ ናቸው ፤” ብለው አመስግነዋታል፡፡ “ትውልድ ዘኢይሀልፍ ያመሰግኑኛል” ማለት ይህ ነው፡፡
ቅዱስ ዮሐንስ ወደ ሐዋርያቱ በተመለሰ ጊዜ ሐዋርያቱ “እመቤታችንስ?” እያሉ በጥያቄ አፋጠጡት፡፡ እርሱም ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በገነት በዕፀ ሕይወት እንዳስቀመጣት ነገራቸው፡፡ እነርሱም ዮሐንስ ያየውን እኛም ማየት አለብን ብለው ከነሐሴ ፩-፲፬ ሱባኤ ገቡ፡፡ ጌታችንም የሐዋርያቱን ጽናት ፍቅር ተመልክቶ የእመቤታችንን ትኩስ ሥጋ ከዕፀ ሕይወት አምጥቶ ሰጣቸው፡፡ እነርሱም ተቀብለው በጌቴሴማኒ ቀበሯት፡፡ በሦስተኛውም ቀን ሐዋርያው ቅዱስ ቶማስ ከሀገረ ስብከቱ ሕንድ በደመና ተጭኖ ሲመጣ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በመላእክቱ ታጅባ ስታርግ ተገናኙ፡፡ ሐዋርያው ቶማስም ሐዋርያት ያዩትን እኔ ሳላይ ብሎ አዘነ፡፡ “ቀድሞ የልጅሽን ትንሣኤ፤ ዛሬ ደግሞ ያንቺን ትንሣኤ ሳላይ ቀረሁን?” በማለት ከደመናው ወደ መሬት ራሱን ሊጥል ሲቃጣው እመቤታችን ማረጓን እርሱ ብቻ እንደተመለከተ ነግራ የተገነዘችበትን ሰበን ሰጥታው ዐረገች፡፡
ሐዋርያው ቶማስ ወደ ሐዋርያት በተመለሰ ጊዜም “የእመቤታችን ነገር እንደምን ሆነ?” አላቸው፡፡ እነርሱም “አግኝተን ቀበርናት” አሉት፡፡ “ሞት በጥር በነሐሴ መቃብር እንዴት ይሆናል?” አላቸው፡፡ ከሐዋርያት መካከል ቅዱስ ጴጥሮስ ከዚህ በፊት የጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ትንሣኤ ተጠራጥሮ እንደነበር በመግለጽ ገሰጸው፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስም ተቈጥቶ የእመቤታችንን ክቡር ሥጋ ለቅዱስ ቶማስ ለማሳየት ሔዶ መቃብሯን ቢከፍት የእመቤታችንን ሥጋ ሊያገኘው አልቻለም፡፡ በዚህ ጊዜ ቅዱስ ጴጥሮስ ደንግጦ ቆመ፡፡
ቅዱስ ቶማስም “አታምኑኝም ብዬ ነው እንጂ እመቤታችንስ ከሙታን ተለይታ ተነሥታ ስታርግ አግኝቻታለሁ” ብሎ የሰጠችውን ሰበን ለሐዋርያት ሰጥቷቸዋል፡፡ እነርሱም በእመቤታችን ትንሣኤና ዕርገት እየተደሰቱ ሰበኑን ለበረከት ተካፍለውታል፡፡ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን እንደሚያስተምሩን በቅዳሴ ጊዜ ሠራዒ ዲያቆኑ በሚይዘው መስቀል ላይ የሚታሠረው መቀነት መሰል ልብስ፤ እንደዚሁም አባቶች ካህናት በመስቀላቸው ላይ የሚያደርጉት ቀጭን ልብስና በራሳቸው የሚጠመጥሙት ነጭ ሻሽ የእመቤታችን ሰበን ምሳሌ ነው፡፡
ሐዋርያትም ቶማስ ያየውን እውነት ለማየትና ከእመቤታችን በረከት ለማግኘት ከነሐሴ ፩-፲፮ በጾምና በጸሎት ተወስነው ቆይተዋል፡፡ እግዚአብሔር አምላካችን ጸሎታቸውን ሰምቶ ነሐሴ ፲፮ ቀን እመቤታችንን መንበር፤ ጴጥሮስን ተራዳኢ ካህን፤ እስጢፋኖስን ሠራዒ ዲያቆን አድርጎ ቀድሶ እመቤታችንንም ሐዋርያትንም አቍርቧቸዋል፡፡ እነርሱም እመቤታችንን በዓይናቸው ከማየት ባሻገር አብረው ሥጋውን ደሙን ተቀብለዋል /ትርጓሜ ውዳሴ ማርያም/፡፡ እንደ ልጇ እንደ ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከሙታን ተለይታ ተነሥታለች፡፡ “ከመ ትንሣኤ ወልዳ፤ እንደ ልጇ ትንሣኤ” ያሰኘውም ይህ ታሪክ ነው፡፡
በጾመ ፍልሰታ በቤተ ክርስቲያናችን በየቀኑ በማኅሌቱ፣ በሰዓታቱና በቅዳሴው በሚደርሰው ቃለ እግዚአብሔር ነገረ ማርያም ማለትም የእመቤታችን ከመፀነሷ ጀምሮ እስከ ዕርገቷ ድረስ ያለው ታሪኳ፣ ለአምላክ ማደሪያነት መመረጧ፣ ንጽሕናዋ፣ ቅድስናዋ፣ ክብሯ፣ ርኅርራኄዋ፣ ደግነቷ፣ አማላጅነቷ፣ ሰውን ወዳድነቷ በስፋት ይነገራል፡፡ እመቤታችንን ከሚያወድሱ ድርሳናት መካከልም በተለይ ምሥጢረ ሥላሴን፣ ምሥጢረ ሥጋዌንና ነገረ ድኅነትን ከነገረ ማርያም ጋር በማዛመድ የሚያትተው ቅዳሴ ማርያም፤ እንደዚሁም ነገረ ድኅነትን ከምሥጢረ ሥጋዌ (ከነገረ ክርስቶስ) እና ከነገረ ማርያም ጋር በማመሣጠር የሚያትተው ውዳሴ ማርያምም በስፋት ይጸለያል፤ ይቀደሳል፤ ይተረጐማል፡፡ በሰንበታት የሚዘመሩ መዝሙራት፤ በየዕለቱ በቅዳሴ ጊዜ የሚነበቡ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎችም እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ለተዋሕዶ በእግዚአብሔር መመረጧን፣ ዘለዓለማዊ ድንግልናዋን፣ ክብሯን፣ ቅድስናዋን፣ ንጽሕናዋን የሚያወሱ ናቸው፡፡
ምእመናንም በረከት ያገኙ ዘንድ የዲያብሎስንም ፈተና ድል ይነሡ ዘንድ ከነሐሴ ፩-፲፮ ከቤተሰቦቻቸው ተለይተው በየገዳማቱና በየአብያተ ክርስቲያናቱ በዓት አዘጋጅተው፣ ሱባዔ ገብተው፣ ፈቃደ ሥጋቸውን ለፈቃደ ነፍሳቸው አስገዝተው ይጾማሉ፤ ይጸልያሉ፤ እንደዚሁም ቅዱስ ሥጋውን ክቡር ደሙን ይቀበላሉ፡፡ ይህ ጾም ለእመቤታችን ያለንን ፍቅር የምንገልጽበት ወቅት ነው፡፡ በተለይ ኦርቶዶክሳውያን ሕፃናት ከሌላው ጊዜያት በተለየ ሁኔታ ትምህርተ ወንጌል የሚማሩት፤ ቅዱስ ሥጋውን ክቡር ደሙን የሚቀበሉት በዚህ በጾመ ፍልሰታ ነው፡፡
የእግዚአብሔር ቸርነት፣ የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም አማላጅነት፣ የቅዱሳን ሐዋርያት ጸጋና በረከት አይለየን፡፡
Leave a Reply
Want to join the discussion?Feel free to contribute!