“የእግዚአብሔር ቀን እንደ ሌባ ድንገት ትመጣለች” (፪ጴጥ ፫፡፲)
መ/ር ቢትወደድ ወርቁ
በቤተ ክርስቲያን የሚከበሩ በዓላት በሙሉ ኃላፍያትን የሚያስታውሱና እነርሱንም በማሰብና በማክበር በረከት የሚገኝባቸው ሲሆኑ የደብረ ዘይት በዓል ግን ገና ያልተፈጸመውና ወደፊት ሊፈጸም ያለው ምጽአተ ክርስቶስ የሚታሰብበት በዓል ነው፡፡
ምጽአተ ክርስቶስ ማስተዋል የተሰጣቸው የሰው ልጆች የመጨረሻውን ፍርድ ከእግዚአብሔር ዘንድ የሚቀበሉበት፣ ሰማይና ምድር የሚያልፉበት፣ መንግሥተ ሰማያት የምትገለጥበት ነው፡፡ ፃድቃን “እናንተ የአባቴ ቡሩካን ዓለም ሳይፈጠር የተዘጋጀላችሁን መንግሥት ትወርሱ ዘንድ ኑ፡፡” የሚለውን የሕይወት ቃል የሚሰሙበት፤ ኃጥአን ደግሞ “እናንተ የተረገማችሁ ለሰይጣንና ለመልእክተኞቹ ወደተዘጋጀው ወደ ዘለዓለም እሳት ሂዱ” የሚለውን ይግባኝ የሌለውን የእግዚአብሔርን የመጨረሻ ፍርድ የሚቀበሉበት ቀን ነው፡፡ (ማቴ ፳፭፡፴፬-፵፩)
ስለዚያች ቀን ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ ሲያስተምር “ሰማያት የሚነዋወጡባትና የሚያልፉባት ቀድሞ የነበረው ፍጥረት ሁሉ በእሳት ነበልባል የሚቃጠልባት የእግዚአብሔር ቀን ግን እንደ ሌባ ድንገት ትመጣለች” (፪ጴጥ ፫፡፲) በማለት ተናግሯል፡፡ የክርስቶስን የምጽአት ቀን፤ ማሰብ ሲባል በቀኑ ሊሆኑ ያላቸው እነዚህን እያሰቡ መጨነቅ አይደለም ሊሆንም አይገባውም፤ ቀኑን እያሰባችሁ ተጨነቁ አልተባለምና፡፡ ወይም ደግሞ ለቀኑ አንዳች የሕይወት ዝግጅት ሳያደርጉ ንስሓ ሳይገቡ ከክፋት ሳይመለሱ “ጌታ ሆይ ና” በማለት ቀኑን መናፈቅም አይደለም፡፡ ይህንን በተመለከተ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ለተሰሎንቄ ምእመናን ሲያስተምራቸው “ነገር ግን ወንድሞች ሆይ ስለ ጌታችን ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ መምጣትና ወደ እርሱ ስለ መሰብሰባችን በመንፈስ ወይም በቃል ወይም ከእኛ እንደሚመጣ በመልእክት የጌታ ቀን ደርሶአል ብላችሁ ከአእምሮአችሁ ቶሎ እንዳትናወጡ እንዳትደነግጡም እንለምናችኋለን፡፡” ብሏቸዋል (፪.ተሰ ፪፡፩-፪)
ስለ ቀኑ በማሰብ በመጨነቅና ቀኑን በመናፈቅ የተጎዱ ብዙ ሰዎች አሉ፡፡ ለምሳሌ፡- ቢቢሲ የተባለው የዜና አውታር መጋቢት ፲፯ ቀን ፳፻ (እ.ኤ.አ.) ዘገባው በኡጋንዳ ውስጥ በምትገኝ ካኑንጉ በምትባል መንደር በፈረንጆቹ ሚሊኒየም ላይ የዓለም ፍፃሜ ይሆናል ብለው ያመኑና ራሳቸውን “የእግዚአብሔርን ዐሥርቱን ትእዛዛት የማስጠበቅና ዳግም የማደስ ንቅናቄ ቡድን” በማለት የጠሩ ሰባት መቶ አባላት ቤት ተዘግቶባቸው በእሳት እንዲቃጠሉ ሆነው ተጨፍጭፈዋል፡፡ (Uganda’s Kanungu cult massacre that killed 700 followers – BBC News)
በተመሳሳይ መንገድ “ጌታ ሊመጣ ነውና ይህን አድርጉ፤ ይህን ስጡ እንዲህ ዓይነት ስፍራ ሄዳችሁ ራሳችሁን ደብቁ ወዘተ” በሚሉ መልእክቶች ትዳራቸውን የበተኑ ሥራቸውን ትተው ለጉስቁልና፤ ትምህርታቸውን አቋርጠው ለማኅበራዊ ቀውስ የተዳረጉ ሰዎች አያሌ ናቸው፡፡ ሠርተው ኑሯቸውን ለውጠው ሀገራቸውን፣ ወገናቸውንና ቤተሰቦቻቸውንም መርዳት ሲገባቸው ውድና መተኪያ የሌለውን ጊዜያቸውን ሰውተው ለነዚህ የሐሰት ነቢያት አገልጋይ ሆነው የቀሩ ሰዎችም ብዙ ናቸው፡፡
ይህ ሊሆን ሰለሚችልም ጌታችን አስቀድሞ በደብረ ዘይት ለደቀ መዛሙርቱ ባስተማረው የምጽአት ትምህርቱ “በዚያን ጊዜ ማንም፡- እነሆ ክርስቶስ ከዚህ አለ፤ ወይም ከዚያ አለ ቢሏችሁ አትመኑ፤ ሐሰተኞች ክርስቶሶችና ሐሰተኞች ነቢያት ይነሣሉና ቢቻላቸውስ የተመረጡትን እንኳ እስኪያስቱ ድረስ ታላላቅ ምልክትና ድንቅ ያሳያሉ” በማለት አስጠንቅቆናል፡፡ (ማቴ. ፳፬፡፳፫-፳፭)
ሰዎችን ወደ ንስሓና እግዚአብሔርን ወደ ማመን ከማቅረብ ይልቅ በዚህ መንገድ የምጽአትን ቀን ምክንያት ሕዝብን በማስደንገጥና በማስደንበር ጥቃቅንና ዐበይት ምልክቶችን በማሳየት ወደ ራሳቸው በመምራት ገንዘቡን በመበዝበዝ ኑሮውን በማጎሳቆልና ከዚያም ሲያልፍ ሕይወቱንም በመንጠቅ ልቡን ከፍቶ የሰጣቸውን ሕዝብ መጫወቻ የሚያደርጉ ነቢያተ ሐሰት አሉ፡፡
በኢትዮጵያ ታሪክም በተመሳሳይ መንገድ ራሳቸውን “ክርስቶስ” አድርገው በመሾም ያሳቱ ለማሳትም የሞከሩ ሰዎች ነበሩ፡፡ እንደ ምሳሌም በዐሥራ ስድስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን በዐፄ ዘድንግል ዘመነ መንግሥት በአማራ ሳይንት በኩል “እኔ ክርስቶስ ነኝ” የሚል ሰው ተነሥቶ ነበር፡፡ ጌታ ያደረገውን በማስመሰል ዐሥራ ሁለት የሐሰት ሐዋርያት፣ ሰባ ሁለት የሐሰት አርድእት፣ ሠላሳ ስድስት የሐሰት ቅዱሳት አንስት አስከትሎ ትምህርቱን እስከ ማሠራጨት ደርሶ ነበር፡፡ንጉሡ ይህን ሰምተው በወታደር አስያዙት፤ ጭፍሮቹም ተበታተኑ፡፡ እርሱም ወደ ንጉሡ ቀርቦ ቢጠየቅ “አዎ እኔ ክርስቶስ ነኝ ከድንግል ማርያም ተወልጄ ሞቼ ተነሥቼ ወደ ሰማይም ዐርጌ ነበር፡፡ ከቤተ እሥራኤል በመወለዴ እሥራኤል ያልሆኑት ሁሉ ባዕድ አደረገን እንዳይሉኝ አሁን ደግሞ ከቤተ አሕዛብ ከምትሆን ከመርዐተ ወንጌል ተወለድኩ፡፡” አላቸው፡፡ (ወላጅ እናቱ መርዐተ ወንጌል ትባላለች) ንጉሡም “ሰይጣን በሰው እያደረ እንዴት ይጫወትብናል፡፡” ብለው በመገረም በሰይፍ እንዲቀጣ እንዳደረጉት የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ታሪክ ይመሰክራል፡፡(ብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ፡- የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ታሪክ ገጽ ፺፮)
በቅርቡ እንኳን በሀገረ ኬንያ ኤልዩድ ሲሚዩ የተባለ የ፰ ልጆች አባት “እኔ ኢየሱስ ክርስቶስ ነኝ!” በማለት ዐውጆ አያሌ ተከታዮችን አፍርቷል፡፡ ሚስቱም ኤን ቲቪ ከተባለ የቴሌቪዥን ጣቢያ ጋር ባደረገችው ቃለ ምልልስ የባሏን “ኢየሱስነት” በማስረጃ ለማረጋገጥ ስትሞክር “ባሌ ተራውን ውኃ ጥዑም ወደ ሆነ ሻይ ለውጦ አብዝቶአል፡፡ ብዙዎችም ከሻይው ቀምሰው በጣዕሙ ተገርመዋል፣ ወደ ቤታቸውም ወስደዋል” በማለት ተናግራለች፡፡
በተግባሩ የተበሳጩ ሰዎችም “ክርስቶስ ሕማምን ተቀብሎ እንደተሰቀለ፤ ኤልዩድ ሲማዩም ከስቅለት በዓል በፊት ተሰቃይቶ በመስቀል መሰቀል አለበት፤ ሞትንም አሸንፎ ይነሣ እንደሆነ እናያለን” በማለታቸው ይህ ሰው ፈርቶ ጥበቃ እንዲደረግለት ለፖሊስ እንዳመለከተ ኦፕላንዲያ የተባለው ድረ ገጽ በየካቲት ፳፱ ቀን ፳፻፲፭ ዓ ም (March 08,2023) ዘገባው አስነብቧል፡፡ (https://www.opindia.com/author/opindia/amp/)
ምን እናድርግ?
ዕለተ ምጽአት ሲታሰብ ክርስቲያኖች ሊጠይቁት የሚገባቸው ጥያቄ ምን እናድርግ? የሚለውን ጥያቄ ነው፡፡ ምን እናድርግ? ለሚለው ጥያቄም ቅዱሳት መጻሕፍት በስፋትና በጥልቀት መልስ የሰጡን ቢሆንም ጥቂቶቹን ጠቅለል አድርገን እንመልከት፡-
፩. እንጠንቀቅ
ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ቅዱሳን ደቀ መዛሙርቱ የመምጣትህና የዓለም መጨረሻ ምልክቱ ምንድነው? በማለት በጠየቁት ጊዜ ምልክቶችን ከነገራቸው በኋላ በመደጋገም “ማንም እንዳያስታችሁ ተጠንቀቁ” በማለት እስከ ዓለም ፍፃሜ የሚነሣው ትውልድ ሊያደርግ የሚገባውን ነገር አስተምሯል፡፡ (ማቴ. ፳፬፡፬) ዘመናችን እውነት በሚመስሉ ግን በሐሰት በተሞሉ ትምህርቶችና አስተሳሰቦች፤ እውነተኛ በሚመስሉ ነገር ግን ደግሞ እውነትን በየቀኑ እየገደሉ ለመቅበር በሚሞክሩ ሐሰተኞች የተሞላ ጊዜ ነው፡፡ አደገኛ የሚመስለውም ሐሰትና ሐሰተኞቹ ከእውነት ጋር እጅግ መመሳሰላቸው ነው፡፡ “የአምልኮት መልክ አላቸው ኃይሉን ግን ክደውታል፡፡” እንዳለ ቅዱስ ጳውሎስ (፪.ጢሞ. ፫፡፭)
፪. እንጠበቅ
ጌታችን በሁለተኛ ደረጃ ልናደርግ የሚገባን ነገር መጠበቅ እንደሆነ አስተምሮናል፡፡ “ይህ ሊሆን ግድ ነውና ተጠበቁ፡፡” እንዲል (ማቴ ፳፬፡፮) መጠበቅ (ጠ) ፊደልን አላልተን ስናነብ ለካህናት ሥራቸው ሲሆን፤(ጠ) ፊደልን አጥብቀን ስናነብ ለምእመናን በአንድ ቦታ መወሰንን የእግዚአብሔርን ሕጉን ትእዛዙን መጠበቅን በሥርዓት መመላለስን ገንዘብ እንዲያደርጉ ያስገነዝባል፡፡ “ተጠበቁ!” ሲልም ከቤተ እግዚአብሔር አትውጡ፤ በሕገ እግዚአብሔር ጸንታችሁ ቁሙ፤ በሥርዓተ እግዚአብሔር ተመላለሡ በእምነት ጽኑ ማለቱ ነው፡፡
፫. እንዘጋጅ
ጌታችን በወንጌል “ስለዚህ እናንተ ደግሞ ተዘጋጅታችሁ ኑሩ የሰው ልጅ በማታስቡበት ሰዓት ይመጣልና” በማለት እንዳስተማረን፡፡ (ማቴ ፳፬፡፵፬) መዘጋጀት በኃጢአት የተበላሸን አኗኗርና ሕይወት በንስሓ ማደስ በቅዱስ ሥጋውና በክቡር ደሙ ማተም ነው፡፡ (ራእ. ፯፡፲፬) መዘጋጀት ከተጣሉት ጋር መታረቅ፤ የሰረቁትን መመለስ፤ የበደሉትን መካስ፤ ከወደቁበት መነሣት ከርኩሰት መቀደስ ነው፡፡ መዘጋጀት የራስን ኃጢአት ብቻ እያሰቡ በሰው ከመፍረድ መቆጠብ ነው፡፡ መዘጋጀት አሁን እንደሚሞቱ ሆኖ ማሰብ ዘለዓለም እንደሚኖሩ ሆነው እግዚአብሔርን ማስደሰት ድርሻን መወጣትና እግዚአብሔርን መፍራትን፣ እምነትን፣ ራስን መግዛትን፤ ንስሓን፣ ትዕግሥትን፣ ሕሊናን መጠበቅን ገንዘብ አድርጎ መገኘት ነው፡፡
በቅድስት ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንም ዕለተ ምጽአትን አስመልክቶ ከዋዜማው ጀምሮ የሚነበቡ ምንባባት፣ የሚዘመሩ መዝሙራት፣ የሚሰበከው ምስባክ ሁሉ ነገረ ምጽአትን የሚያስታውሱ ናቸው፡፡ ቀኑ ግን መቼ እንደሚሆን አናውቅም፡፡ ወንጌላዊው ቅዱስ ዮሐንስ “ክርስቶስ በሚመጣበት ጊዜስ ከወዴት እንደሆነ ማንም አያውቅም” እንዲል (ዮሐ. ፯፥፳፯)፡፡ ድንገት ባልታሰበ ጊዜ እንደሚመጣም “የእግዚአብሔር ቀን እንደ ሌባ ድንገት ትመጣለች” (፪ጴጥ ፫፡፲) በማለት ቅዱስ ጼጥሮስ በመልእክቱ እንደተናገረው በዘመናችን ሁሉ እንደ እግዚአብሔር ቃል መመላለስ፣ በንስሓ ራስን አዲስ አድርጎ ተዘጋጅቶ መጠበቅ ይገባል፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
Leave a Reply
Want to join the discussion?Feel free to contribute!