ግዝረት

ግዝረት ማለት መገረዝ(ከሸለፈት ነጻ መሆን) ማለት ነው፡፡ የተጀመረውም በአበ ብዙኃን አብርሃም ነው፡፡  “በእኔና በአንተ መካከል ከአንተም በኋላ በዘርህ መካከል የምትጠብቋት ቃል ኪዳኔ ይህች ናት፣ ከእናንተ ወንድ ሁሉ ይገረዝ፡፡ የሰውነታችሁን ቍልፈት ትገረዛላችሁ፣ በእኔና በእናንተም መካከል ላለውም ቃል ኪዳን ምልክት ይሆናል፡፡ ሕፃኑንም በስምንተኛው ቀን ትገርዙታላችሁ”(ዘፍ.፲፯.፲) በማለት እግዚአብሔር ለአብርሃም ቃል ኪዳኑን ይጠብቅ ዘንድ፣ ከእርሱም በኋላ የሚመጣው ትውልድ ይህንን ቃል ኪዳን ይጠብቅ ዘንድ ተናግሮታል፡፡

ግዝረት ከጌታችን ከመድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ዘጠኙ ንዑሳን በዓላት አንዱ ነው፡፡ እነዚህ ንዑሳን በዓላት የሚባሉትም ስብከት፣ ብርሃን፣ ኖላዊ፣ ግዝረት፣ ቃና ዘገሊላ፣ ልደተ ስምዖን፣ ደብረ ዘይት፣ የመስከረም ፲፯ እና የመጋቢት ፲ መስቀል የምናከብራቸው በዓላት  ናቸው፡፡ በዚህም መሠረት የጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዓለ ግዝረት በየዓመቱ ጥር ፮ ቀን በቅድስት ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያናችን ይከበራል፡፡

ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ እንግዲህ ክርስቶስ የእግዚአብሔርን ቃል እውነት ለማድረግ የአባቶቻችንንም ተስፋ ያጸና ዘንድ ለግዝረት መልእክተኛ ሆነ እላለሁ” በማለት ለሮሜ ክርስቲያኖች ጽፎላቸዋል፡፡ የክብር ባለቤት መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በተወለደ በስምንተኛው ቀን ወደ ቤተ ግዝረት በመግባት የኦሪትን ሕግ ፈጽሟል፣ በሥጋው ግዝረትንም ተቀበለ፣ ለአባቶች የሰጠውንም ቃል ኪዳን ፈጸመ፡፡(ሮሜ.፲፭፥፰)፡፡

በቅዱስ ወንጌል እንደ ተጻፈው በስምንተኛው ቀን እንደ ኦሪቱ ሥርዓት ግዝረት ይፈጸምለት ዘንድ ሕፃኑ ጌታችንን ወደ ቤተ መቅደስ ወሰዱት፡፡ ስሙም ገና ሳይፀነስ የእግዚአብሔር መልአክ ባወጣለት ስም ኢየሱስ” ተብሎ ተጠራ(ሉቃ.፪፥፳፩-፳፬)፡፡ መጥምቁ ዮሐንስ ሲገረዝ የሊቀ ካህን ልጅ ነው ብለው ሊገርዙት ወደ እርሱ መጡ፡፡ ጌታችን ግን ወደ ምድር የመጣው ለትሕትና ነው እንጂ ለልዕልና አይደለምና ወሰዱት አለ (ትርጓሜ ወንጌለ ሉቃስ)፡፡

አይሁድ የአብርሃም ልጅ ለመሆናቸው ማረጋገጫ ግዝረት ማኅተም ነው፡፡ በሕግና በሥርዓት የሚመሩ መሆናቸውንና በአንድ አምላክ ማመናቸውን የገለጡበት ነው፡፡ አይሁድ በግዝረት የአብርሃም ልጅነታቸውን እንዳረጋገጡ፣ ክርስቲያኖችም በጥምቀት የሥላሴ ልጅነታቸውን ያረጋግጣሉ፡፡ ይህም ግዝረት የጥምቀት ምሳሌ መሆኑን ያስረዳል፡፡ በሐዲስ ኪዳን ጥምቀት እንጂ መገረዝ፣ አለመገረዝ አይጠቅምም፡፡

ጥር ስድስት በሚነበበው ስንክሳር እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም አረጋዊ ዮሴፍን ሕፃኑን የሚገርዝ ባለሙያ ፈልጎ እንዲያመጣ እንደነገረችው፣ አረጋዊውም ባለሙያውን ፈልጎ እንዳመጣ ይናገራል፡፡ ባለሙያውም “ሕፃኑን በደምብ ያዙልኝ” ብሎ ለመግረዝ ሲሰናዳ “ባለሙያ ሆይ ደሜ ሳይፈስ መግረዝ ትችላለህን?” ብሎ እንደጠየቀው፣ ከስቅለቱ በፊት ደሙ እንደማይፈስ እንዳስተማረው፣ በዚህም ምክንያት ለመግረዝ የመጣው ባለሙያ፣ አምላክ ወልደ አምላክ መሆኑን አምኖ እንደሰገደለት፣ ለመግረዣ ያዘጋጀው ምላጭም እሳት ላይ እንደተጣደ ቅቤ መቅለጡን ይተርካል፡፡

ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የእመቤታችንን ማኅተመ ድንግልና ሳይፈታ በግብረ መንፈስ ቅዱስ ተፀንሶ ዘጠኝ ወር ከአምስት ቀን ሲሞላው በድንግልና እንደመወለዱ ግዝረቱም አይመረመርም፡፡ እንዲሁም በተዘጋ ቤት ወደ ሐዋርያት እንደ ገባና እንደ ወጣ ሁሉ እርሱ በሚያውቀው ረቂቅ ጥበብ ምንም ደም ሳይፈሰው መገረዙ በተአምር ተገለጠ፡፡

ገራዡም የጌታችንን ቃል ከመስማቱ ባሻገር በሥጋው ላይ የተደረገውን ተአምር ባየ ጊዜ እጅግ አደነቀ፡፡ ከክብር ባለቤት ከጌታችን አምላካችንና መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እግር በታች ወድቆም ሦስት ጊዜ ሰገደና “በእውነት አንተ የእግዚአብሔር ልጅ፣ የእስራኤልም ንጉሥ ነህ!” በማለት በክርስቶስ አምላክነት አመነ፡፡ ከዚህ በኋላ ያየውንና የሰማውን ሁሉ እየመሰከረ ወደ ቦታው ተመለሰ፡፡ (ስንክሳር ጥር 6)፡፡

በአጠቃላይ ግዝረት በኦሪት የአብርሃም ልጅነትን፣ የአብርሃምን ሃይማኖት መያዝን ማረጋገጫ ማኅተም ሲሆን በሐዲስ ኪዳን በጥምቀት ተተክቷል፡፡ ለአማናዊው ግዝረት /ለጥምቀት/ ምሳሌ በመሆኑም በሥራ የአብርሃም ልጅነትን፣ በእምነት የሥላሴ ልጅነትን አግኝተንበታል፡፡  በዮርዳኖስ የተቀበረው የባርነታችን ደብዳቤም በጌታችን ጥምቀት የሚደመሰስ መሆኑን በምሳሌ ያወቅንበት ግዝረት ነው፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

0 replies

Leave a Reply

Want to join the discussion?
Feel free to contribute!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *