ዳግም ትንሣኤ

ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዕለተ ዐርብ ተሰቅሎ፣ በሦስተኛውም ቀን መቃብር ክፈቱልኝ መግነዝ ፍቱልኝ ሳይል በዝግ መቃብር ሞትን ድል አድርጎ ከተነሣና በትንሣኤው ትንሣኤአችንን ካወጀልን በኋላ ሐዋርያት በአንድነት ተሰብስበው ሳለ ተገልጦላቸዋል፡፡ ይህንንም ወንጌላውያኑ በመተባበር ገልጸውታል፡፡ በተለይ ቅዱስ ዮሐንስ ወንጌላዊ “ያም ከሳምንቱ የመጀመሪያው ቀን በመሸ ጊዜ ደቀ መዛሙርቱ አይሁድን ስለ ፈሩ ተሰብስበው የነበሩበት ቤት ደጁ ተቆልፎ ሳለ ጌታችን ኢየሱስ መጥቶ በመካከላቸው ቆመና ‘ሰላም ለእናንተ ይሁን’ አላቸው፡፡ ይህንም ብሎ እጆቹንና ጎኑን አሳያቸው፤ ደቀ መዛሙርቱም ጌታችንን ባዩት ጊዜ ደስ አላቸው” (ዮሐ. ፳፥፲፱-፳፤ ማቴ. ፳፰፥፲፮-፳፤ ሉቃ. ፳፬፥፴፮-፵፱) በማለት ገልጾታል፡፡

ይህ ሁሉ ሲሆን ግን ዲዲሞስ የተባለው ቶማስ አብሯቸው አልነበረምና የሆነውን ቢነግሩት አላምንም አለ፡፡ ይህንንም ወንጌላውያኑ ሲገልጹት “… ጌታችንን አየነው” አሉት፡፡ እርሱ ግን “የችንካሩን ምልክት በእጁ ካላየሁ፤ ጣቱንም ወደተቸነከረበት ካልጨመርሁ፤ እጄንም ወደ ጎኑ ካላስገባሁ አላምንም” አላቸው፡፡ (ዮሐ. ፳፥፳፬-፳፭)፡፡

ከስምንት ቀን በኋላም ሐዋርያት፣ ካላየሁ አላምን ያለው ቶማስን ጨምሮ በአንድነት ተሰብስበው ባሉበት በሩ እንደተዘጋ ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መጥቶ በመካከላቸውም ቆመ፡፡ እንዲህም አላቸው፡- “ሰላም ለእናንተ ይሁን፡፡” ከዚህም በኋላ ቶማስን “ጣትህን ወዲህ አምጣና እጆቼን እይ፤ እጅህንም አምጣና ወደ ጎኔ አግባ፤ እመን እንጂ ተጠራጣሪ አትሁን” አለው፡፡ ቶማስም ”ጌታዬ አምላኬም” ብሎ መለሰ፡፡ ጌታችን ኢየሱስም “ስለአየኸኝ አመንህን? ብፁዓንስ ሳያዩ የሚያምኑ ናቸው” አለው፡፡ (ዮሐ. ፳፥፳፮-፳፱)፡፡

በዚህም መሠረት ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ይህንን ዕለት ዳግም ትንሣኤ ብላ ሰይማ ሥርዓቱንም እንደ ትንሣኤው ትፈጽማለች፣ በድምቀት ታከብራለች፡፡

በዕለቱ በቅዳሴ ጊዜ የሚነበቡ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች፡-

  • መልእክታት፡- (፩ቆሮ. ፲፭፥፩-፳)
  •                   :- (፩ዮሐ. ፩፥፩- ፍጻሜው)
  • ግብረ ሐዋርያት፡- (ሐዋ. ፳፫፥፩-፲)
  • ወንጌል፡-       (ዮሐ. ፳፲፱-ፍጻሜው)
  • ቅዳሴ፡-         ዲዮስቆሮስ
0 replies

Leave a Reply

Want to join the discussion?
Feel free to contribute!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *