“የጽድቅንም ጥሩር ልበሱ”/ኤፌ.፮.፲፬/
በእንዳለ ደምስስ
ክፍል ሦስት
“የጽድቅንም ጥሩር ልበሱ” በሚል ርእስ በክፍል አንድ ዝግጅታችን ስለ ጾም በጥቂቱም ቢሆን ያቀረብን ሲሆን በክፍል ሁለት ደግሞ ጸሎትና የጸሎት ጥቅሞችን ማየት ጀምረን እንደነበር ይታወሳል፡፡ በክፍል ሁለት ዝግጅታችንም የጸሎት ጥቅሞችን በተመለከተ ከተጠቀሱት ውስጥ፡- በጸሎታችን ስለተደረገልን ሁሉ ምስጋና ማቅረብ፣ ስለ በደላችን ይቅርታን እናገኛለን፣ እንዲሁም መንፈሳዊ ኃይልን እናገኛለን በሚል አቅርበን ነበር፡፡ ቀሪዎቹ የጸሎት ጥቅሞችን ደግሞ ቀጥለን እናቀርባለን፡፡
. . .የጸሎት ጥቅሞች፡-
ምሥጢር ይገለጽልናል፡- ምሥጢር አመሥጠረ፣ አራቀቀ ካለው የግእዝ ግስ የወጣ ሲሆን ትርጉሙም ረቂቅ፣ የማይታይ፣ ኅቡእ፣ ሽሽግ፣ ማለት ነው፡፡ ምሥጢር የሰው ልጅ በራሱ ጥበብ መርምሮ ሊደርስበትና ሊያውቀው የማይችል፣ በእግዚአብሔር ፈቃድ ብቻ ሊገለጥ የሚችል ነው፡፡ “ያለ እኔ ምንም ልታደርጉ አትችሉምና” እንዲል(ዮሐ.፲፭.፭)፡፡
ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በባሕር ላይ በታንኳ ወጥቶ ሳለ ብዙ ሰዎች ወደ እርሱ ተሰበሰቡ፡፡ ጌታችንም የሰዎቹን መሰብሰብ በተመለከተ ጊዜ ስለ ዘርና ዘሪው በምሳሌ አስተማራቸው፡፡ ደቀ መዛሙርቱም ቀርበው “ስለምን በምሳሌ ትነግራቸዋለህ?” አሉት፡፡ ጌታችንም ለደቀ መዛሙርቱ “ለእናንተ የመንግሥተ ሰማያትን ምሥጢር ማወቅ ተሰጥቶአችኋል፣ በውጭ ላሉት ግን በምሳሌ ይሆንባቸዋል” አላቸው፡፡ (ማቴ.፲፫.፲፩፤ ማር.፬.፲፩)፡፡ ደቀ መዛሙርቱ ከእርሱ ጋር እየዋሉ እያደሩ የቃሉን ትምህርት፣ የእጁን ተአምራት እየተመለከቱ ኖረዋልና የመንግሥተ ሰማያትን ምሥጢር የማወቅ ጥበብ እንደሰጣቸው ነግሯቸዋል፡፡ ስለዚህ ወደ እግዚአብሔር ለቀረቡና እንደ ቃሉም ለሚጓዙ እንደ አቅማቸውና መንፈሳዊ ጥንካሬያቸው ምሥጢርን ይገልጻልና ለሕዝቡም በሚገባቸውና በሚረዱት ምሳሌ ገልጾ አስተማራቸው፡፡
ሰው ከወዳጆቹ፣ ከሚወዳቸውና ከሚወዱት በውስጡ የያዘውን(የደበቀውን) ምሥጢር ነው ብሎ የያዘውን ጉዳይ ገልጾ ላይናገር ይችላል፡፡ ለሌሎች ፍቅር አለኝ ቢልም እንኳን ሸሽጎ የሚያስቀምጠው ምሥጢር ይኖረዋል፡፡ ነገር ግን ከሰዎች ቢደበቅም ከእግዚአብሔር ሊሰወር አይቻለውም፡፡ እግዚአብሔር ግን ለመረጣቸውና ለፈቀደላቸው ብቻ በሚችሉት መጠን ምሥጢርን የሚገለጥ ነው፡፡ ለተመረጡት ስንል ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ብርሃነ መለኮቱን ይገልጥላቸው ዘንድ ከዐሥራ ሁለቱ ደቀ መዛሙርት መካከል ጴጥሮስን፣ ዮሐንስንና ያዕቆብን መርጦ ወደ ታቦር ተራራ እንደወሰዳቸው ቅዱስ ወንጌል ያስተምረናል፡፡ ሌሎቹን ግን በእግረ ደብር ትቷቸው ሦስቱን ብቻ ይዞ ሲወጣ ቀሪዎቹ እኛን ከምሥጢሩ ሸሸገን ብለው ከመከተል ወደ ኋላ አላሉም፣ እነርሱ ተለይተው በመቅረታቸው ስላላዘኑም ለሦስቱም ረቀ መዛሙርት የተገለጸው ምሥጢር ለቀሩትም ተገልጾላቸዋል፡፡ “ከስድስት ቀንም በኋላ ጌታችን ኢየሱስ ጴጥሮስን፣ ያዕቆብንና ወንድሙ ዮሐንስን ይዞ ለብቻቸው ወደ ረጅም ተራራ አወጣቸው፡፡ መልኩም በፊታቸው ተለወጠ፣ ፊቱም እንደ ፀሐይ በራ፣ ልብሱም እንደ ብርሃን ነጭ ሆነ፡፡ እነሆ ሙሴና ኤልያስም ከእርሱ ጋር ሲነጋገሩ ታዩአቸው”(ማቴ.፲፯.፩) እንዲል፡፡ ምሥጢር ዝም ብሎ አይገለጥም በመንፈሳዊ ሕይወት መጋደል፣ ዲያብሎስንም ድል የምንነሣበት ዕቃ ጦር መያዝ ያስፈልጋል፡፡ ከእነዚህም መንፈሳዊ መሣሪያዎች ውስጥ አንዱ ጸሎት ነው፡፡ ስለዚህ በጸሎት መትጋት ከእኛ ክርስቲያኖች ይጠበቃል፡፡
ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ወደ ቆላስይስ በላከው መልእክቱ “ስለ እርሱ የታሰርሁለትን የእግዚአብሔርን ምሥጢር እንድናገር እግዚአብሔር የቃሉን በር ይከፍትልን ዘንድ ለእኛም ደግሞ ጸልዩልን፣ ለምኑሉንም፡፡ ልናገርም እንደሚገባኝ እገልጠው ዘንድ ጸልዩልኝ” እያለ ሲማጸን እንመለከታለን፡፡ ይህም የእግዚአብሔር ቃል ምሥጢሩን ተረድተን፣ እንደሚገባው እንዲገለጥና ለሌሎች ብርሃን ለመሆን ጸሎት ምን ያህል ዋጋ እንዳለው ያሳየናል፡፡
ከፈተና እንድናለን፡- ፈተና በተለያዩ ምክንያቶች ሊመጣ ይችላል፡፡ የማይገባንን ምኞት በመመኘትና ይህንንም ለማሳካት በምናደርገው ውጣ ውረድ ውስጥ ወደ ማንወጣው ፈተና ውስጥ እንገባለን፡፡ ቅዱስ ዳዊት የጦር አለቃውን የኦርዮንን ሚስት በማይገባ ሁኔታ ተመኘ፣ ምኞቱንም ለማሳካት ባደረገው ጥረት ውስጥ ወደ ሌላ ፈተና ተሸጋገረ፡፡ ከቤርሳቤህ ጋር ዝሙትንም ፈጸመ፣ ኦርዮንንም እስከማስገደል አደረሰው፣ በዚህ አላበቃም በኃጢአት የተወለደውንም ልጅ በሞት አጣ፣ እግዚአብሔርንም አሳዘነ፡፡ በማይገባ ሁኔታ መመኘቱ ለከፋ ኃጢአት አሳልፎ ሰጠው፣ ፈተናውንም መቋቋም ተሳነው፡፡ በመጨረሻም ወደ ልቡናው ሲመለስ ልብሰ መንግሥቱን አውልቆ፣ በትረ መንግሥቱን ጥሎ ትቢያ ለብሶ፣ ዐመድ ነስንሶ በጾምና በጸሎት ወደ እግዚአብሔር ጮኸ፣ ጩኸቱንም እግዚአብሔር ተቀበለው፣ ይቅርም አለው፡፡ (ሳሙ.፲፩ እና ፲፪)፡፡
ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ጌቴሴማኒ ከቅዱሳን ሐዋርያት ጋር ሔዶ ከእነርሱ ፈቀቅ ብሎ ይጸልይ ነበር፡፡ ሐዋርያት ግን ከእርሱ ጋር በጸሎት ከመትጋት ይልቅ እንቅልፍ አሸንፏቸው ተኝተው አገኛቸው፡፡ በዚህም ምክንያት “አንድ ስዓት እንኳ ከእኔ ጋር እንዲህ ተሳናችሁን? ወደ ፈተና እንዳትገቡ ተግታችሁ ጸልዩ” ሲል ነግሯቸዋል፡፡ ከፈተና ለመጠበቅም ሆነ ከፈተና ለመውጣት ጸሎት እጅግ አስፈላጊ መሆኑን ያመለክተናል፡፡ (ማቴ.፳፮.፵፩)፡፡ መከራ ሲመጣ መሸሽ ሳይሆን በጽናት በሃይማኖት መቆምን ይጠይቃል፣ በሃይማኖት ለመቆም ደግሞ ጸሎት እጅግ አስፈላጊ ነው፡፡ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በገዳመ ቆሮንቶስ ዲያብሎስን ድል እንዳደረገው አባቶቻችንም አምላካቸውን አርአያ አድርገው በጸሎት በመትጋት ፈተናውን ታግሠው ድል ነስተው ተሻግረውታልና እኛም አባቶቻችንን አብነት አድርገን ተግተን መጸለይ ይገባል፡፡ ፍጻሜው መንግሥተ ሰማያት ነውና፡፡
የጎደለንን እናገኛለን፡- የሰው ልጅ በዚህ ምድር ላይ አንዱ ሲሞላለት ሌላው ሲጎድልበት በድካም ይኖራል፡፡ የጎደለውን ለማግኘትም ሰማይን ካልቧጠጥኩ፣ ምድርን ካልቆፈርኩ እያለ ይባዝናል፡፡ ይህ ደግሞ ከንቱ ድካም ነው፡፡ ነገር ግን ሥጋዊ ፍላጎታቸውን በመግታት፣ በጸሎት በመትጋት የጎደላቸውን መንፈሳዊ ሕይወት ይሞላላቸው ዘንድ አምላካቸውን እየተማጸኑ ራሳቸውን ለእግዚአብሔር ትእዛዛት ያስገዙ ቅዱሳን፣ ፃድቃን ሰማዕታት ይህንን ኃላፊውን ዓለም ድል ነሥተውታል፣ የጎደላቸውንም አግኝተዋል፡፡
የጎደለንን ለማግኘት በእግዚአብሔር መታመንን ይጠይቃል፣ ዘወትር በዓለማዊው ጥበብ ያጣነውን ለማግኘት ከመማሰን ወደ እግዚአብሔር በመጸለይ የሚገኘውን በረከት መጠበቅ መልካም ነው፡፡ ሳምራዊቷ ሴት ጎዶሎዋን ይሞላላት ዘንድ፣ ዳግመኛም ወደ ወንዝ እየወረደች ውኃ እንዳትቀዳ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ተማጽናለች፡፡ “ጌታ ሆይ እንዳልጠማ ዳግመኛም ውኃ ልቀዳ ወደዚህ እንዳልመጣ እባክህን ከዚህ ውኃ ስጠኝ” ስትል ጌታችንን የጎደላትን ነገር ጠየቀችው፡፡ (ዮሐ.፬.፲፭)፡፡
በቅድሚያ የጎደለንን ነገር ለይተን እንወቅ፣ የጎደለንን ለማግኘትም እግዚአብሔርን ተስፋ በማድረግ በጸሎት መትጋት ከእኛ ኦርቶዶክሳውያን ይጠበቃል፡፡ ሕዝቅያስ ታሞ ለሞትም በደረሰ ጊዜ በልቅሶና በዋይታ ከሞት ያድነው፣ ጤናውንም ይመልስለት ዘንድ ወደ እግዚአብሔር ጸለየ፣ እግዚአብሔርም የሕዝቅያስን ጸሎት ተቀብሎ ነቢየ እግዚአብሔር ኢሳይያስን ልኮም “የአባትህ የዳዊት አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፣ ጸሎትህን ሰምቻለሁ፣ ዕንባህንም አይቻለሁ፣ እነሆ እኔ እፈውስሃለሁ፣ . . . በዕድሜህም ላይ ዐሥራ አምስት ዓመት እጨምርልሃለሁ” ሲል ተናግሮታል፡፡ ያጣነው ጤና ቢሆን፣ የመንፈሳዊ ሕይወት ጉድለት ቢሆን፣ . . . ጉድለታችን ወደሚሞላው ወደ እግዚአብሔር በመጸለይ ነው፡፡ ሕዝቅያስ ጸልዮ እንደተከናወነለት እኛም ብንጸልይ እግዚአብሔር ይሰማናል ጉድለታችንንም ሞልቶ ይሰጠናል፡፡(፪ነገ.፳.፭)፡፡
ይቆየን፡፡
Leave a Reply
Want to join the discussion?Feel free to contribute!