የግቢ ጉባኤያት ፲፫ኛው ዓለም አቀፍ ሴሚናር ሁለተኛ ቀን ውሎ
የማኅበረ ቅዱሳን ፲፫ኛውን ዓለም አቀፍ የግቢ ጉባኤያት ሴሚናር ሁለተኛ ቀን ውሎውን በጸሎት ተጀምሮ የቀጠለ ሲሆን በደብረ ሰላም ቅዱስ እስጢፋኖስ ቤተ ክርስቲያን ስምዐ ጽድቅ ሰንበት ትምህርት ቤት መዘምራን ያሬዳዊ ዝማሬ አቅርበው በመ/ር ዳንኤል ሰይፈ ሚካኤል በኢ/ኦ/ተ/ቤተ ክርስቲያን ጠቅላይ ቤተ ክህነት የሊቃውንት ጉባኤ ሰብሳቢ “ለራሳችሁ አይደላችሁም” ፩ኛቆሮ. ፮፥፲፱-፳) በሚል የወንጌል ቃል መነሻነት የዕለቱን የወንጌል ትምህርት በመስጠት ቀጥሏል፡፡
የማኅበረ ቅዱሳን ሰብሳቢ የሆኑት አቶ ካሳሁን ኃይለ ማርያም በሴሚናሩ ላይ ተገኝተው ባስተላለፉት መልእክት “በኃላፊነት የምንማረው መንፈሳዊ ሕይወታችንን በእግዚአብሔር ቃል አንጸን እንድንኖር ነው፡፡ በመንፈሳዊም በሥጋዊም ሕይወታችሁ ይህንን ዓለም በማሸነፍ ለእናንተ ብቻ ሳይሆን ወንድሞቻችሁና እኅቶቻችሁም በትምህርታቸው በርትተው ለሀገርም ለቤተ ክርስቲያንም የሚጠቅሙ ሆነው እንዲወጡና ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ማገዝ ይጠበቅባችኋል፡፡ ይህንን መሰባበሰብና አንድነት የሰጠን እግዚአብሔር ነውና በጥንቃቄ ተምራችሁ ሕይወታችሁን እንድትመሩ፣ ከራሳችሁ አልፋችሁ ቤተ ክርስቲያንን እንድታገለግሉ ይገባል፡፡ ችግር ፈቺም ሆናችሁ የበኩላችሁን ኃላፊነት እንድትወጡና እንድታግዙ አደራ ማለት እፈልጋለሁ” ብለዋል፡፡
በተያዘው መርሐ ግብር መሠረት ቀጥሎ የቀረበው የግቢ ጉባኤያት መምህራን ማፍሪያ ፕሮጀክት የተመለከተ ሲሆን በ፲፫ኛው ዓለም አቀፍ የግቢ ጉባኤ ሴሚናር አዘጋጅ ዐቢይ ኮሚቴ ሰብሳቢ በሆኑት በአቶ ዳንኤል ተስፋዬ እና በሓጋዚ አብርሃ በግቢ ጉባኤያት አገልግሎት ማስተባበሪያ የአቅም ማጎልበቻ ዋና ክፍል ም/ኃላፊ ቀርቧል፡፡ በቀረበውም ጥናት በርካታ ጉዳዮች የተነሡ ሲሆን፡- የፕሮጀክቱ ዓላማ፣ የፕሮጀክቱ አስፈላጊነት፣ የፕሮጀክቱ ወሰን፣ የፕሮጀክቱ ማስፈጸሚያ ስልት፣ የፕሮጀክቱ ማስፈጸሚያ በጀት፣ የበጀቱ ምንጭ፣ የፕሮጀክቱ ትግበራ እና የፕሮጀክቱ ክትትልና ግምገማ ያካተተ ጥናት ቀርቧል፡፡ በቀረበው ጥናት መሠረትም ከተሳታፊዎች አስተያት እና ጥያቄዎች ቀርበው ማብራሪያ ተሰጥቶባቸው ጸድቋል፡፡
የቤተ ክርስቲያን ፈተናዎችና የግቢ ጉባኤያት አገልግሎት የተሰኘው ጥናት በሴሚናሩ ላይ ከቀረቡ መርሐ ግብሮች አንዱ ነበር፡፡ ጥናቱን ያቀረቡት አቶ አማረ በፍቃዱ የማኅበረ ቅዱሳን ሥራ አመራር አባል ሲሆኑ በጥናታቸውም ዘመናዊነት፣ የሉላዊነት መስፋፈት፣ በሃይማኖትና ሃይማኖተኝነት እያሳደረ ያለው ተጽእኖ፣ ዓለም ለሃይማኖት የሚሰጠው ዋጋ ዝቅ እያለ መሄዱ፣ የአስተሳሳብ ዘይቤ እየተዛባ መምጣቱ፣ በቅድስት ቤተ ክርስቲያን ህልውና ላይ እያሳደረ ያለው ተጽእኖ፣ በፖለቲካ፣ በብሔር፣ … በመከፋፈል የትርክት ሰለባ ማድረግ፣ ኢ-ኦርዶክሳዊነትን ከፍ ማድረግ፣ … የመሳሰሉትን በማንሣት ሰፊ ጥናት አቅርበዋል፡፡ ባቀረቡት ጥናት ላይ በመመርኮዝም ከተሳታፊዎች አስተያየት እንዲሁም ጥያቄዎች ተነሥተው ማብራሪያ ተሰጥቶባቸዋል፡፡
የቀኑ መርሐ ግብር ከመጠናቀቁ በፊት ዶ/ር ወርቁ ደጀኔ፣ ወ/ሮ የሱነሽ ተሾመ እና ዶ/ር ዲ/ን መገርሣ ዓለሙ የሕይወት ተሞክሯቸውን አካፍለው የሴሚናሩ ተሳታፊዎች የማኅበረ ቅዱሳን ብሮድካስት ተቋምንና የልማት ተቋማትን ኅትመት ክፍል ጎኝተዋል፡፡ በመጨረሻም ማምሻውን ለተሳታፊዎች ዘጋቢ ፊልም (ዶክመንተሪ) ቀርቦ በመ/ር ዋሲሁን በላይ በማኅበረ ቅዱሳን ዋና ሥራ አስፈጻሚ፣ በአቶ አበበ በዳዳ በማኅበረ ቅዱሳን የግቢ ጉባኤያት አገልግሎት ሥራ አስፈጻሚ እና በሴሚናሩ አዘጋጅ ዐቢይ ኮሚቴ ሰብሳቢ በአቶ ዳንኤል ተስፋዬ መልእክት የሴሚናሩ ፍጻሜ ሆኗል፡፡
Leave a Reply
Want to join the discussion?Feel free to contribute!