የደወሉ ምሥጢር

 

መ/ር ለይኩን አዳሙ(ባሕር ዳር)

  ደወል ማለት ምን ማለት ነው ? ቢሉ ‹‹ጠቅዐ›› መታ፣ደወለ አቃ ጨለ፣አነቃቃ፣አነሳሳ፣ አሳሰበ ከሚለው የግእዝ ግስ የተወሰደ ሲኾን ትርጉሙም መጥቅዕ፣ መረዋ፣ቃጭል ማለት ነው፡(ኆኅተ ሰማይ በቀሲስ ያሬድ ገ/መድኀን)

ደወል ከብር፣ከነሐስ፣ከብረት እና ከመሳሰሉ ድምፅ ሰጪ ከኾኑ ነገሮች በመጠኑ አነስተኛ፣መካከለኛ፣በጣም ግዙፍ ኾኖ ይዘጋጅና ከፍ ካለ ቦታ ላይ ወይም ዛፍ ላይ ይንጠለጠልና ከውስጥ የምትገኘውን ምላስ የምትመስል ብረት በረጅም ገመድ በማሰር ከታች ገመዱን በማወዛወዝ ደወሉን በመምታት ድምጽ እንዲሰጥ ይደረጋል፡፡

ደወል በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ለመንፈሳዊ አገልግሎት ከሚውሉት ንዋያት ቅዱሳት አንዱ ሲኾን በቤተ ክርስቲያን  በተለያዩ ጊዜያት ይደወላል፡፡ ሲደወልም ራሱን የቻለ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ምሥጢርና ትርጉም አለው፡፡ይህንም በቅደም ተከተል የምናየው ይኾናል፡፡

ደወል መቼ ? እንዴት  ይደወላል?

  በኢትዮጵያ ኦርቶዶስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አምስት ጊዜ ደወል ይደወላል፡፡ እርሱ ራሱን የቻለ የረቀቀና የመጠቀ ትርጉም አለው፡፡ ቤተ ክርስቲያን የምትገለገልባቸው የከበሩ ንዋያት ምሳሌያዊና  ምሥጢራዊ ትርጉማቸውን ለመግለጽ ብቁ ናቸው፡፡

ኦርቶዶክሳውያን ሊቃውንት በትርጓሜ ወፍጮ ፈጭተው በምሥጢር መዶሻ ሰልቀውና  አለስልሰው ምሥጢረ ደወልን ሲያመሠጥሩትና ለምእመናን ዘወትር ሲመግቡት ኑረዋል ወደፊትም ይኖራሉ፡፡ ለመኾኑ ደወል መቼና እንዴት ይደወላል? ብሎ የሚጠይቀን ቢኖር መልሳችን  እንደሚከተለው ነው፡፡

                       ፩ የተጋብኦ ደወል

ይህ የተጋብኦ ደወል ለአገልግሎት የተመደቡ ካህናት ወደ ቤተክርስቲያን እንዲሰበሰቡ በዋይዜማ፣ በመንፈቀ ሌሊት፣ ለሰዓታት፣ ለማሕሌት፣ ለኪዳን፣ ለቅዳሴ የቤተ ክርስቲያን በር ከመከፈቱ በፊት ይደወላል፡፡ የተጋብኦ ደወል ዓላማው የራቁትን ማቅረብ የተበተኑትን  መሰብሰብ  የተኙትን ከእንቅልፍ መቀስቀስ፣ ማንቃት ነው፡፡

የተጋብኦ ደወል የሚደወለው የዋይዜማ ሲኾን ዐሥራ አምስት ጊዜ፣ለማሕሌትና ለሰዓታት ሲሆን  ዐሥራ ሁለት ጊዜ ይደወላል፡፡ ይኽ ሁሉ ምሳሌ ነው፡፡

ዋይዜማ የኦሪት ምሳሌ ሲኾን፣ዐሥራ አምስት ጊዜ መደወሉ የዐሥራ አምስቱ ነቢያት ምሳሌ፣ድምጹ የድምፀ ነቢያት ምሳሌ ነው፡፡ የደወሉ ድምጽ ከሩቅ እንደሚሰማ ሁሉ የነቢያትም ትምህርታቸው በአራቱ ማዕዝናተ ዓለም ተሰምቷል፡፡

የነቢያትን ትምህርት ሰምተው እስራኤል ዘሥጋ ከአምልኮተ ጣኦት ወደ አምልኮተ እግዚአብሔር ከገቢረ ኃጢአት ወደ ገቢረ ጽድቅ ተመልሰው ለጌታችን ልደት ለሐዲስ ኪዳን  እንደ ተዘጋጁ ሁሉ ዛሬም እስራኤል ዘነፍስ የደወሉን ድምፅ ሰምተው ለሰዓታት፣ለማኅሌት ፣ለጸሎት፣ለንስሓ ፣ለቊርባን ለጾም ለጸሎት ይዘጋጃሉ፡፡

መንፈቀ ሌሊት የዕለተ ምጽአት፤ እንቅልፍ የሞት ምሳሌ፤ ሊቀ ዲያቆኑ የሊቀ መላእክት ቅዱስ ሚካኤል ምሳሌ፤ ሊቀ ዲያቆኑ ደወሉን ደውሎ ካህናትን ከእንቅፍ ማስነሣቱ የመላእክት አለቃ ቅዱስ ሚካኤል ንፍሐተ ቀርን መትቶ ሙታንን የማንቃቱ ምሳሌ ነው (፩ኛተሰ.፬፥፲፭ ፩ኛ ቆሮ. ፲፭፥፶፪)

ካህናት ምእመናን የሙታን፣ ሙታን በንፍሐተ ቀርን ተነሥተው ጻድቃን በቀኝ ኃጥአን በግራ ቁመው ፍርድ እንዲቀበሉ ካህናትና ምእመናንም በደወሉ ከእንቅልፋቸው ነቅተው በግራ በቀኝ ቁመው እግዚአብሔርን የማመስገናቸው ምሳሌ፡፡

ዛሬ የደወሉን ድምጽ ሰምቶ ከኃጢአት ከእንቅልፍ ነቅቶ ቤተ ክርስቲያን ገብቶ ያላመሰገነ በኋለኛው ዘመንም ገነት መንግሥተ ሰማያት አይገባም፡፡ዛሬ ቤተክርስቲያን መግባታችን ነገ ገነት መንግሥተ ሰማያት ለመግባታችን ዋስትና ነው፡፡

የተጋብኦ ደወል መቼ ተጀመረ ? ማን ጀመረው? ብሎ ለሚጠይቀን  ሰው መልሳችን ጻድቅና ትሑት የሆነው አባታችን ኖኅ ነው፡፡ (ዘፍ ፮ ) ኖኅ የደወለውን የደወል ድምጽ ሰምተው ነፍሳት ወደ መርከቡ ገብተው ከሰማይ ከሚወርደው ዶፍ  እንደተረፉ ሁሉ ዛሬም  በቤተ ክርስቲያን የሚደወለውን ድምጽ ሰምተው ከኃጢአት፣ ወደ ጽድቅ፣ ከጨለማ ፣ወደ ብርሃን፣ ከሥጋዊ ሐሳብ ወደ መንፈሳዊ ሐሳብ ተመልሰው አማናዊቷን መርከብ ጥግ አድርገው እግዚአብሔርን ተስፋ አድርገው በረከተ ሥጋ በረከተ ነፍስን አግኝተው ያሉ የተዋሕዶ ልጆች እጅግ ብዙ ናቸው፡፡

በኖኀ ዘመን ግእዛን የሌላቸው የማይጠየቁ እንስሳት የደወሉን ድምጽ ሰምተው ወደ መርከቡ ገብተው ሥጋን አፍርሶ አጥንትን ከስክሶ ከሚጥል ከሰማይ ከሚወርድ ዶፍ ከሞት ሲተርፉ አእምሮ  ያላቸው የሰው ልጆች ግን የደወሉን ድምጽ ሰምተው ችላ በማለታቸው በነፍስ በሥጋ የዘለዓለም ሞት እንደገጠማቸው ቅዱስ መጽሐፍ ይነግረናል፡፡

ዛሬም ቢሆን የተፈጠሩለትን ዓላማ ረስተው በዕለተ ዓርብ የተከፈለላቸውን ዋጋ ችላ ብለው ወደ አማናዊቷ መርከብ መምጣታቸውን ትተው ቀኝና ግራ የሚቀጥፉ እጅግ ብዙ ናቸው፡

ወዳጄ አንተስ ከወዴትኞቹ ነህ? ኪዳኑን፣ማሕሌቱን፣ቅዳሴውን ወንጌሉን ችላ ብለው ሥልጣኔ በሚመስል ኋላ ቀርነት ዕውቀት በሚመስል ድንቁርና ውስጥ ተጠልፈው በዳንኪራና በዝሙት በዘረኝነትና በስግብገብነት ከወደቁት ወገንነህ ወይስ የቤተ ክርስቲያንን ድምጽ ሰምተው በቤተ ክርስቲያን ጥላ ሥር ተጠልለው በሕጓና በሥርዓቷ ከሚመሩት ከወዴትኞቹ ነህ ወንድሜ ?

. ፪ የቅዳሴ መግቢያ ደውል

ይህ የቅዳሴ መግቢያ ደወል ካህናቱ መሥዋዕቱን አክብረው ከቤተልሔም ወደ ቤተ መቅደስ ሲገቡ የሚደወል ደወል ነው። ዲያቆኑ ወደ ቤተልሔም ሂዶ እጅ ነሥቶ ‹‹ተፈሥሒ ኦ ቤተ ልሔም ሀገሮሙ ለነቢያት እስመ በኀቤኪ ተወልደ ክርስቶስ ›› ብሎ ከጸለየ በኋላ ታጥቦ ንጹሕ ሆኖ ‹‹አፍኣዊ እድፌን በውኃ ታጥቤአለሁ ውሳጣዊ በደሌን ግን አንተ በቸርነትህ አንጻኝ›› ብሎ ተማጽኖ  ኅብስቱን በመሶበ ወርቅ ወይኑን በጽዋው አድርጎ ካጠናቀቀ በኋላ ካህኑ እንደ መጣ በመሶበ ወርቅ ያለውን ኅብስት ተሸክሞ ጽዋውን በእጁ ይዞ ካህኑን እየቀደመው ደወሉን ወይም ቃጭሉን እያቃጨለ ‹‹መስቀል አብርሃ፣ኵሉ ዘገብራ ለጽድቅ እና እምነበሐ›› የሚሉ ዜማዎችን እያዜመ ወደ ቤተ መቅደሱ ካህኑን እየቀደመው ይገሰግሳል፡፡ ይህ ሁሉ ምሳሌ ነው መሶብ የእመቤታችን ወርቅ የንጽሕናዋና የቅድስናዋ ምሳሌ ነው፡፡

ዲያቆኑ የመጥምቀ መለኮት የቅዱስ ዮሐንስ ምሳሌ ሲሆን ካህኑ ደግሞ የመድኃኔዓለም የኢየሱስ ክርስቶስ ምሳሌ ነው፡፡ ዲያቆኑ ከካህኑ እየቀደመ ፊት ፊት መሄዱ ዮሐንስ ከክርስቶስ መንፈቅ ቀድሞ ለመምጣቱ ምሳሌ ነው፡፡ በዚህን ጊዜ የሚደወለው የደወል ድምጽ ሁለት ምሥጢራውያን ትርጉሞች እንዳሉት መተርጉማን  ሊቃውንት ያትታሉ፡፡

አንደኛ የብሥራተ ገብርኤል ምሳሌ፣ መልአከ ብሥራት ቅዱስ ገብርኤል እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምን ምልእተ ጸጋ ምልእተ ክብር ሆይ ደስ ይበልሽ እግዚአብሔር ካንቺ ጋር ነውና እያለ የምሥራቹን ነግሯታልና የዚያ ምሳሌ እንደሆነ መተርጉማኑ ያስተምራሉ(ሉቃ ፩፥፳፮)

ኢትዮጵያዊው የነገረ መለኮት ሊቅ አባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫም መጽሐፈ ምሥጢር በተባለ መጽሐፉ ላይ እንዲህ በማለት የቅዱስ ገብርኤልን አብሣሪነት ይገልጣል፡፡‹‹ወአመ ትስብእተ መለኮቱ ለወልድ ይቤላ ቅዱስ ገብርኤል ለድንግል ማርያም በእንተ መንፈስ ቅዱስ መንፈስ ቅዱስ ይመጽእ ላዕሌኪ ወበእንተ አብኒ ይቤ ወኃይለ ልዑል ይጼልለኪ ወበእንተ ወልድኒ ይቤ ወዘኒ ይትወለድ እምኔኪ ቅዱስ ውእቱ ወይሰመይ ወልደ ልዑል፣ወልድ ሰው በኾነ ጊዜ ቅዱስ ገብርኤል ስለ መንፈስ ቅዱስ ድንግል ማርያምን መንፈስ ቅዱስ በአንቺ ላይ ይመጣል ብሎ ነግሯታል፡፡

ስለአብም የልዑል ኃይል ይጋርድ ሻል አላት፡፡ስለወልድም ከአንች የሚወለደው ቅዱስ ነው የልዑል ልጅም ይባላል..ብሎ ቅዱስ ገብርኤል እንዳበሠራት ይናገራል (መጽሐፈ ምሥጢር ገጽ ፻፴፩)

የብሕንሳው ሊቅ አባ ሕርያቆስም እመቤታችንን ባመሰገነበት በቅዳሴው ላይ የቅዱስ ገብርኤልን የምሥራች ነጋሪነት እንዲህ ሲል ይመሰክራል ‹‹ወሶበ ርእየ ንጽሕናኪ ለሊሁ እግዚአብሔር አብ ፈናወ ኀቤኪ መልአኮ ብርሃናዌ ዘስሙ ገብርኤል ወይቤለኪ መንፈስ ቅዱስ ይመጽእ ላዕሌኪ ወኃይለ ልዑል ይጼልለኪ መጽአ ኀቤኪ ቃል እንዘ ኢይትፈለጥ እምሕጽነ አቡሁ ፀነስኪዮ እንዘ ኢይትጋባእ ተዐቁረ ውስተ ከርሥኪ እንዘ ኢየሐጽጽ በላዕሉ ወኢይትዌሰክ በታሕቱ ኀደረ ውስተ ከርሥኪ እሳተ መለኮት ዘአልቦቱ ጥያቄ ወኢመጠን፣እርሱ ቅሉ እግዚአብሔር አብ ንጽሕናሽን ባየ ጊዜ ስሙ ገብርኤል የሚባል ብርሃናዊ መልአኩን ወደ አንቺ ላከ መንፈስ ቅዱስ በላይሽ ይመጣል የልዑል ኀይልም ይጋርድሻል አለሽ ከአባቱ አጠገብ ሳይለይ ቃል ወደ አንቺ መጣ ሳይወሰን ፀነስሽው በላይ ሳይጎድል በታችም ሳይጨምር በማሕፀንሽ ተወሰነ መጠንና መመርመር የሌለበት እሳተ መለኮት በማሕፀንሽ ዐደረ›› በማለት በአድናቆት ይገልጻል፡፡ (ቅዳሴ ማርያም ቁጥር ፵፭) ደወል ቅዳሴ መገባቱን መሥዋዕት የሚሠዋበት ጊዜ መሆኑን እንደሚገልጽ ሁሉ ቅዱስ ገብርኤልም የክርስቶስን መወለድ አብሥሯል፡፡ልደቱም በቤተልሔም ተፈጽሟል፡፡

ሁለተኛ የስብከተ ዮሐንስ ምሳሌ፤ ይህ ደወል መጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ “ተራራው ዝቅ ይበል ጎድጓዳው ይምላ የጌታን መንገድ አዘጋጁ ጥርጊያውን አስተካክሉ፣እንሆየዓለምን ኃጢአት የሚያስተሰርይ የእግዚአብሔር በግ›› (ማቴ ፫፣ዮሐ ፩፥፳፱) ብሎ የጮኸው ድምጽ ምሳሌ ነው። ይህንም ኢትዮጵያዊው ሊቅ ቅዱስ ያሬድ በድጓው እንዲህ ሲል ተርጉሞና አብራርቶ ይነግረናል፡

‹‹ኢሳይያስኒ ይቤ ናሁ እፌኑ መልአኪየ ኅቤከ ቅድመ ገጽከ ዘይጸይሕ ፍኖተከ ቃለ ዐዋዲ ዘይሰብክ ጥምቀተ ለንስሓ፣የንስሓን ጥምቀት የሚሰብክ በፊትህ መንገድን የሚጠርግ አዋጅ ጋሪ መልክተኛየን እልካለሁ ብሎ ኢሳይያስ እንደተናገረ››

‹‹ቃለ ዐዋዲ ዘይሰብክ ጥምቀተ ለንስሓ ከመ ይእመኑ ሕዝብ በብርሃኑ ዮሐንስ ክቡር ሰባኬ ቃለ ወንጌል ተፈኖኩ ቅድሜሁ ዐርኩ ለመርዓዊ ሰማያዊ፣ሕዝቡ በብርሃኑ ያምኑ ዘንድ የንስሓ ጥምቀትን የሚሰብክ ዐዋጅ ነጋሪ የተከበረ የወንጌል ሰባኪ የሰማያዊ ሙሽራ ወዳጅ እኔ ዮሐንስ በፊቱ ተላክሁ››

‹‹ ዮሐንስ ካህን ወድንግል እንዘ ይሰብክ ቃለ ወንጌል ወይቤሎሙ ለሐራ ጺሑ ፍኖቶ ለልዑል፣ካህንና ድንግል የሆነ ዮሐንስ የወንጌልን ቃል እየሰበከ ለጭፍሮቹ ወይም ለወታደሮች ለታላቁ ንጉሥ መንገዱን ጥረጉለት ጥርጊያውንም አስተካክሉለት››ሰባኬ ወንጌል ዘጥዑም ልሳኑ ርስነ መለኮት ገሠሠት የማኑ፣ፀጒረ ገመል ተከድነ ዘባኑ ለዮሐንስ ኂሩቶ ንዜኑ፣አንደበቱ የጣፈጠ የወንጌል ሰባኪ ቀኝ እጁ የመለኮትን ግለት ዳሠሠች የዮሐንስ ጀርባ በግመል ፀጉር ተሸፈነ ይህን የዮሐንስን ቸርነት እንናገራለን ›› በማለት ቃለ ዐዋዲ የተባለ ዮሐንስ በስብከቱ የራቁትን እንዳቀረበ የተበተኑትን እንደሰበሰበ ሊቁ በድጓው ነግሮናል፡፡ የደወል ምሳሌም ይህ ነው፡፡

                 ፫ የወንጌል ደወል

  በቅዳሴ ሰዓት ወንጌል ከተነበበ በኋላ ዲያቆኑ “ፃኡ ንኡሰ ክርስቲያን”ብሎ ሲያውጅ የሚደወል ደወል ነው፡፡ ንኡሰ ክርስቲያን የሚባሉት ክፉውን ምግባር በጎ ምግባር፣ ክፉን ሃይማኖት በጎ ሃይማኖት መስሏቸው ይዘውት ሲኖሩ በኋላ ግን ቃለ መምህራንን ሰምተው ክፉውን ትተው ወደ በጎው ከተመለሱ በኋላ ነገረ ሃይማኖት እየተማሩ ወደቤተ ክርስቲያን እየሔዱ የትምህርትና የንባብ ክፍለ ጊዜውን ከተከታተሉ በኋላ ፍሬ ቅዳሴ ላይ ሲደረስ የክርስቲያን ታናናሾች ለዚህ ምሥጢር ያልበቃችሁ ውጡ ሲል ደወል ይደወላል እነርሱም እየወጡ ይሔዳሉ፡፡ ውጡ ሲል የወጡት የኃጥአን ከዚያው ቁመው የቀሩት የጻድቃን ምሳሌ ሲሆን የደወሉ ድምጽ ደግሞ የስብከተ ዮሐንስ፣ የሐዋርያት እና የሰብአ አርድእት ምሳሌ ነው፡፡ ጌታችን ሕገ ወንጌልን ከማስተማሩ በፊት የሰዎችን ልብ ለንስሓ ለማዘጋጅት መንገድ ጠራጊው አዋጅ ነጋሪው መጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ የንስሓ ትምህርት አስተምሯል (ሉቃ ፩፥፴፩)

ቅዱሳን ሐዋርያትም ከዓለም ለይቶ የጠራቸው ጌታችን ሲሰቀል አልቅሰዋል የወንጌል ደወል ከተደወለ በኋላ መሥዋዕት ይሠዋል ሥጋ ወደሙ ተፈትቶ ለሚቀበሉ ይቀርባል እንዲሁም ከመጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ የንስሓ ትምህርት በኋላ ጌታችን ሦስት ዓመት ከሦስት ወር ካስተማረ በኋላ በመስቀል ተሰቅሎ ለዓለሙ ድኅነት ራሱን አሳልፎ ሰጥቷል፡፡

                         ፬ የእግዚኦታ ደወል

 በፍሬ ቅዳሴ ላይ ገባሬ ሠናይ ሆኖ ቅዳሴ የገባው ካህንና ተጨማሪ ካህናት እና ምእመናን እየተቀባበሉ ፵፩ ጊዜ “እግዚኦ መሐረነ ክርስቶስ” ይባላል በዚህን ጊዜ የሚሰማው የደወል ድምፅ የእመቤታችን እና የወንጌላዊው ዮሐንስ የለቅሶ ድምፅ ምሳሌ ነው። እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምና ቅዱስ ዮሐንስ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዕለተ ዐርብ ሲሰቀል ባዩ ጊዜ  ከእግረ መስቀሉ ሥር ኾነው  አልቅሰዋል (ዮሐ ፲፱፥፳፭)

ዛሬም ምእመናን በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ኾነው ‹‹አቤቱ ማረን ይቅርም በለን›› እያሉ ዘወትር ሞተ ወልደ እግዚአብሔርን ግፍዐ ሰማዕታትን የራሳቸውን በደልና ኃጢአት እያሰቡ ዮሐንስን ምሳሌ አድርገው እንዲያዝኑ እንዲያለቅሱ ይህ የደውል ድምፅ በኢትዮጵያ በኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ዘወትር ይሰማል።

                      ፭ የድርገት ደወል

ድርገት ማለት አንድነት ኅብረት ማለት ሲሆን ይኸውም ሀብተ ወልድና ስመ ክርስትናን የታደሉ ምእመናን አንድ ሆነው በአንዲት ቤተ ክርስቲያን የአንዱን የክርስቶስን ቅዱስ ሥጋውንና ክቡር ደሙን የሚቀበሉበት እና  ካህናቱም ሥጋ መለኮትንና ደመ መለኮትን ለማቀበል አንድ ኾነው ‹‹ቅዱስ ቅዱስ ቅዱስ ››እያሉ ከመቅደስ ወደ ቅድስት የሚወጡበት ነውና  ድርገት ተባለ ሲወጡም ደወል ይደወላል፡፡

በዚህን ሰዓት የሚደወለው የደወል ድምጽ የቅዱስ ዮሴፍ እና የቅዱስ ኒቆዲሞስ ለቅሶ ምሳሌ ነው፡፡ እንዲሁም የቅዱሳን ሐዋርያት እና የሰብአ አርድእት ትምህርት ምሳሌ ነው( ሉቃ ፳፫፥፶)

ዮሴፍና ኒቆዲሞስ ጌታን ከቅዱስ መስቀሉ አውርደው እያለቀሱ ‹‹ቅዱስ እግዚአብሔር ቅዱስ ኃያል ቅዱስ ሕያው ዘኢይመውት ዘተወልደ እማርያም እምቅድስት ድንግል ተሣሃለነ እግዚኦ ቅዱስ እግዚአብሔር ቅዱስ ኃያል ቅዱስ ሕያው ዘኢይመውት ዘተጠምቀ በዮርዳኖስ ወተሰቅለ ዲበ ዕፀ መስቀል ተሣሃለነ እግዚኦ ቅዱስ እግዚአብሔር ቅዱስ ኃያል ቅዱስ ሕያው ዘኢይመውት ዘተንሥአ እሙታን አመ ሣልስት  ዕለት ዐርገ በስብሐት ውስተ ሰማያት ወነበረ በየማነ አቡሁ ዳግመ ይመጽእ  በስብሐት ይኰንን ሕያዋነ ወሙታነ ተሣሃለነ እግዚኦቅዱስ እግዚአብሔር ፡ቅዱስ ኃያል ፡ቅዱስ ሕያው የማይሞት የማይለወጥ  ከቅድስት ድንግል ማርያም የተወለደ  አቤቱ ይቅር በለን፣፣ቅዱስ እግዚአብሔር ፡ቅዱስ ኃያል ፡ቅዱስ ሕያው የማይሞት የማይለወጥ በዮርዳኖስ የተጠመቀ  በመስቀል የተሰቀለ አቤቱ ይቅር  በለን፣፣ቅዱስ እግዚአብሔር ፡ቅዱስ ኃያል ፡ቅዱስ ሕያው የማይሞት የማይለወጥ በሦስተኛው ቀን ከሙታን ተለይቶ የተነሣ  በክብር፡ በምስጋና ወደ ሰማይ  ወጣ በአባቱም ቀኝ ተቀመጠ  ዳገመኛም በሕያዋንና በሙታን ለመፍረድ  በጌትነት ይመጣል አቤቱ ይቅር በለን ›› እያሉ በአዲስ መቃብር አኑረውታል፡ (የኪዳን ጸሎት )

ዛሬም የዮሴፍና የኒቆዲሞስ ምሳሌ የሆኑ ካህናት የቀራንዮ ምሳሌ ከሆነው ከመንበሩ አውርደው አፍዓዊ እድፋቸውን በሳሙና ውሳጣዊ በደላቸውን በንስሓ ወልውለው ራሳቸውን አዲስ ባደረጉ በምእመናን ልቡና ውስጥ ይቀብሩታል፡፡ የምእመናን ልቡናም ያንጊዜ መቃብረ ክርስቶስ ይሆናል፡፡ ለዚህ ነው ኦርቶዶክሳውያን ሥጋውን እንደበሉና ደሙን እንደጠጡ አፋቸውን የሚሸፍኑት ፡፡

የመሸፈናቸው ምሥጢርም አንደኛ ዮሴፍና ኒቆዲሞስ ጌታን በአዲስ መቃብር ከቀበሩት በኋላ መቃብሩን በድንጋይ የመግጠማቸው ምሳሌ ሁለተኛ ለእኛ ስትል የተቀበልኸው መከራ ከመናገር በላይ ነው ሲሉ፤ ሦስተኛ ክርስቶስ በውስጤ አለ ሲሉ፣ አራተኛ ከአሁን በኋላ ለኃጢአት የተዘጋው በር ነኝ ሲሉ! ስለሆነም ምእመናን የጌታን መከራውን ሥቃዩን ግርፋቱን ሞቱን ትንሣኤውን እያሰቡ በፍርሃት እና በመንቀጥቀጥ ወደ ቅዱስ ሥጋውና ክቡር ደሙ ይቀርቡ ዘንድ ድርገት ሲወርድ ሁል ጊዜ ደወል ይደወላል፡፡

በመሆኑም በደወሉ ድምጽ የተኛን ተቀስቅሰን የዛልን በርትተን የተለያየን በዓላማ አንድ ሆነን የመንግሥቱ ወራሾች እንሆን ዘንድ አምላከ ቅዱሳን ይርዳን !

 

 

0 replies

Leave a Reply

Want to join the discussion?
Feel free to contribute!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *