ጸሎተ ኀሙስ

ከመምህር አዲሱ በዛብህ
ከስቅለትና ከትንሣኤ በፊት በሕማማት ሳምንት ያለው ሐሙስ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ልዩ ልዩ ስያሜዎች አሉት፡፡ እነዚህንም ስያሜያት እንደሚከተለው እንመለከታለን።
ሀ. ጸሎተ ሐሙስ ይባላል።
የዓለም መድኃኒት ኢየሱስ ክርስቶስ ይለምን ይማልድ የነበረን ሥጋ የተዋሐደ ፍጹም አምላክና ፍጹም ሰው መሆኑን ለማጠየቅ እንዲሁም ለአርአያነት ጠላቶቹ መጥተው እስኪዙት ድረስ ሲጸልይ በማደሩ ምክንያት ይህንን ስያሜ አገኘ። (ማቴ ፳፮፥፴፮-፵፮፣ ፲፯፥፩)
ለ. ሕጽበተ እግር ሐሙስ ይባላል።
ሕጽበተ እግር፦ ይህ ስያሜ የተሰጠው ጌታችን በዚህ ዕለት የደቀመዛሙርቱን እግር በማጠቡ ምክንያት ነው፤ ይህም የሚያሳየው የዓለምን ሁሉ ኃጢአት ለማጠብ የመጣ መሆኑን ነው፡፡ ይህን ለማስታወስ ዛሬም ካህናት በተለይም ሊቃነ ጳጳሳትና የደብር አስተዳዳሪዎች በመካከላችን ተገኝተህ የእኛንና የሕዝብህን ኃጢአት እጠብ ሲሉ ከአገልጋዮቹ ጀምረው በቤተክርስቲያን የተገኙትን ምእመናን እግር በወይንና በወይራ ቅጠል ሲያጥቡ ያረፍዳሉ፡፡
ሐ. የምሥጢር ቀን ይባላል።
ከሰባቱ ምሥጢራት አንዱ በዚህ ዕለት ተመሥርቷልና፤ ይኸውም ‹‹ይህ ስለእናንተ በመስቀል ላይ የሚቆረሰው ሥጋዬ ነው፡፡ እንካችሁ ብሉ›› ጽዋውንም አንሥቶ አመሰገነ፤ ‹‹ይህ ስለእናንተ ነገ በመስቀል የሚፈስ ደሜ ነው ከእርሱ ጠጡ›› በማለት እኛ ከእርሱ ጋር፣ እርሱ ከእኛ ጋር አንድ የምንሆንበትን መንገድ ከጠላት ዲያብሎስ ሰውሮ ለደቀ መዛሙርቱ የገለጠበት ቀን በመሆኑ የተሰጠ ስያሜ ነው፡፡
በዚህ ዕለት ቅዳሴ ይቀደሳል፤ የሚቀደሰውም በለሆሳስ ሲሆን እንደ ቃጭል ሆኖ የሚያገለግለውም ጸናጽል ነው፡፡ ይህም አይሁድ ጌታችንን ለመያዝ ሲመጡ ድምጻቸውን ዝቅ አድርገው፣ በለሆሳስ እየተነጋገሩ መምጣታቸውን ለማሰብ ነው፤ በቅዳሴውም ጸሎተ ተአምኖ፣ ኑዛዜ አይደረግም፤ ሥርዓተ ቁርባን ግን ይፈጸምበታል፤ ይህም ጌታችን የሰጠውን ዘለዓለማዊ ቃል-ኪዳን ለማሰብ ነው፡፡ በዚህ ዕለት ክርስቲያን የሆነ ሁሉ በንስሓ ታጥቦ ተዘጋጅቶ ቅዱስ ሥጋውንና ክቡር ደሙን መቀበል ይኖርበታል፡፡
መ. የሐዲስ ኪዳን ሐሙስ ይባላል።
ጸሎተ ሐሙስ (የፋሲካ እራት) ፦ ምክንያቱም መሥዋዕተ ኦሪት ማለትም በእንስሳት ደም የሚቀርበው መሥዋዕት ማብቃቱን ገልጦ ለድኅነተ ዓለም ራሱን የተወደደ መሥዋዕት አድርጐ ያቀረበበት ዕለት በመሆኑ ነው፡፡ ‹‹ይህ ጽዋዕ ስለ እናንተ በሚፈሰው በደሜ የሚሆን ሐዲስ ኪዳን ነው፡፡ ከእርሱም ጠጡ›› በማለቱ ይታወቃል፡፡ (ሉቃ.22፥20) ኪዳን ማለት በሁለት ወገን መካከል የሚደረግ ውል፣ ስምምነት፣ መሐላ ማለት ነው፡፡ በዚህ መሠረት ጌታችን ለአዳምና ለልጆቹ ሁሉ ዘለዓለማዊ ቃል-ኪዳን በራሱ ደም የፈጸመበት ዕለት መሆኑን በማሰብ የቃል-ኪዳኑ ፍጻሜዎች፣ ጠባቂዎች መሆን እንደሚገባን እንማራለን፡፡
ሠ. አረንጓዴ ሐሙስ ይባላል።
አምላካችን የጸለየበትን የአትክልት ቦታ ወይም ጌቴሴማኒ ለማሰብ ይህ ስያሜ ተሰጥቶታል።
ጌታ እንዴት፣ ምን እና ለምን ጸለየ?
እንዴት ጸለየ?
አምላካችን የምሥጢር ሐዋርያቱን (ዮሐንስ ፣ ያዕቆብ እና ጴጥሮስ) አምስት ትእዛዛትን (ተቀመጡ ፣ ትጉ ፣ ጸልዩ ፣ ተኙ ፣ ዕረፉ) በማዘዝ ግንባሩን ምድር አስነክቶ ሰግዶ ጸለየ።(ማቴ፳፮፥፴፮-፵፭)
ምን ጸለየ?
ሦስት ጊዜ ደጋግሞ የጸለየው ጸሎት አንድ ዓይነት ነው ይኸውም: – “አባቴ ቢቻልስ ይህች ጽዋ ከእኔ ትለፍ፤ ነገር ግን አንተ እንደምትወድ ይሁን እንጂ እኔ እንደምወድ አይሁን አለ።” (ማቴ፳፮፥፴፮-፵፭)
ለምን ጸለየ?
፩. ምሣሌ ይሆነን ዘንድ ነው።
፪. ፈቃዱን ማስቀደም እንዳለብን እናውቅ ዘንድ ነው።
፫. ወደፈተና እንዳንገባ መጸለይ እንደሚገባ እናውቅ ዘንድ ሊያስተምረን ነው።
➣ የጸሎቱ ትርጓሜ ምንድ ነው?
፩. ዓለም እንድትድን እና ክብርን እንድታገኝ ለሞት ተላልፎ እንደሚሰጥ ገልጿል።
“ያለ እኔ ሞት የዓለሙ ድኅነት ያለ እኔ ሐሳር የዓለሙ ክብር አይቻልም እንጂ የሚቻልስ ከሆነ ይህ ጽዋዕ ሞት ይለፍልኝ። ነገር ግን ያንተ ፈቃድ ይደረግ እላለሁ እንጂ የእኔ ፈቃድ ይደረግ አልልም።” (ወንጌል አንድምታ ገጽ ፪፻፸፱)
፪. ሞት እንዲቀርልን እንደ ሞተ ገልጿል። “በእኔ ሞት የዓለም ድኅነት በእኔ ኃሣር የዓለም ክብር የሚቻልስ ከሆነ እኔ ከሞትሁላቸው ከእኔ ሞት የተነሳሣ ይህ ጽዋዕ ሞት ይቅርላቸው። (ወንጌል አንድምታ ገጽ፪፻፸፱)
፫. አብነት ይሆነን ዘንድ ሞትን እንደሚቀምስ ገልጿል። ” ከእኔ ለምዕመናን ይለፍላቸው ። እኔን አብነት አድርገው ይሙቱ ። ነገር ግን የእኔ ፈቃድ ካንተ ፈቃድ ልዩ ሁኖ የእኔ ፈቃድ ይሁን አልልም። የእኔ ፈቃድ ካንተ ፈቃድ ጋራ አንድ ነውና ያንተ ፈቃድ ይሁን እላለሁ እንጂ። ” (ወንጌል አንድምታ ገጽ፪፻፸፱)
➣ በዚህ ዕለት በወንጌላት የተመዘገቡ ድርጊቶችን ቀጥለን እንመልከት፦
ሀ. የፋሲካ ዝግጅት የተደረገበት ዕለት ነው።
ዝግጅቱ በሦስቱ ወንጌላት ላይ ተመዝግቧል፡፡ ማቴ. ፳፮፥፲፯-፲፱ ማር. ፲፬፥፩-፲፮፣ ሉቃ. ፳፪፥ ፮-፲፫)
ፋሲካ ማለት ማዕዶት ፣ መሻገር ፣ ማለፍ ማለት ነው፤ ይኸውም እሥራኤላውያን በግብጽ ምድር ሳሉ መልአኩን ልኮ እያንዳንዱ እሥራኤላዊ የበግ ጠቦት እንዲያርድና ደሙን በበሩ ወይንም በመቃኑ እንዲቀባ ለሙሴ ነገረው፤ ሙሴም ለሕዝቡ ነገረ፤ ሁሉም እንደታዘዙት ፈጸሙ፤ መቅሠፍት ከእግዚአብሔር ታዞ መልአኩ የደም ምልክት የሌለበትን የግብጻውያን ቤት በሞተ በኵር ሲመታ፤ የበጉ ደም የተቀባውን የእሥራኤላውያንን ቤት ምልክቱን እያየ ማለፉን ለማመልከት ነው፡፡ (ዘዳ.12፤1-13) በዚህ መነሻነት በየዓመቱ እሥራኤላውያን በመጀመሪያ ወራቸው በዐሥራ ዐራተኛው ቀን በግ እያረዱ የፋሲካን በዓል ያከብራሉ፡፡ ሀገራችንም አስቀድማ ብሉይ ኪዳንን የተቀበለች ሀገር እንደመሆኗ ይህ ድርጊት ይፈጸምባት ነበር፡፡ በአንጻሩም ዛሬ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ትንሣኤ ፋሲካ ተብሎ የተጠራበት ምክንያት በዚህ በፋሲካ በዓል ራሱን የተወደደ መሥዋዕት አድርጎ ደሙን ስላፈሰሰልን ነው፡፡ በደሙ መፍሰስ ሞተ በኵር የተባለ ሞተ ነፍስ ቀርቶልናልና፤ ‹‹ፋሲካችንም ክርስቶስ ነው፡፡›› (1ኛቆሮ. ፭፥፮፣ 1ኛ ጴጥ. ፩፥፲)
ለ. በዚህ ዕለት እንደ ማክሰኞ ለደቀመዛሙርቱ ረጅም ትምህርት አስተምሯል።
ምሥጢረ ሥላሴ (የሦስትነት ትምህርት) ፤ ምሥጢረ ሥጋዌ (የአምላክ ሰው መሆን) ፤ (ዮሐ. ፲፬፥፲፮) የሚገኘው በጠቅላላ የዚህ ዕለት ትምህርት ነው፡፡ የትምህርቱም ዋና ዋና ክፍሎች ምሥጢረ ትንሣኤ ሙታንና የዳግም ምጽአቱ ነገር ነው፡፡ እነዚህም በስፋትና በጥልቀት መማር እንደሚገባ ሲያስረዳን በተአምራት ሊገልጥላቸው ሲችል በረጅም ትምህርት እንዲረዱት አድርጓል፡፡ ተማሪዎቹን እሱ እያስተማራቸው ሳለ ያልገባቸውን እየጠየቁ ተረድተዋል፡፡ ከዚህም እያንዳንዳችን በቤተክርስቲያን ተገኝተን መማርና ያልገባንን ጠይቆ መረዳት እንደሚገባን እንማራለን፡፡
ሐ. ይህ ዕለት ከደቀመዛሙርቱ አንዱ የአስቆሮቱ ይሁዳ ጌታ ሆይ፣ መምህር ሆይ ብሎ በመሳም አሳልፎ የሰጠበት ዕለት ነዉ።
ጭፍሮቹም በዚሁ ዕለት ሌሊት የክብር ባለቤት የሆነውን ጌታችንን ይዘው ወደፊት፣ ወደኋላ እየጐተቱ፣ እያዳፉ ወደ ሊቀ ካህናቱ ወደ ቀያፋ ወስደውታል።
የመዝሙረ ዳዊት ምንባባት
በአንድ ሰዓት፡- “አፉ ከቅቤ ይልቅ ለዘበ፤ በልቡ ግን ሰልፍ ነበረ፤ ቃሎቹም ከዘይት ይልቅ ለሰለሱ፤ እነርሱ ግን እንደ ተመዘዘ ሰይፍ ናቸው” (መዝ፶፬፥፳፩)
በሦስት ሰዓት፡- “የጻድቅን ነፍስ ያደቡባታል፤ በንጹህ ደምም ይፈርዳሉ፡፡” (መዝ፺፫፥፳፩)
በስድስት ሠዓት፡- “የብዙ ሰዎችን ስድብ ሰምቻለሁና በዙሪያው ፍርሃት ነበረ በላዬ በአንድነት በተሰባሰቡ ጊዜ፤ ነፍሴን ለመንጠቅ ተሰባሰቡ፡፡” (መዝ ፴፥፲፫)
በዘጠኝ ሰዓት፡- “እግዚአብሔር እረኛዬ ነው፤ የሚያሳጣኝም የለም፤ በለመለመ መስክ ያሳድረኛል፡፡” (መዝ. ፳፪፥ ፩-፪)
ኅጽበተ እግር፣ ሲጀመር ደግሞ “በሂሶጵ እርጨኝ እነጻማለው እጠበኝ ከበረዶም ይልቅ ነጭ እሆናለው፡፡” (መዝ ፶፥፯)
በመጽሐፈ ግብረ ሕማማት፡- “ከዚህ በኋላ የእግር እጥበት ሥርዓት ነው፤
ዲያቆን ሁለት ኲስኲስቶች ያቅርብ በውስጣቸውም ውኃ ይምላባቸው አንዱ ለእጅ መታጠቢያ እንዲሆን ካህኑም እስከ መጨረሻው ጸሎተ አኮቴት ይበል።
ጸሎተ ዕጣኑንም ደግሞ ዕጣንን ያሳርግ፤ ስለ ሰላም ስለ ሊቀ ጳጳሳት ስለ ማኅበር ይጸልይ፡፡ ሕዝቡም ለአብ ለወልድ ለመንፈስ ቅዱስ ምስጋና ይሁን ዛሬም ዘወትርም ለዘላለሙ አሜን ይበሉ፡፡ አቡነ ዘበሰማያትም ይበሉ ፤ ኀምሳኛውንም የዳዊትን መዝሙር ይበሉ፡፡” (ግብረ ሕማማት ገጽ ፭፻፵፪)
“ከዚህ በኋላ ሕዝቡ ይነሱ አርባ አንድ ጊዜ ኪራላይሶን ይበሉ፤ ካህኑም መስቀል ይዞ ውኃውን ሦስት ጊዜ አሐዱ አብ ቅዱስ (ልዩ ክቡር ንጹሕ ጽኑዕ ነው) ፤ አሐዱ ወልድ ቅዱስ (ልዩ ክቡር ንጹሕ ጽኑዕ ነው) ፤ አሐዱ ውእቱ መንፈስ ቅዱስ (ልዩ ክቡር ንጹሕ ጽኑዕ ነው) እያለ ሦስት ጊዜ ውኃውን ይባርክ፡፡” (ግብረ ሕማማት ገጽ ፭፻፶፱)
“ከዚህ በኋላ ካህኑ እንደ ሥርዓቱ ኅጽበተ እግርን ያድርግ (ይፈጽም) ከዚህ በኋላም ጥቁር ልብስ ለብሰው ሥርዐተ ቅዳሴውን ይጀምሩ የቃጭል ድምጽንም አያሰሙ፡፡” (ግብረ ሕማማት ገጽ ፭፻፷፩)
በአሥራ አንድ ሰዓት፡- “በፊቴ ገበታን አዘጋጀህልኝ በጠላቶቼ ፊት ለፊት ራሴን በዘይት ቀባህ ጽዋዬም የተረፈ ነው” (መዝ. ፳፪፥ ፭-፮)
የአይሁድ ካህናት ያለበደል እና ያለጥፋት ንጹውን ክርስቶስን ለመስቀል ሞት እንዲደርስ በጭካኔ በዕለተ ሐሙስ ከሌሊቱ 3፡00 ጀምሮ ብዙ መከራ አደረሱበት እጅጉን ተሠቃየ፤ እያዳፉ አንዳች ሳይናገር አሠቃዩት ነቢየ እግዚአብሔር ኢሳይያስ በትንቢት መነጽር የተመለከተውን የጌታችንን ሥቃይ እንዲህ ሲል ያመጣዋል፤
“ተጨነቀ፣ ተሠቃየም አፉንም አልከፈተም ለመታረድ እንደሚነዳ ጠቦት በሸላቾቹም ፊት ዝም እንደሚል በግ እንዲሁ አፉን አልከፈተም፡፡ በማስጨነቅና በፍርድ ተወሰደ ስለ ሕዝቤ ኃጢአት ተመቶ ከሕያዋን ምድር እንደተወገደ ከትውልዱ ማን አስተዋለ? ከክፉዎቹም ጋር መቃብሩን አደረጉ…” እንዲል (ኢሳ፶፫፥፩-፰)
እንበለ ደዌ ወሕማም እንበለ ፃማ ወድካም አመ ከመ ዮም ያብጽሐነ ያብጽሕክሙ ለብርሃነ ትንሣኤሁ እግዚአብሔር በፍስሓ ወበሰላም አሜን! ፤ ያለ ደዌና ያለ ሕማም ያለ ፃማና ያለ ድካም እግዚአብሔር ለትንሣኤው ብርሃን እንደ ዛሬ ቀን በደስታና በፍቅር በአንድነት ያድርሰን ያድርሳችሁ አሜን!

0 replies

Leave a Reply

Want to join the discussion?
Feel free to contribute!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *