“የግቢ ጉባኤያት ተመራቂዎች ዲጂታል የምረቃ መጽሔት ዘመኑን ለዋጀ አገልግሎት አንዱ ማሳያ ነው”
በማኅበረ ቅዱሳን የግቢ ጉባኤያት አገልግሎት ማስተባበሪያ የተዘጋጀው የግቢ ጉባኤያት ተመራቂዎች ዲጂታል የምረቃ መጽሔት ዘመኑን የዋጀ አገልግሎት ለመስጠት አንዱ ማሳያ መሆኑን የማኅበረ ቅዱሳን ዋና ጸሓፊ መ/ር ዋሲሁን በላይ ገለጹ፡፡
ማኅበረ ቅዱሳን ከዐሥር ወራት በላይ መረጃ በማሰባብ የዲጂታል መጽሔቱን ለማዘጋጀት ጊዜ እንደወሰደበትና በጥሩ አፈጻጸም መጠናቀቁን ሐምሌ ፲፪ ቀን ፳፻፲፭ ዓ.ም በነበረው የመጽሔት ምረቃ መርሐ ግብር ላይ ገልጸዋል፡፡ የዲጂታል የምረቃ መጽሔት ማዘጋጀት የተጀመረው ከ፳፻፲፩/፲፪ ዓ.ም ጀምሮ ሲሆን ለዐራተኛ ጊዜ መዘጋጀቱንና ወደፊትም እንደሚቀጥል ጠቁመዋል፡፡
የግቢ ጉባኤያት አገልግሎት ማስተባበሪያ ኀላፊ አቶ አበበ በዳዳ በበኩላቸው ይህን የዲጂታል መጽሔት ማዘጋጀት ያስፈለገበት ዋና ዋና ምክንያቶችን ሲያብራሩም “በወረቀት መጽሔት ታትሞ ለተመራቂዎች ለማድረስ ከፍተኛ የሰው ኀይልና የገንዘብ ወጪ መጠየቁ፣ የግቢ ጉባኤያት ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣትና የወረቀት ዋጋ መናር፣ ወደ ማእከላትና ግቢ ጉባኤያት ለማዳረስ ከፍተኛ ወጪ መጠየቁ፣ …” ወደ ዲጂታል መጽሔት ዝግጅት ለመሸጋገር በምክንያትነት ካነሧቸው ምክንያቶች ውስጥ ይጠቀሳሉ፡፡
የዲጂታል መጽሔቱን ለማዘጋጀት ሲጀመር በተማሪዎች ዘንድ በርካታ ተግዳሮቶች የነበሩ ቢሆንም ከጊዜ በኋላ ግን ተማሪዎች እየተረዱት በመምጣታቸው ቁጥራቸው ሊጨምር እንደቻለ አቶ አበበ ገልጸዋል፡፡ እንደ ችግር ካነሧቸው ውስጥም፡- ከሕገ ወጥ የኤጲስ ቆጶሳት ምርጫ ጋር ተያይዞ ያልተካተቱ ግቢ ጉባኤያት መኖራቸው፣ አስፈላጊ መረጃዎችን በተያዘለት ዕቅድ መሠረት ማእከላትና ግቢ ጉባኤያት አሰባስበው ያለመላካቸው፣ የጽሑፎች መዘግየት፣ በወረቀት እናሳትማለን እያሉ ተማሪዎቹን ልብ የሚከፍሉ አካላት መኖራቸው፣ ከቅባት አስተምህሮ ጋር ተያይዞ በተማሪዎች ላይ ይደርስ የነበረው ጫና፣ … የመሳሰሉት ጉዳዮች ይገኙባቸዋል፡፡
የዲጂታል መጽሔቱ ዝግጅት ጠንካራ ጎን በተመለከተም አቶ አበበ ሲገልጹ፡- “መጽሔቱ በየግቢ ጉባኤያቱ ተለይቶ መዘጋጀቱንና በወረቀትም ኮፒ ማድረግ እንደሚቻል፣ ሦስት ቋንቋዎችን ያካተተ መሆኑ (አማርኛ፣ አፋን ኦሮሞ እና እንግሊዝኛ)፣ የተመራቂ ተማሪዎች የምስጋና ቃል (Last words) መካተቱ፣ ክትትል ላይ ያሉ ግቢ ጉባኤያት መካተታቸው፣ በውጪ ሀገራት ያሉ ግቢ ጉባኤያት መካተት፣ ድጋፍ ሰጪዎች (Sponsers) አካላት ለመጀመሪያ ጊዜ መሳተፋቸውና ፕሮጀክቱን በታቀደለት ጊዜ ማጠናቀቅ መቻላችን ውጤታማ አድርጎናል” ብለዋል፡፡ የዲጂታል መጽሔቱን ለማዘጋጀት ሙሉ ሥራውን በኀላፊነት ወስዶ ውጤታማ አገልግሎት መፈጸም እንዲቻል የበኩሉን ድርሻ የተወጣውን የ“ተክሌ ኮንሰልቲንግ” ድርጅት ኀላፊን ኪዳኔ መብራቱንና በዚህ አገልግሎት ውስጥ የተሳተፉትን ሁሉ አመስግነዋል፡፡
የዲጂታል መጽሔቱ መታተም ከጀመረበት ጊዜ አንሥቶ አገልግሎቱን በመፈለግ የሚካተቱ ተመራቂ ተማሪዎች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ የጨመረ ሲሆን በ፳፻፲፩/፲፪ ዓ.ም አሥራ አንድ ሺህ ሁለት መቶ ሠለሳ፤ በ፳፻፲፫ ዓ.ም አምስት ሺህ ስምንት መቶ ሃምሳ አንድ፤ በ፳፻፲፬ ዓ.ም አሥር ሺህ ሃያ ስድስት፤ በ፳፻፲፭ ዓ.ም አሥራ ሁለት ሺህ አራት መቶ ሃምሳ አምስት ተመራቂዎች ተካ’ተዋል፡፡ የእያንዳንዱ ዓመት ተመራቂዎች ዳታም እንደ ተካተትና አንድ ተመራቂ ተማሪ አገልግሎቱን በስድሣ ብር ማግኘት እንደቻለ በምረቃው ሥነ ሥርዓቱ ላይ ተገልጿል፡፡
Leave a Reply
Want to join the discussion?Feel free to contribute!