የእግዚአብሔር ፈቃድ
ክፍል ሁለት
በመ/ር ተርቢኖስ ቶሎሳ
ሰው ወደ ክርስትናው ዓለም ሲገባ የራሱን ፈቃድ ያወርድና የጌታውን ፈቃድ ተሸክሞ ወደ ቀራንዮ ሲጓዝ ይኖራል። እንደ ሰውኛ የግል ስሜትና የግል ፈቃድ ቀራንዮ አያደርስም። መድኅነ ዓለም ክርስቶስ ያን ወጣት “ወደ ሕይወት መግባት ብትወድ ትእዛዛትን ጠብቅ … ያለህን ሸጠህ ለድሆች ስጥ” ማለቱ ለምን ይመስላችኋል? ሰው በእግዚአብሔር ፈቃድ እንጂ በሰውነቱ ፈቃድ መንግሥቱን እንደማይወርስ ለማጠየቅ ነው።
ቀሬናዊው ስምዖን የጌታውን መስቀል ተሸክሞ ያንን አስቸጋሪ ጎዳና የተጓዘው ቤተ ክርስቲያኒቱ በጌታዋ ፈቃድ ትኖር ዘንድ እንዳላት ለማሳየት እንጂ ጌታውን ደክሞት ሊያሳርፍ አልነበረም። ስለዚህ የክርስትና ጉዟችን እንደ ሰው ፈቃድ ሰውን እናስደስት ዘንድ ሳይሆን እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ መንግሥቱን እንወረስ ዘንድ ነው። ለዚህም ነው ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ እንዲህ ብሎ የሚመክረን፦ “የእግዚአብሔርን ፈቃድ እንደሚያደርጉ እንደ ክርስቶስ ባሪያዎች እንጂ ለሰው ደስ እንደምታሰኙ ለታይታ የምትገዙ አትሁኑ!” በማለት። (ኤፌ. ፮፥፮)
ባሪያ ለራሱ ፈቃድ የለውም፤ ፈቃዱ ሁሉ ለጌታው ነው። የቆመን ቁረጥ፣ የወደቀን ፍለጥ ቢል ለጌታ ይገባዋል፤ ባሪያ በጌታው ሥር ይኖራልና። ሐዋርያውም “እንደ ክርስቶስ ባሪያዎች” ማለቱ በፈቃዱ ጥላ ሥር የሚኖሩትን ለመጠቆም ነበር። ስለዚህ በበጎ ፈቃዱ ውስጥ የሰው ልጅ ታላቅ ድርሻ አለው። ድርሻውም የጌታውን ፈቃድ በጸሎት መጠየቅ ነው። በክርስትና አስተምህሮ ፈቃደ እግዚአብሔርን ጸሎት አብዝቶ ይገልጠዋል። “ለምኑ ይሰጣችኋል” እንደተባለ። ስለዚህ ጸሎት የፈቃዱ መገለጫ እንደሆነ በዚህ እናውቃለን።
የሰውን ጉድለትና ምልዓት ይነግሩት ዘንድ የማይሻ ጌታ ሆኖ ሳለ ነገር ግን በጸሎት እንጠይቀው ዘንድ ይወዳል። ምክንያቱ ደግሞ ጸሎት የፈቃዱ መገለጫ ስለሆነ ነው። ለመከሩ ሠራተኛ እንደሚያስፈልገው ያወቀው ፍጥረት አመልክቶት አይደለም። በባሕርይው ዕውቀት እንጂ። “እንግዲህ የመከሩን ጌታ ወደ መከሩ ሠራተኞችን እንዲልክ ለምኑት” ብሎ የሚናገር ራሱ የመከሩ ጌታ ነው። (ዮሐ. ፪፥፳፭) ለገዛ መከሩ ግን በጸሎት እንዲጠየቅ ሐዋርያትን ያነሣሣል። ይህም የሆነው በፈቃዱ ውስጥ የሰው ልጅ ድርሻ እንዳለው ለማስረዳት ነው።
ስለ ደቀ መዝሙሩ ኤጳፍራ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ በተናገረበት ክፍል “በእግዚአብሔር ፈቃድ ሁሉ ተረድታችሁና ፍጹማን ሆናችሁ እንድትቆሙ ስለ እናንተ በጸሎቱ ይጋደላል።” ይላል። (ቆላ. ፬፥፳፪) የእግዚአብሔር ፈቃድ በረድኤትነት የሚገለጠው ኤጳፍራ በጸሎት ሲጋደል እንደሆነ መመዝገቡ በፈቃደ እግዚአብሔር ዘንድ ያለውን የሰውን ልጅ ድርሻ ጠንቅቆ የሚያስረዳ ዐውድ ነው። ድርሻ አለው ማለት ግን ፈቃድን ይወስናል፣ ፈቃድን ይሰጣል፣ ያስረዝማል፣ ያሳጥራል ማለት ሳይሆን ይህ ፈቃዱ እንዲሰጠው በጸሎት ለእግዚአብሔር ምሕረት ምክንያት ይሆናል ማለት ነው። “ስለዚህ እኛ ደግሞ ይህን ከሰማንበት ቀን ጀምረን የፈቃዱ ዕውቀት መንፈሳዊ ጥበብንና አእምሮን ሁሉ እንዲሞላባችሁ እየለመንን ስለ እናንተ ጸሎትን አልተውንም።” እንዲል (ቆላ. ፩፥፱) ፈቃዱ የነገሮች ሁሉ በር ነውና ለዚህ ነው ጸሎት ያስፈለገው።
በክርስትና ሕይወት መኖር ማለት እንደ ፈቃዱ እንኖር ዘንድ ተጠርተናልና በተፈጸመው ፈቃድ እርሱን እያመሰገንን ባልተፈጸመው ፈቃድ የቀረንን እየጠየቅን መኖር ማለት ነው። ይህ ሲሆን የእግዚአብሔርን ፈቃድ እንዴት እናውቃለን? ቢሉ እግዚአብሔር የቀደመ ፈቃዱን በነቢያት፣ በካህናት፣ በራእይ፣ በትንቢት፣ በምሳሌ፣ በሱባኤ ገልጧል።
በአዲስ ኪዳን ደግሞ የማይፈጸም ፈቃዱን በአንድ ልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ገልጦልናል። እርሱም እንዲህ ብሎ ነገረን። “ዓለምን ላድን እንጂ በዓለም ልፈርድ አልመጣሁም…” ። (ዮሐ. ፲፪፥፵፯) ክርስቶስ አስቀድሞ መጾሙ መጾማችን ፈቃዱ እንደሆነ ሊያስረዳን ነበር። ወደ ገዳም መግባቱም ገዳማውያኑ በግብር ይመስሉት ዘንድ ፈቃዱን እየሰጣቸው ነበር። ወደ ዶኪማስ ቤት መሄዱም በትዳር ተወስነው፣ ልጅ ወልደው፣ ጎጆ ቀልሰው ለሚኖሩ ሰዎች ኑሯቸውን ባርኮ ለመስጠት ነበር። ሥጋውና ደሙ፣ እናቱና መስቀሉ ፈቃዱን ያወቅንባቸው መገለጫዎቹ ናቸው። ይበልጥ ደግሞ ፈቃዱን ለማወቅም ሆነ ለመጠየቅ እግዚአብሔርን በጾምና በጸሎት አብዝቶ መቅረብ፣ በበጎ ምግባር መጽናት፣ ሰውነትን ከኃጢአት አንጽቶ በፊቱ ለምሕረት መቆም፣ ወደ ቤተ ክርስቲያን በተሰበረ ልቡና፣ በቀና ሕሊና መመላለስ ፈቃዱን የምናውቅባቸውና ፈቃዱን የምንፈጽምባቸው መንገዶች ናቸው፡፡
ስለ ፈቃደ እግዚአብሔር ስናጠና ልናድርጋቸው የሚገቡን ጥንቃቄዎች
ፈቃደ እግዚአብሔርን ስንጠይቅ ኃጢአታችንን ተናዝዘን ከኃጢአት ነጻ ልንሆን ይገባል። ከዚያም ቀጥሎ ስሜቶቻችን ሁሉ ሊያሳስቱን ስለሚችሉ ጥንቃቄ ልናድርግ ይገባል። የምንፈጽመው ድርጊት ሁሉ “እግዚአብሔርን ያስደስተዋልን?” ብለን ልንጠይቅ ይገባል። መልካምና ክፉ ነገሮችም ወደ እግዚአብሔር ፈቃድ ሊመሩን ስለሚችሉ ቶሎ ከመማረርና ቶሎ ከመደሰት ልንቆጠብ ይገባል። “ወያመጽእ እግዚአብሔር ደዌ በእንተ ጥኢናሃ ለነፍስ፤ ስለ ነፍስ ድኅነት እግዚአብሔር በሥጋ ላይ ደዌን ያመጣል” እንደተባለ (ማር ይስ. ፪) ሁኔታዎችም ሁሉ ከእግዚአብሔር ፈቃድ ሊያወጡን ይችላሉ። “በእስያ ስለ ደረሰብን መከራ ወንድሞቻችን ሆይ ታውቁ ዘንድ እንዳለንና ስለ ሕይወታችን እንኳ ተስፋ እስክንቆርጥ ድረስ ከዐቅማችን በላይ ያለ ልክ ከብዶን ነበር። ”፪ኛ ቆሮ. ፩፥፰-፱)።
ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ በዚህ ብቻ ሳያበቃ “አይሁድ አንድ ሲጓድል አርባ ግርፋት አምስት ጊዜ ገረፉኝ፣ ሦስት ጊዜ በበትር ተመታሁ፣ አንድ ጊዜ በድንጋይ ተወገርኩ፣ መርከቤ ሦስት ጊዜ ተሰበረ፤ ሌሊትና ቀን በባሕር ውስጥ ኖርኩ፣ ብዙ ጊዜ በመንገድ ሄድኩ፡፡ በወንዝ ፍርሃት፣ በወንበዴዎች ፍርሃት፣ በወገኔ በኩል ፍርሃት፣ በአሕዛብ በኩል ፍርሃት፣ በከተማ ፍርሃት፣ በምድረ በዳ ፍርሃት፣ በውሸተኞች ወንድሞች በኩል ፍርሃት ነበረብኝ። በድካምና በጥረት ብዙ ጊዜም እንቅልፍ በማጣት በረሃብና በጥም በብርድና በራቁትነት ነበርኩ።” ይላል። (፪ኛቆሮ. ፲፩፥፳፬)
ስለዚህ ቅዱስ ጳውሎስ ይህ ሁሉ መከራና እንግልት በፈቃደ እግዚአብሔር መሆኑን ስለ ዐወቀና ስለተረዳ መከራውን ሳይሰቀቅ ጸንቷል። መከራም ሆነ ደስታ በፈቃደ እግዚአብሔር ሊሆን ስለሚችል በሁሉ ልንታገሥ እና በጸሎት ልንጸና ይገባል። በጥቅሉ የእግዚአብሔር ፈቃዱ በምልዐት ባይታወቅም ባወቅነውና በተረዳነው መጠን የሰው ልጅ ስሙን ጠርቶ ክብሩን ወርሶ እንዲኖር ነው።
የእግዚአብሔርን ፈቃድ ዐውቀን፣ በፈቃዱም ኖረን፣ ስሙን ጠርተን፣ ክብሩን ወርሰን እንድንኖር መልካም ፈቃዱ ይሁንልን። አሜን።
ስብሐት ለእግዚአብሔር ለዘገብረ ሰማየ ወምድረ!
Leave a Reply
Want to join the discussion?Feel free to contribute!