የክርስቶስ ትንሣኤ በሊቃውንት

የጌታችን መድኀኒታችን ኤሱስ ክርስቶስን ትንሣኤ በተመለከተ በተለያዩ ዘመናት የተነሡ አባቶቻችን ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ብዙ አስተምረዋል፣ ጽፈዋል፡፡ ለዛሬ ከቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን መጻሕፍት መካከል በሃይማኖተ አበው ያገኘውን በጥቂቱ እናቀርባለን፡፡

“ጌታ ለደቀ መዛሙርቱ ‘በትንሣኤ ከእናንተ ጋር እስከምመጣበት ቀን ድረስ ከዚያ ወይን ጭማቂ አልጠጣም፤ በሐዲስ ግብር በምነሣበት ጊዜ የምታዩኝ እናንት ምስክሮቼ ናችሁ’ ያለውን የማቴዎስን ወንጌል በተረጐመበት አንቀጽ እንዲህ አለ፤ ሐዲስ ያለው ይህ ነገር ምንድን ነው? ይህ ነገር ድንቅ ነው! መዋቲ ሥጋ እንዳለኝ ታያላችሁ፤ ነገር ግን ከትንሣኤ በኋላ የማይሞት ነው፤ አይለወጥም፤ ሥጋዊ መብልንም መሻት የለበትም፤ ከትንሣኤ በኋላ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ቢበላም ቢጠጣም መብልን ሽቶ አይደለም፤ እርሱ ከሙታን ተለይቶ እንደ ተነሣ ያምኑ ዘንድ በላ ጠጣ እንጂ፡፡ ይህ ድንቅ ሥራ ነው! ያለ መለወጥ ሰው የኾነ ቃል የተቸነከረበትን ምልክት (እትራት) አላጠፋምና፡፡ በሚሞቱ ሰዎች እጅ እንዲዳሠሥ አድርጎታልና፡፡ አምላክ የኾነ ሥጋ የሚታይበት ጊዜ ነውና አላስፈራም፡፡ እርሱ በዝግ ደጅ ገባ፤ ግዙፉ ረቂቅ እንደ ኾነ ሥራውን አስረዳ፡፡ ነገር ግን በትንሣኤው ያምኑ ዘንድ የተሰቀለው እርሱ እንደሆነ የተነሣውም ሌላ እንዳይደለ ያውቁ ዘንድ ይህን ሠራ፡፡ ስለዚህም ተነሣ፤ በሥጋውም የችንካሩን ምልክት (እትራት) አላጠፋም፤ ዳግመኛም ከትንሣኤው አስቀድሞ ደቀ መዛሙርቱ ጧት ማታ ከእርሱ ጋር ይበሉ እንደ ነበረ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር በላ፤ ስለዚህም በአራቱ መዓዝነ ዓለም ትንሣኤውን አስረዱ፡፡ ከትንሣኤውም በኋላ ‘ያየነው ከእርሱም ጋር የበላን የጠጣንም እርሱ ነው’ ብለው አስረዱ” (ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ሃይ. አበ. ፷፮፥፯-፲፪)፡፡

“ክርስቶስ የሙታን በኵር እንደምን ተባለ? እነሆ በናይን ያለች የድሀይቱን ልጅ አስቀድሞ አስነሣው፤ ዳግመኛም አልዓዛርን በሞተ በአራተኛው ቀን አስነሣው፡፡ ኤልያስም አንድ ምውት አስነሣ፡፡ ደቀ መዝሙሩ ኤልሣዕም ሁለት ሙታንን አስነሣ፤ አንዱን ሳይቀበር፣ ሁለተኛውን ከተቀበረ በኋላ ሥጋውን አስነሣ፡፡ እነዚያ ሙታን ቢነሡ ኋላ እንደ ሞቱ፤ እነርሱ ኋላ አንድ ኾነው የሚነሡበትን ትንሣኤ ዛሬ ተስፋ ያደርጋሉ፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ግን የሙታን ትንሣኤያቸው በኵር ነው፡፡ ‘እንግዲህ ወዲህም ሞት የሌለበትን ትንሣኤ አስቀድሞ የተነሣ እርሱ ነው፤ ዳግመኛም ሞት አያገኘውም’ ተብሎ እንደ ተጻፈ” (ቅዱስ ኤጲፋንዮስ፣ ሃይ. አበ. ፶፯፥፫-፮)፡፡

“ከሙታን ተለይቶ ተነሥቶ ሲኦልን ረግጦ፣ በሞቱ ሞትን አጠፋው፤ በሦስተኛው ቀንም ከሙታን ተለይቶ ከተነሣ በኋላ ‘አባት ሆይ፤ አመሰግንሃለሁ’ ብሎ ሥግው ቃል አመሰገነ” (እልመስጦአግያ ዘሐዋርያት ፭፥፩)፡፡

“የሥጋን ሕማም ለመለኮት ገንዘብ በአደረገ ጊዜ የእግዚአብሔር አካል በባሕርዩ በግድ ሕማምን አልተቀበለም፤ ሕማም በሚስማማው ባሕርዩ ኃይልን እንጂ፡፡ ሞትም በሥጋ ለእግዚአብሔር ቃል ገንዘብ በኾነ ጊዜ ሞትን አጠፋ፡፡ ከሞትም በኋላ ፈርሶ፣ በስብሶ መቅረትን አጠፋ” (ቅዱስ ቴዎዶጦስ ሃይ. አበ. ፶፫፥፳፯)፡፡

“እንደ ሞተ እንዲሁ ተነሣ፤ ሙታንንም አስነሣ፡፡ እንደ ተነሣም እንዲሁ ሕያው ነው፤ አዳኝ ነው፡፡ በዚህ ዓለም እንደ ዘበቱበት፣ እንደ ሰደቡት፣ እንዲሁ በሰማይ ያሉ ዅሉ ያከብሩታል፤ ያመሰግኑታል፡፡ ለሥጋ በሚስማማ ሕማም ተሰቀለ፤ በእግዚአብሔርነቱ ኃይል ተነሣ፤ ይኸውም መለኮቱ ነው፡፡ ወደ ሲኦል ወርዶ ነፍሳትን ማረከ” (ቅዱስ ሄሬኔዎስ፣ ሃይ. አበ. ፯፥፳፰-፴፩)፡፡

“እንዲህ ሰው ኾኖም ሰውን ፈጽሞ ያድን ዘንድ ታመመ፤ ሞተ፤ ተቀበረ፡፡ በሦስተኛውም ቀን ከሙታን ተለይቶ ተነሣ” (ሠለስቱ ምዕት፣ ሃይ. አበ. ፲፱፥፳፬)፡፡

“ሞትን ያጠፋው፣ ከሙታን ተለይቶ በመነሣቱ የሞት ሥልጣን የነበረው ዲያብሎስን የሻረው እርሱ ነው፡፡ ሰው የኾነ፣ በሰው ባሕርይ የተገለጠ አምላክ ነው፡፡ እግዚአብሔር ያደረበት ዕሩቅ ብእሲ አይደለም፤ ሰው የኾነ አምላክ ነው እንጂ፡፡ ፈጽሞ ለዘለዓለሙ በእውነት ምስጋና ይገባዋል” (ቅዱስ አትናቴዎስ፣ ሃይ. አበ. ፳፭፥፵)፡፡

ይቆየን፡፡

0 replies

Leave a Reply

Want to join the discussion?
Feel free to contribute!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *