ጸሎተሐሙስ

ጸሎተ ሐሙስ

ጸሎተ ሐሙስን ሕፅበተ ሐሙስ፣ የምስጢር ቀን፣ የሐዲስ ኪዳን ሐሙስ፣ የነፃነት ሐሙስ እየተባለ ይጠራል፡፡

ሕጽበተ ሐሙስ

ጌታችን በዚህ ዕለት የደቀ መዛሙርቱን እግር በፍጹም ትሕትና ዝቅ ብሎ አጥቧል፡፡ ይህም ኢየሱስ ክርስቶስ የዓለምን ሁሉ ኃጢአት ለማጠብ የመጣ የንጽሕና፣ የቅድስና አምላክ መሆኑን ያጠይቃል፡፡ ስለዚህም ዕለቱ “ሕጽበተ ሐሙስ” ይባላል፡፡ ይህን ለማስታወስ ዛሬም ሊቃነ ጳጳሳትና ቀሳውስት በመካከላችን ተገኝተህ የእኛንና የሕዝብህን ኃጢአት እጠብ፤ እኛም የአንተን አርአያነት ተከትለን የልጆቻችንን እግር እናጥባለን ሲሉ በቤተ ክርስቲያን የተገኙ ምእመናንን እግር በወይንና በወይራ ቅጠል ያጥባሉ፡፡

የምሥጢር ቀን

ከሰባቱ ምሥጢራተ ቤተ ክርስቲያን አንዱ ምሥጢረ ቍርባን በዚህ ቀን ተመሥርቷልና ዕለቱ “የምሥጢር ቀን” ይባላል፡፡ ይኸውም ጌታችን ኅብስቱንና ጽዋውን አንሥቶ ይህ ስለ እናንተ በመስቀል ላይ የሚቈረሰው ሥጋዬ ነው፡፡ እንካችሁ፤ ብሉ፡፡ ይህ ስለ እናንተ ነገ በመስቀል ላይ የሚፈስ ደሜ ነው፤ ከእርሱም ጠጡ በማለት እርሱ ከእኛ፤ እኛም ከእርሱ ጋር አንድ የምንሆንበትን ምሥጢር ከጠላት ዲያብሎስ ሰውሮ፣ ለደቀ መዛሙርቱ የገለጠበት ቀን በመሆኑ የተሰጠ ስያሜ ነው፡፡ በዚህ ዕለት ክርስቲያን የሆነ ሁሉ በንስሐ ታጥቦ ቅዱስ ሥጋውንና ክቡር ደሙን ለመቀበል ይዘጋጃል፡፡

የሐዲስ ኪዳን ሐሙስ

መድኃኒታችን ክርስቶስ መሥዋዕተ ኦሪት ማለትም በእንስሳት ደም የሚቀርበው መሥዋዕት ማብቃቱን ገልጦ፣ ለድኅነተ ዓለም ራሱን የተወደደ መሥዋዕት አድርጎ ያቀረበበት ዕለት በመሆኑ ይህ ዕለት “የሐዲስ ኪዳን ሐሙስ” ይባላል (ሉቃ. ፳፪፥፳)፡፡ “ኪዳን” ማለት በሁለት ወገን መካከል የሚደረግ ውል፣ ስምምነት፣ መሐላ ማለት ነው፡፡ በዚህ መሠረት ጌታችን ለአዳምና ለልጆቹ ሁሉ ዘለዓለማዊውን ቃል ኪዳን በራሱ ደም የፈጸመበት ዕለት ስለ ሆነ ሐሙስ “የሐዲስ ኪዳን ሐሙስ” ተባለ፡፡

የነጻነት ሐሙስ

ይህ ዕለት ለኃጢአትና ለዲያብሎስ ባሪያ ሆኖ መኖር ማብቃቱ የተገለጠበት፤ የሰው ልጅ ያጣውን ክብር መልሶ ማግኘቱ የተረጋገጠበት ቀን ስለ ሆነ “የነጻነት ሐሙስ” ይባላል፡፡ ጌታችን ስለ ሰው ልጅ ነጻነት ሲናገር ከእንግዲህ ወዲህ ባሮች አልላችሁም፤ ባርያ ጌታው የሚያደርገውን አያውቅምና፡፡ ወዳጆች ግን ብያችኋለሁ በማለት ከባርነት የወጣንበትን፤ ልጆች የተባልንበትን ቀን የምናስብበት በመኾኑ “የነጻነት ሐሙስ” ይባላል (ዮሐ. ፲፭፥፲፭)፡፡ እያንዳንዱ ክርስቲያንም ከኃጢአት ባርነት ርቆ፣ ከእግዚአብሔር ጋር የሚያወዳጀውን መልካም ሥራ በመሥራት ሕይወቱን መምራት ይኖርበታል፡፡ ባሮች ሳይሆን ወዳጆች ተብለን በክርስቶስ ተጠርተናልና፡፡

በዚህ ዕለት እንደ ማክሰኞ ሆሉ ጌታችን በዮሐንስ ወንጌል ፲፬፥፲፮ የሚገኘውን ሰፊ ትምህርት ለደቀ መዛሙርቱ አስተምሯል፡፡ የትምህርቱም ዋና ዋና ክፍሎችም ምሥጢረ ሥላሴን፣ ምሥጢረ ሥጋዌንና ምሥጢረ ትንሣኤ ሙታንን ያካትታሉ፡፡ ጌታችን እነዚህን ትምህርቶች በስፋትና በጥልቀት መማር እንደሚገባ ሲያስረዳ፣ ለደቀ መዛርቱ ምሥጢሩን በተአምራት ሊገልጥላቸው ሲቻለው በሰፊ ማብራርያ እንዲረዱት አድርጓል፡፡ ደቀ መዛሙርቱም ያልገባቸውንም እየጠየቁ ተረድተዋል፡፡ ምእመናንም በቤተ ክርስቲያን ተገኝተን መማርና ያልገባንን ጠይቀን መረዳት እንደሚገባን ከዚህ እንማራለን፡፡ መድኃኒታችን ክርስቶስ ራሱን ለአይሁድ አሳልፎ የሰጠውም በዚሁ ዕለት ከምሽቱ በሦስት ሰዓት ነው (ማቴ. ፳፮፥፵፯-፶፰)፡፡

በጸሎተ ሐሙስ በቤተ ክርስቲያን የሚፈጸም ሥርዓት

በዚህ ዕለት ስግደቱ፣ ጸሎቱ፣ ምንባባቱ እንደ ተለመደው ይከናወናሉ፡፡ መንበሩ (ታቦቱ) ጥቁር ልብስ ይለብሳል፡፡ ጸሎተ ዕጣን ይጸለያል፤ ቤተ ክርስቲያኑም በማዕጠንት ይታጠናል፡፡ ሕጽበተ እግር ይደረጋል፡፡ ቅዳሴ ይቀደሳል፡፡ በየቤቱ ደግሞ ጉልባን ይዘጋጃል፡፡

ሕጽበተ እግር

ከቀኑ በዘጠኝ ሰዓት ዲያቆኑ ሁለት ኵስኵስቶችን ውኃ ሞልቶ ያቀርባል፤ አንዱ ለእግር፣ አንዱ ለእጅ መታጠቢያ፡፡ ‹ጸሎተ አኰቴት› በመባል የሚታወቀው የጸሎት ዓይነት ይጸለያል፡፡ ወንጌል ተነቦ ውኃው በካህኑ (በሊቀ ጳጳሱ) ይባረክና የሕጽበተ እግር ሥርዓት ይከናወናል፡፡ ይኸውም ጌታችን የደቀ መዛሙርቱን እግር በማጠብ ያሳየውን የተግባር ትምህርት ለማሳየት ነው (ዮሐ. ፲፫፥፲፬)፡፡ ከውኃው በተጨማሪ የወይራና የወይን ቅጠልንም ለሥርዓተ ሕጽበቱ ማስፈጸሚያነት እንጠቀምባቸዋለን፡፡ ምሥጢሩም የሚከተለው ነው፡-

ወይራ ጸኑዕ ነው፡፡ ወይራ ክርስቶስም ጽኑዕ መከራ መቀበሉን ከማስረዳቱ በተጨማሪ እኛም (እግራችንን የሚያጥቡን አባቶች እና የምንታጠበው ምእመናን) መከራ ለመቀበል ዝግጁ ነን ለማለት ሥርዓተ ሕጽበቱን በወይራ እንፈጽማለን፡፡ የወይኑ ቅጠልም መድኃኒታችን ክርስቶስ በወይን የተመሰለ ደሙን አፍስሶ ለምእመናን የሕይወት መጠጥ አድርጎ መስጠቱን ለማዘከር በወይን ሥርዓተ ሕጽበትን እናከናውናለን (ማቴ. ፳፮፥፳፮)፡፡ በቀኝና በግራ የቆሙ ሊቃውንትም ‹‹ሐዋርያቲሁ ከበበ እግረ አርዳኢሁ ሐጸበ›› እያሉ ይዘምራሉ፡፡ ይህ ሥርዓት ከተጠናቀቀ በኋላ ሥርዓተ ቅዳሴው ተከናውኖ ቅዱስ ሥጋውን ክቡር ደሙን ምእመናን ይቀበላሉ፡፡

 ቅዳሴ

የጸሎተ ሐሙስ ቅዳሴ የሚከናወነው በተመጠነ ድምፅ ሲሆን፣ እንደ ደወል (ቃጭል) የምንጠቀመውም ጸናጽልን ነው፡፡ ልኡካኑ የድምፅ ማጉያ ሳይጠቀሙ በለኆሣሥ (በቀስታ) ይቀድሳሉ፡፡ ምክንያቱም ይሁዳ በምሥጢር ጌታችንን ማስያዙን ለመጠቆም ሲሆን፣ በሌላ በኩል ደግሞ የዘመነ ብሉይ ጸሎት ዋጋው ምድራዊ እንደ ነበር ለማስታወስ ነው፡፡ በመቀጠል ክብር ይእቲ፣ ዕጣነ ሞገር፣ ዝማሬ የተባሉ የድጓ ክፍሎች ተዘምረው አገልግሎቱ ይጠናቀቃል፡፡ ሕዝቡም ያለ ኑዛዜና ቡራኬ ይሰናበታሉ፡፡

ጉልባን

ጉልባን ከባቄላ ክክ፣ ከስንዴ ወይንም ከተፈተገ ገብስ ጋር አንድ ላይ ተቀቅሎ የሚዘጋጅና የጸሎተ ሐሙስ ዕለት የሚበላ ንፍሮ ነው፡፡ በጸሎተ ሐሙስ በቤት ውስጥ ከሚፈጸሙ ተግባራት አንዱ ጉልባን ማዘጋጀት ነው፡፡ ጉልባን እስራኤላውያን ከግብጽ ባርነት ሲወጡ በችኮላ መጓዛቸውን የምናስታውስበት ከእስራኤላውያን የመጣ ትውፊታዊ ሥርዓት ነው፡፡ በአገራችን ኢትዮጵያ አብዛኞቹ የትውፊት ክንዋኔዎች የብሉይ ኪዳን መነሻ ስላላቸው ይህ ሥርዓት ዛሬም በኢትዮጵያውያን ምእመናን ዘንድ ይከበራል፡፡

ጉልባን እስራኤላውያን ከባርነት በወጡ ጊዜ አቡክተው፣ ጋግረው መብላት አለመቻላቸውን ያስታውሰናል፡፡ በወቅቱ ያልቦካውን ሊጥ እየጋገሩ ቂጣ መመገብ፤ ንፍሮ ቀቅለው ስንቅ መያዝ የመንገድ ተግባራቸው ነበርና፡፡ ይህን ታሪክ ለማሰብም በሰሙነ ሕማማት በተለይም በጸሎተ ሐሙስ ቂጣና ጉልባን ይዘጋጃል፡፡ በጸሎተ ሐሙስ የሚዘጋጀው ጉልባንና ቂጣ ጨው በዛ ተደርጎ ይጨመርበታል፡፡ ይኸውም ጨው ውኃ እንደሚያስጠማ ሁሉ፣ ጌታችንም በመከራው ወቅት ውኃ መጠማቱን ለማስታወስ ነው፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

0 replies

Leave a Reply

Want to join the discussion?
Feel free to contribute!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *