ጥምቀተ እግዚእ፣ የጌታ ጥምቀት

በመምህር ፍቃዱ ሳህሌ

ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከድንግል ማርያም በተወለደ በ፴ ዘመኑ በማየ ዮርዳኖስ፣ በእደ ዮሐንስ መጠመቁ ይታወቃል። በዚህ ጥምቀቱም ወንጌላውያን እንደገለጹት ሰማያት ተከፍተዋል። መተርጉማኑ እንዳስተማሩን ሰማያት በርና መስኮት ኖሯቸው፣ መከፈትና መዘጋትም ኖሮባቸው አይደለም፤ ምሥጢራት ተገለጡ ማለቱ ነው እንጂ። በዕለተ ጥምቀት በዮርዳኖስ ወንዝ የተገለጡት ምሥጢራት በርካታ ናቸው። ዋና ዋናዎቹን ብቻ መርጠን በማሳያነት እናቀርባቸዋለን።

ምሥጢረ ሥላሴ፡- በብሉይ ኪዳን ዘመን የእግዚአብሔርን ሦስትነት የሚገልጡ በርካታ ምንባባት ከቅዱሳት መጻሕፍት በአስረጂነት ይገኛሉ። ይሁንና በተረዳ ሁኔታ መጻሕፍት ይናገሩ የነበረው አንድነቱን በማጉላት ነው። “እስራኤል ሆይ ስማ! አምላካችን እግዚአብሔር አንድ እግዚአብሔር ነው” እንዲል። (ዘዳ.፮፥፬) በድንግዝግዝ ዓይነት የታወቀው የእግዚአብሔር ሦስትነት በሚገባ የተገለጠው በዚህ ዘመን በክርስቶስ መጠመቅ ነው። (ማቴ. ፫፥፲፮-ፍጻሜ)፡፡ ወልደ እግዚአብሔር ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ተጠምቆ ከወጣ በኋላ አብ በሰማይ ሆኖ “የምወደው ልጄ ይህ ነው” የሚል የምስክርነት ቃሉን ገለጠ። መንፈስ ቅዱስም አርጋብ ከማደሪያቸው በማይንቀሳቀሱበት ሰዓተ ሌሊት በነጭ ርግብ አምሳል ወርዶ በራሱ ላይ አርፎ ታይቷል። በዚህም መሠረት ለዘመናት ሥውር የነበረ የእግዚአብሔር የአካላት ሦስትነት ተገለጠ። በተጨማሪም ምንም እንኳ የመንፈስ ቅዱስ ግብር በጎላ በተረዳ ባይገለጥም የአብ ወላዲነት፣ የወልድም ተወላዲነት በዕለተ ጥምቀቱ ተገልጧል።

የክርስቶስ የባሕርይ አምላክነት፡- ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በተጠመቀ ጊዜ ከተገለጡት    ምሥጢራት አንዱ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ የባሕርይ አምላክነት ነው። ሥጋን ተዋሕዶ በመገለጡ ግራ የተጋባው ዓለም ማንነቱን ያውቅ ዘንድ ከላይ እንደገለጥነው አብ “ልጄ ነው”  ብሎ፣ መንፈስ ቅዱስም በራሱ ላይ ዐርፎ (ተቀምጦ) በመሰከሩት ምስክርነት የባሕርይ አምላክ መሆኑ ተገለጠ። ነቢዩ ቅዱስ ዳዊት እንደ ተነበየው ባሕር አይታ ስትሸሽ፣ ዮርዳኖስም ፈርቶ ወደ ኋላው ሲመለስ፣ ክርስቶስም በቦታው ተረጋግቶ እንዲቆም ሲያዝዘውና ፀጥ ብሎ ሲቆም በመታየቱ በዮርዳኖስ የተገኘው እርሱ አምላካቸው፣ ፈጣሪያቸው እንደሆነ ተገለጠ። (መዝ.፸፮፥፲፮፣ ፻፲፫፥፫) “…ሶበ መጽአ ቃል እምሰማይ ለተናብቦ፣ ነድ ለማየ ባሕር ከበቦ፣ ማይ ኀበ የሐውር ጸበቦ፤ቃል ከሰማይ በተሰማ ጊዜ የባሕሩን ውኃ (ዮርዳኖስን) እሳት (መለኮታዊ) ከበበው፤ ውኃውም የሚሄድበት ጨነቀው (ስፍራ ጠበበው)” እንዲል።

መጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ ስለ እርሱ ባስተማራቸው ትምህርቶች የክርስቶስን የባሕርይ አምላክነት ገለጠ። መጥምቀ መለኮት ነገረ ክርስቶስን ሲገልጥ፡- “ጫማውን እሸከም ዘንድ የማይገባኝ፤ ከእኔ በኋላ የሚመጣው ከእኔ ይልቅ ይበረታል፤ እርሱ  በመንፈስ ቅዱስ በእሳትም ያጠምቃችኋል፤ መንሹ በእጁ ነው፤ ዐውድማውንም ፈጽሞ ያጠራል፤ ስንዴውን በጎተራ ይከታል፤ ገለባውን ግን በማይጠፋ እሳት ያቃጥለዋል፤ ከእኔ በኋላ የሚመጣው እርሱ ከእኔ በፊት ነበርና ከእኔ ይልቅ የከበረ ሆኗል፤ ጸጋና  እውነት  በኢየሱስ  ክርስቶስ ሆነ፤ መቼም ቢሆን እግዚአብሔርን ያየው አንድ ስንኳ የለም፤ በአባቱ እቅፍ ያለ አንድ ልጅ እርሱ ተረከው፤ እኔ ክርስቶስ አይደለሁም፤ እናንተ የማታውቁት በመካከላችሁ ቆሟል፤ እነሆ የዓለምን ኃጢአት የሚያስወግድ የእግዚአብሔር በግ” እያለ የሰጠው ምስክርነት የባሕርይ አምላክነቱን ግልጽ አድርጎታል። ይህንኑ ሲያጠቃልል “እኔም አላውቀውም ነበር፤ ዳሩ ግን ለእስራኤል ይገለጥ ዘንድ ስለዚህ በውኃ  እያጠመቅሁ እኔ መጣሁ።…በውኃ አጠምቅ ዘንድ የላከኝ እርሱ፡- መንፈስ ሲወርድበትና ሲኖርበት የምታየው፣ በመንፈስ ቅዱስ የሚያጠምቅ እርሱ ነው አለኝ። እኔም አይቻለሁ፤ እርሱም የእግዚአብሔር ልጅ እንደሆነ መስክሬአለሁ።”  (ዮሐ.፩.፴፩፥፴፭) ብሏል።

ከላይ የገለጻቸው የቅዱስ ዮሐንስ መጥምቅ ምስክርነቶች የዕሩቅ ብእሲ (የሰው) ተግባራት እንዳይደሉ ከእግዚአብሔር በቀር ሌላ ፍጡር ሊከውናቸው እንደማይችሉ ግልጽ ነው። ለዚህ ነው መጥምቁ “እርሱ የእግዚአብሔር ልጅ እንደሆነ መስክሬአለሁ”  በማለት ያጠቃለለው። “መምህር ሆይ እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር (በተዋሕዶተ ሥላሴ) ከሆነ በቀር አንተ የምታደርጋቸውን እነዚህን ምልክቶች ሊያደርግ የሚችል የለምና መምህር ሆነህ ከእግዚአብሔር ዘንድ እንደመጣህ እናውቃለን”  እንዲል። (ዮሐ. ፫፥፪)

የዕዳ ደብዳቤያችን መቀደዱ፡ ከዚሁም ጋር አንዱ የዕዳ ደብዳቤ መቀደዱ ተገለጠ። ዲያብሎስ “አዳም የዲያብሎስ ባርያ፣ ሔዋን የዲያብሎስ ገረድ” በማለት መከራ አጽንቶ ያስፈረማቸው የዕዳ ደብዳቤ ነበረ። ይህንንም በሁለት ቅጅ አድርጎ አንዱን በዮርዳኖስ ጥልቅ ባሕር፣ አንዱንም በሲኦል ጥልቅ ረግረግ ቀብሮት ነበር። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዮርዳኖስ በተጠመቀ ጊዜ እንደ ሰውነቱ ረግጦ፣ እንደ አምላክነቱም አቅልጦ በዚህ ተጥሎ የነበረውን የዕዳ ጽሕፈት ደመሰሰው። ከዚህም የተነሣ ነው ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ “በእኛ ላይ የነበረውን የሚቃወመንንም በትእዛዛት የተጻፈውን የዕዳ ጽሕፈት ደመሰሰው። እርሱንም በመስቀል ጠርቆ ከመንገድ አስወግዶታል”  በማለት ያስተማረን። (ቆላ.፪፥፲፬) ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ይህን በማድረጉም ሁሉን ማድረግ የሚችል እውነተኛው የሰው ልጆች ሐኪምና መድኃኒት መሆኑ ተገለጠ። “ስለዚህ የዲያብሎስን ሥራ እንዲያፈርስ የእግዚአብሔር ልጅ ተገለጠ” እንዲል። (፩ኛ ዮሐ. ፫፥፰)

ከክርስቶስ ሞትና ትንሣኤ መተባበራችን፡– በተጨማሪም ጥምቀተ ክርስቶስ ሞቱንና ትንሣኤውን እያዘከረ ሰዎች ሁሉ በሚጠመቁበት ጊዜ ከክርስቶስ ሞት (መስቀል) እና ትንሣኤ ተሳታፊ መሆናቸው የተገለጠበት ታላቅ ምሥጢር ነው። ለመጠመቅ ወደ ማዩ ሲወርዱ ሞቱን፣ መቀበሩን፣ ከውኃው ሲወጡ ደግሞ ትንሣኤውን ይመሰክራሉ። ግብሩ ሦስት ጊዜ መደጋገሙም ክርስቶስ በከርሠ መቃብር ሦስት መዓልትና ሦስት ሌሊት ማደሩንና ምሥጢረ ሥላሴን ይገልጣል።   “እንግዲህ   ክርስቶስ በአብ ክብር ከሙታን እንደተነሣ እንዲሁ እኛም በአዲስ ሕይወት እንድንመላለስ ከሞቱ ጋር አንድ እንሆን ዘንድ በጥምቀት ከእርሱ ጋር ተቀበርን። ሞቱን በሚመስል ሞት ከእርሱ ጋር ከተባበርን ትንሣኤውን በሚመስል ትንሣኤ ደግሞ ከእርሱ ጋር እንተባበራለን።”(ሮሜ.፮፥፬-፮) በማለት ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ የገለጠው ይህንን ነው። በተመሳሳይም ይኸው ሐዋርያ “በጥምቀት ከእርሱ ጋር ተቀበራችሁ በጥምቀት ደግሞ ከሙታን ባስነሣው በእግዚአብሔር አሠራር በማመናችሁ ከእርሱ ጋር ተነሣችሁ።”  (ቆላ.፪፥፲፪) በማለት በጥምቀቱ የተገለጠውንና የተገኘውን ነገረ ድኅነት አመሥጥሮታል።

ከክርስቶስ ጋርና እርስ በእርሳችን አንድ መሆናችን፡ በጌታችን ጥምቀት ከተገለጡት ምሥጢራት መካከል ሌላኛው የሰው ልጆች ሁሉ በሥጋ ከአንድ አባትና እናት (አዳምና ሔዋን) የተገኙ እንደመሆናቸው በተጠመቁ ጊዜ ደግሞ በመንፈሳዊ ልደት ዳግመኛ አንድ መሆናቸው የተገለጠበት ምሥጢር ነው። በቀናች ሃይማኖት ሆነው የተጠመቁና የሚጠመቁ ሁሉ ምድራዊ የሆነ ማንኛውም ዓይነት መሥፈርት ሳያግዳቸው ወንድማማችና እኅትማማች ይሆናሉ።   ሁሉም ከአንድ አብራክ (ከመንፈስ ቅዱስ) የተከፈሉና በአንድ ማኅፀነ ዮርዳኖስ ማየ ጥምቀት በመንፈስ ቅዱስ ግብር ተገኝተው የተወለዱ ናቸውና። ቅዱስ ጳውሎስ “ከክርስቶስ ጋር አንድ ትሆኑ ዘንድ የተጠመቃችሁ ሁሉ ክርስቶስን ለብሳችኋል” በማለት እንዳስተማረው። (ገላ.፫፥፳፯)። እንደገናም “አይሁድ ብንሆን፣ የግሪክ ሰዎችም ብንሆን፣ ባርያዎችም ብንሆን፣ ጨዋዎችም ብንሆን እኛ ሁላችን በአንድ መንፈስ አንድ አካል እንድንሆን ተጠምቀናልና፤ ሁላችንም አንዱን መንፈስ ጠጥተናልና” እያለ በግልጽ አስተምሮናል። (፩ኛ ቆሮ. ፲፪፥፲፫)።

የክርስቶስ መካነ ጥምቀት ተፈጥሮአዊ ገጽታ በራሱ የሰው ልጆች በክርስቶስ ጥምቀት  ያገኙትን  አንድነት ያሳያል። እንደሚታወቀው ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሊጠመቅበትና ምሥጢራትን ሊገልጥበት ከአፍላጋት ሁሉ የመረጠው ወንዝ ዮርዳኖስ ነው። ይህ ወንዝ ከላይ ነቅዑ (ምንጩ) አንድ ሆኖ ይወርዳል። ከዚያም አወራረዱ በሁለት የተከፈለ ይሆናል። እነዚህም ሁለት ወንዞች “ዮር” እና “ዳኖስ” በመባል ይታወቃሉ። ወርደው ዳግመኛ አንድ ላይ ተገናኝተው “ዮርዳኖስ”   ተብለው ይፈሳሉ። ዲያብሎስ መገናኛቸው ላይ ከተፈጠረው ጥልቅ ባሕር ነበር አንዱን የዕዳ ደብዳቤ የቀበረው። ጌታችንም ከዚሁ መገናኛ ባሕር ላይ ነው የተጠመቀው። ይህንንም በማድረጉ አንድ ሆነው ወርደው ተለያይተው የነበሩ ወንዞች እንደተገናኙ ሰዎች ሁሉ የአዳምና የሔዋን ልጆች ሆነው (አንድ ሁነው) ሳለ ሕዝብ፣ አሕዛብ፣ የተገረዘ፣ ያልተገረዘ፣…በመባባል ተለያይተው የነበሩ ሰዎች በክርስቶስ ጥምቀት ያለምንም ልዩነት አንድ መሆናቸው በምሥጢር ተገልጧል። “ዮር”  ከግዙራን ወገን፣  “ዳኖስ”ም ከኢ-ግዙራን ወገን ሆነው ሳለ አንድ ሆነው በመፍሰሳቸው ሰዎች ያለ ልዩነት በጥምቀት አንድ እንደሚሆኑ ሲመሰክር ኖሯል ይኖራልም።

ከመገለጥ ጋር በተያያዘ ጌታችን መድኃኒታችን   ኢየሱስ   ክርስቶስ ሳይውል ሳያድር ገዳመ ቆሮንቶስ ገባ። ዐርባ መዓልት ዐርባ ሌሊት ከጾመ በኋላ ከገዳም ወጥቷል። በሦስተኛውም ቀን ወደ ሠርግ ቤት ተጠራ።

ቃና ዘገሊላ

ከጥር ዐሥራ ሁለት እስከ ዐሥራ ስምንት ባለው ጊዜ ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያናችን የምትዘምረው መዝሙር አንድ ወጥ ምሥጢር ያለው ነው። “ሖረ ኢየሱስ በትፍሥሕት ውስተ ከብካብ እንዘ ይገብር ተአምረ ወመንክረ በውስተ አሕዛብ፤ ጌታችን ኢየሱስ በደስታ ወደ ሠርጉ ቤት ሔደ፤ በአሕዛብ መካከል ድንቅ የሆነ ተአምርን እያደረገ።”  እያለ የሚቀጥል ነው መዝሙሩ። “ክብሩን ገልጦ አሳይቷቸዋልና ደቀ መዛሙርቱ አመኑበት። ውኃን ቀድታችሁ ጋኖቹን እስከ አፋቸው ድረስ ሙሏቸው አላቸው። የአሳላፊዎቹ አለቃ የባሕርይ አምላክ ኢየሱስ ክርስቶስ በተአምር ያደረገውን በረከት ቀምሶ አደነቀ።” ቤተ ክርስቲያንም በዚህ መሠረት አዳኛችንና ተስፋችን የሆነ ወልደ እግዚአብሔር ውኃውን ግሩም ወይን ወደ መሆን ለውጦታልና። እያለች ትዘምራለች፤ እኛም እንዘምራለን። በዚህ ሠርግ ቤት የተገለጡ ዋና ዋና ምሥጢራትም የሚከተሉት ናቸው፡፡

የድንግል ማርያም አማላጅነት፡ ይህን የቃና ዘገሊላውን የዶኪማስ ሠርግ በተመለከተ በዝርዝር የሚናገረው የቅዱስ ዮሐንስ ወንጌል ምዕ. ፪ ቁጥር ፲፩ ላይ በግሩም ሁኔታ ነው የጠቀለለው። “ኢየሱስ ይህን የተአምራት መጀመሪያ በቃና ዘገሊላ አደረገ፤ ክብሩንም ገለጠ፤ ደቀ መዛሙርቱም በእርሱ አመኑ።” በማለት ያስረዳናል። በዚህ ሠርግ ቤት እንደሚታወቀው ከፍተኛ የሆነ ጭንቀት ተፈጥሮ ነበር፤ የወይን ጠጃቸው አልቆ፣ የሚሰጡትም አጥተው በኀፍረት ተሸማቅቀዋልና። በዚህ አስቸጋሪ ሰዓት “የወይን ጠጅ እኮ የላቸውም” በማለት በእነሱና በልጅዋ መካከል ምልጃዋን ያቀረበችው እናታችን እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ናት። ከአንቺ ጋር ምን አለኝ፤ ያልሽኝን ላላደርግልሽ ከአንቺ ሰው ሆኛለሁን? ባላትም ጊዜ ‹‹የሚላችሁን አድርጉ!”  ብላ በማዘዝ የሠርጉ ባለቤቶች (ደጋሾች) ከስጋትና መረበሽ ከኀፍረትም ነጻ እንዲሆኑ ምክንያት በመሆኗ የጭንቅ አማላጅነቷ ተገለጠ። ለሰው ልጆች ሁሉ ያላት ፍቅርና አዛኝነቷ፣ የጭንቅ ቀን ደራሽነቷ፣ ልመናዋም አንገት የማያስቀልስ፣ ፊት የማያስመልስ መሆኑ በግልጽ ታወቀ።

ይህን ድንቅ ምሥጢር በተመለከተ ኢትዮጵያዊው ቄርሎስ አባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫ በመጽሐፈ ምሥጢር ላይ “ድንግል ውኃውን ወይን ወደ መሆን እንደሚለውጠው አላወቀችም፤ ነገር ግን በአብ ጥላ (ጽላሎት) እንደፀነሰችው በልዑል ኃይልም እንደወለደችው ታውቃለችና፤ ስለዚህም ድንግል የምሥራቹን ከነገራት መልአክ ዘንድ አባቱ ሰማያዊ እንደሆነ ተረድታለችና ስለ ወይን ማለደችው፤ በልቧ ድንቆችን የሚያደርግ የእርሱ ልጅ እንደ አባቱ ድንቅን ያደርጋልና አለች።››  በማለት የድንግል ማርያም አማላጅነት የእርሱም (የልጇ) የባሕርይ አምላክነት መገለጡን ጽፎልናል። (የቃና ዘገሊላ ምንባብ ቁጥር. ፰)

የክርስቶስ ክብር፡- ጌታችን  አምላካችን  መድኃኒታችን  ኢየሱስ  ክርስቶስ በቅዱስ  ወንጌል  እንደተጻፈውና  ከላይ  እንደገለጽነው በዚህ ሠርግ ቤት ክብሩን ገልጧል። “የቱን ክብሩን ነው ለመሆኑ የገለጠው?” የሚል ጥያቄና ምላሽ መፈለግ ተገቢ ይሆናል። ለዚህ ጥያቄ መልስ የሰጠው ወንጌላዊው ቅዱስ ዮሐንስ በጻፈልን ወንጌል ራሱ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። እንዲህ ሲል፡- “አርአዮሙ ስብሐቲሁ አምኑ ቦቱ አርዳኢሁ፤ አምላካዊ ተአምራቱን አሳያቸው፣ ደቀ መዛሙርቱም አመኑበት” (ቅዱስ ያሬድ)። የሥጋን እንግድነት ሲያይ “አክብረኝ” አለ እንጂ ክብሩስ ቅድመ ዓለም ከባሕርይ አባቱ ከአብ ከባሕርይ ሕይወቱ ከመንፈስ ቅዱስ ጋር የነበረና በአንድነት፣ በሦስትነት የሚሰለስ፣ የሚቀደስ አምላክ ነው። በቃና ዘገሊላ “ክብሩን ገለጠ”   ያለውም የአምላክነትን ሥራ ሠርቶ የባሕርይ አምላክ መሆኑን የገለጠበትን ነው። ጣዕም፣ መልክ፣ መዓዛ ያልነበረውን ውኃ በሐልዮ (በሐሳብ) ወደ ተደነቀ ወይን ጠጅነት የቀየረና ሊቀይርም የሚችል ያለ እግዚአብሔር በቀር ሌላ የለምና። ከዚህ ሁሉ ጋር ወልደ እግዚአብሔር ኢየሱስ ክርስቶስ የሰውነት ጣዕም፣ መልክና መዓዛ በኃጢአቱ ወደ ተበላሸበት የሰው ልጅ መጥፎ ሕይወት መጥቶ ወደ ተደነቀው (ፈጣሪውን ወደሚመስልበት) ማንነቱ የሚመልሰው መሆኑን በዚህ ሠርግ ላይ በአደረገው ተአምር ውስጥ ገለጠልን። በዚህ የመገለጥ ዘመን መድኃኔዓለም ክርስቶስ የገለጠውና ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያናችን የምታመሠጥራቸው ትምህርቶች በርካታ ናቸው። ስለዚህ አስተርእዮ ማለት መገለጥ ማለት እንደሆነና የተገለጡትም ምሥጢራት በረካታ እንደሆኑ ተመልክተናል።

ማጠቃለያ

“አሥተርአየ ዘኢያስተርኢ ኮነ እሙነ አሥተርእዮቱ ለመድኃኒነ ክርስቶስ ፤ የማይታየው ታየ፣ የመድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መታየቱም የታመነ ሆነ። ተገሠ ዘኢይትገሠሥ ወዘይትርአይ ተርየ፣ የማይዳሰሰው ተዳሰሰ፣ የማይታየው ታየ” በማለት ቅዱስ ያሬድ የክርስቶስን መገለጥ ገልጿል።

“ዘመነ አስተርእዮ፤ የመገለጥ በዓል ነው” የሚለውን ማወቅ፤  ምን  ምን  እንደተገለጠም  መረዳት  ጠቃሚ ጉዳይ ነው። ይሁንና ዋናው ጠቃሚ ቁም ነገር ከዚህ ከፍ ያለ መሆኑን መገንዘብ ይገባል። የመገለጥ ሃይማኖት የሆነችውን  ክርስትናን  ይዞ፥  ክርስቲያንም  ተብሎ ተጠርቶ ተደብቆ መኖር ማክተም አለበት። ብዙዎቻችን ክርስትናችንን ከመግለጥ ይልቅ ሸፋፍነን ደብቀነዋል። ከላይ እንደገለጥነው መንፈሳዊው የሕይወት ምግብ ጠፊ በሆነ ምድራዊ መብል መጠጥ ተሸፍኗል። ዘለዓለማዊው በጊዜያዊው፣ መንፈሳዊው በሥጋዊው፣ የማይጠፋው በሚጠፋው፣. . .ወዘተ ተደብቋል። እኛም ራሳችንን በነዚህ ጭንብሎች ውስጥ ተደብቀን ራሳችንን እየደለልን ነው።

ቅዱስ ያሬድ ስለ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መገለጥ “አሥርአየ ዘኢያስተርኢ ኮነ እሙነ አሥተርእዮቱ ለመድኃኒነ ክርስቶስ፤ የማይታየው ታየ፣ የጌታችን መድኃኒታን የኢየሱስ ክርስቶስ መታየቱም የታመነ ሆነ” በማለት ተናገረ። ከዚህም በተጨማሪ “ተገሠ ዘኢይትገሠሥ ወዘኢይትረአይ ተርእየ፤ የማይዳሰሰው ተዳሰሰ፣ የማታየው ታየ” ብሏል።

ሃይማኖቴ የመገለጥ ነው፤ ዘመኑም የመገለጥ ነው፤ የምንል እኛ ክርስቲያኖች በነገሮች፣ በቦታና በጊዜያት ሁሉ  ሳንፈራ፣  ሳናፍርና  ሳንሸማቀቅ  ክርስትናችንን መግለጥ አለብን። ባለንበት የሰማዕታት ዘመን “ማዕተባችን ከሚበጠስ አንገታችን ይበጠስ!” እያሉ ራሳቸውን የሰጡ የተገለጡ ክርስቲያኖችን አይተናል። ከዚህ አንጻር በሰዎች መካከል አማትበንና ስመ ሥላሴን ጠርተን ማዕድ መቁረስ የሚያሳፍረንና የሚያሸማቅቀን እኛ ምን ልንባል እንችላለን?

ስለዚህ ይህ በዓል እየነገረን ያለው “የተገለጠ ክርስትና ይኑራችሁ! ክርስትና ለድርድር አይቀርብምና መስቀሉን ተሸክማችሁ  ወደ  ቀራንዮ  ተጓዙ!፣  …  በማስመሰል (ለሰው ይምሰል) የተመላለሳችሁበት ዘመን ይብቃችሁ! ለሥጋ የምትጨነቁትን ያህል ለነፍሳችሁም ቦታና ክብር ስጡ! ለምስክርነት ራሳችሁን አዘጋጁ!. . .” የሚሉትን ጭብጦች ነው። እኛ ቤተ ክርስቲያንን ጠጠር መጣያ እስኪጠፋ እየሞላን፤ ልባችን በጥላቻ፣ በዘረኝነት፣ በዝሙት፣ በስርቆት፣ በኑፋቄ፣ በትዕቢት፣. . . ከተሞላ ምን ይረባናል? ክርስቲያናዊ ሕይወታችን በፍቅር፣ በሰላም፣ በንጽሕና፣ በአንድነት፣ በምሕረት፣ በይቅርታና በቅዱሱ ምሥጢር የተገለጠና የታተመ ሊሆን ካልቻለ የተፈለገውንና ሰማያዊውን ጥቅም ሊያስገኝ አይችልም። ስለዚህ ይህን ድንቅና ልዩ ምሥጢር የጠገለጠበትን በዓል ማክበር በሚገባን መልኩ አክብረን በረከተ ሥጋ፣ በረከተ ነፍስ እንድናገኝ የእግዚአብሔር መልካም ፈቃዱ ይሁንልን አሜን።

0 replies

Leave a Reply

Want to join the discussion?
Feel free to contribute!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *